Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow የጎርፍ አደጋ ስለደረሰ ዝናብ ይቅር?
የጎርፍ አደጋ ስለደረሰ ዝናብ ይቅር? Print E-mail
Wednesday, 06 February 2008
Imageበጎርፍ ምክንያት በሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰው አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ ሰጥመው ሕይወታቸው የሚያልፍ የሰዎች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ባህር ውስጥ አደጋና ብዙ የሕይወትና የንብረት መጥፋት የሚደርስባቸው መርከቦችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ውሃ ሲጠጡ ትን ብሏቸው ሕይወታቸውን የሚያጡም አይጠፉም፡፡
በውሃ ምክንያት በሚደርሱ እነዚህን በመሳሰሉ አደጋዎች የተነሳ ከአሁን በኋላ ዝናብ፣ ከአሁን በኋላ ውሃ አያስፈልግም ማለት ይቻላል?

በእሳት ምክንያትም በርካታ ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፡፡ ሕንፃዎች ይጋያሉ፡፡ አውሮፕላኖች ይቃጠላሉ፡፡ በእሳት ምክንያት ንብረትና ሕይወት በመጥፋቱ ከአሁን በኋላ እሳት የሚባል አያስፈልግም ማለት ይቻላል?

ለውሃውም ለእሳቱም የምንሰጠው መልስ ቀላል ነው፡፡ በውሃና በእሳት ምክንያት አደጋ እንዳይደርስ፣ ንብረትና ሕይወት እንዳይጠፉ እንከላከል፣ እንጠንቀቅ፣ አስፈላጊውን እርምጃ እንውሰድ፡፡ አስፈላጊ የመከላከያ ትምህርት ይሰጥ፤ ዝግጅት ይደረግ ይባላል እንጂ፣ ዝናብ ወይም ውሃ ወይም እሳት በዓለም እንዳይኖር ይከልከል ሊባል አይቻልም፡፡

የውሃና የእሳት ድርሻ ሕይወትና ንብረት ማጥፋትና ማውደም ብቻ አይደለም፡፡ ውሃና እሳት ሕይወትን የሚያለመልሙ፣ ሕይወት እንዲቀጥል የሚያደርጉ የተፈጥሮ ጸጋዎች ናቸው፡፡ ያለ ውሃና እሳት ሕይወት አይኖርም፡፡ ሕብረተሰብ ሊኖር አይችልም፡፡ ውሃና እሳት አሉታዊ  ብቻ ሳይሆን አዎንታዊና ወሳኝ የሕይወት ሚናም ይጫወታሉ፡፡

ከመንግሥት የሚወጡ አንዳንድ አዋጆችና መመሪያዎች ግን "ጎርፍ አደጋ ስላደረሰ ከአሁን በኋላ ዝናብና ውሃ አያስፈልጉም" የሚሉ ይመስላሉ፡፡ "እሳት አደጋ ስላደረሰ ከዚህ በኋላ እሳት መኖር የለበትም" ብለው የሚያውጁ ናቸው፡፡

አንዳንዶቹን እንጥቀስ፡፡ በሩዋንዳ በደረሰው ጭፍጨፋ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሆነው አሉታዊ ሚና የተጫወቱና ጭፍጨፋውን ያባባሱ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሊከለከል ይገባል? መከልከል የለበትም፡፡ ውሃ ለመጠጥ፣ ለመታጠቢያ፣ ለትራንስፖርት ወዘተ. ጠቀሜታ እንደዋለና ሕይወት እንደሆነ ሁሉ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያም ለመረጃ፣ ለማህበራዊ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

"ቴሌቪዥን የማንፈቅድበት ምክንያት በሕዝብ ላይ አደጋና ብጥብጥ እንዳይፈጠር ብለን ነው" ብሎ መከልከል "የጎርፍ አደጋ ስለደረሰ ከአሁን በኋላ ዝናብ አያስፈልግም" እንደማለት ነው፡፡ የተሳሳተ ውሳኔ፡፡

መሬት በድርድር ወስደው ምንም ልማት ሳያካሂዱ የሸጡ ግለሰቦች አሉ? አዎን አሉ፡፡ ለሪል ስቴት ብለው መሬት በድርድር በአስር ሺህ ሄክታር የሚቆጠር ወስደው ሳያለሙ ቆመው የቀሩና የሸጡ አሉ? አዎ አሉ፡፡ ዝናብና ጎርፍ አደጋ እንደሚያስከትል ሁሉ በአሰራሩ ላይ አደጋ የሚያስከትሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ከአሁን በኋላ በድርድር መሬት አይሰጥም ብሎ ማወጅ የጎርፉ አደጋ ስለደረሰ ከአሁን በኋላ ዝናብ አያስፈልግም እንደማለት ነው፡፡

ሆስፒታልና ትምህርት ቤት ሊያቋቁም ከውጭ ባለሀብቶች እስኪመጡ፣ ተጫራቾች እስኪመጡ ጠብቅ ማለት ልማትን ማደናቀፍ ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊ ሪል ስቴት እሰራለሁ ብሎ የመጣ ባለሃብት ከ25 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ አይሰጥህም ማለት (የአዲስ አበባ አስተዳደር ብሏል) ልማትን ማደናቀፍ ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንደዚህ ስላለ ባለሀብቶች አዲስ አበባን ትተው ወደ ኦሮሚያ ክልል እየጎረፉ ነው፡፡ ዝናብ ጎርፉ ፈጥኖ አደጋ ስላስከተለ ከአሁን በኋላ ዝናብ አያስፈልግም እንደማለት ነው፡፡

አንድ ላፕቶፕ ይዞ ከውጭ የመጣ ኢትዮጵያዊ ግብር ላለመክፈል ብሎ "ይዤው የመጣሁት ላፕቶፕ ነው እንጅ አዲስ አይደለም" ብሎ ካጭበረበረ ከዚያ በኋላ ወደ ውጭ የሚወጣ ኢትዮጵያዊ ላፕቶፕ ይዞ ለስራ ስለወጣ ለጉምሩክ ይዞ እየወጣ መሆኑን ካላሳወቀ እንደ አዲስ ተቆጥሮ ግብር ይከፍላል የሚል መመሪያ ይወጣል፡፡ አንድ ላፕቶፕ ይዞ መውጣትና መመለስ ለኢትዮጵያዊ አስፈሪ፣ አስንጋጭ፣ አድካሚ ተግባር ይሆናል፡፡ ከጭቅጭቁ ላፕቶፕ ለስራ መውሰድ ይቅርብኝ ይላል፡፡

በትራፊክ የተቀጣ አንድ ሰው ወደ መገናኛ ሄዶ ሳይከፍል ስለቀረና ውጭ ስለሄደ በግድ እንዲከፍል ከአሁን በኋላ መንጃ ፈቃድህን ቀይር የሚል መመሪያ ይወጣል፡፡

አንድ ጋዜጣ አቋቁሞ የማንወደው ነገር ፅፏል ተብሎ፣ ሬዲዮ ጣቢያ ከደገመማ አያስቀምጠንም በሚል እሳቤ፣ ጋዜጣ ያለው ሬዲዮ አይፈቀድለትም የሚል ሕግ ይወጣል፡፡

አንዱ ኤስ ኤም ኤስ በሞባይል ሕዝብን የሚያጋጭ መነሳሳት የሚፈጥር መልዕክት ስላስተላለፈ ኤስ ኤም ኤስ የሚጫወተው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይረሳና "ቶሎ ዝጋልኝ" ይባላል፡፡ የጎርፍ አደጋ ስለደረሰ ዝናብ አያስፈልገንም አይነት፡፡

የሚያሳስቡ ነገሮች የሉም፣ አደጋ የሚባል ነገር የለም፣ መንግሥት ምንም መነሻ የለውም ማለታችን አይደለም፡፡ በላፕቶፕ የሚያጭበረብሩ አሉ፣ በኤስ ኤም ኤስ ፀረ ሕዝብ መልዕክት የሚያስተላልፉ አሉ፣ መሬት ወስደው የሚያጭበረብሩ አሉ፣ መገናኛ ብዙሃንን ለፀረ ሕዝብ ተግባር የሚያውሉ አሉ ወዘተ. እነዚህ የሉም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ አሉ ማለት ግን ለእነዚህ መቆጣጠሪያ ዘዴ ይበጅላቸው ይባላል እንጅ አሉታዊ ገፅታቸውን በማየት አዎንታዊውን መደምሰስ አያስፈልግም፡፡

መንግሥት እንደዚህ ዓይነት በርካታ አዋጆችና መመሪያዎች አሉት፡፡ ሊፈትሻቸው ይገባል፡፡ ፣የጎርፍ መከላከያ እርምጃ እወስዳለሁ ፣እንጂ፣ ፀረ ዝናብ አቋም አልይዝም፣ ማለት አለበት፡፡
 
< Prev   Next >