Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ጽዳት፣ ጤንነትና መብት
ጽዳት፣ ጤንነትና መብት Print E-mail
Wednesday, 06 February 2008
(ጌታቸው፣ ከአራት ኪሎ)

አካባቢያችንን “ጽዱና አረንጓዴ” የማድረግ መጠነ ሰፊ ዘመቻ በተለይም የመናገሻ ከተማችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጭምር አጀንዳ በነበረበት በአንድ ወቅት “የጋሸ አበራ ሞላ” እንቅስቃሴ አንጻራዊ አካባቢያዊና ክልላዊ ንቅናቄ ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ይህ ጉዳይ ከሌሎች ተዛማጅ ወይም አቻ ተመጋጋቢ እርምጃዎች ጋር አብሮ የማይሄድ በገዛ ራሱና ለብቻውም ዘልቆና ጠልቆ መሰረታዊውን ችግር አውቆና ለይቶ ወደ መፍትሄው አቅጣጫ የማይጓዝ ይመስል ሌሎች አዳዲስ የሚባሉ አጀንዳዎች በመጡ ቁጥር የዘመቻውን የወር ተራ እየለቀቀ እንዳለቀ እየተቆጠረ ወይም እየቀረ በመሄድ ላይ ያለ ይመስላል፡፡

በዚህ ረገድ የቀረና አለ የሚባል ነገር ቢኖር አካባቢያችንን ለመንከባከብና ለማስዋብ የተባበሩ የተባሉ የከተማው ዋና ዋና መንገዶች አደባባዮች እንደ ግል ሀብት ወይም ይዞታ የተመሩላቸው ኩባንያዎችና የንግድ ድርጅቶች የያዙት በየትም አገርና ከተማ የማይታይና የማይገኝ የንግድ ማስታወቂያና ማስታወቂያው የያዘው ሰፊ ቦታ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ሰብሰባ ከየአቅጣጫው ወደ አዲስ አበባ ከተማ አሰባስቦ ያመጣቸው በርካታና ልዩ ልዩ ተሳትፎና ሚና ያላቸው እንግዶቻችን ኢትዮጵያን በተለይም አዲስ አበባን ተዘዋውረው አይተው ከሚደነቁበት ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህ ሳይሆን አይቀርም ብሎ አለመጠርጠር፣ ጉዳዩን ተገቢ ነው የትም አገር የተለመደ አሰራር ነው፣ ብሎ መመረቅ ጭምር ይመስለኛል፡፡

“በጋሸ አበራ ሞላ” ስም አማካኝነት የተጀመረው የከተማ ጽዳትና ውበት እንቅስቃሴ የማንንም አመራር ከበላይ ሳያገኙ በገዛ ራሳቸው ፈቃድ ተነሳስተው እንደየአቅማቸው በየአካባቢያቸው ተንቀሳቅሰው ሰፈራቸውን እንደነገሩ ያስዋቡትን አስዋብን ያሉትን ጠረግ ጠረግ፣ አበስ አበስ ያደረጉትን ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ከጽዳቱም፣ ከውበቱም በልጦ ጎልቶ የሚታይ አካባቢያዊ መፈክር የጻፉትን ወጣቶች ጥረትና ምኞት ያስታውሰናል፡፡ በየጉራንጉሩ በተለይም ለተከለከለው ድርጊትና ተግባር በተጋለጡ ስፍራዎች ተጽፈው እናያቸው፣ እናውቀቸው የነበሩት እንደ “መሽናት ክልክል ነው፡፡ ከመሽናትዎ በፊት ኪሰዎን ይዳብሱ” አይነት ማስጠንቀቂያዎች ለየት ያለ ቅርጽ “ውበት”ና “ጥበብ” ይዘው ነጻ መገለጫ አግኝተው ተመልክተናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን መልዕክታቸው መሽናት ክልክል ነው እዚህ ቦታ አይሸናም የሚል ነው፡፡

የከተማውን ውበት ከሚያበላሹት የሕዝቡን ጤና ለአደጋ ከሚያጋልጡ ምቾቱን (ተድላ ደስታውን) ከሚያሳጡት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የመፀዳጃ ቤቶች ችግር ነው፡፡ የወጣውን የጤና ፖሊሲ ለመተግበር ሕብረተሰቡን በጤና አጠባበቅ ዘርፍ እንዲሳተፍ ለማድረግ በማስፈለጉ አብዛኛው የጤና ችግር በመሰረታዊ የጤና ክብካበቤ የህዝቡን ስነ ልቦናዊ አመለካከት በመለወጥ ሊፈቱ እንደሚችል በመታመኑ እንዲሁም ከግል ንጽህና አንስቶ ህብረተሰቡ በየደረጃው ጤናውን እንዲጠብቅና የወደፊቱም ትውልድ ጤናው ተጠብቆ ኃላፊነቱን እንዲረከብ ለማስቻል የጤና አጠባበቅ ሕግን መቅረጽ በማስፈለጉ የወጣው የሀገራችን የጤና አጠባበቅ ሕግ ከሚደነግጋቸው ጉዳዮች መካከል የመፀዳጃ ቤት አስፈላጊነት አንዱ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ለምሳሌ ማንኛውም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ወይም ድርጅት ንጽህናው የተጠበቀ በቂ የመፀዳጃ ቤት የማዘጋጀትና ለደንበኞቹ ክፍት የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማናቸውም የከተማ አስተዳደር የሕዝብ መጸዳጃ ቤት እንዲኖር የማድረግና ንጽህናውም ሁልጊዜ የተጠበቀ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት ይላል፡፡

ለግንባታ ሥራዎች ቅድመና ድህረ የጤና አጠባበቅ ፈቃድና ምዝገባ ስለማስፈለጉ የሚወስነውም የዚህ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ሕግ ድንጋጌ፣

1ኛ) ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ሕንጻዎች ግንባታ የሚያካሂድ ማንኛውም ሰው ከግንባታው እቅድ አንስቶ እስከ ግንባታው ፍጻሜ ድረስ በዚሁ አዋጅ መሰረት በሚወጣ ደንብና መመሪያ መሰረት ከጤና አጠባበቅ ባለሥልጣን አስፈላጊውን ፈቃድ የማግኘት የመመዝገብ ግዴታ አለበት፡፡

2ኛ) ማናቸውም ሰው የመኖሪያ ቤት የማምረቻና የአገልግሎት መስጫ ድርጅት ውጭ ተቋም ሲገነባ የመፀዳጃ ቤት አብሮ መስራት ይኖርበታል ሲል ይደነግጋል፡፡

የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ሕግም እንደዚሁ፡፡ በተለይም የከተማ ቆሻሻ አያያዝን በተመለከተ ለሕዝብ ክፍት የሆነ ቦታን የሚያስተዳድር ማንም ሰው ምንጊዜም በቂና ተስማሚ የመፀዳጃ ቤት”. አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች መገልገያዎች በቦታው መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥ እንዳለበት ይወስናል፡፡

ይህ ሁሉ ከላይ የተዘረዘረውን ግን ድፍንና አጠቃላይ ነው፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ስለመወሰኑ፣ የወሰነው ሕግ የሚመለከታቸው ሁሉ የዕለት ተዕለት መመሪያ የብዕርና የጥበብ መጀመሪያ ስለመሆኑ፣ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ የሚጠበቅና የሚያስጠይቅ ሌላው ቀርቶ ለምሳሌ ለጠቅላላ እውቀትም ሆነ ለ”ጭንቅ” ጊዜ ተፈልጎ የሚገኝ የሚፈለግበት ቦታ የሚታወቅ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከላይ የገለጽናቸው የጤና እና የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ስለ “በቂ” የመጸዳጃ ቤት ይናገራሉ፡፡ ንፅህናው የተጠበቀ ወይም ተስማሚ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ትተን “በቂ” ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ በተለይም “ለሕዝብ ክፍት የሆነበት”ን ወይም “ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ወይም ድርጅት”ን በተመለከተ ምን ማለት ነው ብለን እንጠይቅ፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ እነዚህን “ንጽህናው የተጠበቀ በቂ የመፀዳጃ ቤት “. ለደንበኞቹ ክፍት የማድረግ ግዴታ” ምን ማለት እንደሆነ እንጠይቅ፡፡

በተለይም የኋለኛው ጥያቄ በቅርቡ ከግልና ከየብቻ የጓደኛሞች ወሬ ወጥቶ አደባባይ ላይ የተነሳ ጥያቄ ሆኖ ነበር፡፡ ጥያቄውን ያነሱት ሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጉዳዩን አደባባይ አውጥተውት ያየሁት በሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛው እትም ላይ ነው፡፡ ሁለቱ ሴቶች እንደጻፉት ጉዳዩና ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፡

ሁለቱ ሴቶች መኪና ይዘዋል፡፡ አንድ መኪና ውስጥ አንድ ላይ ናቸው፡፡ ጉዞ ላይ እንዳሉ ከመካከላቸው አንዷ ቀጠሮ እማይሰጥ እቤት እማያደርስ አጣዳፊ የተፈጥሮ ጥሪ ያጋጥማታል፡፡ ወዳዩት ሆቴል ጎራ ይላሉ፡፡ ሆቴሉ በከተማው የሚያዘወትሩት እንደሚባለውም ለኔ ቢጤው ተራ መደዴ ሰው የማይቀመስ ነው፡፡ እነሱ ግን የፈለገውን ለማዘዝ አስፈላጊም ቢሆን የፈለጉትን አገልግሎት ብቻ አግኝተው ለመክፈል ዝግጁ ነበሩ፡፡ እምቢ ይባላሉ፡፡ በመፀዳጃ ቤቱ መገልገል አትችሉም ብቻ ሳይሆን መዶልም?? የደረሰባቸውም መሰላቸው፡፡

ይህን ጉዳይ ምናልባትም ጋዜጣው ከሚታተምበት ቋንቋ የተነሳ ብዙው የአገራችን ሰው አዕምሮና ጉዳይ ውስጥ የሚፈለገውንና የሚገባውን ያህል የተደረሰና የተብላላ አይመስለኝም፡፡ የሚገባውንና የሚፈለገውን ያህል የምለው በአንጻራዊነት ሁለቱ ሴቶች የደረሰባቸውን ችግር የጻፉት በየትኛውም ጋዜጣ ቢሆን በአማርኛ የነበረ ቢሆንም ኖሮ ሊያስነሳ ይችል ነበር የምለውን ውይይትና ሞቅ ያለ ክርክር እንዲሁም እሰጥ አገባ ከቁጥር በማስገባት ነው፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የወጣው ጽሁፍና የባለ ጉዳዮቹ ብሶት በቀረበበት መልክ ጭብጥ አድርጎ ያስነሳው ወይም እንዲነሳ ያደረገው የተጠቀሰው “ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም” ያዘጋጀውን የመፀዳጃ ቤት “ለደንበኞቹ ክፍት የማድረግ ግዴታውን” ሳይወጣ ቀረ ወይም “ሳይወጣ መቼ ቀረ” ለመሆኑ እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች ደንበኞች ናቸው እንዴ? ወይም “መቸ ደንበኞች ናቸው?” የሚለውን ሳይሆን ከዚህ የተለየ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡

ይህም በውጭ አገር የምናውቀው “ጋሸ አሸብር በአሜሪካ” በውጭ አገር ቆይታቸው የሚያውቁትና በሳቸው ላይ ሲመጣ ግን “እኔ ደግሞ መደቤ ከነዚያኛዎቹ ነው እንዴ?” ያሉት በዘር በቆዳ ቀለም ምክንያት ከሰው ሰው ከልጅ ልጅ የመለየት እጅግ በጣም በቀላሉ አነጋገር የዘር መዶለን  ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህም በሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ክስ መሰረት የተባለው ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ወይም ድርጅት እነዚህ ሴቶች በድርጅቱ የመፀዳጃ ቤት እንዳይገለገሉ የከለከለው ብከለክል መብቴ ነው ማን አለኝ ከልካይ ያለው (ወይም አለ የተባለው) ሰዎቹን ጥቁር ናችሁ ነጭ አይደላችሁም ብሎ እንጂ “ደንበኞች” አይደላችሁም ብሎ አይደለም ማለት ነው፡፡ ክሱን (ክስ ስል የመደበኛና በደንበኛው ቋንቋ ሳይሆን ሰው በዕለት ተዕለት ኑሮው በሚጠቀምበት ከወቀሳ ጋር በሚተባበረው ቃል መንፈስ ነው) ወቀሳውን ያቀረቡት የግል ተበዳዮች ጎልቶ እንዲወጣ የፈለጉት ጎልቶ ቢወጣ ይበልጥ ክብደትና ትኩረት እንዲሁም አድማጭ እንዲያገኝ የፈለጉት የጉዳዩን ይህንን ገጽታ እንዲሆን አድርገው ሊሆን ይችላል፡፡ የጋዜጣው ማለትም የቋንቋውም ምርጫ መሰረትና ምክንያትም ይህንን ግምት ሊያጠናክር ይችላል፡፡

በየትኛውም ቋንቋ በየትኛውም የአንባቢ መድረክ ተጻፈ የትኛው ገጽታ ይበልጥ እንዲጎላ ተፈለገ በኔ በኩል ይበልጥ መነሳት የሚገባውና ተዳፍኖ መቅረት የሌለበት አንድ ያ የሴቶቹ ጽሁፍ አደባባይ አውጥቶት ነገር ግን “ሳይያያዝ” የቀረ ጉዳይ ቡና ቤቶች ሆቴል ቤቶች ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋሞች የመፀዳጃ ቤቶቻቸውን ለደንበኞቻቸው ክፍት የማድረግ ግዴታ የተፈፃሚነት ዳር ድንበር ምን ይመስላል? የሚለው ነው፡፡

ጽዱ እና ውብ አካባቢ እንዲኖረን ብቻ ሳይሆን በተራ ሰው ቋንቋ ስለውበት ስለ ዓይን ምግብና ቀለብ ብለን ብቻ ሳይሆን ከመሰረታዊ የሕዝብ የጤና ጥበቃ አኳያ ከዚህ ቀደም ሲል (በዚህ ጽሁፍ) በአንድ በኩል በግል ሰዎች በነጋዴዎች ላይ የተቋቋመውን ግዴታ በሌላ በኩል ደግሞ በከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ላይ የተጣለውን የሕዝብ የመፀዳጃ ቤት የማዘጋጀት ሌላ ምናልባትም ከባድ ግዴታ ተናግረናል የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ወይም መንግሥት ይህን ግዴታውን ስለመወጣቱ እናገራለሁ ማለት አፍ ማበላሸት ትዝብት ማትረፍ ነው፡፡ ከየጓዳው (የመፀዳጃ) መውጣት መመጠጥ የሚገባው የፍሳሽ አገልግሎት የመስጠት ተግባር ራሱ ተመዝግበው የረዥም ጊዜ ሰልፍ የሚያዝበት ሙስና የሚፈፀምበት የነበረ መሆኑ ዛሬም ታሪክ ሆኖ አልቀረም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ለዚህ አገልግሎት ተሰጥተው የነበሩ የሕዝብ የመፀዳጃ ቤቶች በየትኛውም ዓይነት የመንግሥት አስተዳደር ሊኖር የሚገባውን ተራ አያያዝና “መልካም አስተዳደር” አጥተው እራሳቸው ቆሻሻ ስም የሚያሰጡት ሆነዋል፡፡ ፒያሳ ሲኒማ ኢትዮጵያ ፊት ለፊት ወይም “ባርቴንትሮ” ጥግ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን የተሰራው ሻል ያለ የሕዝብ የመፀዳጃ አገልግሎት እጣ ፋንታ አንድ ለእናቱ ሆኖ መቅረቱ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም ያላማረበትና ያልተዋጣለት በመሆኑ ብቸኛው አማራጭ የኢትዮጵያን የከተሞች አስተዳደርን (በአዲስ አበባና በማዕከላዊ መንግሥት  ደረጃ እንኳን) ሳይሳካ የቀረ ሙከራ በቁሳዊ ማስረጃነት እንዲመሰከር የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲረከበው ማድረግ ነው፡፡

አገሪቷ የግንባታ ኮድ የግንባታ ሥራ ፈቃድ ደንብ አላት ሲባል እናውቃለን፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ አዋጅ ሆኖ የወጣው የአገራችን የሕዝብ ጤና ጥበቃ የ1992 ዓ.ም ሕግም ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎች ግንባታ ከግንባታው እቅድ አንስቶ እስከ ግንባታው ፍጻሜ ድረስ ለዚያውም ከጤና አጠባበቅ ባለሥልጣን አስፈላጊውን ፈቃድ የማግኘትና የመመዝገብ ግዴታ የሚያስከትል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ፈቃዱም የሚሰጠው ይህን የጤና ጥበቃ አዋጅ መሰረት በማድረግ በሚወጣ ደንብና መመሪያ መሰረት ነው ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ስለመኖሩ/ ስላለመኖሩ የምናውቀው የከተሞች በተለይም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች መለያ ሆኖ የሚታወቀው የግንባታ ስራ ፈቃድ ሰልፍ ውጣ ውረድና ወዘተ ጋር ስንጋፈጥ ነው፡፡

ሕዝብ ዕለት ተዕለት የሚያውቃቸው የምግብ የመጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች እንኳንስ የመፀዳጃ ቤታቸው የሚከራይ ክፍላቸው እንኳን አንዳንዶቹ ገጠመኛቸውን ሲናገሩ እንደሚሉት የለበሱትን ሸሚዝ/ ኮት ለማውለቅ መስኮት መክፈትን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ መስኮት ካላቸው፡፡

የተባለው ወቀሳና ክስ የተነሳበት ምግብ ቤት በቂና ንፅህናውን የጠበቀ የመጸዳጃ ቤት የለውም አላዘጋጀም ስላልተባለና ስለዚህም “እዳው ስለቀለለን” ወደዚህ አልገባም፡፡ ይህን ያዘጋጀውን የመፀዳጃ ቤት ለደንበኞቹ ክፍት የማድረግ ግዴታ ተወጥቷል ወይ? ስንጠይቅ ግን እንዲህ ያሉ ቤቶች ደንበኛ ማለት ከዚህ ቀደም የምናውቀው እኛ ራሳችን ደንበኛ የምንለው ነው ሲሉን ነው፡፡ ወይም የደንበኝነት የምስክር ወረቀት እያያዝን አለዚያም የተባለውን አገልግሎት እናግኝ ብለን በመብትነት ከመጠየቃችን በፊት የበላን የጠጣን መሆኑን ማስመስከር ወይም ይህንን ለማረጋገጥና ለዚህ ብቁ ለመሆን በተወሰነ የሙከራ ጊዜ ውስጥ ማለፍ ደርሰን መሰብሰብ ሊያስፈልገን ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ እንዲነሳና ዛሬ በዚህ በመጠኑም ቢሆን እንድንነጋገርበት ያደረጉትን ጉዳይ እንደ መስከኑ የገለጹልኝ ሁለቱ ሴቶች (እውነትም እነሱ የሚሉት የቀለም የዘር ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር) እንዲያውም አዕምሮ የማመዛዘንን ሕግ ተከትሎ ይያቸው ከተባለ ሊያስቸግሩ የሄዱ በልተው ጠጥተው ሳይከፍሉ ይሄዳሉ አለዚያም ሌሎችን የድርጅቱን መገልገያዎች ያበላሻሉ ተብለው የሚጠረጠሩ “ወስላቶች” የሚባሉ አይደሉም፡፡ ከመካከላቸው አንድን ቀጠሮ የማያሰጥ የተፈጥሮ ጥሪ ስላስጨነቃት ነው እዚያ ቤት የገቡት፡፡ መኪና ይዘዋል፡፡ ጭቅጭቅ ያስከተለው እምቢታ ሲመጣም እንክፈል ብለዋል፡፡ አዲስ አበባ በየዘርፉ የወስላታ የአስመሳይ፣ የአታላይ አገር መሆኑን ቢያንስ ቢያንስ መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ባለጉዳይ ሆነው በምሳሌነት የተነሱት ሁለት ሴቶች የገቡበት ቤት የንግድ ቤት ነው፡፡ የንግድ ሥራ ከሚያስከትላቸው “ሪስኮች” መካከል አንዱ ይኸው ዓይነት መበለጥ ሊሆን ይችላል በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይም ይህን የመሰለው የሕዝብ መስተንግዶ ልቆ የሚታይበት የንግድ ሥራ ሰዎቹ  ጨዋዎች ናቸው ከሚለው ግምቱ አኳያ ቢሳሳት ይመረጣል፡፡ ፖሊሲውም መሆን ያለበት ይኸው ነው፡፡    

“የብቃት ማረጋገጫ” ሰጭ የሥልጣን አካል በሞላበት አገር አገልግሎት ሰጭዎች ቀርተው ተጠቃሚው የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርብ መጠየቅ ያህል ግዴታችን በዛ “መከራ”ው ከበደ፡፡
 
< Prev   Next >