| በኦሮሚያ በ13 ቢሊየን ብር... |
|
|
| Wednesday, 06 February 2008 | |
|
በኦሮሚያ በ13 ቢሊየን ብር የቱሪስት ከተማ ሊገነባ ነው
በኦሮሚያ ክልል በ13 ቢሊዮን ብር የቱሪስት ከተማ ሊገነባ መሆኑን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ ስሜ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡ ግንባታው በሻላና አቢያታ ሐይቆች አካባቢ እንደሚከናወንና የግንባታውም ሥራ መቀመጫው ዱባይ በሆነው ኢንጃዝ ግሩፕ በተባለ ካምፓኒ እንደሚሰራ ታውቋል፡፡ ካምፓኒው ግንባታውን ለማከናወን 13 ቢሊየን ብር ማጽደቁ ታውቋል፡፡ የካምፓኒው ተወካዮች በቅርቡ አዲስ አበባ እንደሚመጡና ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተገልጿል፡፡ ኮሚሽነሩ ከጥቂት ወራት በፊት የካምፓኒው ተወካዮች ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር ፕሮጀክቱን በተመለከተ የመግባብያ ሰነድ መፈራረማቸውን አስታውሰዋል፡፡ በኮሚሽነሩ ገለፃ መሰረት ተወካዮቹ የመግባብያ ሰነዱን አስመልክቶ በዱባይ ከሚገኙ የካምፓኒው አመራር አካላትን ማነጋገራቸው ታውቋል፡፡ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ካምፓኒው ግንባታውን በአባያና ሻላ ሐይቆች አካባቢ በሚገኝ በ38"000 ሔክታር ቦታ ላይ እንዲያከናውን መፍቀዱን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለቱሪስት ከተማው ግብአት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለማምረቻ አራት ሔክታር መሬት ለካምፓኒው ተሰጥቷል፡፡ የቱሪስት መንደሩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ መካከለኛና ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው ደንበኞች ግልጋሎት የሚሰጡ ቪላዎች፣ የስፖርት ማዕከል፣ ሆስፒታል፣ የእንግዳ ማረፊያና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን እንደሚያካትት አቶ አለሙ ገልፀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ዲዛይን በቻይና ካምፓኒ ተሰርቶ መጠናቀቁን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ትግበራ ሲጀመር ከ20"000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርና ከእነዚህም 12ሺ ለሚሆኑት ቋሚ የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑ ታውቋል፡፡ ፕሮጀክቱ በያዝነው በጀት ዓመት እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |