Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow አቋም መለወጥና የፖለቲካ ፖርቲዎቻችን
አቋም መለወጥና የፖለቲካ ፖርቲዎቻችን Print E-mail
Sunday, 06 January 2008
በምርጫ 97 ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የነበረው ቅንጅት ዛሬ 6ዐዎቹ የላዕላይ ምክር ቤት ዓባላት ተከፋፍለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት (ኢዴኅህ) ዋነኛ አባል የነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ከኢዴኀህ ራሱን ገንጥሎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከአራቱ የቅንጅት አባል ድርጅቶች አንዱ የነበረው ኢዴአፓ መድኀን በተመሳሳይ ከቅንጅት ተገንጥሎ የራሱን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በሌላ በኩል ቀድሞ በአብኮ መሪነታቸው የምናውቃቸው ዶክተር መራራ ጉዲና የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ (ኦህኮ) በሚል ድርጅት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡

ቅንጅት እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት /ኢዴኀህ/ በምርጫ 97 ጥሩ የሚባል ውጤት በማምጣታቸው የፖለቲካ ሂደቱን ወደ አንድ ከፍታ ይወስዱታል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት አባል የሆነው የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ /ኦህኮ/ አመራርና አባሎች የቀድሞው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ /ኦብኮ/ አባላት ናቸው፡፡ ኦብኮ በኢዴኀህ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበረው፡፡ ዛሬ በኢዴኀህ አባል የሆነው ኢህኮ እንጂ አብኮ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት የፖለቲካ ፖርቲዎች ቀደም ብለው ከነበሩበት የፖለቲካ ፖርቲዎች የተለያዩት ለምንድን ነው? ልዩነቱስ መሰረት ያደረገው የግለሰብ አመራሮችን ስሜትና ፍላጎት ነው ወይስ የፖርቲውን ጠቅላላ ፖሊሲና ስትራቴጂ? ከአንድ ፖርቲ ወደ ሌላ ፖርቲ የሚደረገው ጉዞስ በእነዚህ የፖለቲካ ፖርቲዎች እይታ እንዴት ነው የሚታየው?

ከላይ የተገለፁትን ጥያቄዎች እንዲመልሱልን የኢዴአፖ-መድህን ሊቀመንበር የሆኑትን የፖርላማ አባል አቶ ልደቱ አያሌውንና የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ /ኦህኮ/ ሰብሳቢ የሆኑትን የፖርላማ አባል ዶክተር መራራ ጉዲናን ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል፡፡

..አንድ ቋሚ ነገር ካለ እሱም ለውጥ ብቻ ነው፡፡.. የሚለው አባባል ብዙ የሚነግረን ነገር ይኖራል፡፡ ይህች ዓለምም ሆነች ነዋሪዎቿ ከነፈጠሩት ስርዓት ተለዋዋጭና ያልተረጋጉ ከሆነ የፖለቲካ ስርዓቱና የፖርቲዎቹ ሁኔታም እንደዛው ነው፡፡ ለዘለዓለም ወዳጅ ለዘለዓለም ጠላት የለም፡፡ በዚህ ሳምንት የተጠናቀቀው የኬንያ ብሔራዊ ምርጫ በኘሬዚዳንቱ ምዋይ ኪባኪና ሬይላ ኦዲንጋ መካከል ከፍተኛ ፉክክርን አስተናግዷል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ግን ሁለቱ ተፎካካሪዎች የአንድ ፖርቲ አባላት ነበሩ፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት ቀደም ብለው በኤርያል ሻሮን የሚመራው የሊኩድ ፖርቲ አባል የነበሩ ቢሆንም ከዚያ ወጥተው ከድማ የሚባል ፖርቲ አቋቁመው ሊኩድን በማሸነፍ ሥልጣን ይዘዋል፡፡ በአሜሪካዎቹ ሪፐብሊካንና ዲሞክራት መካከልም ሆነ በእንግሊዞቹ ሌበርና ኮንሰርቫቲቭ የፖርቲ አቋም መለዋወጡ ግለሰቦችም እንደወቅታዊ አቋማቸው ከአንዱ ፖርቲ ወደ ሌላው ፖርቲ መሄዳቸው የእለት ተእለት ተግባር ባይሆንም የተለመደ ክስተት ነው፡፡

ለእኛ ሀገር ፖለቲካ ግን ይህ አስደንጋጭና ነውር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ግለሰቦች የፖርቲ አባል ሲሆኑ የግል አመለካከታቸውን ይተዋሉ? ለምን? አቶ ልደቱ አያሌው እንዲህ ይላሉ፡፡

..በእኛ ፖርቲ መሰረታዊ የሆኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች በፖርቲ ደረጃ በቂ የሆነ ጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸው አቋም ይወሰድባቸዋል፡፡ የፖርቲውም አመራሮች ያንኑ ነው የሚያንፀባርቁት፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ ያልሆኑና ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥቃቅን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የአመራር አባሎች የግድ አንድ ዓይነት አቋም እንዲኖራቸው ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያንን አቋማቸውን ለመገናኛ ብዙሀን ሲገልፁ ..ይህ የግል አቋሜ ነው፡፡.. ማለት መቻል አለባቸው፡፡ በፖርቲ ደረጃ አቋም የተወሰደበትና በፖርቲው የውሳኔ አሰጣጥ ደንብ በአብላጫ ድምፅ የተወሰነ ከሆነ ሁሉም አመራሮች ያንን ነው ለህዝብ የሚገልፁት፡፡ የግል አቋሙንም የሚገልፅ አመራር በእሱ አቋምና በፖርቲው አቋም መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት በግልፅ ማሳየት መቻል አለበት፡፡ በፖርላማ ውይይት ጊዜ በተለየ ሁኔታ የፖርቲው አቋም ካላስፈለገ በቀር እያንዳንዱ ሰው የግል አቋሙን ማንፀባረቅ ይችላል፡፡ በኢዴአፖ-መድህን በኩል በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ችግር ገጥሞን አያውቅም..

ዶክተር መራራ ጉዲና በበኩላቸው ..ማንም የፖርቲው አባል መቶ በመቶ የፖርቲውን ፖሊሲና ስትራቴጂ አይደግፍም፡፡ በተለይ ሰፊ ስብስብ በሚሆንበት ጊዜ በአንድ ሀሳብ ያምናል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቁ ዓለም ፖለቲካ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሚባለው መርህ ይመራል፡፡ አንድ ውሳኔ ከላይ ሲወሰን የበታች አካላት ቢያምኑበትም ባያምኑበትም የሚፈፅሙበት ሂደት ነው፡፡ የእኛም ድርጅት በዚህ መርህ ተፅእኖ ሥር ነው፡፡ እርግጥ ጥሩም መጥፎም ገፅታዎች አሉት፡፡ አንድ የፖለቲካ ፖርቲ በአብላጫ ድምፅ አንድ ነገር ከወሰነ አባላት ያንን ለማስፈፀም መንቀሳቀሳቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ልዩነቶች በማይሆን መንገድ ይጨፈለቁና ችግር ይፈጠራል፡፡ በአግባቡ ልዩነቶች ከተስተናገዱ በኋላ ላይ ውሎ አድሮ ያ የተጨፈለቀው ሀሳብ ብዙ ሰው ከደገፈው ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል.. በማለት ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

የፖለቲካ ፖርቲ አቋም በአባላቱ አብላጫ ድምፅ ይወሰናል፡፡ ስለዚህ አባላቱ አቋማቸው ከተለወጠ ፖርቲውም ፖሊሲና ስትራቴጂውን ለመቀየር ይገደዳል፡፡ በተቀየረው ፖሊሲና ስትራቴጂ ያመኑበት አባላት ሲቀጥሉ የተቃወሙትና ያላመኑት ከፖርቲው ይለያሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም የአባላቱን አመለካከት ያስቀይራሉ፡፡ ሁኔታዎች አጣብቂኝ ውስጥ ሲከቷቸውም በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣን እስከመልቀቅ ይደርሳሉ፡፡ በእንግሊዝ የሌበር ፖርቲ የእንግሊዝን የአውሮፖ ህብረት አባል መሆን ሲቃወም የነበረና አባላትንም በዚህ ሀሳብ ሥር ያሰባሰበ ቢሆንም ቶኒ ብሌር አመራሩን ሲረከቡ ግን ፖርቲው ሀሳቡን ቀይሮ እንግሊዝ የአውሮፖ ህብረት አባል መሆን አለበት የሚል አቋም ያዘ፡፡ ብሌር የኮንሰርቫቲቭ ፖርቲ መሪን ጭምር በማሳመን ወደ ሌበር ፖርቲ ማምጣት ችለው ነበር፡፡ በእኛስ ሀገር ግለሰቦች ከፖርቲው የተለየ አቋም ሲኖራቸው ምን ያደርጋሉ? አቶ ልደቱ አያሌው እንዲህ ይላሉ፡፡

..በፖርቲው መሰረታዊ የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳይ ላይ ልዩነት ካለው አንድ ግለሰብ አባል ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡ ያ ሰው መነጠልና መውጣት አለበት፡፡ ነገር ግን ያ አቋመ ትክክል ነው፤ ብሎ የሚያምን ከሆነ የውይይት መድረክ ተፈጥሮ የእሱ ሀሳብ በፖርቲው ውስጥ ተቀባይ እንዲሆን መታገል አለበት፡፡ ማሳመን ካልቻለ ጥሎ መውጣት መቻል አለበት..

ዶክተር መራራ ጉዲናም ..በአንድ የፖለቲካ ፖርቲ ውስጥ በጣም ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ በምስራቁም በምዕራቡም ዓለም ያለ ነው፡፡ የፖርቲ ምሰሶ የሆኑ ሰዎች ፖርቲው የሚወስናቸውን ነገሮች አቅጣጫ ያስይዛሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በሚወጡ ጊዜ ችግር ይፈጠራል፡፡ ግለሰቦች በአንድ ፖርቲ ህልውናም ሆነ በአንድ ሀገር የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና አለ፡፡ ግለሰቦች ለፖርቲው ደንብ ሊገዙ ይገባል፡፡ ነገር ግን ፖርቲውን ያደራጀው ሰው ..ይህ የእኔ ቤት ነው፤ እንደፈለኩ አዝበታለሁ.. ካለ ችግር ይፈጠራል፡፡ በእኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ይሄ ሲፈጠር አያለሁ፡፡ ፖርቲዎች በግለሰቦች እጅ ቢደራጁም የሕዝብ ንብረት በመሆናቸው ግለሰብ ከፖርቲ በላይ መሆን የለበትም፡፡ ግለሰቦች ራሳቸው ፖርቲ የሚሆኑበት ስርዓት መፈጠር የለበትም፡፡ በዚያኑ ያህል ፖርቲ የግለሰብን ነፃነትና ሰብአዊ መብት በሚነካ መልኩ ባሪያ ሊያደርጋቸው አይገባም.. በማለት የእኛን ሀገር ችግር ያሳያሉ፡፡

በግለሰብ ደረጃም ይሁን በድርጅት በኩል አቋም ከተለወጠ መሰልን ፍለጋ ሌላ አማራጭ መፈለጉ የዘመናዊ ዲሞክራሲ አንድ አካል ነው፡፡ በእኛስ ሀገር ግለሰብ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎችና አጠቃላይ ህብረተሰቡ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ገዢውን ፖርቲ ጨምሮ ከአንዱ ፖርቲ ወደ ሌላው ፖርቲ መዘዋወር ምን ችግር አለው?

አቶ ልደቱ አያሌው እንዲህ ይላሉ ..ምንም ችግር የለውም፡፡ የሀገራችን የፖለቲካ አቅጣጫ መሄድ ያለበት በዚህ መልክ ነው፡፡ ሁሉም ፖለቲካ ፖርቲዎች ዓላማቸው ሀገሪቱን ከድህነት ማውጣት፣ ሠላም እንዲሰፍንባት ማድረግና የበለፀገች እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡ ፖሊሲ እና ስትራቴጂአቸው ይለያይ እንጂ ዞሮ ዞሮ ለሀገር ጥቅም ነው የሚታገሉት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አቋምህ ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከአንድ ፖርቲ መዘዋወር እንደ ጤናማ እንቅስቃሴ ነው መታየት ያለበት፡፡ ይህ እንደ ነውር እየታየ ያለው ስለዲሞክራሲ፣ መድብለ ፖርቲ ስርዓትና ስለመቻቻል ፖለቲካ ያለን አመለካከት ከሚጠበቀው በታች ደካማ በመሆኑ ነው፡፡ ተቀናቃኞቼ ..ልደቱ ኢሕአዴግ ሆነ፡፡..የሚል አሉባልታ ሲያስወሩ ነበር፡፡ አመለካከቴና የምከተለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ከኢሕአዴግ ጋር የማይሄድ በመሆኑ እንጂ እስከአሁን የሄድኩበት መንገድ ስህተት መሆኑን ባምን ኢሕአዴግ መሆን መብቴ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ማለት ሁለት ፖርቲዎች ጠላት ናቸው፤ ማለት አይደለም፡፡ ወደፊት ..ሰዎች እንዲህ ተብለው ይወቀሱ ነበር.. የምንልበት ጊዜ ይኖራል ብዬ ነው የማስበው..

ዶክተር መራራ ጉዲና ..የእኛ ሀገር ፖለቲካ የአድማ ፖለቲካ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ምስጢር ነው፡፡ ግልፅ መሆን፣ መወያየትና ሀሳብ መለዋወጥ ምስጢር ከማውጣት ጋር ነው የሚያያዘው፡፡ ስርዓቱ በብዙ መልኩ ክፍተት የሌለውና ዝግ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ማድረግ ከጥርጣሬ ፖለቲካ ላልወጣ ስርዓት አስቸጋሪ ነው፡፡ የድሮ የልጅነት ጓደኞቼ የነበሩና አሁን የኦህዴድ ባለሥልጣናት የሆኑ ሰዎች ከዶክተር መራር ጉዲና ጋር ታዩ ተብለው እንዳይወቀሱ በመስጋት መንገድ ላይ ሲያገኙኝ በፍርሀት ጥለውኝ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሆነ ፖርቲ ይህን ሆደ ሰፊነት ካላሳየና ምሳሌ ካልሆነ በችግር ውስጥ የምንቀሳቀሰው ተቃዋሚ ፖርቲዎች ይህን ማድረግ አንችልም፡፡ እስኪ ብዙ ነገር ማድረግ የሚችሉትን ኢትዮጵያዊ ምሁራን እያቸው፤ ለተቃዋሚም ሆነ ለመንግሥት እየጠቀሙ አይደለም፡፡ ተቃዋሚ ሲሆኑ መንግሥት ጫና ያሳድርባቸዋል፡፡ ለመንግሥት ሲሰሩ ..ለሆዳቸው ነው.. ይባላል፡፡ ገዢው ፖርቲ አባላቱ እንዳይለወጡ ነፃነት የማይሰጠው ራሱ ሳይለወጥ ፖሊሲ ለውጫለሁ ስላለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለምን በአፍ እንጂ በተግባር አልተወውም፡፡ ስለዚህ ከራሱ የዘለለ ቋሚ ስርዓት ስላልዘረጋ ለሌሎች ምሳሌ መሆን አልቻለም.. ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱ ፖርቲዎች አሁን ስላሉበት ሁኔታና የሥም ችግር ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ልደቱ አያሌው ..ከሦስት ዓመት በፊት ቅንጅቱን ስንቀላቀል ችግር እንዳለ እያወቅን ነው፡፡ ፖርቲያችን እንደ ተለጣፊና አፍራሽ ተደርጎ የአሉባልታ ዘመቻ ይደረግበት ነበር፡፡ ስለዚህ ያኔ ወደ ቅንጅቱ እንድንገባ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ ግፊትና ጫና ነበረብን፡፡ ችግሮቹም ይበልጥ በመተዋወቅና በመነጋገር ምናልባት መስመር ሊይዙ ይችላሉ ብለን ነው የገባነው፡፡ አሁን ሦስት ዓመት አልፎ በአጠቃላይ በቅንጅቱ የደረሰውን ኪሳራና እኛ ላይ የደረሰውን ጉዳት ስንመዝን የትኛውም ተፅእኖ ቢደርስብን፣ የትኛውንም ያህል አስቸጋሪ ውሳኔ ቢሆን ኖሮ አብረን ላለመስራት ወስነን ቢሆን ኖሮ ይሻል ነበር፣ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰናል፡፡ አብረን በነበርንበት ወቅት በነበረው አሠራር ቅንጅት የሚባለው አካል የትም እንደማይደርስ፣ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የሚችል ኃይል እንዳልሆነ፣ እንደ አንድ የፖለቲካ ስብስብም አብሮ ሊቀጥል እንደማይችል መቶ በመቶ እርግጠኞች ነበርን፡፡ ለዚህ ነው በታሪክም ተጠያቂ ላለመሆን በተፅእኖ ሥር ሆነን ለመገንጠል የወሰንነው፡፡ አሁን ህዝቡ እያዬ የሚደነግጥባቸውና የሚገረምባቸው ነገሮች ለእኛ አዲስ አይደሉም፡፡ ህዝቡ ያኔ ማዳመጥ የፈለገው የተማሩ ሰዎችን ነበር፡፡ ስለዚህ አደጋውን መታደግ ሳይቻል ቀረ፡፡ በዚህ እናዝናለን፡፡ ዛሬ ሕዝቡ ትክክለኛውን ነገር እያወቀ በመምጣቱ ደስተኞች ነን..

ዶክተር መራራ ጉዲና በአብኮና በአህኮ መካከል ምንም የፖለቲካ የሀሳብ ልዩነት እንደሌለ ይገልፃሉ፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ ፖርቲዎች ሀቀኛ ፌደራላዊ ስርዓት /ተገቢ የሆነ የራስ አስተዳደርና የሥልጣን ክፍፍል ያለው/ መመስረት፣ ኦሮምኛን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ማድረግ እና የመሬትን ጥያቄ በሪፈረንደም መመለስ ዋነኛ አላማቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በፖርቲያችን ላይ መፈንቅለ ድርጅት ለማድረግ የተወሰኑ አባሎቻችንን ይዞ ሄደ፡፡ ስለዚህ ከውጭ የመጣ ተፅእኖ ነው፡፡ ኦህዴድን በምርጫ ስላሸነፍነው ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤት ሥማችንን ለተገነጠሉ በጣም ጥቂት ሰዎች ሰጡብን፡፡ ስለዚህ የስም ለውጥ ለማድረግ ተገደድን፡፡ መንግሥት ፖርቲያችንን ለማዳከም ስማችንን ለመንገደኛ መስጠቱ ማንንም አይጠቅምም..

ዶክተር መራራ ጉዲና /ኢትዮጵያ ኮምፒቲንግ ኤቲክ ናሽናሊዝም ኤንድ ዘ ኩዌስት ፎር ዲሞክራሲ/ በተሰኘ መፅሀፋቸው ..የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች በክልል፣ በሀይማኖትና በብሔር ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው አቋም መለወጥን ከባድ አድርጎታል.. ብለዋል፡፡ ነገር ግን ለድሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና እና ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች በውይይት በመተማመን ግትር አቋምን በመለወጥ ሊደገፉ ይገባል፡፡

ከላይ እንደምሳሌ ያነሳናቸው ኦህኮና ኢዴአፖ-መድህንን ጨምሮ በበርካታ የፖለቲካ ፖርቲዎቻችን የሚስተዋለው ሽኩቻና አለመግባባት የወጡበት ማህበረሰብ መገለጫ ነው፡፡ ልዩነት እንደ ነውር በሚታይበት አገር ከ8ዐ በላይ ብሔርና ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ቋንቋችን፣ ባህላችን፣ አስተዳደጋችን፣ የፖለቲካ አመለካከታችን፣ ሀይማኖታችን ለቁጥር በሚታክትበት ሀገር ሁለት ሰዎች በግድ አንድ ካልሆኑ በምንልበት ማህበረሰብ ልዩነታቸው እንድዳኝ ለህዝቡ እንዴት ይቅረቡ? የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚባልበት ሀገር ..ጠላቴን ለምን ጠላው?.. የሚባለውስ እንዴት ነው? አማራጭ ሀይልን መፈለግ ሳይሆን ያለውን ኃይል ደምስሶ የሚገነባ ሀይል በሚፈለግበት ሀገር ገዥና ተገዢ እንዴትስ የሚስማሙበት ባህል ይፈጠራል? እርግጥ ዶክተር መራራ ጉዲና በመፅሀፋቸው ላይ እንደሚገልፁት ክልል፣ ሀይማኖትና ብሔርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ፖርቲ አባል የሆነ ሰው ሀሳቡን ለመቀየር መቸገሩ ላይገርም ይችላል፡፡

የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከመሆኑ አንፃር ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፖርቲዎች መብዛታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ሃይማኖትን በቀጥታ በመጠቀም የፖለቲካ ፖርቲ ማቋቋም እርግጥ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ይህ የማይለወጥ አቋም አይደለም፡፡ ሀገራችን አጥብቃ የምትፈልገውን ሰላም፣ ዲሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ሊያመጣ የሚችልን አካል በምንም ምክንያት ይቋቋም ሰዎች ይደግፉታል፡፡ አንዳንዴ አቋሞቹ አፋዊ ይሆኑና ልንታገልለት የቆምነው የሚሉትን ሰፊውን ህዝብ መገልገያ እቃ በማድረግ ለኃይል፣ ገንዘብና ዝና ጥማቸው ማርኪያ ሊያደርጉት የሚቋምጡ ኃይሎች መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ እኛስ ለምንደግፈው ሰው ያለን ድጋፍ ዘላለማዊ ነው? የምንቃወማቸውንስ ሁልጊዜም እንደማይለወጡ ነው የምናስባቸው? ሀሳብና አመለካከት በእውነታ፣ በጊዜ ሂደት፣ በተግባራዊ ተሞክሮ ሊለወጥ አይችልም? በሰዎች ሀሳብና አመለካከት የሚመሩት የፖለቲካ ፖርቲዎቻችንስ አቋማቸውን ሊለውጡ አይችሉም? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንመልሳቸው መልሶች መላ ቅጡ ለጠፋበት የፖለቲካ ፖርቲዎች የአሁኑ ሁኔታ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡

ለእያንዳንዷ የነገ ምኞች የአሁኑ ተግባራችን ስኬት ወይም ውድቀት ይሆናል፡፡ የማንም ኢትዮጵያዊ ምኞት የሆነው ዲሞክራሰያዊ ስርዓት ከግለሰብ፣ ከቤተሰብ፣ የህብረተሰብና ከህዝብ አጠቃላይ አመለካከት ይወለዳል፡፡ ገዢው ፖርቲና ተቃዋሚ ፖርቲዎች እንደ ሁለት አማራጭ ኃይሎች፣ የተጀመረውን እድገት የሚያፈርስ ሳይሆን የሚቀጥል ኃይል መፍጠር፣ ማደራጀትና ለሥልጣን ማብቃት የመንግሥት፣ የዜጎችና የተቃዋሚ ፖርቲዎች ተግባር መሆኑን ማመን፣ መቀበልና ማረጋገጥ እንዳለብን ልንረዳ የሚገባው አሁን ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን ከሀሳብ ልዩነቶች ጀርባ ሁከትና ውድቀትን ሳይሆን የልዩነቱን ሥር ለመፈለግ ጉጉት ሊያድርብን ይገባል፡፡ ለምን እንደተለያየን ሲገባን መስማማት የምንችልበት ቀዳዳም በግልፅ እንገነዘባለን፡፡

በመጨረሻም የፖለቲካ ፖርቲዎቻችን የወደቁ እለት ሳይሆን፣ የእለት እለት ህይወታቸው የአቋም መለወጥን እንደ ገጠመኝ ሳይሆን እንደ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ሊቆጥሩት ይገባል እንላለን፡፡ ዘመናዊውን ሀሳብ የመግለፅ መብት መልክ ያስያዘው ቶማስ ኤመርሰን ..ሀሳብ የመግለፅ መብት ሀሳብህን ከመግለፅም በላይ የምትቃወመውን ሀሳብ በመስማት ይበልጥ ይገለፃል.. ያለው እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በሰለሞን ጐሹ

 
< Prev   Next >