| “ሃያ ጊዜ ደም ይለግስ” |
|
|
| Wednesday, 06 February 2008 | |
|
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በደም ባንክ አገልግሎት የለጋሾች ማስተባበሪያ በተዘጋጀው የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ በርካታ ወጣቶች ተሳትፈው ነበር፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው ጥር 25 ቀን 2000 ከጧቱ ሦስት ሰዓት ላይ ሲሆን በ1999 ዓ.ም የተመሰረተው የአገር አቀፍ ወጣት ደም ለጋሾች ክበብ አባላትና በፍቃደኝነት በየቀበሌው ካሉ ወጣት ማኅበራት እንደመጡ ለመረዳት ችለናል፡፡
ይህ አገር አቀፍ የወጣት ደም ለጋሾች ክበብ በዓመት ሁለት ጊዜ የደም ልገሳ ፕሮግራሞችን የሚያዘጋጅ ሲሆን እያንዳንዱ ወጣት በወጣትነት ዘመኑ ለሃያ ጊዜ ደም ይለግስ በሚል ራዕይ የተመሰረተ ነው፡፡ የክለቡ መሠረታዊ ሃሳብ ወጣቶች ከ16 እስከ 25 የእድሜ ክልል ውስጥ ሃያ ጊዜ ደም መለገስ ይኖርባቸዋል ከሚለው የዚምባብዌ አገር አቀፍ ወጣት የደም ለጋሾች ክበብ 20/25 የተወሰደ መሆኑን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደም ባንክ አገልግሎት የለጋሽ ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ አቶ በቀለ ጥሩወርቅ ገልፀውልናል፡፡ ቀይ መስቀል በር ላይ በርካታ ወጣቶች ደም ለመለገስ ተሰልፈዋል፡፡ ግቢ ውስጥም እንደዚሁ፡፡ ደም ወደሚሰጥበት አዳራሽ ስንገባ በርካታ ወጣቶች ደም ሲለግሱ ሌሎች ደግሞ የደም መስጫ ከረጢት በመያዝ ቦታ እስኪለቀቅላቸው ሲጠብቁ ተመለከትን፡፡ ጎን ለጎን ተኝተው ደም እየሰጡ የሚጨዋወቱ ጓደኛሞችን ጠጋ ብለን ሊያነጋግሩን ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠየቅን፡፡ አንደኛዋ ፈቃደኛ መሆናቸውን በፈገግታ ገለፀችልን፡፡ ሕሊና ፍቃዱ የሃያ ስድስት ዓመት ወጣት ነች፡፡ በዚያ ዕለት ደም የምትለግሰው ለዘጠነኛ ጊዜዋ እንደሆነና በተለያዩ የኅብረተሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚንቀሳቀሰው የሮትራክት ክለብ ኦፍ አቡጊዳ አባል እንደሆነችና የመጣችውም ክለቧን በመወከል እንደሆነ ነግራናለች፡፡ ሕሊና የሮትራክት ክለብ ኦፍ አቡጊዳ መስራች አባል ስትሆን የክለቡ አባል መሆኗ ከበፊት ጀምሮ በውስጧ የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማበርከት መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላት አመልክታለች፡፡ በማንኛውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፍ ኅብረተሰቡን ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውና ደም መለገስ ደግሞ የሰውን ልጅ ሕይወት ለማዳን የሚደረግ በመሆኑ ፍፁም የተለየ ደስታን እንደሚሰጥ ገልፃለች፡፡ በማንኛውም አጋጣሚ ደም ወደ ሚለገስባቸው ፕሮግራሞች ስትሄድ ጓደኞቿንና ዘመዶቿን በማስረዳትና በማሳመን ደም እንዲለግሱ እንደምታደርግ የምትናገረው ሕሊና በዚያ እለትም ሁለት ዘመዶቿን ይዛ መጥታለች፡፡ ታናሽ እህቷም በዚያ ዕለት ለአስራ አንደኛ ጊዜ ደም ሰጥታለች፡፡ እሷም ሆነ እህቷ በት/ቤት ባገኙት መረጃ በእንደዚህ ዓይነቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሰማሩ መቻላቸውን አስረድታለች፡፡ “በእኛ ማኅበረሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብዙም ያልተለመደ በመሆኑ በዚህ ረገድ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማምጣት መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል” ብላለች፡፡ ያነጋገርነው ሌላው ወጣት ናሆም አድነው ይባላል፡፡ በማይክሮሊንክ ሁለተኛ ዓመት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪ ነው፡፡ በአስኮ አካባቢ ከሚንቀሳቀሰው ፍቅርና ሰላም ከተባለ ወጣት ማኅበር ነው የመጣው፡፡ ፍቅርና ሠላም የወጣቶች ማኅበር በአካባቢው የሚያስፈልጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ የገለፀልን ወጣት ናሆም ደም ሲሰጥ ለሁለተኛ ጊዜው ነው፡፡ ከፍቅርና ሠላም ወጣቶች ማኅበር ስምንት አባላት ደም ሊለግሱ የመጡ ሲሆን ማንኛውም ወጣት ክብደቱ እስከፈቀደና ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ደም ከመስጠት የሚያግደው ምንም ነገር አለመኖሩን መረዳት እንዳለበት አመልክቷል፡፡ ለአስረኛ ጊዜ ደም ሲሰጥ ያገኘነው ወጣት ብሌን ግደይ ይባላል፡፡ እሱም የሮትራክት ክለብ ኦፍ አቡጊዳ አባል ነው፡፡ የደም ሥሩ አልገኝ ብሎ በአንድ አጋጣሚ ደም ሳይለግስ የተመለሰበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማንኛውም መልኩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሻሻል እያሳየ እንደሆነ በመጠቆም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ ቤተሰብ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ አጠገቡ የነበረች አንዲት ወጣትን በማመልከት ጓደኞቹንና የቅርድ ዘመዶቹን መጥተው ደም እንዲለግሱ መጥራቱንና እዚያው ፕሮግራም ላይ ቆይቶ ስልክ በመደወል መምጣት አለመምጣታቸውን እንደሚያረጋግጥ ነግሮናል፡፡ ሰዎችን መርዳት ትልቅ እርካታ እንደሚሰጥ ይህን ለማድረግ ደግሞ የግድ ገንዘብ እንደማያስፈልግ፣ ወጣቱ ጊዜውንና ጉልበቱን በእንደዚህ ዓይነት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማዋል እንደሚችል አስረድቷል፡፡ በዚያ ዕለት ለሰባት መቶ ወጣቶች ደም እንዲለግሱ ጥሪ መደረጉንና ከአንድ መቶ ሃምሳ እስከ ሁለት መቶ ዩኒት ደም ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደም ባንክ አገልግሎት የለጋሽ ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ አቶ በቀለ ጥሩወርቅ ገልፀውልናል፡፡ አቶ በቀለ እንዳብራሩት፣ ጥሪ ከተደረገላቸው ወጣቶች አምስት መቶ ያህሉ ቢመጡና ከእነዚህ መካከል ደም መስጠት የሚችሉት ሁለት መቶ ያህል ቢሆኑ የታቀደውን ያህል ደም ለመሰብሰብ ይቻላል፡፡ ከአርባ አምስት ኪሎ በላይ የሆነ ማንኛውም ወጣት ደም መለገስ የሚችል ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውለው የ450 ሚሊ ሊትር ደም መቀበያ የደም ከረጢት ነው፡፡ በዚያ የደም ከረጢት ደም ሊሰጡ የሚችሉት ደግሞ ክብደታቸው ከሃምሳ ኪሎ በላይ የሆኑ ወጣቶች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የደም ልገሳ ፕሮግራም የደም ባንኩን የደም ክምችት አስተማማኝ በማድረግ በኩል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ይህ አጋጣሚ ከተለያዩ ወጣት ክበባት የመጡ ወጣቶች ልምድ የሚጋሩበት መድረክም እንደሚሆን፣ ወጣቶች በሚያደርጓቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ቀይ መስቀል የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ “ወጣትነት ኃይል፣ ጉልበት ያለበት የእድሜ ክልል በመሆኑ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ የሚቻልበት ወቅት ነው” ብለዋል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |