| ኢራን ሮኬት አመጠቀች |
|
|
| Wednesday, 06 February 2008 | |
|
ኢራን ባለፈው ሰኞ የህዋ ማዕከሏን ስታስመርቅ ለጥናት አገልግሎት ትውላለች የተባለችውን ሮኬት አምጥቃለች፡፡ ድርጊቱ በአሜሪካ ወዲያውኑ ውግዘት የደረሰበት መሆኑን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙሀንን ዘገባ የጠቀሰው የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርት እንዳለው ሮኬቷ የተተኮሰችው ሴምናን እየተባለ በሚጠራው አውራጃ ከሚገኝና ከዋና ከተማዋ ቴህራን ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ካለ በረሀ ሲሆን ስሟም ካቮሽጋር 1 ይሰኛል፡፡ ትርጉሙ አጥኚ-1 ማለት ሲሆን የመተኮሱ ሂደት ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ የተሠራውን ሳተላይት ለማምጠቅ ያላት ዕቅድ አንድ አካል መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ሲን ማክኮርማክ ድርጊቱን “ሌላ አስፈሪ አዝማሚያ፣ ባለስቲክ ሚሳይሎችን ወደማምረት የሚያሸጋግር ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ተግባር” ብለውታል፡፡ የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አህመዲንጃድ በበኩላቸው በምረቃው ወቅት ባደረጉት ንግግር “በህዋ ውስጥ ወሳኝ ቦታ ሊኖረን ይገባል፡፡ ዛሬ ያየነው ኢራን በህዋ ውስጥ የመጀመሪያ ርምጃዋን ማድረጓን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህንንም ያደረገችው በተጠናና ትክክለኛ በሆነ መልኩ፣ አስባበት ነው” ብለዋል፡፡ ኢራን ሳተላይት መላክ የምትፈልገው የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቆጣጠር፣ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለደህንነት ተግባራት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሙስጠፋ መሐመድ ናጃር ኢራን “ኦሚድ” የተሰኘችውንና “ተስፋ” የሚል ትርጉም ያላትን በሀገር ውስጥ የተሰራች ሳተላይት በሰኔ ወር እንደምታመጥቅ መግለፃቸውንም የሀገሪቱን ዜና አገልግሎት ፣ፋርስን፣ ጠቅሶ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡ የሜርኩሪ እሳተ ገሞራ ታየ የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ድርጅት (ናሳ) የላካት መንኰራኩር ሜርኩሪን ቀርባ በማለፍ ስለኘላኔቷ አዲስ መረጃ ልካለች ሲል የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል፡፡ እንደዘገባው ከፀሐይ አጠገብ የመጀመሪያ ኘላኔት በሆነችው ሜርኩሪ ተጠግታ ለማለፍ የቻለችው መንኩራኩር ሜርኩሪ በሰፊው ተከስቶ የነበረ እሳተ ገሞራ ምልክት እንደሚታይባት የሚያሳይ መረጃ ለማዕከሉ ልካለች፡፡ በተጨማሪም ከመንኰራኩሯ የተገኘው መረጃ ከዚህ በፊት በካርታ ይታወቅ የነበረውን 45 በመቶ የኘላኔቷ ክፍል በ30 በመቶ በማሳደግ የኘላኔቷ 75 በመቶ ክፍል ካርታ እንዲኖር ያስቻለ ነው፡፡ በተጨማሪም በኘላኔቷ አካል ላይ ፣ስፓይደር፣ ብለው የጠሩት ድር መሰል ገፅታ መታየቱን አጥኚዎቹ የጆንስ ሆኘኪንስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጠቅሶ የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡ ይኸው ድር መሰል ገፅታ፣ ለስላሳ ሆኖ ከቆየ የኘላኔቷ አካል ጋር ተዳምሮ በኘላኔቷ በስፋት የተከሰተ እሳተ ገሞራ የነበረ መሆኑን ያመላከተ ነው ተብሏል፡፡ ህንድ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመመለስ እየሠራች ነው የህንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የሀገሪቱን ኢንተርኔት ፍጥነት በ8ዐ በመቶ ወደ ቀድሞ ለመመለስ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ የአሶሽየትድ ኘሬስ ዘገባ እንደሚለው አገልግሎት ሰጪዎቹ ጥረቱን በማድረግ ላይ ያሉት ሜዲትራኒያን አካባቢ በባህር ውስጥ በተከሰተ ብልሽት የእስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ኢንተርኔት አገልግሎት ችግር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ነው፡፡ የግብፅ ኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ታሪክ ከሚል በበኩላቸው አገልግሎቱ እስከ 8ዐ በመቶ ፍጥነቱን መልሶ ለማግኘት ተጨማሪ 48 ሠዓታት ይፈጅበታል ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት በሜዲትራኒያን ባህር ወለል የተቀበረ የአንተርኔት መስመር ሁለት ኬብሎች በመበላሸታቸው ችግሩ ሲፈጠር በህንድ ረቡዕ የሥራ ቀን ባለመሆኑ ችግሩ የታወቀው ሐሙስ ዕለት ነው፡፡ ህንድ በብልሽቱ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁት ቀዳሚውን ሥፍራ ስትይዝ በህንድ የመረጃ ቴክኖሎጂ ላይ ተመርኩዘው የሚሰሩ የአሜሪካና የአውሮፓ ኩባንያዎች ጥሪዎች አጨናንቀውት መክረማቸው ተጠቁሟል፡፡ በጊዜያዊነት የኬብል አገልግሎቱን ወደ ፓስፊክ ውቂያኖስ ማዞር በመቻላቸው አገልግሎቱ በመጠኑ ሊሻሻል መቻሉም ተጠቁሟል፡፡ ታዋቂው የኢንተርኔት ስያሜ ፣ያሁ፣ ለጨረታ ቀረበ ታዋቂውና ተወዳጁ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ያሁ ለጨረታ ሲቀርብ ማይክሮ ሶፍት 44.6 ቢሊዮን ዶላር የግዢ ጥያቄ ባለፈው ሰኞ አቅርቧል፡፡ ሳይንስ ኒውስ እንደዘገበው ሽያጩ ከተሳካ የያሁ እውቅና ጠፍቶ እንደ አንድ የንግድ ስም ስያሜ ሊሆን ይችላል፡፡ ያሁ በአንድ ወቅት በሠራተኞች ተፈላጊ የነበረ መሆኑን የሚገልፀው ዘገባው ሁኔታዎች ጥሩ አለመሆናቸውን በመገንዘብ ባለአክሲዮኖች ሠራተኞች ድርጅቱን ጥለው መሄድ የጀመሩት ቀደም ሲል ጀምሮ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ እንደ ዘገባው ድርጅቱ ራሱ ባለፈው ሳምንት 1 ሺህ ሠራተኞችን እንደሚቀንስ ይፋ አድርጓል፡፡ የድርጅቱን ውድቀት ያፋጠነው እንደ ፣ጉግል፣ እና ፣ማይ ስፔስ፣ ያሉ አዳዲስና ብርቱ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች እንቅስቃሴ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የተለየ አመጋገብ ያላቸው ተኩላዎች ተገኙ በካናዳ አርክቲክ በረዶ የሚኖሩ የተኩላ ዝርያዎች በቢቢሲ ፊልም ቀራጮች በተነሳ ምስል ከውሀ ውስጥ አነስተኛ እንስሳ አውጥተው ሲመገቡ መታየቱ ሲገለፅ ቢቢሲ ኤክስፐርቶች ጉዳዩ ያልተለመደ እንደሆነ ገልፀዋል ይላል፡፡ በካናዳ ሰሜናዊ አርክቲክና በግሪንላንድ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖሩትን እነኝህ ተኩላዎች መመልከት እጅግ አልፎ አልፎ የሚታይ ክስተት ሲሆን እንስሳቱ ከሰው ርቀው መኖርን የሚመርጡ ናቸው ተብሏል፡፡ የቢቢሲ ፊልም አንሺዎች ቡድን እንስሳቱን ለመቅረፅ በአቅራቢያው ባለ በኤልስሚር ደሴት ለሳምንታት መኖር ግድ ሆኖበት ነበር፡፡ ዘገባው የአሜሪካ የእንስሳቱ ኤክስፐርቶችን ጠቅሶ እንዳመለከተው ተኩላዎቹ ትላልቅ እንስሳትን በመብላት ብቻ የተወሰኑ እንደነበሩና ትናንሽ የባህር እንስሳትን መብላታቸው አዲስ ነገር መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ቡድኑ ወደ ስፍራው የተጓዘው ተኩላዎቹ ከዓመታት በፊት በአካባቢው ታይተዋል ከሚል ጥቆማ ተነስቶ ሲሆን ተኩላዎቹ ወሀ ውስጥ (በሐይቅ መካከል) እየዋኙ ትናንሽ እንስሳት ማደናቸውን መመልከት አስገራሚ መሆኑ ተገልጿል፡፡ “ጉግል” የተጠበቀውን ትርፍ አላገኘም በዌብ ሳይት በሚደረጉ ፍለጋዎች ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነው “ጉግል” ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የመጨረሻ ሩብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ከተገመተው ያነሰ መሆኑን ቢዝነስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ጉግል በሩብ አመቱ ለሸሪኮቹ ከከፈለው ክፍያ በኋላ ያገኘው የተጣራ ትርፍ 3.39 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ትርፉ ከአሜሪካ የስቶክ ገበያ (ዎልስትሪት) ግምት በ60 ሚሊዮን ዶላር ያንሳል፡፡ ኤሪክ ሽሚድት የጐግል ሊቀመንበርና ቺፍ ኤክዚጊዩቲቭ ኦፊሠር በበኩላቸው ድርጅቱ ሞዴል አሠራሩን እንደሚቀጥልበትና አዲሱ የፈረንጆች ዓመት ለድርጅቱ የተሻለ ጊዜ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡ የአራተኛው ሩብ ዓመት ትርፍ ካለፈው በ17 በመቶ ያደገ መሆኑን፣ ሽያጩም በ51 በመቶ መጨመሩን ሚ/ር ሽሚድት ተናግረዋል፡፡ የፍለጋ ድረ-ገፁ ባለቤት የሆነው ኩባንያ ዋና ገቢ በድረ ገፁ ላይ የሚደረግ ማስታወቂያና ሽያጭ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |