| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 06 February 2008 | |
|
/መንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራን ለማጠናከር በሁሉም መስክ አስፈላጊ ኢንፎርሜሽን እንዲሰበሰብና አዲስ የመረጃ ድረ ገፅ እንዲከፈት በወሰነው መሰረት በክቡር ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ያሰባሰበውን መረጃ በማጠናቀር ለካቢኔ ሪፖርት እያዘጋጀ ነው/
- በሉ፣ በሉ ሁሉም መረጃ ዌብ ሳይት ላይ ጫኑ፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ በአገራችን ያለው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ሁኔታ በሚመለከት ያለውን ተጨባጭ አሃዝ ጫናችሁ? - ኧረ d ገና ነን፡፡ - ለምን? ፍጥነት ያስፈልጋል ብዬ አልነበረም፡፡ የዘገያችሁበትን ምክንያት ኋላ በፅሁፍ ታቀርባላችሁ፡፡ አሁን ግን ጫኑት፡፡ - ችግሩ እሱ አይደለም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ችግሩ እሱ ነው፡፡ ሌላ ችግር የለም፡፡ መረጃ እንደልብ ነው፡፡ - አይደለም፣ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ምንድን ነው ችግሩ? - ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር፣ ከጤና ጥበቃ የመጣው መረጃ ይህን ያህል ሰው በኤች.አይ.ቪ እንደተያዘ ያሳያል፡፡ - ትክክል ነዋ፡፡ - ይቆዩ ክቡር ሚኒስትር፣ እዚህ ጋ ደግሞ ከብሄራዊ ኮሚቴ የመጣው እጥፍ ያደርገዋል፡፡ አሃዙ መቶ በመቶ ይለያያል፡፡ እዚህ ያለው፣ የውጭ ተቋም ያጠናው አሃዝ ደግሞ ሁለት መቶ ጨምሮ አስቀምጦታል፡፡ ይህ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ደግሞ 50 በመቶ አሃዙን ይቀንሰዋል፡፡ - እና? - እናማ ክቡር ሚኒስትር የትኛውን አሃዝ ነው ትክክለኛ ብለን የምንጭነው? - ሁሉንም ጫኑታ፡፡ - እንዴ መሳቂያ ልንሆን? - ትመሰገናለህ እንጂ ለምን መሳቂያ ትሆናለህ? - ክቡር ሚኒስትር፣ እርስ በራሱ የሚጣረስ መረጃ እኮ ነው፡፡ አስር ዓይነት የተለያየ አሃዝ ነው ያለው፡፡ - አገራችን በዴሞክራሲ ታምናለች፡፡ የተለያዩ አመለካከቶች ቢንፀባረቁ ምን ችግር አለበት? - እንዴ ክቡር ሚኒስትር ስለአሃዝ ነውኮ የምናወራው፡፡ - አሃዝ ከዴሞክራሲ ጋር አይሄድም ያለህ ማነው? - ዴሞክራሲ አለ ተብሎ እኮ አንዱ የአድዋ ጦርነት በ1888 ዓ.ም ነበር ሲል ሌላው መብት አለኝ ብሎ በ1456 ዓ.ም ነበር ይላል ማለት አይደለም፡፡ - በል በል አትፈላሰፍብኝ፡፡ ይልቁንስ ጊዜ የለም በአስቸኳይ የኢንቨስትመንት መረጃ በሙሉ ዛሬ ጭናችሁ ጨርሱ፡፡ - እሱም ችግር አለበት ክቡር ሚኒስትር፡፡ - የእናንተ ነገር አሁንስ አልገባ አለኝ፡፡ ስራ ነው የያዛችሁት ቀልድ ወይስ የመጣላችሁ መረጃ አላስደሰታችሁም? - እንዴት ክቡር ሚኒስትር? - ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የአስር ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አገኘች የሚለው አናደዳችሁ እንዴ? - ክቡር ሚኒስትር፣ እሱም ቢሆን ብር እንጂ ዶላር ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ ዓመት ያን ያህል ዶላር ማለት መቶ ቢሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ - ታዲያ ብር አድርጉትና ጫኑታ፡፡ - እሱ ብቻም አይደለም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እሺ ሌላ ምን አለ ታዲያ? - ክቡር ሚኒስትር የተገኘ ኢንቨስትመንት ማለትና የተመዘገበ የኢንቨስትመንት ጥያቄ ማለት አንድ አይደለም፡፡ - በል ለያያቸው፡፡ - ለመመዝገብ ሁሉም ሊመዘገብ ይችላል፡፡ ተመዘገበ ማለት ግን ሥራ ላይ ዋለ ማለት አይደለም፡፡ - ለምን ሥራ ላይ አይውልም? ተመዘገበ ማለት ወደ ኢንቨስትመንት ገባ ማለት ነው፡፡ - አይደለም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ገንዘብ አጥሮት የሚተው አለ፡፡ ቢሮክራሲው አሰልችቶት ትቶ የሚወጣ ዲያስፖራና የውጭ ኢንቨስተር አለ፡፡ ኢንቨስተር ለመምሰል ለጉራ ብቻ ወረቀት የሚይዝ አለ፡፡ - አንተ አሉታዊው እንጂ አዎንታዊው አይታይህም፡፡ በል በል ጫነው፡፡ - ኧረ በኋላ መሳቂያ እንሆናለን፡፡ - ሲሳቅብን እናርመዋለን፡፡ እንዲያውም የኢንቨስትመን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል መሬት ለእርሻና ለኢንቨስተር የተዘጋጀ እንደሆነም ጫኑት፡፡ - መረጃውስ? - በቀደም በእኔ ፊርማ መረጃ ስጡን ብለን ለክልሎች በሙሉ ልከን የለም ወይ? - ተልኳል፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እና? - መልስ ግን አልተገኘም፡፡ - አንድም መልስ የለም? - ሲዘጋጅ ይላክላችኋል አሉን፡፡ - በደንብ ጫን አድርጋችሁ ስለማትጠይቁ ነዋ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር፣ እንኳን ራቅ ያሉት እዚህ አዲስ አበባ ያሉት ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችምኮ መረጃ ላኩልን ብለናቸው አላልኩም፡፡ - ያገኟታላ.. - የእርስዎ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጭምር አላከም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እኔስ እዚህ ኮሚቴውን ስለምመራ የቢሮዬን ሥራ ለመስራት ጊዜ ስላጣሁ ነው፡፡ ሌላው ሚኒስትር ምን ሆነ? - ክቡር ሚኒስትር፣ አሁን ማን ይሙት ኮሚቴ የማይመራ ሚኒስትር አለ? - ምን ለማለት ፈልገህ ነው? - ኮሚቴን መሰብሰብ አይደለም ምክንያቱ፣ የፍላጎት አለመኖር እንጅ የጊዜ እጥረት አይደለም ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ - አትፈላሰፍብኝ፡፡ አሁን ክልልም ይሁን ሚኒስትር የላከ የለም ነው የምትለኝ? - የእነሱ አለመላክ ብቻ እኮ አይደለም ችግሩ፡፡ መረጃ እንዲያሰባስቡ ያሰማራናቸውም የሚያመጡት መረጃ የሚያስቅ ነው፡፡ - እንዴት? - ለምሳሌ እዚህ ላሳይዎት፡፡ በኢትዮጵያ ሃያ የሬዲዮ ጣቢያዎች አሉ የሚል መረጃ ይዘው መጡ፡፡ - እንዴት ሆኖ ሃያ ይሆናል? - የሙዚቃ ፕሮግራም፣ የኤች.አይ.ቪ ፕሮግራም፣ የቻምበር ፕሮግራም ቆጥረው ሬዲዮ ጣቢያ አደረጉት፡፡ - በል፣ በል አሁን ይጫንና ኋላ ይስተካከላል፡፡ ለካቢኔው ሪፖርት የምናደርግበት ቀን እየተቃረበ ስለሆነ ዝም ብለህ ጫን፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርስ ላከ? - የትምህርት ሚኒስቴር የላከው አለ፡፡ እሱም ምስቅልቅል ያለ ነው፡፡ - አንተ ሰውየ ጤነኛ አይደለህም፡፡ ለምንድን ነው የሚመሰቃቀለው? - ኮሌጅ፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚለው የተምታታ ነው፡፡ እውቅና እና ቅድመ እውቅና የሚባለውም የተምታታ ነው፡፡ በትምህርት ላይ አስር ዓይነት የተለያዩ ስታቲስቲክሶች አሉ፡፡ እሱን መጫን መንግሥትን ይጎዳል፡፡ - ለምን? - በ1995 የተመዘገበ መረጃ ብቻ ነው ያለው ክቡር ሚኒስትር፡፡ በመረጃ ላይ ያለው አመለካከት እጅግ ደካማ ነው፡፡ - ሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገርና አራት ሚሊዮን ህዝብ ባላት ከተማ እየተቀመጥን መረጃ አዋቂ የለም ማለት ስድብ ነው፡፡ - እሱም ራሱ አጠያያቂ ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ምኑ? - ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ 80 ሚሊዮን የአዲስ አበባ ሕዝብ 4 ሚሊዮን የሚለው፡፡ - እንዴት? አገር ያወቀውን፡፡ - በመረጃ መደገፍ አለበት፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - በቃ በአንተ አመለካከት ኢትዮጵያ 13 የፀሐይ ወራት አሉዋት የሚለው ካልሆነ ሌላው ሁሉ ማስረጃ የለውም፡፡ - 13 የፀሐይ ወራት የሚለውም አጠራጣሪ ነው፡፡ ዝናቡና ብርዱ አስራ ሶስት የፀሐይ ወራት የሚለውን እየሻረው ነው፡፡ - ለመሆኑ በትክክል ስንት ልጆች እንዳሉህ ታውቃለህ? - በተለምዶ አራት፣ ያልተነገረኝ ግን የእኔ ልጅ የሆነም ሊኖር ይችላል፡፡ - የተመዘገበው ግን አራት ነው ብለህ በእርግጠኝነት ትናገራለህ፡፡ - ለአገር የማይጠቅም ስለሆነ ነው እንጅ በዌብ ሳይቱ በእርግጠኝነት የምጭነው እሱን ብቻ ነው፡፡ - በል በል አሁን ወሬ አታብዛ፡፡ ምን ይሁን አሁን? - በቃ ይህ የእኛ ኮሚቴ ፈርሶ ስራው በስታትስቲክስ ቢሮ ወይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወይም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ይካሄዱ፡፡ - ለካቢኔ የምናቀርበው ሪፖርት ይህ ይሁን እያልከኝ ነው? - በሪፖርቱ ማጠቃለያ ይህ ይቅረብ፡፡ - መደምደሚያ ስለሆነ መግቢያውና ይዘቱ ምን ይሁን? - መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ራሱ በተጨባጭ ማስረጃ መቅረብ ተጀመረ ማለት ነው፡፡ - የተሰጣችሁን ስራ የመስራት አቅም የላችሁም ቢሉንስ? - በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር፣ እሱም ቢሆን ተጨባጭ መረጃ ነው፡፡ - የፈለገው ይሁን የተገኘውን ጫነው፡፡ ከዛ የአዲስ ድረ ገጽ መመረቂያ ብለን በትልቅ ሆቴል የኮክቴል ግብዣ እናድርግ፡፡ በሂደት ይስተካከላል፡፡ ሁሉንም ባለሥልጣን ጠርተን ስናስመርቅ ያኔ ሁሉም ያደንቁታል፡፡ - በኋላ ሲጋለጥ የራሱ አደጋ አለዋ፡፡ እንደ እንትኑ ይሆናል፡፡ - እንደምኑ? - በኤክስፖርትነት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሸልሞ በነገታው ባሌስትራውን ወርቅ አስመስሎ በመላክ ተጠርጥሮ እንደታሰረው ሰውዬ ዓይነት፡፡ - አንተ ደግሞ በጎ ነገር አይታይህም፡፡ ሁልጊዜ ኔጌቲቭ፡፡ - መጀመሪያ ግን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስለ አመራረቁ ብናሳውቅና ራሳቸው መጥተው ቢመርቁት፡፡ - እውነትክን ነው እንደዛ እናደርጋለን፡፡ አሳውቄያለሁም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር መቼ አሳወቁ? - ከሶስት ቀን በፊት፡፡ - አልነገሩኝም፡፡ - ይህች ናት ጨዋታ፡፡ አንተነህኮ ለኔ ማሳወቅ ያለብህ እንጅ እኔኮ ላንተ ማሳወቅ የለብኝም፡፡ ካንተ ጋር ስውል ሚኒስትርነቴን ረሳኸው? - አይደለም፣ አይደለም ክቡር ሚኒስትር ስለአቀራረቡ ተወያይተን የተሻለ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ብዬ ነው፡፡ ለመመካከር፡፡ - እ.. እንደዛ ከሆነ እሺ፡፡ - እና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አሉ? - በሶስት ቀን መልሱ ይነገርሃል ተብያለሁ፡፡ - ሶስተኛ ቀኑኮ ዛሬ ነው፡፡ - አንተ እውነትክን ነው፡፡ ልደውል እንዴ? - አዎን ይደውሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ረክቡር ሚኒስትሩ ደወሉሪ - ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ጤና ይስጥልኝ ደህና ነህ? በቀደም ከሶስት ቀን በኋላ መልስ ይነገርሃል ተብዬ ነበር፡፡ መልስ ተሰጥቶ ከሆነ እስቲ እይልኝና ንገረኝ፡፡ - እንዴ ክቡር ሚኒስትር ወድያውኮ መልስ ተሰጥቷል፡፡ - መቼ? - እስቲ የትናንትናው ሄራልድና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይመልከቷቸው፡፡ - እሺ አመሰግናለሁ፡፡ ረስልኩ ተዘጋሪ - አንተ መልስ ተሰጥቷል አሉ፡፡ እስቲ የትናንትናዎቹን ሄራልድና ዘመን ስጠኝ፡፡ ቶሎ በል፡፡ ረአገላብጠው አዩትሪ - ኧረ ምንም የለም፡፡ ዜናና ሃተታው ላይ የለም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር አለ፡፡ - የት አለ? - እዚህ የጨረታ ዓምድ ላይ፡፡ - ምን ይላል እስቲ አንብበው፡፡ - ጨረታ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ምን የሚል ጨረታ፡፡ - በኢትዮጵያ ላይ መረጃን ያጠናቀረ አዲስ ድረ ገፅ ስለሚከፈት ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እናስ ከዛስ? - መረጃ ለማሰባሰብና ድረ ገፁን ለመስራት መረጃውና አቅሙ አለን የምትሉ ይላል፡፡ - እሺ ከዛስ ምን ይላል፡፡ - ተጫረቱ.. |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |