Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow ጅብ
ጅብ Print E-mail
Thursday, 07 February 2008
ጅብ በጥንታዊው የአማርኛ ሆሄ አጠቃቀም ዥብ ሲሰኝ፣ በግእዙም ዝእብ ይባላል፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት “ዥብ ነጣቂ አውሬ መልከ ውሻ የሚመስል፣ ሆዳም ያህዮች ጠላት” ብለው ይፈቱታል፡፡
የውሻ፣ የድብ፣ የተኩላ፣ የቀበሮ ዓይነት፣ ጥንብ የወደቀበትን በማሽተት አውቆ ወገኖቹን የሚጠራ፣ በዱር የሚኖር አውሬ እንደሆነም የአለቃ ደስታ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ይገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ጅብ በተረትና ምሳሌዎች፣ በአነጋገር ዘይቤዎች ውስጥ ደምቆ ይታያል፡፡

•    ዥብ ሊወጉ፣ ባህያ ይጠጉ
•    ያህያ ባል ተዥብ አያስጥል
•    ባህያ ቆዳ የተሠራ ቤት
    ብትንትን ይላል ዥብ የጮኸለት፡፡

በዘይቤ ሲገልፁም “ዥብ አፍ” ሲል አፈ ሰፊ ሰው ለማለት ይጠቀሙበታል፡፡ አስማተኛ፣ ምትሀተኛ ሰውን “ዥብ ጋላቢ” ይሉታል፡፡

ጅብን የሚጋልቡ የተለየ ጥበብ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከዱር በምትገኝ ጨንገር (ለበቅ) መሬቱን እየመቱ ጅብን ይገሩታል፡፡ ከግልቢያው ሲወርዱ ለጅቡ አተላና አመድ መስጠት ግዴታ ነው፡፡

ጥንታውያን መምህራን ዥብ ፈናፍንታም ነው፤ ጾታው አይለይም ብለው ይጽፋሉ፡፡ በተረትም “ዥብ ሊሰር ኺዶ ተሰሮ ገባ” ይባላል፡፡

በአንዳንድ ጥናቶች እንደተገለፀው የሴቷ አባላዘር ከወንዱ ጋር መመሳሰሉ የጅብን ፆታ ለመለየት በጣም ያስቸግራል፡፡ ፆታውን ለመለየት ማስቸገሩ ወጣት ሴት ጅቦችን ከወንዶች ጥቃት ለመከላከል በጅቷቸዋል፡፡

ጅብ አሰሱን ገሰሱን ሁሉ ይበላል፡፡ እንስሳትንና ሰውን ያጠቃል፡፡ ክፉ ቀን ካልመጣ በቀር ሰውን በሕይወቱ እያለ አይበላም፡፡ ጅብ ሰው ከበላ ወቅቱ መጥፎ ነው፤ በተለይ ነጭ ጅብ ሰውን የሚተናኮልና የሚበላ ሲሆን በክፉ ቀን ጊዜ ይታያል ተብሎ ይታመናል፡፡
በድንጉጥነቱና ቦቅቧቃነቱ የሚታወቀው ጅብ በአፍሪካ አፈታሪኮች (ሌጀንድስ”ና ፎክሎር (የባህል ጥናት) ውስጥ ይገኛል፡፡ ከጥንቆላ፣ ከልዕለ ተፈጥሮ ክስተት ጋር ተዛምዶ ይቀርባል፡፡

የጅብን አጯጯህ ዓይነትና መጠን ተረድተው መጪውን ጊዜ የሚተነብዩ አሉ፡፡ የራሱን ወገን (ዝርያ) ለመጥሪያ የሚጠቀምበት፣ አንድ ነገር ለማግኘት የሚጮህበት፣ ወገኖቹን ለማንቃት የማስካካት ድምፁ እስከ ሦስት ማይልስ ድረስ ይሰማል፡፡

በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ስለ ጅብ ልዩ ልዩ አመለካከት አለ፡፡ በውቂያ ወቅት በአውድማው ውስጥ ካለፈ ወይም የተወቃውን እህል ከረገጠው፣ ከተንከባለለበት እህሉ ይበረክታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለዚህም ሲባል አብዛኛውን ጊዜ አውድማዎች የሚዘጋጁት ከመንደሮች ወጣ ካለ አካባቢና ሜዳማ በሆነ ስፍራ ነው፡፡

በአንዳንዶች አስተሳሰብ የጅብ አጭር እግር ተፈልጎ በጎተራ ውስጥ መክተት እህሉ እንዲትረፈረፍ፣ በረከት እንዲኖረው ያደርገዋል ይላሉ፡፡

ቡዳ ከጅብ ጋር ቅርበት አለው ተብሎ ስለሚታሰብ ቡዳ የበላውን ሰው ለሁልጊዜ እንዲሻለው በማሰብ ከጅብ አካላት ውስጥ ቅንጣቢውን በአንገቱ ላይ ከጥፈት ጋር እንደክታብ ያስሩለታል፡፡ በጅብ ቆዳ (በቁርበት) በማስተኛትም ያስለፈልፉታል፡፡ በዚህ ወቅት ህመምተኛው ወዲያውኑ የበላውን ቡዳ (ዓይን ወጊ) ማንነት ይናገራል፣ ተብሎም ይታመናል፡፡

በጎጃም አካባቢ የጋማ ከብት አሮንቃ ይዟት ገበሬው ወይም ነጋዴው ማውጣት ካስቸገረው ጅብ እስኪመጣ መጠበቅ የተለመደ ነው፡፡ የተቸገረችውንና ያስቸገረችውን ያህል የጅብ ድምፅ በቅርበት ስትሰማ በድንጋጤ ፈንቅላ ትሮጣለች፡፡

አህያ በአካባቢዋ ጅብ መኖሩን መምጣቱን በሽታ በመገንዘብ የተለየ ሁኔታ ስለምታሳይ ነጋዴዎች ለጥበቃ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡

ጅብን ለማዳ በማድረግ በሐረር ውስጥ የሚቀልቡ አሉ፡፡ ለጎብኚዎችም ይታያሉ፡፡ በተለይ በሐረሪ ባህል ከአሹራ በዓል ተያይዞ ምሽቱ ከተጋመሰ በኋላ ጅብን ገንፎ የማብላት ሥርዓት አለ፡፡ ጅብና የሰው ልጅ ረጅምና ውስብስብ ታሪክ አለ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ የጅብ ሬሳን ለልዩ ልዩ መድኃኒትነት ከመቅጽበት የሚቀራመቱ ግለሰቦች በየባህሉ መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡

የጅብና የሰው ዝምድናን በተመለከተ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው የጅብ ጥቅም በርካታ ቢሆንም የጅብ ልዩ ልዩ አካላት፣ ተረፈ ምርቶች ለልዩ ልዩ ሕመሞች መድኃኒት የሚውል ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ለተቅማጥ ማስታገሻ የጅብ ዓይነ ምድር በውሀ ተበጥብጦ ለሦስት ቀናት እንዲጠጣ ይደረጋል፡፡

ጅብ ብዙ ካልሲየም ከሰገራው ስለሚገኝ በጊዜው ፍቱን መድኃኒት ነው ተብሎ የሰው ልጅ ሳይወድ ይህን ድርጊት ተግባራዊ ማድረጉ ይገመታል፡፡ ወረርሺኝ ሲሆን ደግሞ ዓይነ ምድሩን በጢስ መልክ እንዲታጠኑት ይደረግ ነበር፡፡ ለዚህ በሽታም ዓይነምድሩን በድስት ይቀቀልና ከቅቤ ጋር ተቀላቅሎ በሽተኛው ማታ በሚተኛበት ጊዜ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራሱ ድረስ ይቀባና ጠዋት ይታጠበዋል፡፡

ሌባ ወደ ቤት ገብቶ እንዳይሰርቅም የጅብ ፀጉር፣ ከወንዝ የተለቀመ ጠጠር እንዲሁም ከጅብ ዋሻ አፈር በላም ቀንድ ይደረግና አንድ ጊዜ ቤቱን በመዞር መግቢያ በር ስር እንዲቀበር ይደረጋል፡፡

የሚወዷትን ሴት በፍቅር ለማንበርከክ ወይም በማሰር ወይም በወዳጅ ለመወደድም ከሴት ጅብ ብልት ፀጉር መዞ መያዝ ነው፡፡

ሀብት ለማግኘትም ከወንድ ጅብ ብልት ጫፉና ከግራ መንጋጋው ይወሰድና በግምጃ ጨርቅ ይቋጠራል፡፡ ይህም ግምጃ በቆዳ ተጠቅልሎ በአሸንክታብ መልክ ይታሰራል፡፡ ለሚጥል በሽታም ጆሮ አሰፋ የተባለው ተክል ስር ከጅብ ቅዘን ጋር በአፍንጫ እንዲሸተት ይደረጋል፡፡

ሕመምና ፈውሱ በሥርዓቱ ተጠንቶ ከጅብ አካል የሚገኝ ኬሚካል ጠቃሚ መሆን አለመሆኑን በሳይንሳዊ መንገድ መጠናት እንዳለበት ጅብና መንፈሳዊ ግንኙነትን በተመለከተም ባገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ ባህሎች ስለ እምነት አመጣጥና ዕድገት በደንቡ መጠናት እንደሚኖርበት አቶ አህመድ ያስረዳሉ፡፡

ጅብ በሐረር ኅብረተሰብ እንዴት እንደሚታይ ሲገልፁም እንደ ሌሎቹ ኅብረተሰብ ጅብ ከቡዳ ጋር ይገናኛል፡፡ በአንጻሩም የሼኾች መልእክተኛ ሆኖም ይነሳል፡፡ ስሙንም ደርመ ሼክ ወይም ወጣቱ ሼክ ይሉታል፡፡ በጩኸቱ ዓይነትና መጠን መልእክት ከዱር እንስሳ ጋር የሚለዋወጡ ግለሰቦች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ የተለመደ እውነት ሆኖ እነዚህ ግለሰቦች የጅብ ምስጢር ስለሚያጋልጡ በምሽት አይሄዱም ይባላል፡፡

ጅብን ገንፎ የማብላት ባህል ከታሪኩ አመጣጥ እንደምንገነዘበው በድሮ ዘመን በሐረር ረሃብ ነበር፣ ከዚህ አስከፊ ዘመንም በፊት በከተሞች አካባቢ እንደ ጽዳት ሠራተኛ፣ እንደ ለማዳ እንስሳ ሆኖ ይኖር የነበረው ጅብ ሳይቀር እንስሳትና ሰዎችን መተናኮል ጀመረ፡፡

በዚህ ጊዜ በጅብና በሐረሪዎች መካከል የነበረው ሰላማዊ ሕይወት ደፈረሰና አንድም ወዳጅ የሌለው ጠላት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ንጹሕ ልቦና ያለው በሰውና በጅብ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ይረግብ ዘንድ አንድ ጠቃሚ ሕልም አየ፡፡ በሕልሙም መሠረት የሐረር ሕዝብ ከተለያዩ የእህል ዓይነቶች የተዘጋጀውን ንጹሕ ቅቤ እንደ ውሃ የተንቆረቆረበትን ገንፎ በየዓመቱ አንዴ ለጅብ መቀለብ እርቀ ሰላም እንደሚወርድ ብስራት ተናገረ፡፡

የገንፎ አበላሉም ሥነ ሥርዓት የሚያስደንቅ ሲሆን የጅቦቹ     መሪ እየተንጐማለለ መጥቶ ከድንጋይ በተሠራ ቆሬ የቀረበውን ገንፎ ይቃኛል፡፡ የጐደለ ነገር ያለ መስሎ ከታየው ያፈገፍጋል፡፡ በአቅራቢዎቹም አማካይነት ቅቤም ይሁን ገንፎ ይጨመራል፡፡
እንደገና ለተጠናከረው ምርመራ የጅብ ንጉሥ ገንፎውን ያየዋል፡፡ ከተስማማው አንድ ሁለቴ ከጐረሰ በኋላ ለጭፍሮቹ ቦታውን ይተውላቸዋል፡፡ ጭፍሮቹም በሥርዓት ድርሻቸውን ካደረሱ በኋላ ያፈገፍጋሉ፡፡ ጅቦቹ በአበላላቸው ሁኔታ ያመቱ እድል ይወሰናል፡፡ በደንብ ካልበሉ ወይም ጠራርገው ምንም ካላስቀሩ በአድባራቱ አለቆች የተለያዩ ትርጉም ይሰጣቸዋል፡፡ በሽታ፣ ችግር ወይም ረሃብ ይመጣል ተብሎ ይተረጐማል፡፡ ዓመቱ የቀና ነው ተብሎ የሚገመተው በደንብ በልተው ትራፊም ሲያስቀሩ ነው፡፡ ጅብ በሚያበሉ ከከተማው ወጣ ባሉ አድባራት ምሽቱን በጸሎትና ልመና ያሳልፉታል፡፡ ጅቦችን ገንፎ በመመገብ ረገድ ከግንብ ውጭ ያሉ ሁሉም አድባራት ሲሳተፉ የነበሩ ቢሆንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ የሚሳተፉት ግን አቦከር ሐኪም፣ ዓብዱል ቀድር፣ ጅላኒና አወንጉሥ ብቻ ናቸው፡፡

እንደ አቶ አህመድ አገላለጽ፣ ጅቦች ከተፈጥሮ ክስተት ጋር ባላቸው ግንኙነት አማካይነት አንዳንድ ስለ አየር ጠባይ ሁኔታ መተንበይ ይቻል ይሆናል፡፡ ይህን የሥነ ሕይወት ጥናት በስፋትና በጥልቀት ማድረግ ቢቻል አንዳንድ የተፈጥሮ ዑደት በተሻለ መልክ መገንዘብ ይቻላል፡፡
 
< Prev   Next >