| የጥራት መለኪያ መሳሪያ ከአዲስ... |
|
|
| Thursday, 07 February 2008 | |
|
የጥራት መለኪያ መሳሪያ ከአዲስ አበባ ውጪ አገልግሎት ሊሰጥ ነው
ደረጃ ረቂቅ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል የተለያዩ ምርቶችና መሣሪያዎችን የጥራት ደረጃ ለመለካት የሚያስችለው ተንቀሳቃሽ የጥራት ደረጃ መመርመሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ሥራ ሊጀምር ነው፡፡ አገሪቱ የምትመራበት የጥራት ደረጃ ረቂቅ ሕግ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቧል፡፡ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በምህንድስና አቅም ግንባታ ፕሮግራም በኩል የገባው ይህ ተንቀሳቃሽ መሣሪያ ከአዲስ አበባ ውጪ አገልግሎት የሚሰጠው በአዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነው፡፡ ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የምህንድስና አቅም ግንባታ ፕሮግራም መሣሪያዎቹን ለጥራትና ደረጃዎች መዳቢ ባለስልጣን በስጦታ ያበረከተ ሲሆን ዋና አላማውም ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚካሄዱ አገልግሎቶች የጥራት ደረጃ ቁጥጥር እንዲያደርግ ታስቦ ነው፡፡ የተለያዩ መሣሪያዎችን ደረጃ ለመለካት ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አዲስ አበባ መምጣት ግድ ይል እንደነበር ተጠቅሶ አሁን ግን በዚህ ተንቀሳቃሽ መመሪያ ወደ ተፈለገበት ቦታ በመሄድ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ተብሏል፡፡ በአዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ መሣሪያዎችን በመለካት የሚጀመረው ይኸው አገልግሎት በተመሳሳይ በሌሎች የክልል ተቋማት ተዘዋውሮ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ ዛሬ በአዋሳ አገልግሎት የሚጀምረውን መሣሪያ በተመለከተ በአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የምህንድስና አቅም ግንባታ የጥራት መሰረተ ልማት ኤክስፐርት አቶ የኋላሸት እሸቱ ለሪፖርተር እንደገለፁት አገልግሎቱ በምህንድስና አቅም ግንባታ ፕሮግራም ስር ለመከናወን ከታቀዱት አራት ዋና ዋና ሥራዎች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ የጥራት መሰረተ ልማት ግንባታን በተመለከተ ሊከናወኑ ከታቀዱት ሥራዎች ውስጥ አንዱም ይህንን አገልግሎት በሥራ ላይ ማዋል ነው፡፡ “ይህ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ በአገር ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ደረጃዎችን ለመፈተሽ የሚያስችል ነው” ያሉት አቶ የኋላሸት በተለይ የጥራት ደረጃ መለኪያ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ስለነበር ደረጃቸው መታየት ያለባቸው መሣሪያዎች ተጭነው አዲስ አበባ መምጣት ግድ እንደነበር፣ ይህም መሣሪያዎቹን የሚጎዳና ወጪ የሚጠይቅ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ እንደሚዛን ያሉና ሌሎች መሣሪያዎችን ደረጃ ለመለካት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የፋብሪካዎቹ ክፍሎች ሥራ እንዲያቆሙ የሚደረግ በመሆኑ የተንቀሳቃሽ መሣሪያው አገልግሎት ላይ መዋሉ መደረጉ በአገሪቱ ደረጃዎችን ለመለካት የሚደረጉ ጥረቶችን ያሳካል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩልም የአገሪቱን ጥራት ደረጃ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያመለክት አዲስ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ መሆኑን የገለፁት አቶ የኋላሸት ረቂቅ ህጉ ፀደቆ በስራ ላይ ሲውል የአገሪቱ የጥራት ደረጃ የሚሻሻልበትና በሁሉም ቦታዎች አገልግሎት እንዲኖር እንደሚያስችል፣ ጥራታቸውን በጠበቁ መሣሪያዎች ኅብረተሰቡ ተገልጋይ እንዲሆንና የማምረቻ መሳሪያዎችም ጥራትን በቅርብ ለመከታተልና እርምጃ እንዲወሰድም በማድረጉ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |