|
የአፍሪካ ሚሌኒየም ኢንተርናሽናል የንግድና...
|
|
|
|
Thursday, 07 February 2008 |
|
የአፍሪካ ሚሌኒየም ኢንተርናሽናል የንግድና ኢንቨስትመንት ትርዒት ተከፈተ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ያዘጋጀው የአፍሪካ ሚሌኒየም ኢንተርናሽናል የንግድና ኢንቨስትመንት ትርዒት ትናንት ጥር 27 ቀን 2000 ዓ.ም በክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሚሌኒየም አዳራሽ ተከፈተ፡፡
በኤግዚቢሽኑ ከ100 በላይ የመንግስትና የግል ኩባንያዎች፣ ከሌሎች አገሮች የመጡ ተቋማት የግልና የመንግስት ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ተሳታፊ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡ አለም አቀፉን የንግድ ትርዒት የከፈቱት ፕሬዚዳንት ግርማ፣ የንግድ ትርዒቱ አዳዲስ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ ሻጭና ገዢን ለማገናኘት፣ የንግድ ትስስር ለመፍጠር፣ የልምድ ልውውጥን ለማጠናከርና በሕዝቦችና በአገሮች መካከል የባህል ልውውጥን ለማጠናከር እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡ ኤግዚቢሽኑ ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የባህል ግንኙነት ይበልጥ ከማጠናከሩ በላይ አፍሪካ ያላትን የኢንቨስትመንት እድልና ባህላዊ ሃብት ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥርም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ወልዳይ አምሃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እ.ኤ.አ በጥር 2007 የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የአፍሪካውያን ጭምር በመሆኑ አፍሪካውያን በልዩ ሁኔታ እንዲያከብሩት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት አፍሪካን ኢኮኖሚክና ቢዝነስ ሰሚት ፕሮጀክት ቀርፀው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንና ኤግዚቢሽኑ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ክፍል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአስሩም ቀናት የአፍሪካ ምሽት እንደሚኖር ከአገር ውስጥና ከውጪ በመጡ ሙዚቀኞች፣ የፋሽን ሾው፣ የአፍሪካ አመጋገብና አለባበስ የሚያስተዋውቅ ግሩፕ ኦፍ አፍሪካን ሌዲስ በሚል ማኅበር እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የሁለተኛ ክፍል በአፍሪካ የእድገት ማነቆ ተስፋና ፈታኝ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ትንታኔና ማብራሪያ የካቲት 1 ቀን 2000 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደሚቀርብ ዶክተር ወልዳይ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ በኢትዮጵያ ፖሊሲ የመንደፍ ብቃትን ማገዝና በኢኮኖሚ እድገቱ አስተዋጽኦ ለማድረግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምርምር ተቋም በማቋቋም በፖሊሲ ቀረፃና ግምገማ የበኩሉን እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ማኅበሩ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት መፈረሙ የሚያከናውናቸው ምርምሮችና ስልጠናዎች ለአገር ግንባታ እንዲውሉ በር መክፈቱንም ተናግረዋል፡፡ በቤዛዊት ሥዩም |