| የጣና ትራንስፖርት ሠራተኞች ክስ... |
|
|
| Thursday, 07 February 2008 | |
|
የጣና ትራንስፖርት ሠራተኞች ክስ ሊመሰርቱ ነው
ኩባንያው 8 ሠራተኞችን አስቀርቶ 440 አባሯል የጣና ትራንስፖርት ኃ.የተ.የግ.ማ በባንክ እዳ ንብረቶች እንዲወስድ በመደረጉ ከ440 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን ተከትሎ ሠራተኞች የአገልግሎት የሥራ መፈለጊያና ከደሞዛቸው ተቆርጦ ያስቀመጡት የነበረው ገንዘብ እንዲከፈላቸው በሕግ ሊጠይቁ ነው፡፡ የኩባንያው ሠራተኞች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ኩባንያው በባንክ የሚፈለግበትን እዳ መክፈል ባለመቻሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኩባንያውን ንብረቶች ተረክቧል፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎችም በኩባንያው ላይ የደረሰውን ችግር በማስረዳት በቋሚነት ሲያስተዳድሯቸው የነበሩትን ሠራተኞች እንዳሰናበቱ ታውቋል፡፡ በንግግራቸው ወቀት ከደሞዛቸው 5በመቶና ከኩባንያው 7 በመቶ በጥቅሉ የደሞዛቸው 12 በመቶ እየተቆረጠ ይቀመጥ የነበረው ፕሮቪደንት ፈንድ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ ባለንብረቶቹም “ይህ ገንዘብ አለ፡፡ ይሰጣችኋል” ቢሏቸውም ቆይቶ የተቀመጠላችሁ ገንዘብ በባንክ ታግዷል መባሉን ተቃውመዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሠራተኞቹ የምናውቀው ቀጣሪያችንን እንጂ ባንኩን አይደለም በማለት ገንዘባቸው እንዲከፈላቸውና ከደሞዛቸው ተቆርጦ ይቀመጣል ለተባለው ገንዘብም ግብር ይከፍሉበት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ስምንት የሚሆኑ ሠራተኞች ብቻ እንዲቆዩ መደረጉን የገለፁት ሠራተኞች እነዚህም ሠራተኞች በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚሰናበቱ አመልክተዋል፡፡ ከ10 ዓመት በላይ ጭነት ማመላለስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የቆየው ጣና ትራንስፖርት ሠራተኞቹን ያሰናበተው ምንም አይነት የአገልግሎት ሳይከፍል በመሆኑ ይህንን ክፍያ ለማግኘትም በሕግ መጠየቁን ተስማምተውበታል፡፡ ሠራተኞቹ በባንክ ተቀምጦላችኋል የተባለው ገንዘብ መጠንም ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ገንዘቡ ሊንቀሳቀስ አይችልም በመባሉ ገንዘቡን ለማግኘት አለመቻላቸውን የሚገልፁት ሠራተኞቹ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ገንዘባቸውን ለመውሰድ እንዲችሉ ጉዳዩን በሕግ ለሚከታተልላቸው ጠበቃ ውክልና በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደትም ለመረጡት ጠበቃ 330 የሚሆኑ ሰራተኞች ውክልና ሰጥተዋል፡፡ ኩባንያው ያለበትን የባንክ እዳ ለመክፈል ያሉት አነስተኛ ተሽከርካሪዎች በሙሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰዱ ሲሆን ለኩባንያው አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችም መወሰዳቸውን እኚሁ ሠራተኞች ይገልፃሉ፡፡ ኩባንያው ሌብሬ የወሰደባቸው (ተሳቢዎችንና ሌሎችን ጨምሮ) 700 ተሽከርካሪዎች ነበሩት፡፡ ከዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑትን አምቼ በፍርድ አፈፃፀም የሸጠበት ሲሆን ባንክ የተረከበው 90 የማይሞላ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኩባንያው እህት ኩባንያ የሆኑት የሚናና ትሬዲንግ የጢስ አባይ ኩባንያ መኪኖችም በተመሳሳይ ሁኔታ በባንክ መወሰዳቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህንም መኪኖች ለመሸጥ ባንኩ ጨረታ ማውጣቱ ታውቋል፡፡ ባንኩ ባወጣው ጨረታ መሠረትም ተሽከርካሪዎችን በብድር ጭምር ለመሸጥ እድል እንደሚሰጥ አመልክቷል፡፡ ኩባንያው አለበት የተባለው የባንክ እዳ 160 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትም ሠራተኞቹ ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል ኩባንያው አለበት የተባለውን እዳ አሁን በባንክ የተያዙት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ቢሸጡ እንኳን ሊከፍል አይችልም የሚል አስተያየት የሰጡ ሠራተኞችም አሉ፡፡ የጣና ትራንስፖርት አንድ ኃላፊ በበኩላቸው “አሁን ሥራ ቆሟል ሠራተኞቹም ተሰናብተዋል” ካሉ በኋላ ሠራተኞቹ በባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ በሕግ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን እንደሚያውቁና ከዚህ ውጪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ምንጮቹ እንደገለፁት ደግሞ ኩባንያው የ2000 ዓ.ም የንግድ ፈቃዱን አሳድሷል፡፡ ሳይባረሩ ቀሩ የተባሉትም ሠራተኞች በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |