Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ተፈታኙ ኅብረት
ተፈታኙ ኅብረት Print E-mail
Thursday, 07 February 2008
ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ኅብረት አስረኛ መደበኛ ጉባኤ በመዲናችን በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ ይህ ጉባኤ የተካሄደው ኅብረቱ ከእናቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተወለደ ከአምስት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ የኅብረቱ መፈጠር በብዙዎች ዘንድ የአፍሪካ ችግሮችን ያቃልላል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁንም የኅብረቱን ውጤታማነት ለመገምገም ጊዜው ገና ቢሆንም እስከ አሁን የተጓዛቸው እርምጃዎችስ በቂ ናቸው ወይ? ብሎ  ተገቢ ነው፡፡ በኅብረቱ ዙሪያ የነበሩት ታሪካዊና ወቅታዊ ፈተናዎች/ችግሮች እያሸነፉት ወይስ እያሸነፋቸው ነው?
የአፍሪካ ኅብረት እ.ኤ.አ በ2001 ሲመሰረት አንግቦባቸው የተነሳ መልካም ዓላማዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የአፍሪካ ዜጎች ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ ነፃነቶች ማረጋገጥ፣ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ማስቀረት፣ አምባገነን መሪወች መቃወምና መፈንቅለ መንግሥትን ማስቀረት እንዲሁም አፍሪካ ከጥገኝነት ተላቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትክክለኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቦታዋን እንድትይዝ ማድረግ ይገኙባቸዋል፡፡

እንደ ነኩዋሚ ንኩሩማህና አፄ ኃይለስላሴ በመሳሰሉ ትላልቅ የአፍሪካ አባቶች የተገነባው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጨረሻ ግቡ አፍሪካን ማወሃድ እንደነበር ከድርጅቱ ዓላማዎችና ግቦች መመልከት ይቻላል፡፡ ድርጅቱ በቂ ባይባልም በወቅቱ አህጉሪቱ ተደቅኖባት የነበረ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ነፃ ለማውጣት ብዙ ውጣ ወረዶች አልፈዋል፡፡ ድርጅቱ ባደረገው ጥረትና በአፍሪካ ሕዝቦች መራራ ትግል የአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ተሰብሯል፡፡

እነዚህ የድርጅቱ አወንታዊ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አሁንም በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እውነት አፍሪካ ነፃ ወጥታለች? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ስርዓት በአፍሪካውያን እጅ ይውደቅ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነቱ አሁንም አልቀረም፡፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ መሪዎች ከቀድሞ ቀኝ ገዢዎቻቸው ያላቸው ግንኙነት በእኩልነትና በመርህ የተከተለ ሳይሆን በጥቅምና አንዱ በሌላው ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አገራቱ ኢኮኖማያዊ ነፃነታቸው ተረጋግጧል ማለት አይቻልም፡፡

ኢኮኖሚው ከፖለቲካ ዘርፉ ነጥሎ ማየት ስለማይቻል ፖለቲካዊ ነፃነታቸውንም ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጧል ማለት የሚከብድ ነው፡፡ ምዕራባወያን ዕርዳታቸውና ብድራቸው ለአፍሪካ አገራት ለመስጠት የራሳቸውን ስርዓትና ባህል እንደቅድመ ሁኔታ በመስቀመጥ ነው፡፡ ታዲያ ለእነሱ ዴሞክርሲያዊ የአፍሪካ መሪ ማለት የእነሱን ትዕዛዝ የሚያከብር ማለት ነው ቢባል የተሳሳተ አይሆንም፡፡ ለሕዝባቸውና ለዜጎቻቸው ተጠያቂ የልሆኑ የአፍሪካ መሪዎች የእነሱን ትዕዛዝ እስካልጣሱ ድረስ የሚጠይቃቸው የለም፡፡ መሪዎቹ የሚገጥማቸው ዓመፅ ለመቀልበስ በቂ ድጋፍ የሚያገኙት ከእነሱ ነው፡፡ እነሱን የማይከተሉ ከሆነ ደግሞ በተቃራኒው ይሆናል፡፡

የኢኮኖሚ ጥገኝነቱ የፖለቲካ ጥገኝነት ማስከተሉ መሪዎቹ በራሳቸው አፍሪካዊ መንፈስ፣ አገር በቀል ሥርዓትና ባህል እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት ገጥሟቸዋል፡፡ የአፍሪካ ማህበራ፣ ፖለቲካዊና አኮኖማያዊ ችግርች በራሳቸው ተነሳሽነትና አቅም መፍታት አልቻሉም፡፡  የራሳቸው ፖሊሲ አውጥተው ሕዝባቸው አሳታፊ የሆነው ስርዓት በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ አልቻሉም፡፡ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች የተናጠል ችግሮች በዚህ ብቻ አይወሰኑም፡፡

እነዚህ መሪዎች በሚመሰርቱት ኅብረት ላይም ችግሮቹ ይንፀባረቃሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የተለያዩ ፖሊሲዎች ማውጣትና በርካታ ስምምነቶች መፈራረም ቢችሉም እነዚህን ተፈፃሚ ማድረግ ላይ ግን አልቻሉም፡፡ ኅብረቱ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ትልቁ ፈተና የገጠመው ከወስጥና ከውጭ ቢሆንም፣ ዋነኛው የአቅም ማነስ ችግር እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በመግቢያው የተጠቀሱት የኅብረቱ ዓላማዎች ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ መዋቅሮችና ንኡስ ተቋማት የተቋቋሙ ቢሆንም ራሳቸው ችለው መንቀሳቀስ የሚችሉ አይደሉም፡፡

እንደ አገራቱ በተመሳሳይ ኅብረቱና ሌሎች ተቋማቱ ፋይናንስ የሚደረጉ በውጭ እጅ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የአህጉሪቱ ችግሮች ለመፍታት በሚወስኑት ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ከማሳደር ባሻገር እርምጃ መውሰድ የሚቻለው የገንዘብ ሰጪዎቹ ፍላጎት ግምት ባስገባ መልኩ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

ኅብረቱ ከተመሰረተ በኋላ ከተፈጠሩ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሰላምና የፀጥታና ምክር ቤት (Peace and Security Council) ሲሆን ዓላማውም የአፍሪካ ግጭቶችን ለማስቀረትና ጣልቃ ገብቶ ለመፍታት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ የያዛቸውን አጀንዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከተያዘው እቅድ በየሶስት ዓመቱ ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ይህ በኅብረቱ አባል አገራት ሊሸፈን የሚችል አይሆንም፡፡ ትልቁ የገንዘብ ምንጭ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ካልተገኘ ተቋሙ የያዛቸው ዓላማዎች ተግባራዊ ይሆናሉ ማለት ህልም ነው፡፡ ገንዘቡ ቢገኝም የተቋሙ ውሳኔና እርምጃ በአባል አገራቱ ነፃነትና ተነሳሽነት ይተገበራል ማለት አይቻልም፡፡

ይህ በአስተሳሰብ ደረጃ የተመሰረተ ፈተና ሲሆን ራሱ ተቋሙ ካስቀመጠው መርህም ብንነሳ እርምጃ የመውሰድ ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ ይህ የፀጥታ ተቋም እርምጃ መውሰድ የሚችለው ውሳኔው በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ሲፀድቅ ብቻ መሆኑን አስቀምጧል፡፡

ኅብረቱ በፀጥታ ዙሪያ ከተባበሩት መንግሥታት ትብብር መፈጠሩ የሚጠላ ነገር ባይሆንም የድርጅቱ “ግሪን ካርድ” እንዲጠባበቅ መደረጉ ተቋሙስ ለምን አስፈለገ ያስብላል፡፡ ምክንያቱ ገንዘቡም የሚያገኘው ከውጭ፣ ፍቃድም ከውጭ ከሆነ የድርጅቱ የውሳኔ ሰጪነት ነፃነት አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላ ችግርም አለ፡፡ አንዳንድ በኅብረቱ ህገ ደንብ ውስጥ የተካተቱ አንቀፆች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ኅብረቱ በአባል አገራቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን ሲከለክል በሌላ በኩል ኅብረቱ ይዞት ከመጣው አዲስ መርህ በአባል አገራት ውስጥ ችግር ሲፈጠር ወቅት ጣልቃ መግባት ይቻላል የሚል በግልፅ ያልተለየ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡

የእነዚህ አንቀፆች መጣረስ አንድ የሚያሳየው ነገር አለ፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የኅብረቱን ጥንካሬ ችግር ፈቺነት የሚፈልጉት ቢሆንም ከልኡላዊ ስልጣናቸው ቆርሰው ለኅብረቱ የሚሰጡት ኃይል አጠራጣሪ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የመሪዎቹ የፖለቲካ የቁርጠኝነት ማነስና በኅብረቱ ላይ ያላቸው መተማመን እስከዚያም መሆኑን ነው፡፡ ይህ በወረቀት ደረጃ የተቀመጠው የጣልቃ ገብነት መርህ ተፈፃሚነትን እንቅፋት ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ ኅብረቱ በመፈንቅለ መንግሥት በትረ ስልጣን የተቆጣጠረ አካል ዕውቅና እንደማይሰጥ ያስቀመጡ ቢሆንም በአምባገነን መሪዎች ላይ ያለው አቋም ግልፅ አይደለም፡፡ ለሕዝባቸው ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ አፍነው በስልጣን ላይ ሙጥኝ ብለው የሚኖሩ የአፍሪካ መሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ ዕድሜያቸውን በስልጣን ላይ የጨረሱት የሊቢያ መሪው መሐመድ ጋዳፊና የአዲሲቱ የኤርትራ አምባገነን ኢሳያስ አፈወርቅ ይገኙባቸዋል፡፡

እነዚህ መሪዎች እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ዴሞክራሲ ሊሰጡዋቸው ቀርቶ በኅብረቱ ውስጥ ያላቸውን እንቅስቃሴም እንደምናውቀው ሲያፈነግጡና ሲያስተጓጉሉ ይታያሉ፡፡ ታዲያ በእነዚህ አምባገነኖች መሪዎች ላይ መፈንቅለ መንግሥት ቢደረግ ኅብረቱ ዕውቅና አልሰጥ ካለ ድርጊቱ ይዞት ከተነሳ ዓላማ የሚጣረስ አይሆንም?

ከዚህ ተለይቶ የማይታይ ሌላ ጉዳይ የምርጫ አወዛጋቢነትን ነው፡፡ በኢትዮጵያ የ97 የምርጫ ውዝግብ፣ አሁንም ደግሞ የኬንያው ውዝግብና ያስከተለው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ኅብረቱ ግን እንዲህ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል ለሚፈጠር የምርጫ ውዝግብ ላይ ምንም ዓይነት አስቸኳይ መፍትሄ ሲሰጥ አይታይም፡፡ ይህ የኅብረቱ ታማኝነትና የፖለቲካ ብቁነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡

ሌላ በርካታ ተንታኞች የሚያነሱት ነጥብ በአፍሪካ የሚመሰርተው መንግሥት ቅርፅ ላይ ስምምነት አለመድረሳቸውን ነው፡፡ ይህ ኅብረቱን ምን መምሰል እንዳለበት የመሪዎቹ የፍላጎት ልዩነት የሚያንፀባርቅ ሲሆን ከዚህ በተጓዳኝ ሌላ ችግር አለ፡፡ የጉዳዩ ውስብስብነት በተጨማሪ በጉዳዩ ዙሪያ የሚወያዩ መሪዎቹ እንጂ አባል አገራቱን አይመስሉም፡፡ ምክንያቱም መሪዎቹ በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት አስተያየትና የያዙትን አቋም ሕዝባቸውን አማክረው ሳይሆን ራሳቸውን የግል ፍላጎትና አቅም ብቻ ተመርኩዘው መሆኑን በብዙዎች ዘንድ ተተችተዋል፡፡ ኅብረቱ የአፍሪካ መሪዎች ወይስ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ኅብረት ነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ የአህጉሪቱ ምሁራን፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ የግሉ ዘርፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ዜጎች በጉዳዩ ላይ አለመወያየታቸው የኅብረቱ ባለቤትነት የመሪዎቹ “ማህበር” አስመስለውታል፡፡

በአህጉሪቱ ከፍተኛ ግጭቶች የተበራከቱ ሲሆን ኅብረቱ ችግሮቹን መፍታት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ግጭት እንዳይነሳ ለማስቀረት እስከ አሁን የተደረገ ጥረት የለም፡፡ ለዓመታት የቆየው የዳርፉር የእርስ በርስ ግጭት የኅብረቱ ትልቅ ፈተና ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በሱዳንና ሌሎች አካባቢዎች ያሉትን ግጭቶች መፍትሄ ሊበጅለት አልቻለም፡፡ ህብረቱ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በርካታ የውሳኔ ሃሳቦች ማሳለፍ ቢችልም እስከ አሁን ከወረቀት የዘለለ እርምጃ አልወሰደም፡፡ ይልቁን የኅብረቱን ደካማነትና አቅመ ቢስነት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ድክመቶች መንስኤ በአብዛኛው የአቅም ማነስና የመሪዎቹ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት ቢሆንም የውህደቱ መዋቅራዊ ሂደት ከአውሮፓ ኅብረት በቀጥታ መውሰዱ ሌላ ትችት ያስነሳል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አመጣጥ ታሪክ መፈተሽ ለዚሁ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ለዚህ የፖለቲካ ውህደት ደረጃ የደረሰው በአባል አገራቱ በራሳቸው ሃብትና የፖለቲካ ተነሳሽነት ሲሆን ሂደቱ ከተጀመረ ከ50 ዓመት በላይ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ የዚህ ዓይነት የውህደት ጉዞ እንደ ብዙዎች አባባል ከፍተኛ መዋቅራዊ የቢሮክራሲ አሰራርና፣ በሺዎች የሚቆጠር ከፍተኛ የተማረ ሃይል የሚጠይቅ ነው፡፡ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት የመሪዎች ብቻ ኅብረት ሳይሆን በእያንዳንዱ አገር/አካባቢ የነበሩ የፀጥታ ድርጅቶች፣ ብሔራዊ ህጎች፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ማወሃድ ችለዋል፡፡

በተመሳሳይም የአንድ አገር ወደ ኅብረቱ መቀላቀል ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ የተከተለና የኅብረቱ ቅድመ ሁኔታዎች ያከበረ መሆኑን ነው፡፡ በምርጫና በገንዘብ አጠቃቀም አንድ የጋራ መንገድ መጠቀም መቻላቸው ለኅብረቱ ውህደት መሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአፍሪካ ይህ አይገመትም፡፡ በአካባቢ ያሉት እንደ ህ”፣ “፣ COMESA የመሳሰሉ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ መዋቅሮች እየተጠናከሩ ውህደት የመፍጠር ሙከራ ያለ ቢሆንም በኅብረቱና በእነዚህ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት ወጥ ያለው መዋቅር አይደለም፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረት መዋቅራዊ ውህደት በወረቀት ላይ ሲታይ የአውሮፓውን ይምሰል እንጂ፣ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ግን በጭራሽ አይመሳሰልም፡፡ አባል አገራቱ የየራሳቸው ፖለቲካዊ ልኡላዊነት የሚያሰጋቸው፣ ምንም ዓይነት የጋራ የደህንነት ፍላጎት የሌላቸውና፣ ጠንካራ አገራዊ መዋቅርች የሌላቸው ናቸው፡፡

በመሆኑም የአፍሪካ ውህደት ለማሳካት፣ ፀጥታና መረጋጋት ለማረጋገጥ እንዲሁም አህጉሪቱ ከደህንነትና ከድንቁርና ተላቃ ራስዋን እንድትችል ለማድረግ አቅምንና በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ ያገናዘበ ሂደት መከተል ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያ የሚወጡ ውሳኔዎችና ፖሊሲዎች አቅምን ያገናዘቡና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ኅብረቱ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለውን ግንኙነት ሊጠናከር የሚገባ ቢሆንም በአቅም ግንባታ በኩል ሙሉ ለሙሉ ከጥገኝነት ተላቆ አህጉር በቀል የሆኑ ስርዓቶችንና ስልቶች ከመጠቀም ባሻገር የአህጉሪቱ ምሁራን፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ዲያስፖራና፣ የግል ሴክተሩን በማዋሃድ በተወሰነ ደረጃ ራስን መቻል ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መንገድ ኅብረቱ የመንግሥታት (የመሪዎች) ኅብረት ብቻ መሆኑን ቀርቶ ወደ ታች ወደ ሕዝብ በመወረድ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ግድ ይላል፡፡

በመጨረሻ በሕገ ደንቡ ውስጥ የተቀመጡ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱና ለውሳኔ ተግባራዊነት የማይመቹ አንቀፆች መስታረቅ ግድ ይላል፡፡ እንዲሁም የአፍሪካ መሪዎች የጋራ አህጉራዊ ራእይ በመገንባት ለተመሳሳይ ዓላማ መቆምና የአገር ልኡላዊነት ከኅብረቱ ልአላዊነት ማጋራት ትልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡     

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >