| የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር... |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
|
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፅም ሰራተኞች አሳሰቡ
የህይወት ትራንስፖርትና ቴክኒክ አገልግሎት አክሲዮን ማህበር ሰራተኞች፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፅም ሲሉ አሳሰቡ፡፡ ሰራተኞቹ ይኸንን ያሳሰቡት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከ96 በመቶ በላይ ድርሻ ያቋቋመውን ህይወት ትራንስፖርትና ቴክኒክ አገግሎት አክሲዮን ማህበር እንዲዘጋ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ትዕዛዝ አስተላልፏል በሚል ፍራቻ ነው፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአክሲዮን ማህበሩ ሰራተኞች በጥበቃ ሰራተኞች በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከጥር 3ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ሰራተኞቹ በሙሉ የዓመት ፈቃድ ሞልተው እንዲወጡ የሚገልፅ ደብዳቤ በመስሪያ ቤቱ የመግቢያ በር ላይ መለጠፋቸውን ሰራተኞቹ ሰራተኞቹ ገልፀዋል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ የቴክኒክና የትራንስፖርት (የደረቅና ፍሳሽ ትራንስፖርት) አገልግሎት እንደሚሰጥ የገለፁት ሰራተኞቹ፣ ሥራ አስኪያጁ በስልክ በጥበቃ ሰራተኞች በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወደ ተለያዩ ክፍለ አገራት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ባስቸኳይ ወደ መስሪያ ቤቱ እንዲመለሱና እንዲቆሙ፣ በመስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ተሽከርካሪዎች (ለመምሪያ ኃላፊዎች የተሰጡ ጭምር) እንዳይንቀሳቀሱ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ትዕዛዙን ያስተላለፉት፣ "ድርጅቱ ከስሯል" በሚል ሰበብ መሆኑን የሚናገሩት ሰራተኞቹ፣ ከአንድ ዓመት በፊት የአመራር ችግር መኖሩንና ወደ ኪሣራ እያመራ መሆኑን ለቦርድና ለዋና ፀሐፊዋ ቢያሳውቁም ሰሚ ማጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ "ቀይ መስቀል የሚከተለው ዓላማና መርህ ይኸንን አይደለም" የሚሉት የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ቀይ መስቀል እንኳን በስሩ ለበርካታ ዓመታት ይዟቸው የነበሩ ሰራተኞችን በትኖ ለችግር ሊዳርጋቸው ቀርቶ፣ ሌሎች ረዳት ያጡትን ዜጐች በማሰባሰብ መርዳት መሆኑን አውቀው ኃላፊዎች ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ህይወት ትራንስፖርትና ቴክኒክ አገልግሎት አክሲዮን ማህበር በ1999 በጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን ብር መክሰሩን የሚናገሩት ሰራተኞቹ፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለው የሥራ አመራር በቂ ልምድ አለመኖር፣ በመግባባት ሥራውንና ሰራተኛውን ለመምራት አለመቻል፣ የሠራተኛና አሰሪ አዋጅን በመጣስ የሚፈፀሙ ዕድገት፣ ቅጥር፣ ዝውውርና በወጪ ቅነሳ ላይ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ደካማ መሆን ለኪሳራው ቀዳሚ ተጠቃሽ የአሰራር ብልሹነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞች ጨምረው እንደገለፁት፣ በ1998 በጀት ዓመት በውጪ ኦዲተር ተመርምሮ የተረጋገጠ በባንክ ከሚገኝ ገንዘብ 2.9 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ በ1999 በጀት ዓመት ከመለዋወጫ ሽያጭ ገቢ 1.5 ሚሊዮን ብር በመገኘቱ ድርጅቱን አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲሆን ቢያስችለውም፣ በ1999 በጀት ዓመት መጨረሻ በባንክ ውስጥ ያለው ገንዘብ 8ዐዐ ሺ ነው መባሉ ሰራተኛውን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ወገን ያስደነገጠ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክስዮን ማህበሩ ሰራተኛው በ1999 ዓ.ም. በጀት ዓመት ሥራ ሳይሰራ ፔሮል ላይ እየፈረመ ደመወዝ ይውሰድ ቢባል፣ አማካይ ዓመታዊ ያልተጣራ ደመወዝ 1.2 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን የገለፁት ሰራተኞቹ የተቀማጭ ገንዘብ በፍጥነት ማሽቆልቆል ግልፅ አለመሆኑን፣ ሠራተኛ ከጅምሩ የአሰራር ግድፈቶች እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ጩኸት ሲያሰማ ቢቆይም መፍትሄ በመፈለግ ደረጃ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት አካል የዛሬው አሳዛኝ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ለምን ዝምታን መረጠ? በማለት ጠይቋል፡፡ የአክሲዮን ማህበሩ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር (የትራንስፖርትና መገናኛ ሰራተኛ ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌደሬሽን ዋና ፀሐፊ) አቶ ዘሪሁን አለሙን ተፈጠረ ስለተባለው አለመግባባት ጠይቀናቸው "ቀይ መስቀል ከተቋቋሙበት አላማ አንፃር ይኸንን ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአክሲዮን ማህበሩ የሥራ አመራሮች በድርጅቱ ላይ ደረሰ የሚሉትን ኪሣራና ሰራተኛን አላግባብ ለመበተን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በህጋዊ መንገድ የምናየውና የምንሄድበት ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡ "በዚህ ላይ እኛ ምንም የወሰነው ነገር የለም፡፡ ማኔጅመንቱ ወስኖ ከሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ አላግባብ ሰራተኞችን ረፍት ውጡ፣ መኪና አስረክቡ ማለት መስመር የለቀቀ አካሄድ ነው፡፡ ስህተት ስለሆነ መታረም ይኖርበታል" ያሉን የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባል ናቸው፡፡ ማህበሩ እንደ ድርጅት ንብረቱን በአግባቡ ሳይረከብ በስልክ ትዕዛዝ "መኪና አቁመህ ረፍት ውጣ ማለት እቃ ቢጠፋ ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው?" ያሉት የቦርድ አባሉ፣ ሰራተኛ "ቶሎ ብለህ ግቢውን ልቀቅ" የሚባለው እሳት አደጋ ሲነሳ ብቻ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ሲቋቋም የበላይ አስተዳዳሪ ቦርድ እንዳለው የገለፁት የቦርድ አባል፣ ችግርም ሆነ ጥሩ ነገር ሲፈጠር ቦርዱ ተሰብስቦ በሚወስነው ውሳኔ ሁሉም ነገር ይፈፀማል በማለት የተላለፈው ትዕዛዝ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀይ መስቀል ማህበራዊ ግዴታ ስላለበት ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ እንኳን በስሩ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን፣ ሌሎች ዜጐች በሚቸገሩበት ጊዜ የሚደርስ ማህበር ነውና ይኸንን ዓይነት ስህተት ይፈፅማል ብለን አናምን በማለት የቦርድ አባሉ ተናግረዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |