Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር...
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር... Print E-mail
Sunday, 10 February 2008
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሸጣቸው ተሽከርካሪዎች የቀረጥ አከፋፈል አወዛገበ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በግልፅ ጨረታ የሸጣቸው የአርባ አምስት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የቀረጥ አከፋፈል ውዝግብ አስነሳ፡፡ ጉምሩክ ከመመሪያ ውጪ እየሰራ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የጨረታው አሸናፊዎች "ጨረታውን ብናሸንፍም የአዲስ አበባ ጉሙሩክ ከመመሪያ ወጪ ከ12-25 በመቶ የቀረጥ ጥያቄ አቅርቧል" ሲሉ አማረሩ፡፡ ተጫራቾቹ የመኪናዎቹን ግዥ በተመለከተ አስፈላጊውን ክፍያ ለቀይ መስቀል ማህበር መክፈላቸውን ነገር ግን በጉሙሩክ ህገወጥ አሰራር መኪናዎቹን መረከብ አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

የጨረታው አሸናፊዎች፤ መኪኖቹ ከአስር ዓመት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው ከታክስ ነፃ እንደሚሸጡ ተገልጾላቸው በጨረታው መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ላጋር ጉሙሩክ፤ ቀይ መስቀል መንግሥታዊ ተቋም መሆኑን በመጥቀስ በእያንዳንዱ መኪና ከ12 - 25 በመቶ የጨረታ ማሸነፊያ ገንዘብ ክፍያ እንዲፈፅሙ መታዘዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ "ቀይ መስቀል አለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ ሳለ ለመንግሥታዊ ድርጅቶች የጨረታ ሂደት የሚጠየቀውን የቀረጥ ክፍያ መጠየቃችን አግባብ አይደለም" ሲሉ የጨረታው አሸናፊዎች ተናግረዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በቁጥር 3/1999 ዓ.ም አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ባወጣው ሕግ መሰረት ከቀረጥ ነፃ የገቡ መኪኖች ከቀረጥ ነፃ መብት ለሌለው ግለሰብ ሲተላለፍ የአስር አመት የእርጅና ቅናሽ በዜሮ የቀረጥ ታክስ መጣኒ እንዲሸጡ ይፈቅዳል ሲሉ ተጫራቾቹ አውስተዋል፡፡ በዚህ አሰራር መሰረት በ1998ና 1999 ዓ.ም ከቀይ መስቀል በጨረታ መኪና መግዛታቸውን ያስታወሱት ተጫራቾች "ሲሰራበት የቆየው ሕግ የሚሻርበት ምክንያት አልገባንም" ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ በዚህም በአምስት ቀን ውስጥ የሚጠናቀቀው ርክክብ ከአርባ አምስት ቀናት በላይ መጓተቱን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ባለሥልጣን በኤች60/ኤንጂኢ4/02 የደብዳቤ ቁጥር በ15/05/2000 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ላጋር ጉሙሩክ በፃፈው ደብዳቤ፤ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች ለሌላ ወገን በሚተላለፉበት ጊዜ የእርጅና ቅናሽ ስለሚታሰብበት ሁኔታ በወጣ መመሪያ 3/1996 መሰረት እንደ ከዚህ በፊት እንድታስተናግዷቸው በማለት ማሳሰቡን ተጫራቾች ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማህበር የጨረታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ማሞ በተመሳሳይ መልኩ በ96፣ በ98 ሽያጭ ማከናወናቸውን አስታውሰው፤ በቅርቡ ማህበሩ ያከናወነው የመኪና የጨረታ ሽያጭ በአዲስ አበባ ላጋር ጉሙሩክ ምክንያት መስተጓጎሉን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ላጋር ጉሙሩክ ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል ታደሰ፤ የቀይ መስቀል ማህበር የገቢዎች ሚኒስቴር በ1996 ዓ.ም ያወጣው መመሪያ ከመውጣቱ በፊት በ1989 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ መንግሥታዊ ተቋማት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን የሚያስወግድበትን ሁኔታ በተመለከተ በወጣው መመሪያ ሲጠቀም እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ስለዚህ ይላሉ አቶ ፋሲል "በሁለት መመሪያ ማህበሩ ተጠቃሚ መሆን የለበትም" ብለዋል፡፡ ስራ አስኪያጁ ቀይ መስቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን መተዳደሪያ ደንባቸውን አይተው እንዳረጋገጡ ነገር ግን በ1989  ዓ.ም በወጣው መመሪያ ስለመስተናገዳቸው ማረጋገጫ ሰነድ እየተፈለገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ ፋሲል ሰነዱ እስኪገኝ ድረስ የጨረታው አሸናፊዎች የተጠየቀውን የቀረጥ ክፍያ እንዲፈፅሙና ከተጣራ በኋላ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ፋሲል ወጥ የሆነ አሰራር ከመቀየስ አኳያ የማጣራት ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ "ስህተቱ በቀድሞ መመሪያ ሲስተናገዱ ቆይተው በአዲሱ እንዲስተናገዱ መደረጉ ነው" ሲሉ አመላክተዋል፡፡

በተሾመ ንቁ
 
< Prev   Next >