Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow በደራሼ ልዩ ወረዳ ከ30 በላይ...
በደራሼ ልዩ ወረዳ ከ30 በላይ... Print E-mail
Sunday, 10 February 2008
በደራሼ ልዩ ወረዳ ከ30 በላይ ሰላማዊ ነዋሪዎችና 18 የፖሊስ አባላት ተገደሉ

በደራሼ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከጥር 25 እስከ 27/2000 ዓም የልዩ ወረዳ ምስረታን ጥያቄ አስመልክቶ በተነሳ ግጭት 18 የወረዳውና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሲገደሉ ከ30 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን የልዩ ወረዳው የፓርላማ ተወካይ አቶ ሀይለየሱስ ኪቴሞ ለሪፖርተር ገለፁ፡፡
እንደ አቶ ሀይለየሱስ ገለፃ በደራሼ ልዩ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የአዲስ ኦፕቲማ ቀበሌ ነዋሪዎች በአጎራባች ኮንሶ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ጋር በጋራ በደራሼ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ባካሄዱት ጥቃት ከሰላሳ በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንዲሁም አስራ ስምንት የፖሊስ አባላት ተገድለዋል፡፡ በተጨማሪም ከሰላሳ በላይ ሰዎች በግጭቱ ቆስለው በአርባ ምንጭና በጊዶሌ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ሀይለየሱስ አስታውቀዋል፡፡

የግጭቱ መንስኤ የልዩ ወረዳ ምስረታ ጥያቄ እንደሆነ አቶ ሀይለየሱስ አብራርተዋል፡፡ ተወካዩ ከአንድ ወር በፊት (ታህሳስ 25 - 27/2000 ዓ.ም) በተከሰተ የልዩ ወረዳ ምስረታ ግጭት ሁለት የፖሊስ አባላትና አምስት ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ሁለት መቶ አርባ አራት ቤቶች መቃጠላቸውንና ከ5500 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል፡፡

አቶ ሀይለየሱስ የወረዳው አስተዳደር አካላት ግጭቱን እንዳይባባስ ያደረጉት ጥረት አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግጭቱ የኦነግ እጅ እንዳለበት አመላካች ሁኔታዎች እንዳሉ አቶ ሀይለየሱስ ጠቁመው፤ ለዚህም የግጭቱ ተሳታፊዎች ከባድ መሳሪያ መታጠቃቸውን በአብነት ገልፀዋል፡፡

ግጭቱን ለማብረድ ከጥር 29/2000 ዓ.ም ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ተሰማርተው የማረጋጋት ስራ እየሰሩ መሆኑን አቶ ሀይለየሱስ አስታውቀዋል፡፡

የደራሼ ልዩ ወረዳ የፖሊስ ጽህፈት ቤት የአስተዳደርና ፋይናንስ ሀላፊ ዋና ሳጅን ገረሱ ገሪቴ ግጭቱ መከሰቱን አምነው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የደቡብ ክልል የፖሊስ ቢሮ ተወካይ ተጠሪ ኮማንደር ሳሙኤል ኤርገንዶን በማነጋገር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ ግጭት መነሳቱንና ጉዳት መድረሱን የአካባቢውን አስተዳደርና ፖሊስ ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በተሾመ ንቁ
 
< Prev   Next >