| "የቅንጅት" የፓርላማ ቡድን ስያሜ... |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
|
"የቅንጅት" የፓርላማ ቡድን ስያሜ ሌላ ውዝግብ አስነሳ
የቀድሞ የቅንጅት ተመራጮች የፓርላማ ቡድን የሚለውን ስያሜ መጠቀማቸው ውዝግብ አስነሳ፡፡ ከወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ቡድን ጋር ለመዋሃድ የተስማሙት የቀድሞ ቅንጅት የፓርላማ ተመራጮች የስራ ሀላፊ የሆኑት አቶ ተመስገን ዘውዴ እንደገለጹት ሰሞኑን ከወ/ሪት ብርቱካን ጋር አልተሰማማንም ብለው መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች በፓርላማ ቡድንነት አይታወቁም፡፡ "እኛ በፓርላማ ቡድንነት ባንታወቅም በቡድን እየተንቀሳቀስን ነው" ሲል ሌላኛው ወገን ገል ል፡፡ "የፓርላማ ቡድን ነን ብለው መግለጫ እየሰጡ የሚገኙት ወገኖች በፓርላማ ውስጥ በቡድን መልክ የሚታወቁ አይደሉም" ያሉት አቶ ተመስገን የግለሰቦቹ ቁጥርም ከአራትና ከአምስት የሚበልጥ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከወ/ሪት ብርቱካን ቡድን ጋር ድርድር ያደረገው የፓርላማ ቡድን እንዳልተስማማ ተደርጎ የተዘገበውም የርሳቸውን የፓርላማ ቡድን የማይወክል መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡ የፓርላማው ስነ ምግባር ደንብ ከአስር በላይ መቀመጫ ላላቸው የፓርላማ ተመራጮች በቡድን መደራጀት ከፈለጉ እውቅና እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ተመስገን የፓርላማ ቡድን መሆናቸውን የሚገልጹት ግለሰቦች ቁጥራቸው ከአስር በታች ባይሆን ኖሮ በቡድን ሊደራጁ ይችሉ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ አቶ ተመስገንን እንደሚሉት አሁን የፓርላማ ቡድን ነን በማለት ከወ/ሪት ብርቱካን ቡድን ጋር መስማማት ላይ አለመድረሳቸውን የገለጹት የፓርላማ ተመራጮች በኢንጅነር ሀይሉ ሻውልና በወ/ሪት ብርቱካን ቡድን መካከል የአስታራቂነት ሚና ለመጫወት ሙከራ አድርገው ያልተሳካላቸው ናቸው፡፡ የእርሳቸው ቡድን ከወ/ሪት ብርቱካን ቡድን ጋር እየተወያየ ያለበትን ጉዳይ አሁን መግለጽ እንደማይፈልጉ የገለጹት አቶ ተመስገን ሁለቱም ወገኖች ለብዙ ጊዜያት መሰብሰባቸውንና ውይይቱም በተሳካ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አሁን የሚመሰረተው ፓርቲ ምን አይነት ስያሜና ምልክት እንደሚኖረው ለተጠየቁት ሲመልሱም "ብዙ አማራጮች አሉን" ብለዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የቀድሞ የቅንጅት የፓርላማ ተመራጭ አቶ ጌታቸው ባያፈርስ በበኩላቸው እርሳቸው የሚወክሉት የፓርላማ ቡድን ከአቶ አየለ ጫሚሶና ከአቶ ተመስገን ዘውዴ ቡድን ውጭ ሆኖ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የ28 የፓርላማ አባላት ፊርማ ያለው ፒቲሽን ይዘው በፓርላማ ውስጥ በቡድን ለመደራጀት ጠይቀው እንደነበር የገለጹት አቶ ጌታቸው በወቅቱ ፓርላማው በተከፈተበት ጊዜ በቡድን ስላልተደራጃችሁ በሚል ምክንያት በቡድን እንዳይደራጁ መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድም ለአፈ ጉባኤው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለገሰ ቢራቱ የፓርላማ ቡድን አባላት መሆናቸውን ስለሚገልጹት ሰዎች ሲናገሩ የፓርላማ ተመራጮቹ በቡድን ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮም ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመው ነገር ግን በአባላት ስነ ምግባር ደንብ መሰረት በቡድን መደራጀት ያበቃ በመሆኑ ፈቃድ መከልከላቸውን አመልክተዋል፡፡ "የፓርላማ ተመራጮቹ በቡድን የመደራጀት ፈቃድ የተከለከሉት ግን ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ አይደለም" ብለዋል፡፡ "ወ/ሪት ብርቱካንና ኢንጅነር ሀይሉ ሻውል በእስር ቤት በቆዩበት ወቅት መሪዎቻችን ናቸው ብለን ቆይተናል" ያሉት አቶ ጌታቸው ባያፈርስ በአሁኑ ሰዓት በሁለቱ አመራሮች የተፈጠረው የሀሳብ ልዩነት በውይይት እንዲፈታና ለሽምግልና ሂደት ተባባሪ እንዲሆኑ ለሁለቱም ወገኖች ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሰሞኑን ያደረጉት የላዕላይ ምክር ቤት ማሟላትና አዲስ ፓርቲ የመመስረት ስምምነትም የምክር ቤቱን ሕግና ደንብ የሚጥስ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡ አቶ ጌታቸው እንደሚሉት አመራሮቹ የሚያደርጉት ውይይት የኢትዮጵያ ህዝብን በሚያሳትፍ መልኩና የቅንጅትን ቤተሰብ ልዩነት በሚፈታ መልኩ መካሄድ አለበት እንጂ አንደኛው ወገን ብቻ የላዕላይ ምክር ቤት ጥሪ ማድረግ የለበትም፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን የጠሩት የላዕላይ ምክር ቤት ኮረም የሞላ አለመሆኑንና ኢንጅነር ሀይሉን ወይም አቶ አባይነህን ያላካተተ መሆኑን የጠቆሙት የቀድሞው የቅንጅት የፓርላማ ተመራጭ ውሳኔው የፓርቲውን ሕገ ደንብ የሚጥስ መሆኑን ለወ/ሪት ብርቱካን እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካንም "የምክር ቤት ውሳኔ ስለሆነና አግባብ ነው ብዬ ስለማምንበት እንቀጥልበታለን" የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ ከላዕላይ ምክር ቤት እውቅና ውጪ ኢንጅነር ሀይሉ ሻውል የወሰዱት የእገዳ እርምጃ በተመለከተ እርሳቸው የሚወክሉት ቡድን ያለውን አመለካከት ለተጠየቁት አቶ ጌታቸው ሲመልሱ "በአመራሮቹ ላይ የተወሰደው እገዳ ከፓርቲው ሕገ ደንብ ውጭ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ላዕላይ ምክር ቤትና ሥራ አስፈፃሚው ተነጋግሮ የሚወስነው ውሳኔ ነው" ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ኢንጅነር ሀይሉ ሻውል አቶ አባይነህ ብርሃኑን ለመወከል ስልጣናቸው ይፈቅድላቸዋል ወይም አይፈቅድላቸውም የሚለውንም ጉዳይ ለመወሰን ደንቡን አይቶ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ እነ ወ/ሪት ብርቱካን ያካሂዱትን ስብሰባና የድርድር ስምምነት ሕገ ደንቡን የሚጥስ ነው ካላችሁ ኢንጅነር ሀይሉ ሻውል የወሰዱት እርምጃ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን በተመሳሳይ መልኩ ለመናገር እንዴት አልቻላችሁም? በሚል ለተጠየቁት አቶ ጌታቸው "ፕሬዚዳንቱ ለስራ አስፈፃሚዎች ውክልና እንደሚሰጡ ደንቡ ላይ ተቀምጧል፡፡ ውክልናው ሕገወጥ ነው እንዳንል ውክልና መስጠት እንደሚችሉ ደንቡ ላይ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን በምን አይነት ሁኔታ ነው ውክልና መስጠት የሚችሉት የሚለውን ዝርዝር መመሪያው ደንቡ ላይ ስላልተቀመጠ ልንሄድበት አንችልም፡፡ ይህ በሥራ አስፈፃሚውና በላዕላይ ምክር ቤቱ የሚታይ ውሳኔ ነው" ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው እንደገለጹት እርሳቸው የሚወክሉት ቡድን አሁንም ድረስ የኢንጅነር ሀይሉ ሻውልና የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ደጋፊ ነው፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች የቅንጅት አመራሮች መሆናቸውን ይቀበላል፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |