| ከአንቀልባ ወደ “ሙሽርነት” |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
“ሴት ህፃናት ደስታችን ምሉዕ እንዲሆን አንቀልባችንን ጣሉልን” የሚል ፖስተር በቅርቡ በአንድ በሴቶች ላይ የሚሠራ ድርጅት ቢሮ ተሰቅሎ መመልከቴን አስታውሳለሁ፡፡ የፖስተሩ ዓላማ ሴት ልጆች እንደእኩዮቻቸው ወንድ ልጆችና ዕድሜያቸው እንደሚጠይቀው ቦርቀው እንዲያድጉ እንዲፈቀድላቸው፣ በለጋ ዕድሜያቸው ታናናሾቻቸውን የመጠበቅ፣ ፣የማዘል፣ ኃላፊነት እንዲነሳላቸው መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡በቅርቡ የወጣን፣ በኢትዮጵያ በተለይ ሰሜናዊ ክፍል ህፃናትን የመዳሩ ባህል እየቀጠለ መምጣቱን የሚገልፅ ሪፖርት ስመለከት ፣ከአንቀልባ ሳንወርድ አትዳሩን፣ የሚል ፖስተር እንደሚያስፈልግ አሰብኩ፡፡ ከዚህ በታች ያለው ታሪክ አሁንም ሴት ልጆችን ከአንቀልባ ጀምሮ መዳር በህግ የተከለከለን ተግባር መፈፀም ለመቀጠሉ ምስክር ነው፡፡ ጉዳዩ ፣የተማሩ፣ እና ፣ከተማ ቀመስ፣ የቤተሰብ አባላት ባሉበት ጭምር የሚፈፀም ለመሆኑም ምሳሌ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዳይፈፀም የሚከላከሉ በየገጠሩ ትምህርት ቤቶች ያሉ መምህራን፣ የተጀመረ/የተወሰነ ጋብቻ እንዲቋረጥ ያደረጉ፣ ልጆችን ከትምህርት ገበታቸው ለማፈናቀል የሚደረገውን ሴራ ከህግ አካላት ጋር በመሆን ያከሸፉ ሰዎች በየቦታው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ለህጉ ፣ጆሮ ዳባ ልበስ፣ የሚሉ የሚመስሉ ወላጆች ዛሬም ከአንቀልባ ያልወረዱ ልጆችን ያጫሉ፣ ቦርቀው ያልጠገቡ ህፃናትን ፣የልጅ ሙሽሮችን፣ ይድራሉ፡፡ ሰብለ ሸዋንግዛው የአሥር ዓመት ታዳጊ ሕፃን ነች፡፡ የተወለደችው ጅሩ ልዩ ስሙ ይማድጋ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ የሰብለ እናትና አባት የሚተዳደሩት በግብርና ነው፡፡ ሰብለ ለወላጆቿ ሦስተኛ ልጅ ስትሆን ሁለት ታላላቅ ወንድሞችና አንድ ታናሽ እህት አሏት፡፡ ሰብለ የስምንት ዓመት ልጅ እያለች ለባል ታጨች፡፡ ወላጆቿም ዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ለእጮኛዋ ሊድሩለት ቃል ይገቡለታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የሰብለ የአባትዋ ወንድም ቤተሰቡን ለመጠየቅ ወደ ጅሩ በሄደበት ወቅት የስምንት ዓመቷ ሕፃን ለባል መሰጠቷን ሰምቶ ጉዳዩ ስላሳሰበው ወለጋ ወስዶ ሊያስተምራት ወላጆቿን አስፈቅዶ ወደ አዲስ አበባ ይዟት መጣ፡፡ አዲስ አበባ ለሰብለ አክስት፣ ለአባትዋ እህት የሆኑት ወ/ሮ እልፍነሽ ተፈራ ታመው ስለነበር ለጥየቃ ጐራ ያሉት ሰብለ እና አጐቷ ሌላ ዜና ይሰማሉ፡፡ ወ/ሮ እልፍነሽ ሰብለን እንደሚያስተምሯት ቃል በመግባት ወንድማቸውን አሳምነው ከወለጋ ቀርታ አዲስ አበባ መኖር እንድትጀምር ይስማማሉ፡፡ የሰብለ አክስትም በቃላቸው መሠረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንድትማር በ1998 ዓ.ም. አስገቧት፡፡ ሰብለም በትምህርቷ ጥሩ ውጤት አምጥታ ወደ ሁለተኛ ስትዛወር ይበልጥ ጎበዝ ሆነች፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ፍላጎትም እያደረባት መጣ፡፡ ሆኖም ችግር ገጠማት፡፡ ህፃን ሰብለ የገጠማትን ችግር በሪፖርቱ ላይ እንደሚከተለው ገልፃዋለች፡፡ “ወላጆቼ አክስቴን እኔን ወደ ገጠር እንድትመልሰኝና እንድዳር ስላግባቧት ከሰኔ 29 ቀን 1999 ዓ.ም. በኋላ ትሄጃለሽ ብላኛለች፡፡ ጅሩ የሚወስዱኝ የአጎቴ ሚስት ከገጠር መጥተዋልና እባካችሁ አስጥሉኝ፡፡ እኔ ትምህርቴን በጣም እወዳለሁ፡፡ ተምሬም ወላጅ አልባ ህፃናትን መርዳት እፈልጋለሁ፡፡ እኔ እኮ ገና 1ዐ ዓመቴ ነው፡፡ በዚህ ዕድሜዬ እንዴት እዳራለሁ? መዳር በፍፁም አልፈልግም፡፡” መምህራኑ የሰብለን አክስት በተደጋጋሚ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ቢያስጠሯቸው የተለያየ ሰበብ እየፈጠሩ መምጣት እንዳልቻሉ ገልፀው ነበር፡፡ ሰኔ 29 ቀን 1999 ዓ.ም. ሰብለ ሰርተፍኬቷን ለመቀበል ትምህርት ቤት በመጣችበት ወቅት መምህሮቿ ጠይቀዋት የተለወጠ ነገር ያለመኖሩን እያለቀሰች እንደነገረቻቸው ገልፀውልን ነበር፡፡ የተጠቂ ሴቶችና ህፃናት አገልግሎት ማዕከል የ1ዐ ዓመቷ ህፃን የገጠማትን ችግር ለመቅረፍ ወ/ሮ እልፍነሽ ቤት በአካል ተገኝቶ ለረጅም ሰዓት ከፍተኛ የማሳመን ሥራ በመሥራቱ ሰብለ ወደገጠር ሄዳ ያለ ዕድሜዋ እንዳትዳር ታድጓታል፡፡ አክስቷ ሰብለን አስተምራለሁ፡፡ ተባባሪ ሆኜ ሰብለ ያለዕድሜዋ ብትዳር የመጀመሪያዋ ወንጀለኛና በህግ ተጠያቂ እኔ ነኝ በማለት ቃል ገብተው በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡ በ1992 ዓ.ም. የቤተሰብ ህጉ ከፍትሐብሔር ህጉ ተነጥሎ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ አዲሱ ህግ የቀድሞው በሴቶች መብቶች ላይ የጣላቸውን ገደቦችና አድልኦ በማንሳቱ ህጉ እንዲሻሻል ሲሰሩ የነበሩትን ያስደሰተ ነበር፡፡ ይህ ህግ ደንግጐ ካወጣቸው አንቀፆች መካከልም ያለዕድሜ ጋብቻን ያስቀረውና የሁለቱም ተጋቢዎች ዕድሜ 18 መሆን እንዳለበት የደነገገው አንቀፅ ይገኝበታል፡፡ የፌደራሉ መንግሥት ያወጣው ይኸው ህግ ተፈፃሚነቱ ለአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች ቢሆንም ሌሎች ክልሎች ያወጧቸውም ህጐች በተመሳሳይ (የትግራይ ክልል የቤተሰብ ህግ የወንዱን ተጋቢ ዕድሜ 21 ዓመት የሴቷን 18 አድርጐ ከመወሰኑ በቀር) ዝቅተኛ የጋብቻ ዕድሜ ለሁለቱም ፆታዎች ተመሳሳይ 18 እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሆኖም ገጠሩ ያለዕድሜ ጋብቻ በህግ መከልከለን ፣አልሰማማም፣ እስኪባል ድረስ የኢትዮጵያ የገጠር ሴቶች ከህጉ ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ዛሬም ከአንቀልባ ከወረዱ 5 ዓመት ያላለፋቸው ሳይቀሩ ይታጫሉ፤ ለባል ይሰጣሉ፡፡ በዚያ ምክንያት ለሚመጡ የጤና ችግሮችም ይጋለጣሉ፡፡ ከላይ እንዳየነው ታሪክ ከተማ መጥተው የልጅ ሙሽራ ከመሆን ፣አመለጥን፣ ቢሉ እንኳን ተሳደው ተይዘው መመለሳቸው፣ ወደፈሩት ላለመግባታቸው ዋስትና የላቸውም፡፡ ባለፈው ወር አጋማሽ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ህዝብ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ሪፖርት እንዳለው በኢትዮጵያ የገጠር አካባቢዎች በተለይም በሰሜን አካባቢ ልጆችን የመዳሩ ባህል አልተለወጠም፡፡ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ደግሞ ኢትዮጵያ ህፃናት ልጆችን ለጋብቻ መስጠት ከሚከናወንባቸው ጥቂት ታዳጊ የዓለም ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ሪፖርቱ እንዳመለከተው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል፣ አማራ ክልል ሴት ህፃናት 4ዐ በመቶው ከ15 ዓመት በታች ያለዕድሜ ለባል ይሰጣሉ፡፡ ልጆቹን የመዳሩ አንድ ዓላማ ፣በዕድሜ ከፍ ካሉ ድንግልናቸውን ያጣሉ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የሚያገባቸው አያገኙም፣ ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡ ሌላው የኢኮኖሚ ጥያቄ ሲሆን በልጆች ለውጥ (ጥሎሽ) የሚሰጥ የቁም ከብትና ገንዘብ ቤተሰቦቻቸውና ከማህበረሰቡ የተለዩ ፣ሀብታም፣ ስለሚያደርጋቸውም ነው፡፡ የተሻለ ከሚባል ቤተሰብ የተገኙትን ደግሞ በጠለፋም ቢሆን የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው በመደበኛው መንገድ ለትዳር ቢጠይቁ ፈቃደኝነትን አናገኝም ከሚል የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ያለዕድሜ ጋብቻ ጥያቄ የህፃናቱ ለጋነት የሚያመጣቸው እንደ ፊስቱላ ያሉ የጤና ችግሮች ጥያቄ ነው፡፡ ህፃናቱ ያላቸው ትምህርት የማግኘት መብት፣ ለተሻለ ህይወት ያላቸው ተስፋ የሚጨልምበትም ነው፡፡ አንድ የዩኒሴፍ ጥናት እንደሚያስረዳው በልጅነታቸው የሚዳሩ ሴት ልጆች ቁጥር ባለመቀነሱ፤ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በሚከሰት ችግር ምክንያት በለጋ ዕድሜያቸው የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር እጥፍ ሆኗል፡፡ በታዳጊ ሀገሮች ከ15-19 ባለ ዕድሜ ለሚሞቱ ሴት ልጆች የሞት ምክንያት በለጋ እድሜ የሚያጋጥም እርግዝና ዋነኛው ነው፡፡ ልጆቹ ሰውነታቸው ያልጠነከረ በመሆኑም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ ህፃናቱ ያለዕድሜያቸው ከትምህርት ቤት ቀርተው የሚገቡበት ጋብቻ ትምህርትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ከማደናቀፉ ባሻገር ዕድሜያቸውን በሙሉ በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ ሴቶችን ያለዕድሜያቸው መዳር ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች የተለመደ ነው፡፡ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎችም ከ10-19 ዓመት ያሉ ታዳጊዎችን መዳር የተለመደ ነው፡፡ በ2006 331 ሚሊዮን ታዳጊ ልጆች በዓለም በዚህ ዕድሜ ክልል ለጋብቻ ተሰጥተዋል፡፡ 163 ማሊዮኑ ደግሞ በ20 ዓመታቸው የሚያገቡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከ10 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ጭምር እንደሚዳሩ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የዩኒሴፍ ጥናት እንዳለው ከሰሀራ በታች ባሉ 16 ሀገሮች የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ታዳጊ ልጆቹን ከሚያገቡት ወንዶች በአብዛኛዎቹ ከታዳጊዎቹ ከ1ዐ ዓመት በላይ የሚበልጡ ናቸው፡፡ ታዳጊዎቹ ምንም ዓይነት መረጃ የማያገኙ፣ ያልተማሩ አልያም ትምህርት ከጅምሩ ያቋረጡ ስለሚሆኑ ስለወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ዕውቀት የላቸውም፡፡ በዚህም ደጋግሞ ለመውለድ ለጉዳት እንዲሁም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር ለሞት ይጋለጣሉ፡፡ ኮንዶም መጠቀምንም ይሁን ሌሎች ጥንቃቄ የተሞላበት ወሲብ የመፈፀምን ሁኔታዎች ለመደራደር አቅሙም ሆነ ዕውቀቱ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለኤች.አይ.ቪ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በልጅነታቸው በሚያገቡ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትም የተለመደ መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ በዓለም ከ15-19 ዓመት ባለው ዕድሜ ያሉ 15 ሚሊዮን ታዳጊዎች ይወልዳሉ፡፡ ይህም በዓለማችን በየዓመቱ ከሚወለዱ ህፃናት 1ዐ በመቶ የሚሆነው ነው፡፡ በቤተልሔም ነጋሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |