Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow "በኤርትራ ነፃነት የሚያምን ስርዓት...
"በኤርትራ ነፃነት የሚያምን ስርዓት... Print E-mail
Sunday, 10 February 2008
Image"በኤርትራ ነፃነት የሚያምን ስርዓት እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ትክክለኛ የትግል ቦታ ነች"
አቶ መንግሥተኣብ አስመሮም
የተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ (ጀብሃ) - ሳወራ ባይቶ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ

አቶ መንግሥትኣብ አስመሮም በ1967 ዓ.ም. ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ (ደብሃ) ጋር ተቀላቅለው እንደተራ ታጋይ ቀጥለውም እንደ ካድሬ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ጀብሃ በ1973 ዓ.ም. ለሦስት ቦታ የተከፈለ ሲሆን እሳቸው ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ-አብዮታዊ ምክር ቤት (ሰውራዊ ባይቶ) በአሕመድ ናሲር ከሚመራ ወገን ጋር ሲሆኑ በ1987 ዓ.ም. በተደረገው አራተኛ ጉባዔ የድርጅቱ ፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠው እስከአሁን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ይሰራሉ፡፡

አስራ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባል የሆኑበት የኤርትራ ዴሞክራሲያዋ ኪዳን ለሁለት ተከፍሎ የቆየ ሲሆን በቅርቡ ተቀራርበው የጋራ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ ኪዳኑ በመጪው መጋቢት ወር ላይ ጠቅላላ ጉባዔ የሚጠራ ሲሆን ይህንን የሚያመቻች ኮማቴ ተቋቁሟል፡፡

አቶ መንግሥተኣብ የአመቻቹ ኮሚቴ አባል ሆነው የተመረጡ ሲሆን ስለ ስብሰባው፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶችና በኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶች የጋራ ስብሰባ አዲስ አበባ ውስጥ አካሂዳችል፡፡ የስብሰባው ዓላማ ምን ነበር? እነማንስ ተሳትፈዋል?

አቶ መንግስተኣብ፡-
በቅርቡ ከጥር 15-19 ስብሰባ አድርገናል፡፡ በስብሰባው 11 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፡፡ የስብሰባው ዓላማ ደገሞ ባለፈው ዓመት ጉባኤ ያካሄደው የኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ኪዳን ለሁለት ተሰንጥቆ የቆየ ሲሆን ይህንን በማስታረቅ ወደ አንድ ለማምጣት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስብሰባው የተሳካ ነበር ይላሉ? ምን አደረጋችሁ?

አቶ መንግስተኣብ፡-
አዎ፡፡ በጣም የተሳካ ነበር፡፡ ተቀራርበን ተግባብተናል፡፡ በመጨረሻም በሚቀጥለው መጋቢት ወር ላይ ሌሎች ሁለት አዲስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጨምረን ጉባኤ ለማካሄድ ወስነናል፡፡ እንዱሁም በስብሰባው በታዛቢነት እንዲሳተፉ የተመረጡ ወገኖችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙት ከአስር በላይ የኤርትራ ሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶች (ከክርስትናም ከእስልምናም) እንዲሁም ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ በትግል የቆየው አህመድ ስይራ ይገኙባቸዋል፡፡ እንዲሁም ከአሥራ ሦስቱ ተቃዋሚ ድርጅቶች ውጭ የሚገኙ ሌሎች ተቃዋሚዎች በሊቀመንበራቸው አማካኝነት በታዛቢነት እንዲሳረፉ ወስነናል፡፡ እነዚህ አሥራ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ሦስት ሰዎች ይወክላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጉባዔውን የሚያመቻች አመቻች ኮሚቴ አቋቁመናል፡፡ ኮሚቴው ሦስት አባላት ያቀፈ ሲሆን እነሱም ሁሴን ኸለፋ፣ እኔና ኑር መሐመድ ኢድሪስ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- የስብሰባው ዋና ዓላማ ለሁለት የተከፈለውን ኤ.ዴ.ኪ. ለማስታረቅ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ የመከፋፈላችሁን መንስዔ ፈትሻችኋል?

አቶ መንግስተኣብ፡-
አዎ ፈትሸናል፡፡ አንደኛው ምክንያት የቆየው የእርስ በርስ አለመተማመን ነው፡፡ ሁለተኛ የፖለቲካ ልዩነታችን ማቻቻልና ማጥበብ እጥረት እንደነበረን አይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- አለመተማመን ሲሉ . . . ?

አቶ መንግስተኣብ፡-
አንዱ ከሌላው ድርጅት ተገንጥሎ የወጣ ከመሆኑ የተነሳ፡፡ ከታሪካዊ ልዩነት የመነጨ ነው፡፡ አንድ አንድ ልዩነት ካለንም ልዩነታችንን ይዘን አንድ በሚያደርገን ተስማምተን እንዳንሄድ አድርጎናል፡፡ አሁን ግን ይህንን ተገንዝበን ልዩነታችንና የእያንዳንዳችን ድርጅት የፖለቲካ አቋም የሚያጠና ኮሚቴም ፈጥረናል፡፡ በመጨረሻም ኮሚቴው ለጉባዔ የመፍትሄ ሃሳብ ሊረዳ የሚችል ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ያለንን ልዩነት ማጥበብ የማይቻል አለመሆኑ መገንዘብ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባዔው የስደት መንግሥት ለመፍጠር ነው ይባላል፡፡ እውነት ነው?

አቶ መንግስተኣብ፡-
የጉባዔው ዓላማ ሁሉንም ተቃዋሚ ድርጅቶች ያካተተ አንድ ትልቅ የእናት ድርጅት ለመመስረት ነው፡፡ በእሱ በኩል ትግሉን በማፋፋም ሁሉንም መንገድ ተጠቅመን አምባገነኑን የኤርትራ መንግሥት ለማስወገድ ነው፡፡ የስደት መንግሥት የመመስረት አጀንዳ ግን በአሁኑ ወቅት አልተባለም፡፡ በመጪው ጉባዔም የተያዘለት አጀንዳ አይደለም፡፡ ምናልባት ግን አንዳንድ ድርጅቶች በተናጠል አንስተውት ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሁላችሁ አንድ የሚያደርጋችሁ አቋም ምንድን ነው?

አቶ መንግስተኣብ፡-
ኤርትራ ውስጥ ያለው አምባገነናዊ ስርዓት የሁለም ችግሮች ጠንቅ መሆኑና መወገድ እንዳለበት ሁላችን እናምናለን፡፡ እንዲሁም በኤርትራ ውስጥ ዲሞክራሰያዊ ስርዓት መመስረት አለብን የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሻዕቢያ እንዴት መወገድ እንዳለበትስ ስትራቴጂ ላይ ትስማማላችሁ?

አቶ መንግስተኣብ፡-
እንዴት ይወገድ በሚል የተለያዩ ድርጅቶች የተለያየ ስትራቴጂ  አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በሽምቅ ትግል (በዓመፅ) ጭምር የሚሉ አሉ፡፡ ይሄ ስርዓት ሲጀመር ሥልጣን በፍቃዱ ለህዝብ የሚያስረክብ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኃይልን በመጠቀም ብቻ ነው ማስወገድ የሚቻለው ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡

ስለዚህ እኛ ሁላችን ይህንን ስርዓት ለማስወገድ የያዝነውን መንገድ (ስትራቴጂ) አዋህደን ወይ በየእምነታችን ሰላማዊም ሆነ ወታደራዊ ኃይል ተጠቅመን ይህንን ስርዓት ለማስወገድ የጋራ መግባባት ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኤርትራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገና ከስብሰባ ሳይወጡ ይከፋፈላሉ፡፡ ስልጣን ፈላጊዎች ናቸው ወዘተ፤ የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማል፤

አቶ መንግስተኣብ፡-
ይህንን አመለካከት ቀና ነው ብዬ አላምንም፡፡ ልዩነት በኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ዙሪያ የሚታይ ባህሪያዊ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ ላይ በመታየቱም የሚያስገርም አይደለም፡፡ ገና ከስብሰባ ሳይወጡ ነው የሚለያዩት የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ "ኪዳን" ለሁለት ዓመት ያህል አንድ ላይ ተጉዘናል፡፡ ከዛም በፊት ለአራት/አምስት ዓመታት አብረን ነበርን፡፡ የእኛ ችግር በመካከላችን የሚፈጠር ልዩነት በአግባቡ አለመፍታት ነው፡፡ የነበረን ልዩነትም የሚጋነንና ማጥበብ የማይቻል አይደለም፡፡

ስለ ፖለቲካዊ ሥልጣን ከሆነ ደግሞ እኛ በፖለቲካ ዙሪያ የተሰበሰብነው የዕቁብ ሥራ ለመስራት አይደለም፡፡ ፖለቲካ ከሥልጣን ተለይቶ የሚታይ አይሆንም፡፡ ለፖለቲካዊ ስልጣን መታገልም ነውር አይደለም፡፡ ነውር የሚሆነው የፖለቲካ ሥልጣን አለአግባብ ለመያዝ መሞከርና አለአግባብ ጥቅም ላይ ማዋል ነው፡፡ ከዚህ በስተቀር የፖለቲካ ድርጅቶች በመሆናችን የፖለቲካ ሽኩቻ ከታየ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁላችሁም መሪ የመሆን ፉክክርና ፍላጎት አላችሁ ይባላል፡፡ ይሄስ ተፈጥሮአዊ ነው?

አቶ መንግስተኣብ፡-
ይሄም የእያንዳንዱ ግለሰብ መብት ነው፡፡ ሁሉ ሰው መሪ መሆን መፈለጉ፣ ለመሪነት መወዳደሩ አሁንም ኃጥአት አይደለም፡፡ ግን እንዴት የሚል ነው፡፡ ተቋማዊ መዋቅራዊ የሆነ አሰራር ሊኖረን ይገባል፡፡ ከዛ ሁሉ ሰው መሪ ሊሆን ስለማይችል ብዙዎች የተቀበሉት በአሰራሩ መሠረት መሪ ይሆናል፡፡ ለዚህ መዋቅራዊ አሰራርም (ህገ ደንብ) ተገዢ መሆን አለብን፡፡ ልናከብረውም ይገባል፡፡ ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለ3ዐ ዓመታት ያህል ለህዝቡ ነፃነት የታገሉት ኢሳያስ ተመልሰው ህዝቡን ጨቁነዋል ከተባለ ህዝቡስ በእናንተ ላይ እንዴት መተማመን ይችላል?

አቶ መንግስተኣብ፡-
የኤርትራ ህዝብ ዋስትና ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ ሌላ ማንም አካል ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባትም ኢሳያስ ለምን አገሪቱን በዚህ መጥፎ ሁኔታ ላይ አስወደቃት ካልን ህዝቡ መንስኤው በኢሳያስ ላይ ፍፁም የሆነው እምነት በማሳደሩ ነው፡፡ በእኛም ላይም እንዲህ ዓይነት ፍፁም እምነት ሊኖረው አይገባም፡፡ ራሱ በትግሉ መሳተፍ አለበት፡፡ በእኛ እንቅስቃሴ ላይም የቅርብ ክትትል ሊያደርግ ይገባል፡፡ የመፃኢ ዕድሉ መወሰን ያለበት ራሱ የኤርትራ ህዝብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ግን በአገር ውስጥ ምንም ዓይነት ተቃውሞ/አመፅ ሲያደርግ አይታይምኮ፤

አቶ መንግስተኣብ፡-
የአመፅ መገለጫዎች ይለያያሉ፡፡ የኤርትራ ህዝብ አመፅ  መገለጫዎች አሉት፡፡ ህዝብ አይቃወምም፤ የሚል አረዳድ ሊኖረን አይገባም፡፡ የኤርትራ ህዝብ ተቃውሞን በቻለው ሁኔታ እየገለፀ ነው ያለው፡፡ በመሰረቱ ፀጥ ማለት ራሱ ተቃውሞ ነው፡፡ በዋናነት ግን የኤርትራ ወጣቶች በየቀኑ አገር ለቀው እየወጡ ነው ያሉት፡፡ ለምን ይሰደዳሉ ካልን ስርዓቱ እያሳደረባቸው ካለ ግፍ ለማምለጥ ነው፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች ተጋድለዋል፡፡ ሌሎች ወጣቶችም እንዲሁ፡፡ የተቃውሞ ደረጃው ሊለያይ ይችላል እንጂ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተቃውሞአቸውን እየገለፁ ነው ያሉት፡፡ ሌላ ግምት ማስገባት ያለብን ደግሞ የኤርትራ ህዝብ ለሠላሳ ዓመታት ያህል በነፃነት የትጥቅ ትግል የቆየ ህዝብ ነው፡፡ ድካም አለ፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ሰላምና ደስታ ለማግኘት የነበረው ጉጉት ተሰናክሏል፡፡ የነበረው ተስፋ ሲያጣ እንደ አዲስ ወደ ትግል ለመነሳት ቀላል አይሆንም፡፡ ህይወታቸው ሙሉ በነፃነት ትግል ላይ ያሳለፉ ምን አግኝተዋል? አንዳንዶቹ ታስረው፣ አንዳንዶቹ ተገድለው፣ ሌሎቹም ተሰደው የሚያይ "ታግለን የምናመጣው ለውጥ አይኖርል" የሚል ስሜት ይኖራል፡፡ ስለዚህ ድካምና ተስፋ መቁረጥ የመሳሰሉ ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የማታገያ ቦታ አድርጋችሁ የመረጣችኋት ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት የእናንተን የኤርትራ ህዝብ ተቀባይነትና እምነት አያሳጣችሁም?

አቶ መንግስተኣብ፡-
በመሰረቱ የእኛ አንደኛ የትግል ምርጫችን አገራችን ውስጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በኤርትራ ውስጥ ያለው ስርዓት ይህንን የሚፈቅድ አይደለም፡፡ ከእሱ የተለየ ፖለቲካ ኤርትራ ውስጥ እንዲሰማ አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ከአገር ውጭ ሆነን ለመታገል የወሰነው ተገደን ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአባቶች ምሳሌያዊ አነጋገር አለ፡፡ "ካብያ ርሑቅ ዘመድስ ናይ ቀረብ ጎረበት" (ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት"፡፡ ስለዚህ በኤርትራ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መስራት የሚቻለው በጎረቤት አገሮች አካባቢ በመሆን ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ ሾልከን መግባት እንችላለን፡፡ አሁንም አንዳንድ ጊዜ ሾልከን በመግባት መፅሄት እናሰራጫለን፣ ከህዝባችን ጋር እንገናኛለን፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተሻለ ቦታ የለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መሆናችሁ የህዝብ እምነት አያሰጣችሁም ለሚለው ጥያቄ፣ የሻዕቢያ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆናችን በከዳትነት እየፈረጀ ከህዝባችን ጋር ማራራቅ የማጥላላት ኘሮፖጋንዳ አያደርግም አይባልም፡፡ በዚህ የሚደናገር ሰውም አይጠፋም፡፡ እኛም ግን ይህንን ሰግተን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ዘንግተን ከዚህ መራቅ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ሻዕቢያ ኢትዮጵያን የሚገልፁት የኤርትራን ነፃነት ልትወር ነው፡፡ መሬታችን ልትወሰድብን ነው ወዘተ. በሚል ስለሆነ መሰረት የሌለው ኘሮፖጋንዳ ነው፡፡ በመሆኑም በርግጠኝነት ተዋደደም ተጠላም ለኤርትራውያን የተሻለች አጋር ኢትዮጵያ ነች፡፡

እንደውም ሻዕቢያ ይህንን ኘሮፖጋንዳ ይንዛ እንጂ በተቃራኒው እሱ የሚቧደናቸው ጭራሽ በኤርትራ ነፃነትም የማያምኑ ናቸው፡፡ ይህንን ሳያውቅ አይደለም፡፡ ግን እንደ መሳሪያ እንዲጠቀምባቸው ስለሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በኤርትራ ነፃነት ከሚያምን ስርዓት ጋር ሁነን ኢትዮጵያ ውስጥ በመስራታችን ምንም ዓይነት ችግር የለውም፡፡ በኤርትራ ነፃነትና ህልውና የሚያምን ኃይል በሥልጣን እስካለ ድረስ ለትግል ስትራቴጂም ትክክለኛና የተሻለ ነው ብለን ነው የምናምነው፤ አስፈላጊም ነው፡፡ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ከኢትዮጵየ በላይ ረዥም ድንበር የምትዋሰን አገር የለችም፡፡ ይህ የራሱ ጥቅም አለው፡፡ ለሥራችን ቅልጥፍና ከዚህ የበለጠ ቦታ ሊኖር አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርዓት በነፃነት እንድትንቀሳቀሱ ይፈቅድላችኋል? ለምሳሌ በሆነ ጉዳይ እንደ ኤርትራውያን ሆናችሁ ኢትዮጵያን የሚቃወም አቋም መያዝ ትችላላችሁ?

አቶ መንግስተኣብ፡
- እስከአሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዓይነት ቅንጣት ያህል ተፅእኖ አልደረሰብንም፡፡ የተለየ አቋም ባለን ጊዜ ራሱ በነፃነት አቋም የመያዝ፣ የመግለፅና የመንቀሳቀስ መብታችን በጣም የተጠበቀ ነው፡፡ ለምሳሌ በድንበር ጉዳይ አቋማችን እየገለፅን መጥተናል፡፡ በጦርነት ወቅትም ሁለቱም መንግሥት ትክክል አይደሉም ብለን የተቃወምነው ነገር ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስብሰባ ካደረጋችሁ በኋላ ከታላላቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በባለሥልጣናት ተገናኝታችኋል ይባላል፡፡

አቶ መንግስተኣብ፡-
የኢትዮጵያ መንግሥት ኪዳን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ክፍፍል የኤርትራ ህዝብና ወዳጆቹ ተስፋ ያስቆረጠ ነው የሚል ግምገማ አለው፡፡ አሁን ግን እንዲህ ራሳችን ችግራችን መፍታት መቻላችን ጥሩ እርምጃ መሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ከአቶ ስዩም መስፍንም ጋር ተመካክረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የተገባ ድጋፍ አድርጎልናል ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ መንግስተኣብ፡-
እኛ ከዚህ በላይ ድጋፍ እንዲደረግልን እንፈልጋለን፡፡ በኤርትራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢትዮጵያ ህዝብም ይመለከተኛል ብሎ ከዚህ በላይ መንቀሳቀስ እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያ ድሃ አገር ነች፡፡ በርካታ የውስጥ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ቅድሚያ መሰጠትም እንዳለበት እንረዳለን፡፡ መሆንም አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ህዝብ አንድ ህዝብ ነው፣ ሁለቱም ህዝቦች በጋራ ወደፊት መራመድ እንዲችሉ፣ ኤርትራ ውስጥ ያለው ጭቆና ተወግዶ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሮ ያለውን መልካም ዕድል እንዲፈጠር የኢትዮጵያ ድጋፍ እየጨመረ እንዲሄድ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለመሆኑ በእናንተ ግምገማ ኘሬዚደንት ኢሳያስ ኢህአዴግ ከሥልጣን እንዲወርድ ይፈልጋሉ?

አቶ መንግስተኣብ፡
- ዋነኛው ዓላማው ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከሥልጣን እንዲወርድ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ በተለይ የስርዓቱ አጠቃላይ ሐተታ በተለይ ፀረ-ህውሐትና ፀረ-የትግራይ ህዝብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን? ኢህአዴግ እኮ በኤርትራ ነፃነት የሚያምን የኢትዮጵያ ኃይል ነው፡፡

አቶ መንግስተኣብ፡-
የእሱ ግምገማ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከወደቀ ኢትዮጵያ ትበታተናለች ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ኤርትራን የምታሰጋ ኢትዮጵያ አትኖርም የሚል አመለካከት ነው ያለው፡፡ ለዚህ ነው የስርዓቱን ወድቀት የሚመኘው፡፡ ይሄ ደግሞ በተግባር እየተንቀሳቀሰበት ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኤርትራ ህዝብ አሁን በኢትዮጵየ ያለውን ሁኔታ ሲያይ አይቆጭም?

አቶ መንግስተኣብ፡-
በዚህ አይቆጭም፡፡ የመጀመሪያ ጥያቄ የግዛት ጥያቄ ነው፣ የነፃነት ጥያቄ፡፡ ሆኖም ግን ነፃነት ማለት ባንዲራ መስቀል ብቻ አይደለም፡፡ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ነፃነት መከበርም ይጨምራል፡፡ ይሄም መረጋገጥ ነበረበት፡፡ የግዛት ነፃነት ቢገኝም ይህ ተኮላሽቶዋል፡፡ የእኛ ትግል ዓላማም ይህ በመንገድ ላይ የቀረ ዓላማም ለማምጣት ነው፡፡ ይህ ስላልሆነ ግን የኤርትራ ህዝብ በነፃነቱ አይቆጭም፡፡ ቀጣይ ትግል ነው ማድረግ ያለበት፡፡ እምነታችንም ይሄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤርትራውያን ከታሪክ የተማራችሁት ተሞክሮ ምንድ ነው ይላሉ?

አቶ መንግስተኣብ፡-
ከታሪክ የተማርነው አንድ ትልቅ ነገር አንድ ዓላማ ሙሉ ለሙሉ እንዲሳካ የህዝብ ተሳትፎ መኖር ቁልፍ እንደሆነ ነው፡፡ ማንኛወም ነገር ከላይ ወደታች በትዕዛዝ መልክ የሚወርድ መጨረሻው ውድቀት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ህዝብ በግለሰብ መሪ ላይ ፍፁም እምነት ማድረግ እንደሌለበት ነው፡፡ ሁሉም ነገር አንድ መሪ ይሰራዋል የሚል እምነት ማሳደር እንደ ማምለክ ነው፡፡ በኤርትራም የሆነው ይሄው ነው፡፡ ሌላ በተለይ እኛ ኤርትራውያን ከተሞክሮ የተማርነው ጦርነት መፍትሄ እንዳልሆነ ነው፡፡ በጦርነት አሸናፊም ተሸናፊም የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ መንግስተኣብ፡-
የኤርትራ መንግሥት በኤርትራ ህዝብም ሆነ በቀጠናው ህዝብ ላይ ሽብር እየፈጠረ መሆኑን ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ የአሜሪካ መንግሥት ይህ ስርዓት በአሸባሪዎች ተርታ ለማስመዝገብ ሂደት ላይ መሆኑ እንደግፋለን፡፡ ይሁን እንጂ እርምጃው ስርዓቱንና መሪዎቹ ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆን አለበት፡፡ የኤርትራ ህዝብን የሚጎዳ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ እንፈልጋለን፡፡

ከእኛ ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያለን፡፡ ቀደም ሲል እኔ ከአንዳንድ የስቴት ዲፓርትመንት ባለስልጣኖች ጋር ተገናኝቼ ነበር፡፡ አሁንም የቀድሞ የኤርትራ መከላከያ ሚኒስቴር አቶ መስፍን ሐጎስ ከሚስስ ጃንዳይ ፍሬዘር ጋር ተገናኝተዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የኤርትራ ተቃዋሚዎችን የሚረዳበት መንገድ ተወያይተዋል፡፡

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >