| በእሾህ አጥር የታነቀው ብሔራዊ ባንክ |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
|
በአባዋሪ ጅብሪል
ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የብር ኖቶችና ሳንቲሞች የሚያሰራጨው የድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች /ኢሹ ሆልዲንግ ብራንችስ/ አማካይነት ነው፡፡ ከእነዚህም ቅርንጫፎች የሚመለሱ የብር ኖቶችን በመቀበል ከዝውውር የሚወጡትንና ወደ ዝውውር የሚመለሱትን ይለያል፣ መልሶ ያሰራጫል፣ ያቃጥላል፡፡ ቅርንጫፎቹ ጥያቄያቸውን በቴሌግራም የሚያስተላልፉ ሲሆን ባንኩም በዚያው መሠረት ይንቀሳቀሳል፡፡ ሆኖም ግን እጅግ በጣም በሚገርም ሁኔታ በባንኩ ውስጥ ባሉት በ3ቱ ግምጃ ቤቶች ውስጥ፣ ገንዘብ ይዘው በሚያሰራጩት ቅርንጫፎች፣ በቴሌግራም ባንኩ የተቀበለውና ያሰራጨው በዝውውር ላይ አለ የሚባለው የገንዘብ መጠን ለረጅም አመታት በተከማቸና ባልተሰራ ውዝፍ ስራ ምክንያት ባላንስ ባለመደረጉ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ ገዢዎቹም በአሁኑ ሰአት ቢጠየቁ በግምት ከመናገር ውጭ በበቂ መረጃ ተደግፈው መልስ መስጠት አይችሉም፡፡ ለዚህም የሚሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ አሰራር አልተዘረጋም፡፡ ለመምሪያውም የባንኩ መሪዎች ተገቢውን ትኩረት ስላልሰጡት በበቂ የሰው ሀይል የተደራጀ አይደለም፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ በምን መረጃ ተደግፈው ይሆን ውሳኔ እያስተላለፉ ያሉት የሚለው ነው፡፡ ብሔራዊ ባንካችን የተለያዩ የብር ኖቶችን ለማሳተምና ሳንቲሞችን ለማስቀረጽ በርካታ ሚሊዮን ብር ወጪ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ፡-በ1998 ዓ.ም. ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ እንደዚሁም በ1999 ዓ.ም. ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ ይሄ የገንዘብ መጠን ስራው እስከጠየቀና እስካስፈለገ ድረስ በበጀት የሚያዝ ስለሆነ ትክክለኛና ችግር የሌለበት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን ያህል ገንዘብ እየወጣ ያለው ወደ ዝውውር መግባት የሚችል በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የብር ኖት ያለ አግባብ እንዲቃጠል ስለሚደረግና በዚህ ምክንያት በዝውውር ውስጥ የብር እጥረት ስለሚያጋጥም ተጨማሪ ብር እንዲታተም ስለሚታዘዝ ነው፡፡ ለዚህም በዋናነት ሁለት ምክንያኖች አሉ፡፡ አንደኛው በገንዘብ መረጣ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ውጤት ተኮር ነው በሚል ከአቅማቸው በላይና አስቀድሞ ከተጠናው ጥናት ውጪ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በፊት ከሚቆጥሩት የብር መጠን እጥፍ እንዲቆጥሩ በመታዘዛቸውና በሳምንት ውስጥ መቁጠር አለባችሁ ተብለው የታቀደላቸውን የብር መጠን ካልቆጠሩ ዝቅተኛ ነጥብ ስለሚሠጣቸው ሰራተኞቹ ያንን ለማሟላት ሲሉ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለአውሮፓውያን እንዲሆን ተደርጎ የተሰራውና የተገዛው የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽን ትንሽ ቆሻሻ ያለበትን ብር ሁሉ ከዝወውር ውጪ የሚሆን ብር እያለ ስለሚለይና ያንን ብር ደግሞ ባንኩ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ደረጃ ባገናዘበ መልኩ እንደገና በእጅ አስቆጥሮ ወደ ዝውውር ሊገቡ የሚችሉ ኖቶችን ባለመለየቱ እየተከሰተ ያለ ችግር ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ለማረጋገጥ ተብሎ በማሽን ከተቆጠረው ብር ውስጥ ለናሙና የተወሰነው በእጅ ሲቆጠር ከ75 በመቶ እስከ 85 በመቶ የሚሆነው በዝውውር ላይ መዋል የሚችል ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ሂሳብ ሲሰላ ከዝውውር ውጪ የሆነና መቃጠል ያለበት ነው እየተባለ የተቃጠለውና ለመቃጠል የተቀመጠው በቢሊዮን የሚቆጠረው ብር እንደገና ቢቆጠር ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርነው አገሪቱ ለብር ህትመት በየአመቱ የምታወጣውን በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማዳን ይቻል ነበር፡፡ ይህም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ብር በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ኬላዎችን ወዘተ. ሊገነባ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የባንኩ መሪዎች ለቦርዱም ሆነ ለመንግስት የሚያቀርቡት ሪፖርት ስራው በተገቢው ሁኔታ እየተካሄደ እንዳለ በማስመሰል ስለሆነ ቦርዱ በየአመቱ ለገንዘብ ህትመት በሚል በባንኩ መሪዎች ተዘጋጅቶ የሚቀርብለትን ከፍተኛ ገንዘብ (በጀት) ከማጽደቅ ውጪ ትክክለኛ መረጃ ስለሌለው ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ አልቻለም፡፡ ቢሆንም ግን አሁንም አልረፈደምና ቦርዱ ተገቢ ጊዜ ወስዶና ወደታች ወርዶ እየተሰራ ያለውን ስራ ማጣራትና አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ አሁን ከወርቁ ጋር በተያያዘ የባንኩ ጉድ በበለጠ መታየትና መታወቅ ጀመረ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮችን ማባከን ተራ ነገር ሆኖ ከሚታይባቸው ተቋማት ለምሳሌ ቴሌ፣ መብራት ሀይል፣ ልማት ባንክ፣ ንግድ ባንክና የመሳሰሉት አይነት ድርጅቶች ውስጥ ብሔራዊ ባንክም አንዱ ከሆነ በጣም ቆይቷል፡፡ ባንኩ ከባንኮች ና በተለያዩ መንገዶች የሰበሰበውን ዶላር በግምጃ ቤት ውስጥ ካከማቸ በኋላ በየአመቱ ጀርመን አገር በመውሰድ ገቢ ያደርጋል፡፡ ይሄም ስራ የሚሰራው ባንኩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች የሚመጣውን ዶላር ከተቀበለ በኋላ በዶላሩ ላይ ያለውን ቁጥር መዝግቦ በእጅና በማሽን ይቆጠርና የሚመለከታቸወ አካላት ተፈራርመውበት በየጊዜው በግምጃ ቤት ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ወደ ውጪ አገር የሚላክበት ጊዜ ሲደርስ የሚላከው ዶላር ታሽጎ ከከረንሲና ከሪዘርቭ ማኔጅመንት መምሪያዎች ውስጥ የሚወከሉት ሠራተኞች ዶላሩን ይዘው ወደ ጀርመን አገር ይሄዳሉ፡፡ እዚያም አገር ባለው ክሮስፖንዳንስ ባንክ በማሽን ከተቆጠረ በኋላ ሁሉም ነገር ትክክል ከሆነ ገቢ አድርገው ችግር ካለበትም ያለው ሁኔታ ተገልጾላቸው ከ10-15 ባሉ ቀናት ውስጥ ስራቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ፡፡ ከሁለት አመት በፊት የሆነውና ተዳፍኖ የቀረው ጉዳይ ግን የባንኩን ማኔጅመንት የማሽን ግዢና (ወደፊት እንመጣበታለን) ከስራው ጋር በተያያዘ ያለበትን ግዴለሽነት ያሳየ ክስተት ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ ባንኩ በግምጃ ቤት ውስጥ ያለውን ዶላር በእጅና በማሽን አስቆጥሮ ትክክለኛ ዶላር ነው ተብሎ ከታሸገ በኋላ ከላይ ከጠቀስናቸው ሁለት መምሪያዎች ውስጥ ሁለት ሠራተኞች ተመርጠው ገቢ እንዲያደርጉ ወደ ጀርመን አገር ይላካሉ፡፡ እዚያም አገር ደርሶ በማሽን ሲቆጠር ከውስጡ ወደ 500 ሺህ ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ መጠን ፎርጅድ ነው ተብሎ ለብሔራዊ ባንክ ተወካዮች ይነገራቸዋል፡፡ መጠኑም በትንሹ በ8 ብር ምንዛሬ ወደ ብር ሲለወጥ ከ1.2 ሚሊዮን ብር የማያንስ ነው፡፡ በጊዜው አጠያያቂ የነበረውና እስካሁንም ግልጽ ምላሽ ያላገኘው ጉዳይ ዶላሩ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ባለው ማሽን ሲቆጠር ማሽኑ ትክክለኛ ዶላር ነው ብሎ ካሳለፈው በኋላ ጀርመን አገር ባለው ተመሳሳይ ማሽን ሲቆጠር እንዴት ፎርጅድ ሊሆን ቻለ? ምክንያቱም ባንኩ ውስጥም ያለው ማሽን በጨረታ ተገዛ የተባለው ከአውሮፓ ነው እና ችግሩ ያለው የቱ ጋር ነው? ፎርጅዱ ብሔራዊ ባንክ የገዛው የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽን ይሆን? ጠለቅ ያለ ምርመራ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ ለነገሩማ የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽኖቹ ከዚህም የባሰ ችግር አለባቸው የሚባል ጉዳይ ስለነበርና በጥራታቸውም ላይ ጥያቄ ስለተነሳ ከ9 ወራት በፊት ከአስተዳደር አገልግሎት መምሪያና ከኢንፎርሜሽን ሲስተምስ መምሪያ የተወጣጡ ሰዎችን ያካተተ ስለሁኔታው በዝርዝር አጥንቶ ያለውን ችግር እንዲያቀርብ ቴክኒካል ኮሚቴ ተዋቅሮ ነበር፡፡ አሁን ኮሚቴው በተባለው መንገድ ስራውን ይስራ ወይም ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዲቀር በሚፈልጉትና ተጠያቂነትን ያመጣብናል ብለው በሚፈሩት ከማሽኖቹ ግዢ ጋር እጃቸው ባለበት የስራ ሀላፊዎች ከጨዋታ ውጪ ይደረግ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡ ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ ከላይ እንደጠቀስነው የችግሩ ምንጭና ሁኔታው እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ በቅጡ ሳይመረመርና ማንም ተጠያቂ ሳይሆን እንደ 38 ሺህ ብር ሁሉ ባንኩ እንደዋዛ 500 ሺህ ዶላር ቀልጦ ይቅር፡፡ እንዲጣራ ለፖሊስ ሪፖርት ያድርግ ወይም በራሱ መንገድ ተጠቅሞ ብሩን ያስመልስ በሰራተኛውና በአብዛኛው ሥራ ኃላፊ በግልፅ አይታወቅም፡፡ ሁኔታውን የማያውቁት በጉዳዩ ውስጥ ያሉት ገዢዎቻችን ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው በቅርቡ ባንኩ እንደተጭበረበረ የታወቀውና በህዝቡ ዘንድ የመነጋገሪያ ጉዳይ የሆነው፣ የባንኩን ማህበረሰብ ያስደነገጠው፣ የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን፣ የፌዴራል ፖሊስንና የጄኔራል ኦዲተርን የጋራ ጥረትና ከፍተኛ ክትትል የጠየቀው ከወርቅ ግዢ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ወንጀል የባንኩን ማኔጅመንት የመምራትና የማስተዳደር ብቃት ችግር ጥያቄ ውስጥ የጣለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይሄ የወርቅ ግዢ አዲስ ተቀየረ የተባለው መመሪያ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ባንኩ የበፊቱ እንዳለ ሆኖ ሜድሮክ ኢትዮጵያ የለገንደቢን የወርቅ ማምረቻን ከገዛ በኋላ የባንኩ ተወካዮች በተገኙበት ከሻኪሶ እስከ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ድረስ ሂደቱን በመከታተል ወደ ውጪ አገር ሲላክሩ ባንኩ ራሱ የሚገዛውን ደግሞ ወርቁን ከገዛ በኋላ መጀመሪያ 80 በመቶ ወርቁ ወደ ውጪ አገር ተልኮ ቀልጦ ጥራቱ ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ ቀሪውን 20 በመቶ ክፍያ ይፈጸም ነበር፡፡ ሆኖም ይሄ አሰራር ረጅም በመሆኑ ወርቅ አቅራቢ ማህበራት ገንዘባቸውን በጊዜ እንዲያገኙ ስለማያደርጋቸውና የኮንትሮባንድ ንግድን በማስፋፋት በብዙ ኪሎ ግራም የሚቆጠር ወርቅ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ እየወጣ አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ እያደረገ ስለሆነ አሰራሩ መቀየር አለበት የሚል ሀሳብ በመንግስት በኩል ይቀርባል፡፡ ለዚህም ከማዕድንና ኢነርጂ ሚ/ር፣ ከተወካዮች ም/ቤት (ጉዳዩ ከሚመለከተው ከፍል)፣ ከብሔራዊ ባንክ (የአሁኑ የሪዘርቭ ማኔጅመንት መምሪያ ስራ አስኪያጅ ተወክለው) እና ከጉምሩክ ባለስልጣን የተውጣጡ ሰዎችን ያካተተና በቀድሞው የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በአሁኑ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ሚኒስትር ሰብሳቢነት የሚመራ አንድ ኮሚቴ ይዋቀራል፡፡ ይሄ ጥናት ይካሄድ የነበረው እ.ኤ.አ. ከ2006 በፊት ነበር፡፡ ኮሚቴውም ከብዙ ውይይት በኋላ መግባባት ላይ ከደረሰባቸው ሌሎች ሀሳቦች ውስጥ ሁለቱሩ አንድ የወርቅ አቅራቢ ማህበራት ወርቃቸውን በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ካስመረመሩ በኋላ ብሔራዊ ባንክ በሚ/ር መስሪያ ቤቱ የተረጋገጠውን ወርቅ እንዲገዛ የሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ግለሰቦችም ወርቅ ሲያቀርቡ ባንኩ ከግለሰቦችም እንዲገዛ የሚል ይገኝበታል፡፡ ሆኖም ግን ይሄ ሁለተኛው ሀሳብ በጊዜው በባንኩ ውስጥ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሀላፊዎች በኩል ብዙ ሲያወያይ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ የኮሚቴው ሀሳቦች ለሚመለከተው አካል በአግባቡ ቀርበው ይጽደቁ ወይም ይለወጡ ለጊዜው በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ከዚህ የወርቅ ግዢ ጋር በተያያዘ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአዲሱ መመሪያ መውጣት ጋር እጁ በቀጥታ እንዳለበት በተለይም ከቀድሞው አሰራር ጋር በተያያዘ የክፍያው መጓተት ህገወጥ ንግድን ስለሚያስፋፋና የወርቅ ነጋዴዎችን ስለማያበረታታ ክፍያው ነጋዴዎቹ በመረጡት ወር 100 በመቶ ወዲያውኑ እንዲፈጸም የሚል ሀሳብ በማቅረብና ብሔራዊ ባንክም ተግባራዊ እንዲያደርግ የባንኩ የቦርድ አባልና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚ/ር ሚኒስትር ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል እየተባለ ነው፡፡ እዚህ ሚኒስትሩም ሆኑ መመሪያው እንዲቀየር ያጠኑትና የወሰኑት አካላት ወንጀል እንዲፈጸም ብለው ሳይሆን ሀገሪቱ በኮንትሮባንድ ንግድ እያጣች ያለችውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማዳን ብለው ያደረጉት ነው የሚል ግምት አለን፡፡ ሆኖም በባንኩ ውስጥ ሁሉንም እያነጋገረ ያለው ከውጪ ብር ታትሞ ሲገባ ወደ ቅርንጫፎች ሲላክና ከቅርንጫፎችም ወደ ዋናው ግምጃ ቤት ሲመለስ በመከላለከያ ሠራዊት እጀባ እየተጓጓዘ እንዴት ከዚያ ያልተናነሰ ገንዘብ ሊያወጣ የሚችል ወርቅ ከማዕድንና ኢነርጂ በወርቅ አቅራቢዎቹ በራሳቸው ተይዞ እንዲመጣ የሚያደርግ አሰራርን ባንኩ ተከተለ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደሚባለው መመሪያው ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሚል ብቻ በሌላ አካል የተዘጋጀ ከሆነ ወይም ባንኩ ራሱ ተሳትፎበት የተዘጋጀ ከሆነ ክፍተት ያለው መመሪያ ሲወጣና ሲታዘዝ ባንኩ ማዕከላዊ ባንክ እንደመሆኑ መጠን የባንኩ ገዢዎች አደጋውን የማሳየት ሀላፊነት ነበረባቸው፡፡ በተለይም መመሪያውን ተቀብለው ወደ ታች ላሉ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ከማስተላለፋቸው በፊት አዋጭነቱን በደንብ ማየት ነበረባቸው፡፡ በርግጥ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ቀድሞ ለማመዛዘን ችሎታን ይጠይቃል፡፡ ይህንን የምንለው በግልጽ ተዘጋጅቶ የወጣ መመሪያ ካለ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባንኩ ውስጥ ግልጽ መመሪያ የለም፣ አሰራሩ የተቀየረው ዝርዝር አፈጻጸሙን በማያስቀምጥ ሁኔታ በደብዳቤ ትዕዛዝ ብቻ ነው የሚባል ነገር እየተሰማ ነው፡፡ ለዚህም ነው መመሪያው ካለና መመሪያው ደግሞ “ባንኩ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ማረጋገጫን በማየት ወርቁን ከነጋዴዎቹ ላይ እንደታሸገ እንዲገዛ፣ ሻጮቹ በተገኙበት እንዲከፈትና ነጋዴዎቹ በመረጡት ወር ወዲያውኑ መቶ በመቶ ክፍያ ይፈጸም” ብሎ የሚያዝ ከሆነ የታሰሩትም ሆነ ያልታሰሩት የከረንሲ መምሪያ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ያጠፉት ጥፋት ምንድነው? የሚል ጥያቄ በባንኩ ማህበረሰብ በኩል እንዲነሳ አድርጓል፡፡ ይሄ አሰራር ስህተት ከሆነ ደግሞ ከብሔራዊ ባንክ ውስጥ መታሰር የነበረባቸው መመሪያውን እንደወረደ ተቀብለው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት፣ “ነጋዴዎቹን አታበሳጩ እያሉ ትዕዛዝ የሚያከታትሉት ኃላፊዎች ወይስ ማ. . .” የዚህን መጨረሻ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ጄኔራል ኦዲተርና ህግ እውነቱን ያሳዩናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ብሔራዊ ባንክን መምራት ብቃትን ቀጥተኝነትን፣ ሥራን የሚያውቅ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ካልሆነ 160 ሚሊዮን ብር ሲጭበረበር ማወቅ ከሚያቅትበት ደረጃ ላይ ይደረሳል፡፡ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ መጭበርበሩ ከታወቀበት ከህዳር ወር 2000 ዓ.ም. በኋላ ገዢው በቅርቡ በኦፕሬሽን ዘርፍ ያሉ ዳይሬክቶሬቶች በተለይም የውጪ ባንኮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር (በስራቸው የውጪ ምንዛሬና ስታትስቲክስ፣ አገር ውስጥ ባንኪንግ፣ ከረንሲ ማኔጅመንትና ሪዘርቭ ማኔጅመንት መምሪያዎች ይገኛሉ) ክፍተት ወይም ችግር አለባቸው የሚሏቸውን የአሰራር መመሪያዎች በአስቸኳይ አይተውና አጥንተው የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ያስተላለፉት፡፡ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ አሉ አበው፡፡ ቢሆንም ግን ይሄ ትእዛዝ ጉዳዩን ሁሉ ለማድበስበስ ሊሆን ስለሚችል ፀረ-ሙስናና ጄኔራል ኦዲተር ጉዳዩን በጥንቃቄ ይከታተላለታል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በተለይም አሰራሩ እንዴትና ከመቼ ጀምሮ እንደተቀየረ የባንኩ መሪዎች እንዲያስረዱ በቅርቡ በፀረ-ሙስና ከተጠየቁ በኋላ መሯሯጡ በዝቷልና ለሁኔታውና ለባንኩ ምላሽ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ በተከታታይ ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ባንኩ ሲዘረፍ ይህም ከሰኔ 1996 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አመታትና ዘንድሮም ጭምር ሲፈጸም ገዢዎቹ ባንኩ ውስጥ አሉ፡፡ ያለው ችግር ምንድነው? ብለው አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ ሳይወስዱ ቀርተው ባንኩ እንደዚህ አይነት አደጋ ውስጥ ቢገባና የህዝብ ገንዘብ የአገር ፍቅር በሌላቸው ስግብግብ ነጋዴዎችና ተባባሪዎቻቸው ቢዘረፍ ምን ያስደንቃል? ለፀረ-ሙስና ኮሚሽንና ለጄኔራል ኦዲተር እግረ መንገዳችንን ለማስገንዘብ የምንፈልገው ባንኩ በርካታ ችግሮችና በሚሊዮን ብር የሚቆጠሩ ብክነቶች የሚፈጸሙበት ተቋም ስለሆነ በጀመራችሁት መንገድ ሌሎቹንም ለምሳሌ ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል፡- 40 ሚሊዮን ብር አካባቢ ይፈጃል ተብሎ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይና ከ15 አመታት በላይ ስለፈጀው ስለ አዲሱ ህንጻ ኮንትራትና ከአገር ውስጥና ከውጪ ስለተፈጸሙት ግዢዎች፣ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ስለፈጀው የአቃቂ ማስልጠኛ ተቋም ኮንትራትና የተለያዩ እቃ ግዢዎች፣ ከአለም ባንክ ለመንግስት የገንዘብ ተቋማት አቅም ግንባታ ተብሎ በብድር ስለተገኘውና ብሔራዊ ባንክ ፕሮጀክቱን በ3 አመታት ውስጥ ተቆጣጥሮ እንዲያስፈጽም ስለ ተሰጠው ነገር ግን ያለ በቂ ጥናትና እቅድ በዘፈቀደ ለሁሉም እንደ ቡና ቁርስ ይድረሰው በሚል በአብዛኛው የስራ ሀላፊዎችን ስልጠናና ልምድ ልውውጥ በሚል ሰበብ ከአፍሪካ አውሮፓና እስያ በማመላለስ እየባከነ ስላለው የ15 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት፣ መዋቅር ተጠና ተብሎ 500 ሺህ ዶላር ወጪ ስለተደረገበትና በ8 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ በ4 አመታት ውስጥ ስለተጠናቀቀው የመዋቅር ጥናት፣ ለአዲሱ ህንጻ መስታወት ማጽጃ ተብሎ ተገዝቶ ከ3 አመታት በላይ ፎቁ ጎን ተቀምጦ ፀሀይና ዝናብ ሲፈራረቅበት ከቆየ በኋላ ባለፈው አመት አጋማሽ አካባቢ የፎቁ አናት ላይ ተሰቅሎ ያለምንም ስራ ስለተቀመጠውና በ100 ሺህ ፓውንድ ወጪ ስለተገዛው የህንጻው መስታወት ማጽጃ ማሽን፣ በአገር ውስጥ የመለዋወጫ እቃ ይኑራቸው አይኑራቸው ሳይጣራ ለገንዘብ መቁጠሪያነት ተብለው በብዙ ሚሊዮን ብር ስለተገዙት በኋላ ላይ አገር ውስጥ መለዋወጫ የላቸውም ስለተባሉት የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽኖችና ስለሌሎቹም ጉዳዮች በቴሌና በተመሳሳይ ተቋማት ላይ እንደተሰራው አይነት ሰፊና ዝርዝር ምርምራ /ዲቴል ኢንቨስቲጌሽን/ ብታደርጉ የተቋቋማችሁበትን አላማ በማሳካት የሀገርን ሀብት ከውድመት ባንኩንም ከለየለት ውድቀት ትታደጉታላችሁ፡፡ እውነተኛ ፍትህን የሚሹ ሰዎች በእስር ላይ ስላሉ ከወርቁ ጋር በተያያዘ የጀመራችሁትን ምርመራ በአፋጣኝ ጨርሱት፡፡ ይህንን ጽሁፍ በመጻፋችንና እውነቱን ሁሉም እንዲያውቀው በማድረጋችን በባንኩ ውስጥ በብቃታቸው ሳይሆን ለገዢዎቹ ባላቸው ታማኝነት የተሾሙ፣ በእከክልኝ ልከክልህ ከላይ እስከታች ሰንሰለት ሰርተው በጥቅም የተወዳጁ፣ በወንዝ ልጅነትና በዘመድ አዝማድ ያደጉና የተቀጠሩ፣ አንዱ ሀሳብ አቅራቢ፣ አንዱ ፈራጅና ሌላው ቆራጭ ሆነው የተቀመጡ ሰዎችሩ ባጠቃላይ ባንኩ ውስጥ ከመሪዎቹ ጋር የጥቅም ተጋሪ የሆኑ ጥቂት የቤት ልጆች እነማን ናቸው? እንደዚህ የደፈሩንና የእንጀራ አባታችንን ጉድ እየዘረዘሩ የሚያሳጡብን? ብለው ተቆጥተው ዘራፍ ለማለት ይደፍሩ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ለእነዚህ ሰዎች የምንመክራችው መጽሀፉ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ስለሚል ለእናንተም የሚመሽበትና ለባንኩም ቀን የሚወጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንምና ከዚያ በፊት ቢረፍድም በ11ኛው ሰአት ተጠቅመው ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ ነው፡፡ በባንኩ ውስጥ ያለውን ጉድ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ቦርዱ አያውቁምካ ሊያውቁም የሚችሉበት መንገድ የለም በሚል እጅግ በጣም በተሳሳተ ስሌት እየተጓዛችሁ ያላችሁ ሁሉ አሁንም ደግመን የምንላችሁ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ነውና በጊዜ ወደ ትክክለኛው መስመር ብትመለሱ ያዋጣችኋል፡፡ በባንኩ ውስጥ ያሉትን ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ስለወደመባቸውና እየወደመባቸው ስለሚገኙት ጉዳዮች ወደፊት በሌላ ጽሁፍ በዝርዝር እንመጣባቸዋለን፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |