| አዲስ አበባ ከገዳዮቿ ለመሸሽ ወዴት ትሂድ? |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
|
ስብሃት መኰንን ስለ አዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባለ አደራ አስተዳደር ከላይ እስከታች ባሉ ባለ ሥልጣናት ብዙ ተብሏል፡፡ ሥር ሰዶ የነበረው እንደተስቦ በሽታ ከበፊተኞቹ ለአሁኖቹ ተላልፎ ህዝብ እየተበደረ ከተማዋ እየተቸረቸረች መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሮዋል፡፡ ግን ሰሚም መፍትሄ ሰጪም የለም፡፡ ባለአደራው አስተዳደር የተመደበለት ጊዜ ሲራዘም ቆይቶ አሁን ግን ማክተሚያው ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ በአሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ዕቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ኃላፊዎቹ በአስተዳደሩ የመገናኛ ብዙሃኖች ሲገልፁ እንሰማለን፡፡ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፋው የህገ ወጥ የመሬት ወረራና በህገ ወጥ ግንባታ ላይ በአጭር ታጭቀው የተነሱ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፡፡ እንደ እነሱ አባባል የፌዴራል መንግሥት ድጋፍም አለን ይሉናል፡፡ እርግጥ ነው፣ ህገ ወጥ አካሄድን ለማስወገድ የሚደረግን እንቅስቃሴ የማይደግፍ የለም፡፡ ግን ከልብ ነውይ? መግለጫው የአፍ ብቻ ላለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድን ነው? የተመረጠው ጊዜ በማወቅም ይሁን ሆን ተብሎ በቅርቡ ከሚካሄደው በተለይ ከአዲስ አበባ የምርጫ ወቅት ጋር ተገጣጥሟል፡፡ የባለአደራው ሹማምንት ምንም ይምጣ ምን፣ ከህገ ወጥ ጋር አንደራደርም፤ መንግሥትም በዚህ መልኩ የሚመጣ የፖለቲካ ትርፍ አንፈልግም ብሏል ይሉናል፡፡ ከዚህ ቀደም በሚሰጡ የተለያዩ አስተያየቶች በመዲናዋ ህገ ወጥነት ተስፋፋ ተብሏል፡፡ የባለ አደራው መልስ ግን ከእኔ በፊት የተሠራ ነው፡፡ በምርጫ-97 ወቅት የተፈፀመ ነው፡፡ የፍ/ቤቶች ጣልቃገብነት አስቸግሮኝ ነው፤ የሚሉ እንጂ የኔ ድክመት ነው ብሎ ራሱን ያሳየ አስተያየት አልሰጠም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በርከታ ባለጉዳዮች በየክፍለ ከተማው ይጉላላሉ፡፡ ጉዳያቸው ቶሎ አይፈፀምም፡፡ በተለይ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ነግሷል፡፡ ከተማዋ ባለቤት አጥታለች ተብላ በምትጠራበት ወቅት ራሳቸው ክቡር ከንቲባውም ሕዝቡ በክፍለ ከተማና በቀበሌ ሹማምንት መማረሩን እንደገለፀላቸው ያወሱበት ወቅት ነበር፡፡ የባለአደራው አስተዳደርና የክፍለ ከተሞች ሹማምንት “ትንንሾቹ ንጉሶች” “ሰባት ካቢኔ ሰባት ላንድክሩዘር”፣ “መኪና ማማረጥና ቤት ማግኘት የፈለገ ባላደራ ይሁን” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው ቆይቷል፡፡ በእርግጥ ለመናገር ለዚህ ፍሬ መነሻ በቦሌ፣ በየካ፣ በቂርቆስና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ተዟዙሬያለሁ፡፡ የሚሰራው ሥራ አሳዛኝ ነው፡፡ ፍፁም የአገልግሎት ማሻሻያ የሚባል ነገር የላቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ለተለያየ ጉዳይ ፈልጐ ካርታውን ህጋዊ ነው ተብሎ እንዲያመጣ ይታዘዛል፡፡ ይህንን ለማድረግ በሌሊት ሄዶ ቁጥር መቀበል አለበት፡፡ የጊቢው በር እስኪከፈት ውጪ ተኮልኩሎ እየጠበቀ ቁጥር እንዲያገኝ ይህን ጉዳይ ለመፈፀም ያለ ምንም ማጋነን ሦስትና አራት ወር ይፈጃል፡፡ ወይ መንገዱን ካወቀው አልያም ዘመድ ካለው፡፡ እነዚህ ካልተሟሉ ሲማረር መክረሙ ነው፡፡ ይህ የባለ አደራ ዘመን ለከተማው ኗሪ ፍፁም በጭራሽ የማይረሳ የብስጭት ጊዜ ሆኗል፡፡ ሁሉም በወገኑ ላይ ራሱን ለማበልፀግ የሚሯሯጥበት ወቅት፣ የከተማችን የአዲስ አበባን ለውጧን ማድነቅ ጀምረን ተመልሰን ተስፋ የቆረጥንበት ወቅት ሆኗል፡፡ መልካም ሥራ ለመሥራት የሚነሳ ይኖራል፡፡ ግን ከጣት ቁጥር ይበልጥ ይሆን? ይህን አባባል ለማስረገጥ አንዱ ቀበሌ ወይም ክፍለ ከተማ መሄድ በቂ ማስረጃ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ኃላፊነት በጐደለው ሁኔታ ከደንብና ከመመሪያ ውጪ የመንግሥትን ቦታ በጊዜያዊ ሊዝ በሚል ሰበብ የሕዝብና የቀበሌን ድርጅት ማከራየት፡፡ ለአብነት ሰሞኑን የታዘብኩት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦታ ማስረከብ በሚል ሰበብ ጉምሩክ ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ከማስተር ፕላን ውጪ አንድ ግለሰብና ቤተሰቦቻቸው እንዲጠቀሙበት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ በጊዜያዊ ሊዝ ተፈቅዶ በከፍተኛ የሊዝ ዋጋ የሚሸጠው ቦታ አላግባብ ሲሸነሸን ተመልክቼያለሁ፡፡ ቀበሌ ብጠይቃቸው የተወሰኑ የቀበሌና የክፍለ ከተማ ሹማምንት የሸጡት ነው ብለው ገለፁልኝ፡፡ ይኸው ክፍለ ከተማ ከዚህ ቀደም አረንጓዴ ቦታን ባንቢስ አካባቢ ሽጦ ራሳቸው ክቡር ከንቲባው ሄደው አስነስተውታል፡፡ ሌላው በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ የተገለፀው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመቶ ሺህ ብሩ ባለዕዳ፣ መስቀል ፍላወር አካባቢ በሊዝ እንዲዋዋል መፈቀድ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ አንዲት ፋይል ለማውጣት ወራት ማስቆጠሩና ሥራ አስኪያጁ ጋር ፋይል ለማውጣት አንድ ወር አለፈኝ ብለው ቢያመለክቱ መልሱ ዝም መሆኑ የአስተዳደሩን መበላሸት ያሳያል፡፡ ሥራ አስፈፃሚው ጋር ቢሄዱ እዚያው ጠብቀው ይስተናገዱ ይባላሉ፡፡ አሁን አሁን ወደ ክፍለ ከተሞችና ክልሎች ሲሄዱ ላለመሰልቸት ላለመናደድ ራስዎን አሳምነው መሆን አለበት፡፡ ኮልፌ ቀራኒዮ በመስኮት ላነጋግር ቢሉ፣ ቢንጠራሩ እዚያው ሲጮሁ ይውላሉ እንጂ ወይ ፍንክች፡፡ ሁልጊዜ በየክፍለ ከተማው ሰው ለስብሰባ የተጠራ ይመስል ግቢው ውስጥ ሲርመሰመስ ታላቅ ክብረ በዓል የሚከበር እንጂ ጉዳይ የሚፈፀምበት ቢሮ አይመስልም፡፡ በየበሩ ላይ ማለፍ ክልክል ነው፤ ተብሎ ይለጠፋል፡፡ መግባት ክልክል ነው፤ ለደላላና ለጉዳይ አስፈፃሚ ብቻ በሩ የተከፈተበት ሰዓት፡፡ ሕገ ወጡና አጭበርባሪው ከክፍለ ከተማው ባገኘው መረጃ ተነስቶ ቤት ይሸጣል፡፡ ገዢ ገንዘቡን ከፍሎ ውል ክፍል ጨርሶ ሄዶ ስም አዙርልኝ ሲል “የገዛኸው የተጭበረበረ ካርታ ነው” የሚል መልስ ያገኛል፡፡ ህጋዊ መሆኑን ያረጋገጥሁት እኮ እናንተ በሰጣችሁኝ ማስረጃ ነው ቢል የሚያገኘው መልስ እኛ አናውቅም ሂድ ክሰስ የሚል ግልምጫ የታከለበት ኃይለ ቃል ነው፡፡ ያን ጊዜ ዋይታ ጩኸት ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ የተከፈቱ በርካታ የወንጀል ፋይሎች በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይገኛሉ፡፡ የሠራተኛ ዳተኝነት ግለኝነት የባለ ጉዳዩ ዋይታ ከሰማይ የወረደ እንጂ የምድር ኃይል ያየዋል ብሎ ለመገመት አስፈርቷል፡፡ ሁሉ ነገር እንዲህ ምስቅልቅሉ በወጣበት ሁኔታ የህዝብ ደህንነት አለ፤ ፀረ ሙስና አለ ይባላል፣ አስተዳደሩ እያከታተለ የተሻለ የሥራ አፈፃፀም መኖሩን መግለጫ ይሰጣል፡፡ ሹማምንቱ ግን እየተሳሳቁ የነገውን የገንዘብ ማግኛ እቅድ ሲያልሙ ያድራሉ፡፡ የሚገርመው የፌዴራል መንግሥት ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በየ15 ቀኑ ከባለ አደራው የክልልና የክፍለ ከተማ ሹማምንት ጋር ይሰበሰባሉ፡፡ የተሠራውን ሳይሆን የፈረሰው የሰው ቤት ምን ያህል እንደሆነ ያዳምጣሉ፡፡ ታላቅ ስራ እንደተሰራ ቆጥረው መመሪያ ይሰጣሉ፡፡ ሹማምንቱ ኢንስፔክሽን አቋቁመናል፣ ይሄን ይኖረናል ብለው ይናገራሉ፡፡ ቁልፍ የሆኑት የከተማው ችግሮች አይነሱም፡፡ ሚኒስትሮችም አይጠየቁም ወይም ለመጠየቅ አይደፍሩም፡፡ በፈረሰ ላስቲክና ላሜራ ቆርቆሮና በረንዳ ጊዜ ከመፍጀት የሕዝቡን ቁስል ቢጠርጉለት ያገግም ነበር፡፡ አዎ ባዶ መሬት ተወሯል፡፡ ከተማው ተዘርፏል፡፡ መፍትሄው ሙያዊ ብቃት ያላቸውን አካሎች መድቦ ችግሩን ማድረቅ እንጂ በከተማ ስንት ቤት ፈረሰ? ስንት ቀረ? ህዝብና መንግሥት ከማራራቅ ውጭ የሚያመጣው ለውጥ አይታይም፡፡ ወንጀሉን ፖሊስ እንዲያጣራ መረጃውን ማሰባሰቡ የተወረረው መሬት የተጭበረበረው ካርታ በሚመለከተው የህግ አካል በህግ አግባብ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንደሚታየው ነጋዴው ተቆጣጣሪ አግኝቷል፡፡ እውነተኛው ነጋዴ ቁልቁል አጭበርባሪው ወደ ላይ እየተወረወረ ነው፡፡ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈበትን ቀዶ ሌላ መለጠፍ፣ በሚዛን ማጭበርበር፣ ሀሰተኛ ደረሰኝ ማዘጋጀት፣ ግብር መደበቅ፣ በበርበሬው በቅመሙ በዘይቱ ያለውን የተቀነባበረና የተለየዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች እህ ብለው ጆሮ ቢሰጡ የማጭበርበሪያው ስልት ከእለት ወደ እለት እየተራቀቀ መሄዱ ይታያል፡፡ አሁን አዲስ አበባ ላይ ሲሰራ የሚታየው መንገድ ብቻ ነው፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት ከተማዋ በባለ ሙያና በባለ አደራ ትመራ ብሎ ይህን ሁሉ መቋጫ የሌለው ችግር ከሚፈጥር ራሱ ቢመራ ከዚህ ሁሉ ከደረሰው ጉዳት ጥፋትና ኪሳራ የትኛው ያመዝን ነበር? መልሱን ኗሪው ይነጋገርበት፡፡ ገና ሲዋቀርም በጣት ከሚቆጠሩት በቀር የክልል፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ ባለ አደራ ተብለው ሲመረጡና ሲጠየቁ እንዴት ዓይነት ሥውር ዓላማ ይዘው እንደነበር፣ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያዩት በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡ የክፍለ ከተማና የቀበሌ ሥራ አሥፈፃሚ፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ ሥራ አስኪያጅ እየተባሉ እንዲህ በጠራራ ፀሐይ በህዝብ ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የሚያሳዝን ነው፡፡ ነገ መመለሻው እዚሁ ህዝብ መሐል መሆኑን መርሳት አንዱ የስንፍና ምልክት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንግሥት እንደፈለጋችሁ ተቀራመቷት፣ ህዝቡንም “ዝረፉት” የሚል ማዘዣ የሰጣቸው እስኪመስል ድረስ ይሉኝታ እስኪጠፋ ሙስና መባባሱ፣ የአዲስ አበባ አረንጓዴ ቦታዎቿ ጠፍ መሬቷ መዘረፍ ያሳፍራል ያስፈራልም፡፡ በግልፅ አፍ ሞልቶ መናገር የሚቻለው አንድ ሰው የራሱን ካርታ ህጋዊ ነው ብሎ ለማረጋገጥና የግንባታ ፈቃድ ለመውሰድ በክፍለ ከተማው አካባቢ ባሉ ደላሎች አማካኝነት እስከ አሥር ሺ ብር የሚደርስ የሚጠየቅበት የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ነው፡፡ ፍፁም አሠራሩ ግልፅነት የጐደለው ባለ ጉዳይ ዛሬ መረጃ ከጠየቀ በሚቀጥለው ቀን የሚመለስበትና ውጤቱን የሚጠይቅበትን ሥርዓት በመዘርጋት ፋንታ ተጠያቂነት በጐደለው አሰራር ፋይልህ ጠፍቷል ይባላል፡፡ ዋናው ማዘጋጃ ድረስ ሄዶ ያመጣውን መረጃ እኔ አላየሁትም እያሉ ማጉላላት የተለመደ አሠራር ሆኗል፡፡ ይኸንንም ለመናገር ታላቅ ተግባር ፈፅሞ እንደሚሸለም ሰው ደረታቸውን ነፍተው፣ ፊታቸውን አፍክፍተው፣ ትከሻቸውን እየሰበቁ ሲሆን ሆድ ያስብሳል፤ የሾማቸውን ያስረግማል፡፡ የቦሌውን አነሳሁ እንጂ በአብዛኞቹ ክፍለ ከተሞች አሁንም ለባለ ጉዳይም ሆነ መረጃ ለሚጠይቅ መልስ የሚሰጥ የሌለበት ወቅት ሆኗል፡፡ ሁሉም ጋር ጥያቄው የመብት ቢሆንም ስንት ትከፍላለህ የሚል ነው፡፡ የቸኮለ ቦታውን በባንክ አሲዞ ለመበደር የፈለገ፣ ከውጭ የመጣ፣ ጉዳዩን ቶሎ ጨርሶ መሄድ ያሰበ፣ የእነዚህ የቢሮ ቀበኞችና የደላሎች ሲሳይ ከመሆን ሌላ ምርጫ የለውም፡፡ ችግሮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ለብዙዎቹ ችግሮቻችን ግን ጥያቄያችን አንድ ነው፡፡ መንግሥት በእንዲህ ዓይነቱ አሠራር ለነቀዙና ለገለሙ ሹማምንት ለምን አሳልፎ ሰጠን? የፌዴራል ፀረ ሙስና በቅርቡ 66 የሚጠጉ ማህበራትን ማገዱ አስተዳደሩ በነቀዘ ተግባር ለመዘፈቁ ምስክር ነው፡፡ ሌላው በአራዳ ህንፃ የህዝብ መተላለፊያ ተዘግቶ የመጠጥ መነገጃ ሲሆን ደንብ አስከባሪውም ቀበሌውም አይቶ እንዳላየ ለነገሩማ በዚህ አካባቢ ማን ይነካናል ተብሎ የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች ላይ መሳሪያ እስከማውጣት ተደርሷል፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት በቅርቡ የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጆች ተቀያይረዋል፣ ጊዜዬ ሳይደርስ የሚሉት የቀበሌዎቹም እየበረቱ ነው፡፡ ሲሾም ያልበላ የሚለው ብሂል ዛሬ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |