Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow አሜሪካ የኬንያ መንግስትንና ተቃዋሚዎችን...
አሜሪካ የኬንያ መንግስትንና ተቃዋሚዎችን... Print E-mail
Sunday, 10 February 2008
አሜሪካ የኬንያ መንግስትንና ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቀች

የአሜሪካ መንግሥት የኬንያ መንግስትና ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን በሰላም እንዲፈቱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ሮይተርስ ዘገበ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ተጠሪ ጃንዲ ፍሬዘር “የኬንያ መንግስትና ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን ካልፈቱ አሜሪካ ከኬንያ ጋር የነበራትን    ግንኙነት ታቋርጣለች” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ጃንዲ ፍሬዘር በኬንያ ግጭት ተጠያቂ ናቸው ያሉትን የአገሪቱ ፖለቲከኞችንና ባለሃብቶችን ዝርዝር አሳውቀዋል፡፡ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን መዋቅር እስካልተለወጠ ድረስ በአገሪቱ ዳግም ምርጫ ማድረግ አስፈላጊ አለመሆኑን ተጠሪዋ አስታውቀዋል፡፡

በሱዳን የቻይና ሰላም አስከባሪ ኃይል ከተመድ የሰላም ሜዳልያ ተሸለመ

በሱዳን የቻይና የሰላም አስከባሪ ኃይል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ሜዳልያ ሽልማት ማግኘቱን የቤጂንግ ታይምስ ዘገባ አመለከተ፡፡

በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ አሽራፍ ቋዚ ያለፈው ሐሙስ በደቡብ ሱዳን ዋው ለሚገኘው የቻይና የሰላም አስከባሪ ሃይል የሰላም ሽልማት ሜዳልያ አስረክበዋል፡፡ አሸራፍ ቋዚ በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የቻይና የሰላም አስከባሪ ኃይል እውነተኛ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሁም በአካባቢው ነዋሪዎች ተወዳጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የቻይና የሰላም አስከባሪ ኃይል እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በሱዳን ተሰማርቷል፡፡

የቻድ መንግስት የሰዓት እላፊ አወጀ

የቻድ መንግሥት በቅርቡ የአገሪቱ አማጽያን በዋና ከተማይቱ በናጃሜና ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ በአገሪቱ በአብዛኛው ክፍል የሰዓት እላፊ አዋጅ ማወጁን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናውረዲን ዴልዋ ኩማኮይ የአገሪቱን መዲና ጨምሮ በስድስት የአገሪቱ ክፍሎች እወጃውን አስተላልፈዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እድሪስ ዲያቢ የአውሮፓ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል በፍጥነት በቻድ እንዲሰማራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአማጽያኑ ኃይል ቃል አቀባይ በቻድ የተሰማራው የፈረንሳይ መንግሥት የጦር ኃይል ለቻድ መንግሥት ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንና ጥቃት ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም የፈረንሳይ የአየር ኃይል በጦርነቱ መሳተፉን አስታውቀዋል፡፡ የፈረንሳይ መንግሥት በበኩሉ በጦርነቱ ውስጥ አለመሳተፉን ገልጿል፡፡

የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰዓት እላፊው በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የሰዓት እላፊ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመንግስት እና በአማጽያኑ መካከል በቅርቡ በተካሄደው ግጭት ከአንድ መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን የእርዳታ ሰራተኞች አስታውቀዋል፡፡

የቡቶ የሀዘን ጊዜ ተጠናቀቀ

የፓኪስታን ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቤናዚር ቡቶ ሞትን አስመልክቶ በፓርቲው ለአርባ ቀናት የታዘዘው የሀዘን ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የቡቶ ደጋፊዎች በተገኙበት ስነስርዓት ባለፈው ሐሙስ መጠናቀቁን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በስርዓቱ ላይ የቡቶ የቀድሞ ባል አሺፍ አሊ ዛርዳሪ “ከአስር ቀን በኋላ በሚደረገው ምርጫ አሸንፈን ጠላቶቻችንን በዴሞክራሲ እንበቀላለን” ሲሉ ንግግር አድርገዋል፡፡ የቡቶ ደጋፊዎች የቡቶ ግድያ እንዲጣራና ተጠያቂው እንዲታወቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቤናዚር ቡቶ ማንነቱ ባልታወቀ አጥፍቶ ጠፊ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ አደጋ መሞታቸው ይታወሳል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ጉዳዩን በተመለከተ አልቃይዳንና ታሊባንን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ቤናዚር ቡቶ ከመሞታቸው በፊት የፓኪስታን መንግሥት እንዲሁም የአገሪቱ የስለላ ሠራተኞች የግድያ ሴራ ማቀናበራቸውን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
 
< Prev   Next >