Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ኤኮን ሴቶችን አስደንሶ...
ኤኮን ሴቶችን አስደንሶ... Print E-mail
Sunday, 06 January 2008

ኤኮን ሴቶችን አስደንሶ ጃኬቱን ሸለመ ሪሃና ፎጣዋን አሻማች

ጥላሁን በዊልቸር ዘፍኖ የሙዚቃ ንጉስነቱን አስመሰከረ

የሚሌኒየሙ ታላቅ ሰው ተብለው ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እጅ የክብር ሜዳሊያ የተበረከተላቸው ክቡር ዶ/ር ሼህ መሀመድ ሁሴን አል አላሙዲ የሚሌኒየሙን አከባበር የተሳካና የደመቀ ለማድረግ የተለያዩ ስምጥርና ዝነኛ የዓለም ኮከብ ድምፃውያንን ወደ አገራችን አስመጥተዋል፡፡

በዋዜማው ብላክ አይድ ፒሶችን በመቀጠልም ቢዮንሴን ከትላንት በስቲያ ደግሞ ሪሃናና ኤኮንን በከፍተኛ ወጭ በማስመጣት የሙዚቃ አፍቃሪውን ስሜት በደስታ አስክረዋል፣ ከዋክብቱም ስለ አገራችን በዓለም ዙሪያ በሄዱበት ሁሉ ያዩትን ሊመሰክሩ ያስተዋሉትን ሊናገሩና ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በየመድረኩ ሊያወሩ ቃል ገብተዋል፡፡ እየተገበሩም ነው፡፡

..ታዋቂ አርቲስቶችን የማስመጣቱና ኢንቨስትመንታችንን ማስፋፋቱ ይቀጥላል.. ያሉት ሼኽ መሐመድ አላሙዲ ..ታዋቂ አርቲስቶች የኢትዮጵያን ምድር ይረግጣሉ.. በማለት ወደፊትም ዝነኛና ስመጥር አቀንቃኞች በአገራችን ጨፍረው ያስጨፍራሉ፡፡ በሌሎች ዓለማት እንደሚያደርጉት ሁሉ ከኢትዮጵያዊ ታዳሚ ጋር በአንድ መድረክ ይገናኛሉ፣ ታዳሚውን ያስደስታሉ፣ ያዝናናሉ ብለዋል፡፡

በፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅታቸውን ለማቅረብ የመጡት የ23 ዓመቷ ወጣት አቀንቃኝ ሪሃናና ከ3 የተለያዩ ሴቶች አምስት ልጆች የወለደው ታዋቂ የሴኔጋል አቀንቃኝ ኤከን ከአገራችን ታዋቂ አርቲስቶች ጋር በሚሌኒየም አዳራሽ ዝግጅት አቅርበዋል፡፡

ሰኞ ምሽት ታህሳስ 21 ቀን 2000 ዓ.ም እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ድረስ በቆየው በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት የወጣቷ አቀንቃኝ የመድረክ ኮከብነትና የኤከን መድረክ የመቆጣጠር ችሎታ ለተመልካቹ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ አልፏል፡፡

በምሽቱ እስከ ሁለት ሰዓት ገደማ ታዳሚው እራቱን እስኪበላና፣ የሚጠጣውም እስኪጠጣ ድረስ በዲጄ ዘመናዊ ቅንብሮች መድረኩ ሲሟሟቅ ቆይቷል፡፡ ከአዳራሹ መሟሟቅ ጋር ተያይዞ የምሽቱ ኮንሰርት በአገር ወስጥ አርቲስቶች ነበር የተከፈተው፡፡
 
በትግርኛ ሙዚቃዎቹ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ ወዳድ ልብ ውስጥ በቀላሉ የተዋሃደው አብርሃም ገ/መድህን በትግርኛ ዘፈኖች ወደ አማርኛ በመለሰው ሃንቀውታ ..ሀገሬ.. ዜማ አሃዱ ተባለ፡፡
 
የተለያዩ የብሄር ስብጥር ዘፈኖች እንዲኖሩ ታስቦ ይመስላል ዘፋኞቹ የተለያየ የአገራችን ቋንቋን የሚጫወቱ ነበሩበት፡፡ የጉራጊኛ ዘፈኖችን በሚያምር ድምጽ የሚያቀነቅነው ፀጋዬ ስሜ (ኦሴ ባሳ) ከአብርሐም ተቀብሎ መድረኩን አሞቀው፡፡ በቅርቡ ..ተጣልተናል ወይ..  ስትል አዲስ አልበሟን የቀለለችው ወጣቷ ድምፃዊ ህብስት ጥሩነህ ሌላዋ የመድረኩ ፈርጥ ሆና ያመሸች ሲሆን ፀሐዬ ዮሐንስ ነበር እሷን ተክቶ የሞቀ ዘፈኑን ማቅረብ የጀመረው፡፡ በኦሮምኛ ዘፈኖቹ የብዙ ወጣቶች አርአያ የሆነው አሊ ቢራ ከወዲህ ወዲያ በመድረኩ ከዘለለበት በኋላ ሁሉም ታዳሚ ወደ ተደመመለት ጥላሁን ገሠሠ የማይክ ቅብብል ተካሄደ፡፡

በዊልቸር ወደ መድረክ ብቅ ያለው ጥላሁን ገሠሠ ከበሽታው መከሰትና ህክምናው በኋላ ድምፁ ተበላሽቶ ሊሆን ይችላል የሚል የታዳሚ ፍርሃትና ስጋት ቢኖርም የሙዚቃ ንጉስነቱን ብቻ ሳይሆን የመድረክ አንበሳነቱን ያሰመሰከረበትና የሁሌም የሃበሻ እውነተኛ ድምፃዊ መሆኑን ያሳየበትን ሙዚቃ አቅርቧል፡፡ ..ስንቱን ነገር ለይቼ አይቼዋለሁ.. በሚለው ተወዳጅ ዜማ የታዳሚውን ስሜት ሰልቦ ይዞ ስለነበር አንዳንድ ታዳሚዎች ምነው ከመድረክ ባልወረደ ከዚህ በኋላ የፈረንጆችን ባልሰማም ግዴለኝ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከአገራቸን አርቲስቶች የመድረክ የሙዚቃ ጀባታ በኋላ የደቂቃዎች ዕረፍት ቢደረግም ውዝዋዜና ጭፈራ የጠማው እንዲሁም ጠጥቶ ሞቅ ያለው አንዳንድ ታዳሚ በዲጄ  ሙዚቃ ዳንሱን ያስነካው ነበር፡፡

ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ወጣቷ ሪሃና ሰፊውን የሚሌኒየም አዳራሽ መድረክ ተቀላቀለች፡፡ ካሚስተር ዲጄካ የሚለውና በአብዛኛው የዓለም ክፍል ስሟን ያስተዋወቀላትን ዘፈን በቪዲዮ አልያም በሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲያደምጡ የነበሩ ሁሉ አብረዋት እኩል ያቀነቅኑት ጀመር፡፡ የቢዮንሴን ዘፈኖች እንደ ህዝብ መዝሙር ይዘምረው የነበረው ታዳሚ የሪሃናን ዘፈኖች ሁሉ አብሮ ዘፍኗል ከማለት ዘምሯል ማለት ይቀላል፡፡ የዕለቱ ዝግጅት ታዳሚዎች በርካታዎቹ ተማሪዎችና ወጣት ሴቶች መሆናቸው የበለጠ የመድረኩን ድባብ የሞቀ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በርከት ያሉና ፈጣን ዘፈኖችን እያቀረበች ወጣቶቹን ወዲህና ወዲያ እንዲያወዛውዙ እያደረገች ከቆየች በኋላ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት መግባት የማብሰሩ አጋጣሚና ዕድል የሷ ነበርና ቁጥር አስቆጠረች፡፡

ከተመልካቹ ጋር ሆና ..አስር፣ ዘጠኝ፣ ስምንት. . .  አዲስ ዓመት ገባ ሁለት ሺህ ስምንት፤ እንኳን አደረሰን.. ብላለች፡፡  

የአንገት ፎጣዋን ለታዳሚው አሻምታ ታዳሚውን ..በእኔ ልውሰድ በእኔ ልውሰድ.. ያጋፋችው ሪሃና ከሌሊቱ አጋማሽ፣ ከ2008 መግባት በኋላ ከፈጣን ዘፈኖቿ ወደ ለስላሳ ሙዚቃዎቿ ተሸጋግራለች፡፡ እንደ ቢዮንሴና ብላክ ኦይድፒሶች ሁሉ በየጣልቃው ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ስትናገር የነበረችው ሪሃና ከራሷ ዘፈኖች በተጨማሪ የቦብ ማርሌይን ካኢዝ ዚስ ላቭካ በማቀንቀን ለታዳሚው ጋብዛለች፡፡ ከሌሊቱ 7፡30 አካባቢም ዝግጅቷን አጠናቃ ከነሙሉ ባንዷና የሙዚቃ መሣሪያዋ ከመድረክ ተሰውራለች፡፡

ለደቂቃዎች የዕረፍት ጊዜ ባለ ቁንጮው ዲጄ የሙዚቃ ግብዣውን አስተናገደ፡፡ ማይክ በጨበጠ ቁጥርም የኤኮን ስም እየጠራ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ዕድለኛ እንዲሆነ በማሞገስ ይናገር ነበር፡፡

ከተለያዩ ወጣት ሴቶች ጋር መድረክ ላይ በመጨፈሩና ህፃኑን ወደ ተመልካች በመወርወር ክስ የተመሰረተበት የአፍሪካ መኩሪያ የሚባለው ሴኔጋላዊ ኤከን ወደ መድረክ ሲወጣ መድረክ የሚያንቀጠቅጥ ድምጽ ከሞንታርቦዎች ወጣ፡፡ ካሃፒ ኒዉ ይርካ እያለና እየተፍለቀለቀ መድረኩ ላይ ብቅ ሲል በሪሃና ላንቃቸው እስኪዘጋ ሲጮሁ የነበሩ ታዳሚዎች በእጥፍ መጮህ ጀመሩ፡፡

ታዳሚው እንደ ሪሃና ሁሉ ከኤኮን ጋርም አብሮት ይዘፍን ነበር፡፡ በ ካሚስተር ሎንሊካ እና ካስማክ ዛትካ ዘፈኖቹ የብዙ አድማጮችን ቀልብ ያለ ዋጋ የገዛው ኤኮን በዕለቱ የመድረክ ላይ አንበሳነቱን አስመስክሯል፡፡

ጥቂት ዘፈኖቹን በምትሃተኛ አጃቢዎች ታግዞ ካቀረበ በኋላ ወደ ተመልካቹ ተጠግቶ ከታዳሚው መሃል ዕድለኛ የነበሩ 5 ሴቶችን ወደ መድረክ ጋበዘ፡፡ ወደ መድረክ ተጠርተው የሄዱት ወጣት ሴቶች ሁኔታውን ባለማመን ግራ የተጋቡ ሲሆን በተለይ አንዷ ኤከን ላይ ተጠምጥማ ..ብለቅህ ወገቤ ይላቀቅ.. የምትል ይመስል ነበር፡፡

ወጣት ሴቶቹን የዳንስ ውድድር እንዲያካሂዱና ተመልካቹም እንዲዳኘው አዘዘ፡፡ በዲጄ እየታገዘ እሱም እየዘፈነ ወጣት ሴቶቹ ያለ የሌለ ችሎታቸውን አሳዩ፡፡ ታዳሚው በሚያሰማው የጩኸት ልክ አሸናፊዎቹ ተመረጡ፡፡ እናም ሶስተኛ ለወጣችው ፔፕሲ ሲሸልማት ሁለተኛ ለሆነችው ደግሞ እየዘፈነበት የነበረውን ቲሸርት አውልቆ ሰጥቷታል፡፡ የውድድሩ አንደኛ አሸናፊ የሆነችውን ወጣት ደግሞ የአፍሪካ ንግስት ብሎ ሰየማትና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ምሳሌ መሆኗን አስረድቶባታል፡፡ ለኢትዮጵያ ያለውን ክብር ለመግለጽም ዲጄውን ጠርቶ ሦስት ጊዜ እንዲሰግድላት አዘዘው፡፡ ይህ አልበቃው በማለቱም ጉልበቷንና ጫማዋን አስሟታል፡፡ ለአሸናፊነቷም ወደ መድረክ ብቅ ሲል ለብሶት የነበረውን ጃኬት አልብሷታል፡፡

በዳንስ ምርጫው ምክንያት ከታዳሚው ጋር የተቀራረበውና ደስታ የተሰማው ኤከን እያቀነቀነ ከሴኩዩሪቲዎች አፈትልኮ ታዳሚው ጋር ዘሎ ተቀላቀለ፡፡ በታዳሚዎቹ እጅና ትከሻ ላይ በጀርባው ተንጠልጥሎ በአዳራሹ ሙሉ ተውረገረገ፡፡ ተመልካቹ እሱን ለመንካት የሚያደርገው ግፊት ለጉድ ነበር፡፡ በዚህ መሃል የኤከን አንድ እግር ጫማ ወለቀ፡፡ ይሄኔ የታዳሚውን ፍቅር የተረዳው ኤከን አንድ እግሩንም አውልቆ እንደ ሪሃና የአንገት ፎጣ አሻማው፡፡ ጫማውን ለማስቀረት የነበረውን ትርምስ ያየ ጉድ ማለቱ አይቀሬ ነበር፡፡

ይህንን ያስተዋሉና እሱን ከወከባ ለማዳን የፈለጉ ቢጫ ለባሽ ሴኪዩሪቲዎች ወደ መድረክ እንዲወጣ ይከላከሉት ጀመር፡፡ ተዋቸው ብሎ ቢናገርም አልሰማ በማለታቸው እየተበሳጨ ወደ መድረኩ ወጣና ..እነዚህ የሰለጠኑ ታዳሚዎች ናቸው፡፡ ሊከለከልና ሊቆጣጠራቸው የሚገባ አይደለም.. የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡፡

በድጋሚ መድረኩ ላይ ወጥቶ የታዳሚውን ቀልብ በቁጥጥሩ ስር አውሎ ሌሊቱን አጋምሶታል፡፡ የዕለቱ የሙዚቃ ኮንሰርት ፍፃሜም የተካሄደው በኤኮን ዘፈን ነው፡፡

ከሌሊቱ 10 ሰዓት በኋላ ያለቀው ፕሮግራም በጣም የተሳካ መሆኑን የተናገሩት ታዳሚች ከቢዮንሴ ጋር ሲነፃፀር ግን የቢዮንሴ ልዩ ነበር ብለዋል፡፡ በእለቱም የሪሃናን ኮከብነት ኤከን ውጦት ነበር ያሉትም ነበሩበት፡፡

የዕለቱን ዝግጅት እንዲታደሙ ተጋብዘው የነበሩ ተማሪዎች ትኬት ሲታደል የነበረውን ግፊያና ድብድብ የነቀፉት ታዳሚዎች ተማሪዎች በሌሎች ሰዎች መጠጥ እየተሰጣቸው የሰከሩ ነበሩ ብለዋል፡፡

ከልክ በላይ ጠጥተው ሲተፋ የነበሩ ታዳሚ የታየ ሲሆን በዝግጅቱ ማብቂያ ላይ የትራንስፖርት እጥረት በመኖሩ ተማሪዎች ተቸግረው ነበር፡፡  

በደመቀ ከበደ

 

 
< Prev