| ሁለቱን ክልሎች የሚያገናኘው መንገድ... |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
|
ሁለቱን ክልሎች የሚያገናኘው መንገድ የግንባታ ሥራ ስምምነት ተፈረመ
የአፋርና ትግራይ ክልሎችን ያገናኛል የተባለውን የሠመራ - ዲዲባሳላን (ኮንትራት2) መንገድ ሥራ ለመገንባት ሣትኮን የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ጨረታውን አሸንፎ የግንባታ ውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡ ኩባንያው እስካሁን ሰርቶ ያስረከባቸውን መንገዶች ሳይጨምር በአሁኑ ወቅት ብቻ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ የተሰጣቸው የመንገዶች ሥራን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተረክቦ በመገንባት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሣትኮን ኮንስትራክሽን አዲስ የተፈራረመውን የሰመራ - ዲዲባሳላን የመንገድ ግንባታ ለመሥራት በጨረታ ያሸነፈበት ዋጋ 328,257,356.71 ብር መሆኑን የሚያስረዳው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገዱ አይነትም ዲኤስኤስ ስታንደርድ የተባለ የጠጠር መንገድ ነው፡፡ 113 ኪ.ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ የመንገዱ የተሽከርካሪ ተሸካሚ በአማካይ 6 ሜትር ስፋት፣ ግራና ቀኙ 0.5 ትከሻ በጠቅላላው 7 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ሥራው የአነስተኛ ቱቦዎችና ፋካዎችን ግንባታ የሚያካትት እንደሆነ ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ መንገድ በማሳጠር ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚፈጥርና የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ወጪ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ጠቃሚ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡ የመንገድ ግንባታው ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የሚያመለክተው የባለሥልጣን መስሪያ ቤት መግለጫ በአካባቢው የሚመረቱትን ምርቶች በቀላሉ ወደ ገበያ ለማድረስም ሆነ ከሌሎች አካባቢው የሚመረቱ ምርቶችንም ሆነ ሸቀጦች ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ያስችላል፡፡ የመንገዱ ሥራ በኮንትራት ውሉ መሠረት በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ቢሆንም ስምምነቱ በተደረገበት እለት ግን የሣትኮን ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሣሙኤል ተክላይ "የመንገዱን ግንባታ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ ቀደም ብለው እንደሚያጠናቅቁ ቃል ገብተዋል፡፡ ከባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ሣትኮን ኮንስትራክሽን በአሁኑ ወቅት አራት መንገዶችን በጨረታ አሸንፎ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ጥር 29 ቀን 2000 ዓ.ም ከባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት ጋር ውል ከተፈራረመበት አዲስ የመንገድ ሥራ ጋር በእጁ ያሉትን የመንገድ ሥራዎች ቁጥር አምስት የሚያደርሰው ሲሆን አምስቱን መንገዶች ለመገንባት ከባለስልጣኑ ጋር የተስማማው ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሣትኮን በጨረታ አሸንፎ እየገነባቸው ካሉት መንገዶች ውስጥ ኮዳቢና - ጅረካ ያለውን የ120 ኪ.ሜትር መንገድ (ከ447 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ) እና ከሼኽ ሁሴን ሚጨት ያለው የ170 ኪ.ሜ የመንገድ ሥራ (ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |