| በሸማቹ ላይ የተወረወሩ ቀስቶች |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
|
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የግል ቤት ከሌላቸው በሺዎች ከሚቆጠሩ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ራሴን ማስተዳደር ከጀመርኩ (ከቤተሰብ ጥገኝነት ከተላቀቅኩ) ጊዜ ወዲህ ጥቂት የማይባሉ ቤቶችን ቀያይሬያለሁ፡፡
በእስከ ዛሬው የኪራይ ቆይታዬ ከአከራዮቼ ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ ነበር የምኖረው ይህ ሁኔታ መቀየር እንዳለበት በማመኔ ራቅ ወዳለ ሠፈር በመሄድ ግቢ ያለው ቤት ተከራይቼ መኖር ከጀመርኩ ገና ሁለተኛ ወሬ ነው፡፡ ለብቻ ቤት መከራየቴ በብዙ ነገሮች ተጠቃሚ አድርጎኛል፡፡ የተሻለ እንደሆነም አሳይቶኛል፡፡ ከአከራዬ ጋር አለመገናኘቱ በራሱ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ግን ነገሮች ተቀያየሩ፡፡ አከራዬ ስልክ መደወል አበዙ፡፡ ስለቤቱ ጉዳይ መነጋገር አለብን አሉኝ፡፡ የግድ ነውና ተገናኝተን ለምን እንደሚፈልጉኝ ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ ቀጠሮዬ ቦታ ከመሄዴ በፊት ሁለት ነገር ገምቼአለሁ፡፡ አንደኛው ቤቱን ስከራይ አንድ ልጃቸው ከአረብ አገር ከመጣች ትለቃለህ ተብዬ ነበርና እርሱን ሲሆን ሁለተኛው ግምቴ የቤት ኪራይ ጨምር ሊሆን እንደሚችል ነበር፡፡ ቀጠሮዬ ቦታ ስደርስ አከራዬ የጠበቁኝ ከባለቤታቸው ጋር ነው፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን የፈራሁት አልቀረም፡፡ በአጭር ቋንቋ የቤት ኪራይ መጨመር አለብህ አሉኝ፡፡ ገና በሁለተኛ ወሬ? ምን ተገኘ? ብዬ ጠየቅሁ፡፡ "ይሄ ለአንተ አይጠፋህም ነዳጅ ጨምሯል፡፡ ኑሮም ተወዷል. . . እኛም በዚሁ ቤት ኪራይ ነው የምንተዳደረው" አሉኝ፡፡ (እንደሰማሁት ከሆነ እኔ የተከራየሁትን ቤት የሰራችው አረብ አገር ያለች ልጃቸው ነች) እጅግ ስለገረመኝና ስላስደነገጠኝም ልመልስ የምችለው ነገር አልነበረኝም፡፡ አንድ ጥያቄ ግን ነበረኝ፡፡ እርሱም "ምን ያህል ነው የምጨምረው?" የሚለው፡፡ በአሁኑ ወር አንድ መቶ ብር ትጨምራለህ፣ በቀጣዩ ደግሞ እንነጋገራለን አሉኝ፡፡ በአንዴ አንድ መቶ ብር እጅግ ይከብደኛል አልኩ፡፡ የተሰጠኝ መልስ "ምርጫው የአንተ ነው" የሚል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ቀድሞ ከነበረው ንዴቴ የባሰ ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ጭማሪ ግን ለምን? እኔስ ከየት አመጣዋለሁ ብዬ ጨምር የተባልኩትን ክፍያ የተጋነነ መሆኑን ለማስረዳት ብሞክር "ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳል" እንደሚባለው ለመጨረሻው ጥያቄዬ ማብራሪያ የሰጡኝ የአከራዬ ባለቤት ናቸው፡፡ "እኛም ጨንቆን ነው፡፡ አንተ ወንድ ስለሆንክ ገበያ ላትወጣ ትችላለህ፡፡ 8 ብር የምንገዛው ምስር 12 ብር ገብቷል፡፡ ጤፍ 650 ብር. . . . " እያሉ የሰሞኑን የገበያ ዋጋ ይዘረዝሩልኝ ገቡ፡፡ "እናንተንም እንዲህ ዋጋ ሲጨመር መንግሥት ደመወዝ ይጨምርላችኋል" አሉኝ፡፡ እኔ የግል ድርጅት ሠራተኛ መሆኔንና ሰሞኑን ነዳጅ ስለጨመረ መንግሥት ደሞዝ አልጨመረም፡፡ እኔ የምሰራበት ድርጅትም ይህንን አላሰበም ብዬ በሚገባቸው ቋንቋ አስረዳሁ፡፡ ይሄኔ አከራዬ ጣልቃ ገቡና "እና ምን ይሁን ትላለህ? አንተም ኑሮ ሊከብድህ ይችላል፡፡ እኛ ደግሞ ቢያንስ ባለን ነገር መጠቀም አለብን፡፡ የክፋት አይደለም" ብለው ያሰቡትን ጭማሪ እንደማይተውና ለመታረቂያ ይሆን ዘንድ ሃያ አምስት ብሩን ቀንሰናል ሰባ አምስት ብሩን ግን ትጨምራለህ አሉኝ፡፡ ከዚህ የበለጠ መከራከር አልቻልኩም፡፡ በነገራቸው ሳልስማማ ቀርቼ እንደገና ቤት ፍለጋ መንከራተት አልፈለግኩም፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ሌላ አማራጭ አልነበረኝምና ሳልወድ በግድ ተስማማሁ፡፡ ሰሞኑን እንዲህ አይነት ገጠመኞችን ያስተናገዱ ተከራዮች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ በተለይ የነዳጅ ጭማሪ የማያመጣው ጣጣ የለም፡፡ ሸማቹ በተለይ ደመወዝተኛው ለገበያ ወጥቶ እየሰማ ያለው ዋጋ ናላውን እያዞረው ነው፡፡ ቤትም በነዳጅ ይሰራ ይመስል እንደ እኔ አይነት አከራዮች ዋጋ የጨመርነው ነዳጅ ስለጨመረ ነው የሚለውን ምክንያት ይሰጣሉ፡፡ በእርግጥ እነርሱም ላይ ወጪ ሊበዛ ይችላል፡፡ በዚህች አገር አንድ ነገር ሲፈጠር ሸክሙን ሸማቹ ወይም ተከራዩ እንዲሸከም ማድረግ የተለመደ ሆኗል፡፡ እንዲህ ባለውና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሸማቹ ላይ በየአቅጣጫው የሚረወረው ቀስት ቁስሉን እያሰፋው ነው፡፡ ይህንን ቀስት ለመከላከል መፍትሄ ማጣቱ ደግሞ ኑሮውን እንዲያማርር እያደረገው ነው፡፡ የነዳጅ ጭማሪው ጦስና ምንም ልንቆጣጠረው ያልቻልነውን ሁለንተናዊ የዋጋ ግሽበት ቢያንስ ለማርገብ መንግሥት ምን እያሰበ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በዚህ ወቅት መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ መምከር ይኖርባቸዋል፡፡ ነጋ ጠባ የምንሰማው ኢኮኖሚያችን አደገ ተመነደገ የሚለው ዜና ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እስከሌለ ድረስ ትርጉም አልባ ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ እስካሁን እንኖር የነበረውን ያህል ለመኖር ወይም ገበያውን ሊቋቋም የሚችል ገቢ እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ኃላፊነት መውሰድ ያለበት ከማንም በላይ መንግሥት ነው፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |