| "የዳኝነት ነፃነት ማለት ፍሬን... |
|
|
| Sunday, 10 February 2008 | |
"የዳኝነት ነፃነት ማለት ፍሬን የሌለው መኪና ማለት አይደለም"አቶ ታደለ ነጊሾ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት አቶ ታደለ ነጊሾ ባይሳ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት ናቸው፡፡ በ1990 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ደግሞ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነት ጀምረው፣ ለሁለት ዓመት በአዲስ አበባ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች፣ በኦሮሚያ የምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከህዳር 1999 ጀምሮ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት ናቸው፡፡ አሰግድ ተፈራ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በዳኝነትዎ ያለ ተፅእኖ ነፃ ሆነው እየሠሩ ነው? አቶ ታደለ፡- በመጀመሪያ ተፅእኖ ምንድን ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምንጩ ብዙ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተፅእኖ ሲባል በመንግሥትና በሥራ አስፈፃሚ በኩል ያለውን ነው፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ባልተናነሰ መልኩ ከህብረተሰቡ፣ ከግል ፍላጐት፣ ከጓደኛና አብሮ ከሚሠራ ሰው የሚመጣ ተፅእኖ አለ፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ ተፅእኖ ሊኖር ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- በተለይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተፅእኖ የለብዎትም? አቶ ታደለ፡- የተፅእኖዎች አመጣጣቸውም፣ ምንጫቸውም ብዙ ስለሆነ በድፍኑ ነፃ ነኝ ማለት ይከብዳል፡፡ እስከ አሁን በሠራሁባቸው እንዳየሁት አልፎ አልፎ በዞን አካባቢ ተፅዕኖ የማድረግ ሙከራዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ መንግሥትና ሥራ አስፈፃሚው እንደ አቋም ይዞት ሳይሆን ከግለሰቦች የግንዛቤ ማነስና አንዳንድ ጉዳዮች (ሴንሴቲቭ) በመሆናቸው የሚመነጩ ይሆናሉ፡፡ በድፍኑ ተፅእኖ የለም ብሎ ማለት ቢከብድም ታስቦበት አቋም ተይዞ የሚፈጠር ተፅእኖ ግን ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በተለይ እዚህ ከመጣሁ በአንድ ዓመት ከሦስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድም በተፅእኖ የሠራሁት ነገር የለም፡፡ በተለያየ አንግል ከግንዛቤ እጥረት ቢመጣም ከእምነቴና ከህግ ውጪ የሰራሁበት አንድም ቀን የለም፡፡ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ . . . ሪፖርተር፡- ተፅእኖ ቢኖር ይቀጥላሉ? አቶ ታደለ፡- የራስን ህሊና መፍራት ነው፡፡ ቀጥሎ ህጉን በማየት የትኛው የህብረተሰቡ ይጠቅማል ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ተፅእኖ የለም እንጂ ተፅእኖ ቢኖር ተፅእኖ አድራጊውን አካል ለማሳመን እጥራለሁ፡፡ እስከ አሁን ባደረግኳቸው ጥረቶች ያልተሳካልኝ የለም፡፡ ባይሳካ እንኳን ህገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት አለብኝ፡፡ ህገ መንግሥታችን የዳኝነት ነፃነት ያለ ተፅእኖ መሥራትን ያረጋገጠ ነው፡፡ ማንኛውም አካል ይህን ሊቀበለው ይገባል የሚል አቋም አለኝ፡፡ ገፍቶ ከመጣ ግን በተፅእኖ ዳኝነትን ማስኬድ ለአገርም ለራስም ህሊና አዳጋች ስለሆነ የምቀበለው አይመስለኝም፡፡ ሪፖርተር፡- በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ፍትህ የማግኘት ችግር አለ፡፡ ታች ያለውን ችግር ወርደው ለማየት ጥረት አድርገዋል? አቶ ታደለ፡- ወደዚህ ኃላፊነት ከመጣሁ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሆኖኛል፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ አቅጄ የወጣሁበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን ወደ ዞን ስንሄድ ጐራ ብሎ ወረዳዎችን የማየት ልምድ አለኝ፡፡ ብዙ ጊዜ በዞን ወረዳ (በቅርብ ስለምሰራ) መንዛዛት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ዋናው ችግራችን የመንዛዛቱ ሳይሆን ስነ ምግባርንና ዲሲፒሊንን ጠብቆ አለመስራት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በክልሉ የዳኝነት ሥራ ያለውን የሥነ ምግባር ወይም የዲሲፒሊን ጉድለት እንዴት ይገልፁታል? አቶ ታደለ፡- ችግሩ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ በጉቦ መሥራት አልፎ አልፎ ያጋጥማል፡፡ በዘመድ አዝማድ፣ በጓደኛ በተለያየ ጥቅማ ጥቅም መንቀሳቀስ ያጋጥማል፡፡ በተለይ በወረዳ አካባቢ የማመናጨቅ የማስፈራራት የመሳሰሉት ከዳኝነት ሥነ ምግባር የማይጠበቁ ድርጊቶች ብዙ ጊዜ ይታያሉ፡፡ ይህ አልፎ አልፎ በዞን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይታያል፡፡ ሪፖርተር፡- ከተጣለባቸው ኃላፊነትና አደራ አንፃር ጉቦ መብላት እንዴት ይታያል? የወሰዳችሁት እርምጃ አነጋጋሪ ሆኗል፤ አቶ ታደለ፡- የጉቦ አስከፊነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ በኦሮሚያ እስከ አሁን ባደረግነው ማጣራት ገንዘብ ይሰጠኝ ብሎ የመደራደር ነገር እንዳለ አረጋግጠናል፡፡ ባለጉዳይ ቀርቦ ይህን ያህል ካልሰጠኸን አንሰራም በማለት በመጠን ሳይስማሙ የቀሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ዳኛው የጠየቀው 3ዐ ሺህ ብር ሲሆን ባለጉዳዩ እከፍላለሁ ያለው ደግሞ 25 ሺህ ብር ነበር፡፡ ጉዳዩ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በጣም አስነዋሪ የሚባለው ባለ ጉዳይ ስልክ የመደወል በተለይ በሦስት ዳኞች የሚወሰን ከሆነና ዳኞች ተነጋግረው ጉዳዩን ከለዩ በኋላ ባለጉዳይ ጋ ደውለው እጨርስላችኋለሁ የሚል ቀርቧል፡፡ በደላላ የሚሠራበት ሁኔታም ታይቷል፡፡ ሪፖርተር፡- በደላሎች የሚሠራው እንዴት ነው? አቶ ታደለ፡- የስነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው ዳኞች የራሳቸው ደላሎች አሏቸው፡፡ ጉዳዩ በእጃቸው ሲገባ ጉዳዩ ያለው በእከሌ እጅ ነው ብለው ያግባባሉ፡፡ በእነዚሁ ደላሎች አማካይነት ጉዳይዋ እንዲፈፀምላት ወፍጮ ነቅለሽ አምጪ የተባለበት ደረጃም አለ፡፡ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ጭንቅላት የሚነካና አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ምርመራ ለማድረግ መነሻችሁ ምንድን ነው? አቶ ታደለ፡- ችግሩ በአንድ ጊዜ የተፈጠረ አይደለም፡፡ በአንድ ጊዜ እናጥራው በሚል ዘመቻ ሊጠራ የሚችል አይሆንም፡፡ ፍርድ ቤት አካባቢ ስለነበርኩ ሌሎቹም ከእኔ ጋር የነበሩት የሥራ አጋሮቼ ምክትል (ኮሚቴዎች) ፍርድ ቤት የቆዩ ነበሩ፡፡ እዚህ እንደመጣን የፍርድ ቤቱ ዋና ችግር ምንድን ነው ብለን አጠናን፡፡ ኮሚቴ አቋቁመን የመንግሥት አካላት ህብረተሰቡ፣ ተገልጋዩ፣ ሚዲያው የሚለን ነገር ስላለ ራሳችን ከሥነ ምግባር አኳያ እንዴት እንየው በሚል የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ኮሚቴው በዳኞች መካከል የተዋቀረ ነው፡፡ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ከዳኛ ባልተናነሰ ስለሚያጠፉ ኮሚቴው እነሱንም ያካተተ እንዲሆን የተደረገው ሆን ተብሎ ነው፡፡ ኮሚቴው ሥራውን ሲያከናውን በሦስት ተከፍሎ አንደኛው ጠቅላይ ፍርድ ቤት አካባቢ፣ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች የፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ እንዴት ያያቸዋል ብሎ የሚያጣራ፣ ወደ ወረዳዎችና ዞኖች ወርዶ ባለጉዳዮችን አያነጋገረ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለ በማጣራት ህብረተሰቡ ከእኛ የሚጠብቀውን እንዳላሟላን፣ በንብረት አስተዳደር፣ በፋይል አያያዝና ባለጉዳይን በማስተናገድ ብዙ ጉድለት እንዳለብን አረጋግጠናል፡፡ ወደ ሥነ ምግባር ስንመጣ ከፍርድ ቤትና ከዳኛ በማይጠበቅ ሁኔታ ህብረተሰቡ የዚህ ችግር ተጠቂ መሆኑን ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ ኮሚቴው ማጣራቱን ፍርድ ቤት ደረጃ ላለን ሰዎች አቅርቧል፡፡ በዳኞችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች መካከል ያለው ግንኙነት የተበላሸ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እነማን ናቸው? አቶ ታደለ፡- ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የቢሮ ሥራ የሚያከናውኑ፣ የዳኝነት ሥራ የሚደግፉ ያልተሾሙ የሲፒኤ ሰራተኞች ናቸው፡፡ እነሱ ብዙ ጊዜ ከዳኛ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የደላልነት ሥራ ይሠራሉ የሚል ቀርቦ ከተጣራ በኋላ ታመነበት፡፡ ምን እናድርግ? በሚል ኮሚቴው የማጣራት ሥራ ጀመረ፡፡ ኮሚቴው ያመጣቸውን ግኝቶች መሠረት አድርገን በህግ የሚስተካከሉ አሠራሮችን የህግ ማርቀቁን፣ የደንብ ማውጣቱ ጀምረን እየሠራን ነው፡፡ ትልቁ ነገር ግን ማህበረሰቡ የግንዛቤ ችግር አለበት፡፡ ምክክር የለም፡፡ ግንዛቤው አነስተኛ በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በዳኞች ላይ በሰፊው እንስራ በሚል ትልቅ ሥልጠና አካሂደናል፡፡ አዳማ ላይ ለ2ዐ ቀን በተካሄደው ሥልጠና ህብረተሰቡ የሚለው፣ ኮሚቴው ያረጋገጠው የመንግሥት አካል ፍርድ ቤትን በተመለከተ የሚያነሳቸው ጉዳዮች እውነት መሆንን ተሰብሳቢው አረጋገጠ፡፡ በሥልጠናው መጨረሻ አንዳንድ ዳኞች ሕጉን መሠረት አድርገው አለመስራታቸውና ለህገ መንግሥቱ ታማኝ አለመሆናቸው ተገለፀ፡፡ አንዳንድ ካለው አሠራር ርቀው ህዝቡን እያማረሩ ያሉ አሉ፡፡ በእነርሱ ምክንያት የኦሮሚያ ፍርድ ቤት ሊወቀስ አይገባም፡፡ አስተዳደሩ ጠንክሮ ሠርቶ የመለየት ሥራ መስራት አለበት፡፡ በጥቂት ሰዎች ሥም ሁሉም አንድ ላይ መሰደብና ፍርድ ቤቱ መኮነን የለበትም፡፡ የአስተዳደር አካኩ ሊያስተካክለው ይገባል፡፡ የሚለውን ዳኞች አንስተው ድጋፍ ሰጡ፡፡ ሪፖርተር፡- ይህን ስታደርጉ ከክልሉ ወይም ከክልሉ ኘሬዚዳንት ድጋፍ ይሰጣችሁ ነበር? አቶ ታደለ፡- ጥያቄው አጠቃላይ የህዝብ ጥያቄ ስለሆነ ኘሬዚዳንቱ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የመንግሥት አካላት ይደግፉናል፡፡ ዋናው ነገር ፍርድ ቤት እንደ ፍርድ ቤት አምኖበት እየሠራው ያለ መሆኑ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ያገኛችሁት ውጤት አርኪ ነው? አቶ ታደለ፡- የተወሰደው እርምጃ አዳማ ላይ በተደረገው ውይይትና ንግግር ብቻ አይደለም፡፡ ወደ ፍርድ ቤቱ አመራር ተመልሰን ምን ማድረግ አለብን የሚለውን አይተናል፡፡ በተለይ የዞን ፕሬዚዳንቶች፣ ኃላፊዎች ምን መደረግ አለበት ብለን በተደጋጋሚ ተወያይተናል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የተወሰዱ የዲሲፒሊን እርምጃዎች ነበሩ፡፡ የተንጠለጠሉ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከዚያ ተነስተን እያንዳንዱ ዞን አጣርቶ እንዲቀርብ ከፍርድ ቤት የራሱን ነፃነት ጠብቆ መጓዝ ያለበት ተቋም በመሆኑ መጀመሪያ ጥያቄ የሚነሳበትን ዳኛ በተመለከተ የሰራውን ፋይል አይተናል፡፡ ከደንበኛው ሁኔታውን የማጣራቱ አሰራር ሁኔታዎች እንዲለዩ ተደረጉ፡፡ ዞኑ አጣርቶ አመጣ፡፡ ችግር አለባቸው ለተባሉት ማስረጃ ቀረበ፡፡ የፋይል ማጣራት ለማድረግ ከወረዳ ወረዳ ፋይል ሲፈለግ የሕብረተሰቡ ጥያቄ ትክክል ሆኖ ተገኘ፡፡ማስረጃ እያለ ያለአግባብ ነፃ የወጣ ሰው አለ፡፡ አሰራሩን ለማወቅ ሁለትና ሦስት ፋይል ማየት ብቻውን ይበቃል፡፡ የተወሰደው እርምጃ ከዚህ አንፃር ሲመዘን አርኪ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ፋይሎቹ ሲመረመሩ ጥንቃቄ ተወስዷል? አቶ ታደለ፡- ከወረዳ፣ ከዞን ተጣርቶ የመጣውን መረጃ የሚያጣራ ጉባኤ ኮሚቴ አለው የቀረበው ክስ ምን ያህል በአሳማኝ ማስረጃ የተደገፈ መሆኑን ኮሚቴ ያየዋል፡፡ አንዳንድ መረጃ ከማስረጃ ያልተናነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ በዞን ትልቅ ግፊት ሲደረግ የነበረ ጉዳይ እዚያ ያሉ ዳኞች ተቋቁመው ሲወስኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲደርስ በሳምንትና በሁለት ሳምንት ጊዜ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉ በቂ ማስረጃና የታችኛው ፍርድ ቤት ግፊት እያለ በነፃ ይለቀቃሉ፡፡ ኮሚቴው ካጣራ በኋላ 75 ከሚሆኑት ዳኞች 35 የሚሆኑት እንዲከሰሱ ተደርጓል፡፡ እርምጃው ቢወሰድ ንጹህ ዳኛ ተጠቃ ተብሎ ጥያቄ እንዳይነሳ ሰፊ ማጣራት ተደርጓል፡፡ የክልሉ የዳኞች ጉባኤ ሰዎቹ እስከ ማስረጃ ክስ እንደደረሳቸው መልሳቸውን እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡ ያላቸውን ማስረጃ ክርክር፣ መቃወሚያ አቅርበው ቀድሞ በተቋቋመ ኮሚቴ ያነሱት ጥያቄ እንዲጣራ ከሕግ አንፃር እንዲያይ ተደርጓል፡፡ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ሃሳቡ ለጉባኤው አባላት እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ሪፖርተር፡- ማጣራቱ የዳኞቹን ነፃነት አይጋፋም? አቶ ታደለ፡- በአንድ መልኩ የዳኝነት ነፃነት አለ፣ በሌላ መልኩ የተጠያቂነት ሥራ አለ፡፡ የማመዛዘን ሥራ ያስፈልጋል፡፡ የዳኝነት ነፃነት ማለት ፍሬን የሌለው መኪና ማለት አይደለም፡፡ ሲያሻው ሰው ላይ የሚወጣ፣ የሰው ቤት የሚያፈርስ አይደለም፡፡ የሆነ ቦታ ሊያዝ ሊቆም ይገባዋል፡፡ አንዳንዶች የተጠያቂነትን ምንነት ባለመረዳት ፍርድ ቤት ለሚነሳ ችግር ለምን ይህን ተደረገ ተብሎ ሲጠየቅ የዳኝነት ነፃነት ተጣሰ የሚል ነገር ያነሳሉ፡፡ ነፃነት እንዳለ ሆኖ ተጠያቂነትም አለ፡፡ ተጠያቂነት ሲባልም ማንም ሰው እንደፈለገ ገብቶ የሚዘባርቅበት አይደለም፡፡ የራሱ ደንብና ሕግ አለው፡፡ ማን ይቀጣል፣ ማን ይከታተላል የሚለውን ያያል፡፡ የሚቀጧቸው የሚከታተሏቸው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት ናቸው፡፡ የዳኝነት ተጠያቂነት መዝጊያ የሌለው በረት አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ ተጉዘን የወሰድነው ርምጃ በመሆኑ ያረካል አያረካም የሚለው ከሕብረተሰቡ የሚመጣ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ ፍርድ ቤት መንግሥት አለ የሚለውን አረጋግጧል፡፡ የሕዝብን ችግርና ቅሬታ የሚሰማና ከየዞኑ ከወረዳም ሪፖርቱ የተንፀባረቀውም ይሄ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላት ጥርጣሬ የሚያጭሩ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አሉ፡፡ ዋናው ግን ኃላፊነትና ነፃነትን የማመዛዘን ግንዛቤ አናሳ የሆኑ ናቸው እላለሁ፡፡ አብዛኛው ከምክር ቤቱ የተነሳው የድጋፍ አስተያየት ነው፡፡ ከዞን ከወረዳ አካባቢ የደረሰን የሕብረተሰቡን ሮሮ አይቶ ርምጃ የሚወስድ መንግሥት አለ የሚል ሃሳብ የቀረበ ስለሆነ በግሌ አርኪ ሥራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፍትህ ሥርዐት በፍርድ ቤቶች በራሱ ጊዜ የራሱን ችግር አጣርቶ እርምጃ የወሰደ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ አልፀፀትም፡፡ ሪፖርተር፡- ይቀጥላል? አቶ ታደለ፡- ይህ የአንድ ጊዜ ሥራ ሊያስመስለው የቻለው ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ባለመሥራታችን ነው፡፡ የዲሲፕሊን ጉዳዮች፣ የሥነ ምግባር ጉድለቶች የአንድ ቀን ክስተቶች አይደሉም፡፡ ሰው እስካለ ድረስ ጥሩ ነገር አለ መጥፎ ነገርም ይኖራል፡፡ እንዲህ አይነት ክስተቶች የአንድ ጊዜ ክስተቶች እንዳለመሆናቸው መጠን እርምጃውም የአንድ ጊዜ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ማባረር አይደለም፡፡ እርምጃ መወሰዱ አይደለም፡፡ ከወዲሁ ሰው ወደዚያ ስህተት እንዳይገባ ማድረግ ነው፡፡ አሁን በየወሩ የወረዳ ዳኞች በወረዳቸው፣ የዞን ዳኞች በዞናቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ከሰራተኞች ጋር ተሰብስበን እንወያያለን፡፡ በተለይ በሥነ ምግባር በኩል ያለው በዚህ ወር ውስጥ ምን ምን መጥፎ ጎኖች ተሰምተዋል? ምን በጎ ጎኖችስ ነበሩ? እንዴትስ መስተካከል አለባቸው ተብሎ በየወሩ መወያየት እንደ አንድ መደበኛ ሥራችን ይዘነው እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሌላው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ሥነ ምግባር ተኮር የሆኑ ስልጠናዎችን ለመስጠት አቅደናል፡፡ እነኚህ በዋናነት የምንሠራባቸው ናቸው፡፡ የሥነ ምግባርን ለውጥ ለማምጣት የግድ ሰው ማባረር የለብንም፡፡ በየወሩ ሰዎችን እያባረርን እንቀጥላለን ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ከዚያ እንዲወጡ የተለያዩ ዘዴዎችን ፈጥረን የሰዎች ሥነ ምግባር ከፍ እንዲል፣ ሙስናን መሸከም የማይችል ሰው ለመፍጠር ነው የምንሰራው፡፡ የሥነ ምግባር ጉድለት በታየ ጊዜ ግን ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በሥነ ምግባር ጉድለትና በሙስና የተባረሩ ዳኞች በሌላ መንገድ በግል በጥብቅና ሙያ ለመሥራት ፈቃድ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ለእነዚህ ፈቃድ ትሰጣላችሁ ወይም ፈቃድ እንዲሰጥ ትደግፋላችሁ? አቶ ታደለ፡- ፍቃድ የሚሰጠው የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ነው፡፡ ሕጉና ደንቡ እስከዛሬ ባለኝ መረጃ የሚለው በሥነ ምግባር ጉድለት ከዳኝነት የተሰናበተ የጥብቅና ፈቃድ ማውጣት እንደማይችል ነው፡፡ ይህንን መሰረት አድርጎ ነው የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ፍቃድ የሚሰጠው፡፡ እንደ ፍርድ ቤት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲሲፕሊን እርምጃ ወስዷል፡፡ የዲሲፕሊን ጉድለቶች ተከሰቱ፣ ሕጋዊ እርምጃ ተወሰደ፡፡ ስለ እነርሱ ህጋዊነት የምናወራበት መሰረት የለንም ማለት ይቻላል፡፡ ፈቃድ ሰጪው አካል ይበልጥ ሊያብራራው ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- ተቀናጅቶ ከመሥራት አንፃር? አቶ ታደለ፡- ሕጉም የከለከለው እንዲህ አይነት የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች በፍትህ ሥራ ላይ ሊሰማሩ አይገባም በሚል ነው፡፡ የፍትህ ሥራ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ስለ ሰው ሕይወት፣ ስለ ሰው ንብረት፣ ስለ ሰው ነፃነት የሚወስን ነው፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት ነው፡፡ በተለይም በእኛ አገር የኑሮ ሁኔታ ይታወቃል፡፡ ሰውየው ያፈራው ንብረት ከሕይወቱ አሳንሶ የሚያይበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን ኃላፊነት ሊሸከም የሚችል ሰው የጥሩ ሥነ ምግባር ባለቤት ሰው ነው ከሚል አንጻር ነው ሕጉ ያንን የከለከለው፡፡ የፍትህ ሥራ ማለት ዳኝነት ብቻ አይደለም፡፡ ማማከሩ፣ መከራከሩ አይደለም፡፡ እውነትን (ሃቅን) መሰረት አድርጎ መከራከር ነው፡፡ የሥነ ምግባር ችግር ያለበት ሰው ይህንን ማድረግ አይችልም ተብሎ ነው እንደ ፍርድ ቤት የሚታመነው፡፡ እንደ መንግሥት ግን ለእነኚህ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ መዘፈቅ አብሮ ሲሰራ የነበረው የራሱ ድርሻ ነበረው፡፡ ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት የራሱ ችግር ነበረው የሚል ነገር ነው ያለው፡፡ በጊዜ አንድ ነገር ቢባል ኖሮ እንዲህ ዓይነት ልምድ ያላቸው፣ ብዙ ዓመት ያገለገሉ ሰዎች፣ ብዙ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ሰዎች ማጣት ባልተገባን ነበር፡፡ ከቁጥራችው አንፃር ሥራ መሥራት ካልቻሉ የሚያስከፍሉት ማህበራዊ ዋጋ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተቀጡ በኋላ ሰርተው የሚኖሩበት ሁኔታ ይመቻች የሚል ሁኔታ አለ፡፡ በግልፅ ይኼ ይሁን ይኼ ይሁን ማለቱ የእኛ ድርሻ ባይሆንም አሁን ከዘረዘርናቸው ችግሮች አንፃር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰው ይማራል፤ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚያ ታይቶ አንድ ነገር የሚደረግበት ሁኔታ ቢመቻች የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ እስከ መጨረሻው ያለ ሥራ እንዲቆዩ ማድረጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁኑኑ ወደ ሥራ ይመለሱ ወይም ፈቃድ ያግኙ ከተባለ ምን ተቀጡ የሚልም ነገር ስለሚነሳ ሚዛናዊ አቋም ቢወሰድ መልካም ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የሚደራደሩትን ሰዎችስ? ከእነርሱ ጋር ቁጭ ብለው ይህን ልስጥህ፣ ይህን ልስጥህ የሚሉ ሰዎች ፍትህ እንዲዛባ አላደረጉም? አቶ ታደለ፡- ይህንን በተመለከተ ለጨፌ ኦሮሚያ (ለኦሮሚያ ምክር ቤት) ያቀረብነው ሃሳብ አለ፡፡ ዳኞችን በተመለከተ ህጉንና ደንቡን መሠረት አድርገን እርምጃ መውሰድ እንችል ይሆናል፡፡ ሰፊውን ህብረተሰብ በሚመለከት ግን ምን እናድርግ? በሰፊው ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ ሥር ያሉትን እንቆጣጠራለን እናንተ ደግሞ የወከላችሁትን ኀብረተሰብ እንዴት አድርጋችሁ ነው ከዚህ ችግር የምታወጡት? በሰብዓዊነት ከታየ ዳኛው ይታገዳል፡፡ አንድ ተዘዋዋሪ ችሎት ወደ አንዱ ዞን ሲወጣ ገና ለገና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ኮሚቴ ተዋቅሮ ገንዘብ ተሰብስቦ ነው የሚጠብቀው፡፡ ይህ የዳኛው ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የኀብረተሰቡም ጭምር ነው፡፡ ይህ ኀብረተሰብ ባለበት ነው ዳኛው የሚሠራወ፡፡ ፈተናው ቀላል አይደለም፡፡ ኀብረተሰቡ ላይ ሊሠራ የሚገባ ነገር አለ፡፡ ምክር ቤቱ ለእኛ የቤት ሥራ እንደሰጠን ሁሉ እኛም ለምክር ቤቱ የቤት ሥራ ሰጥተናል፡፡ የተደራደሩትን ምን እናድርግ? ሪፖርተር፡- ክስ መመስረት? አቶ ታደለ፡- ክስ መመስረት የሚመለከተው ፖሊስ ነው፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም አለ፡፡ ሪፖርተር፡- የተባረሩት ዳኞች ጉዳያቸው በመባረር ብቻ አይበቃም፡፡ የሚያስከስሱ ጉዳዮች ካሉ በሂደት ይጣራሉ? አቶ ታደለ፡- በትክክል፡፡ እንደየድርጊታቸው፣ እንዳለው ማስረጃ አሳማኝነት፡፡ 1ኛ ከዳኝነት ለማባረር ከበቂ ማስረጃ በላይ አለን፡፡ በዚያም አልፎ ወደ ወንጀልም ሊሄድ የሚችል አለ፡፡ ግን ይኼ የመጨረሻው ጉዳይ ነው ማለት አይደለም፡፡ ወንጀለኛነቱን ሊያረጋግጥ የሚችል ማስረጃ ባለበት የሚመለከተው አካል የሚሄድበት ከሆነ ቀጣይነት ሊኖረው ይችላልና ምን ተሠራ? ምን ማስረጃ አለ? የሚለው ነው እንጂ ዛሬ እኛ ቋጭተነዋልና ከእንግዲህ አይጠየቁ የሚለው ነገር የምናነሳበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ቀጣይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ፍርድ ቤት ራቅ ካለ ቦታ መጥተው የሚጉላሉ ባለጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ለማስተናገድ ምን አቀዳችሁ? አቶ ታደለ፡- በአብዛኛው ያሰብነውን እየሠራን ነው፡፡ የሥራ ብዛቱ፣ የሰው ኃይል ማነሱ እንዳለ ሆኖ በዋናነት የእነዚህ ችግሮች ምክንያት የሥነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ሥነ ምግባር የማይገባበት ቦታ የለም፡፡ በጀመርነው የምክክር ሥራ ችግሮቹን እየቀረፍን እንሄዳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላው የሥራ ብዛቱና የሰው ኃይሉን ማመጣጠን ከመንግሥት ጋር ተነጋግሮ ማመቻቸቱ የሚጠብቀን ነው፡፡ በአንድና በሁለት ዓመት የምንቀርፈው አይደለም፡፡ በተቻለ መጠን ግን ሰዎች ፈጠን ባለ ሁኔታ እንዲስተናገዱ የሚያደርግ ሥራ ጀምረናል፡፡ ሪፖርተር፡- የተደረገ የአሰራር ለውጥ አለ? አቶ ታደለ፡- ከዚህ ቀደም የወረዳና የዞን ዳኞች እንደማንኛውም ዳኛ ነው መዝገብ የሚሠሩት፡፡ አስተዳደራዊ የሆነውን ሥራቸውን ዘንግተው፡፡ በዚህ ዓመት ግን ኘሬዚዳንቶች፣ ዳኞች፣ ሌሎች ሰዎች በጥራትና በፍጥነት የሚሠሩበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ አድርገን እየሠራን ነው፡፡ ሮሮ የሚበረታው ሁሌ ፍርድ ቤት ችግር ፈጣሪም ሆኖ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤት የራሱ አቋምና የአሰራር ሂደት ያለው ነው፡፡ ፍርድ ቤት ዲኘሎማት መሆን አይችልም፡፡ ዲኘሎማት ከሆነ ፍርድ ቤትነቱ ይቀራል፡፡ ይህን ስንቱ የኀብረተሰቡ ክፍል ነው የሚረዳው? አንዳንድ ጊዜ ከኀብረተሰቡ አለመረዳት፣ የመስተንግዶ ጉድለት እንዳለ ሆኖ ያላግባብ የሚሠሩ ነገሮችን የማጉላት ነገር ይታያል፡፡ የፍርድ ቤት ሥራ ይህን ይመስላል፣ ኀብረተሰቡ ሊረዳን ይገባል ብለን አልሠራን ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤት ጉዳይ ተይዞ ይመጣል፡፡ ቅሬታን ይዞ ይመለሳል፡፡ በፍርድ ቤት የሚከሰተው ቅሬታ ምንጩ በአብዛኛው ፍርድ ቤት አይደለም፡፡ ማስረጃዎች፣ ምስክሮች፣ የክሱ አመጣጥና የክርክሩ አመጣጥ ነው፡፡ የችግሩ ባለቤት የሚሆነው ግን መጨረሻ ላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የግንዛቤ ችግሮች በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ? አቶ ታደለ፡- ክሱ እንዴት ተመሠረተ፣ ማስረጃ እንዴት ቀረበ የሚለውን የሚመለከት የለም፡፡ የብዙ አካላትን ችግር የሚቋጨው ፍርድ ቤት ስለሆነ ብቻ ኃላፊነቱ ፍርድ ቤት ላይ ይወድቃል፡፡ ፍርድ ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ የነገሮች መቋጫ መሆናቸው ለችግሮቹ ተጠያቂ ተደርገው ይታያሉ፡፡ ከህክምናና ማዘጋጃ ቤቶች የሚሰጡ ማስረጃዎች አሉ፡፡ እዚያ አካባቢ የተበላሹ ማስረጃዎች መጥተው የውሳኔዎችን አቅጣጫ የሚቀይሩበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ዋናው ምክንያት ከዚያ የተሰጠው ማስረጃ ነው፡፡ ስለዚህ የፍርድ ቤት ችግር ለሚባሉ ጉዳዮች እነዚህ አካላት ድርሻ አላቸወ፡፡ ጠበቃው እንዴት ተከራከረ፣ ምን ማስረጃ አቀረበ፣ አቃቤ ሕጉ በምን ማስረጃ ወንጀል ተከላከለ፣ የምስክር ቃል እንዴት ተሰማ የሚለው ነገር መታየት አለበት፡፡ በተቀነባበረ ሁኔታ ወደ ፍርድ ቤት መጥተው የምስክርነት ቃል የሚሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ለምሳሌ ከህብረተሰቡ ሊቀረፉ ይገባል፡፡ ህብረተሰቡ፣ ተከራካሪ ወገን፣ ማስረጃ ሰጪዎች ፍርድ ቤት ያለውን ችግር በትንሹም ቢሆን ይጋሩታል፡፡ ህብረተሰቡም ከመጀመሪያ በአግባቡ ስለማይከታተል ነገሩ ሲቋጭ የማማረር ልማድ አለው፡፡ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ስለመጣ ብቻ መፍትሔ ያገኘ ይመስል ይመለሳል፡፡ እንዴት ወደ ፍርድ ቤት መጣ፣ ክርክሩ እንዴት በማስረጃ ተካሄደ የሚለውን አይከታተልም፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ፍርድ ቤት እንዲህ አደረገ ብሎ ይነሳል፡፡ የዚህ ሁኔታ ባለቤት ፍርድ ቤት ብቻ አለመሆኑን ህብረተሰቡ መረዳት አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ከዳኞች የሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የፆታ ጥያቄስ አለ? አቶ ታደለ፡- አልፎ አልፎ በዚያ መልኩ ስማቸው የሚነሳ ጓደኞችም አቃቤዎችም አሉ፡፡ ሪፖርተር፡- ምንድን ነው ያደረጉት? አቶ ታደለ፡- ባለጉዳይን ለፆታዊ ግንኙነት የመጋበዝና የማስገደድ ነገር አልፎ አልፎ የሚገጥመን ነገር ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ኮሚቴዎቹ ባጣሩት ለአስተዳደር ኮሚቴው ባቀረቡበት ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ቀርበዋል? አቶ ታደለ፡- በትክክል ቀርበዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ይሄ አያስከስስም? አቶ ታደለ፡- ይህ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ የፍትህ ጉዳይ የፍርድ ቤቶች ብቻ አይደለም፡፡ የህብረተሰብም ነው፡፡ ከቃል አሰጣጥ፣ ከደረጃ አሰጣጥ ጀምሮ፡፡ ፍርድ ቤቱ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ብቻውን ሊወጣ አይችልም፡፡ ህብረተሰቡ፣ እያንዳንዱ የመንግሥት አካል እውነት ከመናገር ጀምሮ የፍትህን ሥራ የማገዙ ነገር በተግባር ሊታይ ይገባል፡፡ ሌላው የሙስና ጉዳይ ዋናው ችግራችን ነው፡፡ በሌሎች የመንግሥት አካላት የሚፈፀምን ሙስና ለመዋጋት በመጀመሪያ ደረጃ የፍትህ አካላት ከሙስና የፀዱ መሆን አለባቸው፡፡ የፍትህ አካላት ከሙስና ካልፀዱ ሙስናን ስለመዋጋት መናገር ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ ከሙስናና ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ህዝቡ ሊደግፈንና ሊያግዘን ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስና የፍትህ አካላት ጋር ያሉ ነገሮች ግልፅ ካልሆኑ ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ነገሮችን መዋጋት ከባድ ስለሚሆን ህብረተሰቡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ሌላው ዳኛው ተጠያቂ ነው ብለን ስንል ማንም ገብቶ የሚረብሸው የሚዘባርቀው አይነት አይደለም፡፡ የራሱ አካሄድ መስመር አለው፡፡ ህጉን ሥርዓቱን ተከትሎ የፍርድ ነፃነቱን በማይረብሽ መልኩ፤ ስለዚህ ህብረተሰቡ አሁን እያደረግን ያለነው ሥራ ዳኛን እንደፈለገ የማያሰራው መስሎት እንዳይታየው እያንዳንዱ ጉዳይ ይህን ካላደረገማ ይህ ይሆናል የሚሉት አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን እያደረግን ያለነው የዳኝነትን መብት የሚሸረሽር አይደለም፡፡ የሚያጠናክር ነው፡፡ ነፃነታችን መጀመሪያ በራሳችን ንፁህ ሆነን ስንገኝ ነው፡፡ ይህንን ነው ህብረተሰቡ መደገፍ ያለበት እንጂ እየተከተልነው ባለው እንቅስቃሴ ዳኛው እንዲሸማቀቅ በነፃነት እንዳይሠራ የሚያደርግ አዝማሚያ እንዳይዝ አደራ እላለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ችግር ያለበትን በበቂ ማስረጃ በሚያሳምን መረጃ የህብረተሰቡን አገልጋይነት ተሸክሞ የማይጓዝ ሰው ይዘን እንሄዳለን ማለት አይደለም፡፡ ዳኛው ህብረተሰቡን ነው የማያገለግለው በህብረተሰቡ እምነት ሊጣልበት ይገባል፡፡ በግል ህይወታችን ስንንቀሳቀስ ይሄ ሰው ፍትህን ይሰጣል ተብሎ በማህበረሰቡ ጭንቅላት መታሰብ አለበት፡፡ ይህንን ልናደርግ የምንችለው ግን የራሳችንን ህይወት ምሳሌ በሆነ መልኩ መምራት ስንችል ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |