| ከአዲስ አበባ - ቢሾፍቱ ዝርፊያ... |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
ከአዲስ አበባ - ቢሾፍቱ ዝርፊያ ሲያካሂዱ የነበሩ ተያዙ
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ተዘርፏል በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ በቢሾፍቱ የኢየሩሳሌም ህፃናት ማሳደጊያ፣ ባቡጋያ ከሚገኘው የገሊላ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንና በተለያዩ ግለሰቦች ቤት በመግባት የተቀነባበረ ዝርፊያ በመፈፀም ወንጀል የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ጉግሳ ታከለ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በተጠቀሱት ቦታዎች ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ዝርፊያ በማካሄድ የተጠረጠሩት በመሳሪያና በተሽከርካሪ የታገዙ ዘራፊዎች ናቸው፡፡ ስድስት ወር የፈጀ ምርመራና ክትትል በማካሄድ በቁጥጥር ስር የዋሉት አስራ ስድስት ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ የተዘረፈውን ንብረት በመደበቅ ተባባሪ የሆኑም ይገኙበታል፡፡ ባቦጋያ ገሊላ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የገቡት ዘራፊዎች በውስጥ የነበሩትን ሰዎች "በማገት" ዝርፊያ መፈፀማቸውንና "ወርቅ፣ ገንዘብ፣ ሞባይልና ንብረት" መዝረፋቸውን" ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡ "ኢየሩሳሌም የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ውስጥ ገብተው ከጥበቃ ሰራተኞች መሳሪያ በመንጠቅና ጉዳት በማድረስ ኮንቴነር ሰብረው ጐማዎች፣ የውኃ ፓምፖች፣ ጄነሬተሮች፣ ግራይንደሮችና ሌሎች ንብረቶችን ዘርፈዋል" ያሉት ኢንስፔክተር ጉግሳ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር የምርመራ ስራ ካገናኛቸው በኋላ የተረጋገጠውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ዝርፊያም ገልፀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ቢሾፍቱ የተደራጁት ዘራፊዎች ከጤና ቢሮው ስልሳ ኮምፒዩተር ከነኘሪንተሩ ጀነሬተር፣ ፍሪጆችና የተለያዩ ንብረቶችን መጋዘን ሰብረው መዝረፋቸውን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የግለሰብ ቤት ለመዝረፍ የጥበቃ ሰራተኛ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው የውጭ አገር ዜጋ መኖሪያ ቤት ወስጥ ገብተው ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀማቸውን የሚናገሩት ኢንስፔክተር ጉግሳ "ዘራፊዎቹ ከአዲስ አበባ አዳማ ድረስ የተደራጁ ተሽከርካሪ የሚጠቀሙ፣ክላሽን መሳሪያ፣ ቦንብና የስለት መሳሪያዎች እጅ ከፍንጅ የተያዘባቸው በመሆኑ ፖሊስ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል" በማለት ህብረተሰቡ ለሚሰነዝረው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የቢሾፍቱ ነዋሪዎች እጅ ከፍንጅ የተያዙ ዘራፊዎችና ከዘራፊዎቹ ጋር ተባባሪ የሆኑ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ እንዲፈቱ በተደረጉት ላይ ቅሬታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ኢንስፔክተር ጉግሳ "የህብረተሰቡን ቅሬታ እጋራዋለሁ፡፡ ፖሊስ ወንጀለኞችን የመያዝና ህግ ፊት የማቅረብ እንጂ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን የለውም" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |