| ታዳጊ ሕፃን የደፈረው በዋስ በመለቀቁ... |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
ታዳጊ ሕፃን የደፈረው በዋስ በመለቀቁ ነዋሪዎችና የሴቶች ጉዳይ ተቃወሙ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት በአሶሳ ከተማ ቀበሌ 04 ውስጥ የ13 ዓመት ታዳጊ ሕፃን በመድፈር ተጠርጥሮ የታሰረው ግለሰብ በ500 ብር ዋስ በመለቀቁ የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤትና የከተማው ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ለክልሉ መንግሥትና ፍርድ ቤቶች ማሰማታቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ የሕፃኗ አመልሄር ሸሪፍ አባት እንደገለፁት እናት የስኳር ሕመምተኛ በመሆናቸው ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና በመጡበት ወቅት ተጠርጣሪው ብቸኝነቷን አውቆ፣ ከቁራን ትምህርት ቤት ስትመለስ ዝናብ ይዘንብ ስለነበር "እንድትጠለል ጠይቋት ወደ ቤቱ ካስገባት በኋላ እንደደፈራት ምስክሮች ለፍርድ ቤት መናገራቸውንና በሐኪም መረጋገጡን ወላጅ አባቷ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ወረዳ ፍርድ ቤት ግለሰቡ ሕፃኗን መድፈሩን የሚያረጋግጡ የሕኪምና የሰው ማስረጃዎች እያሉ፣ "በቂ ማስረጃ አላገኘሁም" በማለት ተጠርጣሪውን መልቀቁ አግባብ አለመሆኑን የወረዳው ሴቶች ጉዳይ ኤክስፐርት ወ/ሮ ዘነበች አለምነህ ገልፀዋል፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤት መዝገቡን መዝጋቱ አግባብ አይደለም ብለው በማመናቸው የክልሉ ፍትህ ቢሮና የዞን ፍትህ፣ እንደገና ማየት ስለሚችሉ፣ የውሳኔው ግልባጭ እንዲሰጥ ቢጠየቅ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን ወ/ሮ ዘነበች ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የወረዳው ሴቶች ጉዳይ ቢሮና ነዋሪው ባሰማው የተቃውሞ ድምጽ ወደ ዞን ፍርድ ቤት እንዲሄድ ማድረጋቸውን ኤክስፐርቷ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዜጎችን እየፈጀ ባለበት ወቅት ህፃናትን በማታለልና በማስገደድ የመድፈር ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ዓለም እያወገዘና የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ባለበት ሰዓት፣ ሙሉ ማስረጃ የቀረበበትን ተጠርጣሪ በዋስና በነፃ ማሰናበት የአገሪቱ የሕግ ጉዳይ ሊፈተሽና ሊታይ የሚገባው መሆኑን ወ/ሮ ዘነቡ አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩ ወደ ሴቶች ቢሮና ኅብረተሰቡ የደረሰው ለወረዳው ፍ/ቤት ተደፋሪዋ ሕፃን አመልሄር ጥር 26 ቀን 2000 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪውን በ500 ብር ዋስ እንዲለቀቅ የወሰነውን በመቃወም የፃፈችው ደብዳቤ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ወላጅ አባቷ ባሰሙት አቤቱታ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |