| የፖስታ አገልግሎት ድርጅት... |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ ከኃላፊነታቸው ተነሱ
ጁነዲን ሳዶ 500 ከሚሆኑ የታገዱ ሰራተኞች ጋር እንዲያወያዩ ተጠየቁ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ተኮላ ሺመልስ ከሀላፊነታቸው ተነስተው፡፡ በምትካቸው ከአቅም ግንባታ አቶ ግደይ ገብረ ዮሐንስ ተመድበዋል፡፡ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር በአዲሱ ምደባ ያልተካተቱን ሰራተኞች እንዲያነጋግሩ በድጋሚ ተጠየቁ፡፡ ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ እንደሚመለክተው በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጁ ምትክ አዲስ ኃላፊ ከመመደቡ በስተቀር ስለቀድሞው ኃላፊ መነሳት የሚለው ነገር የለም፡፡ አንዳንድ ሰራተኞች ሪፎርሙን የሰሩትና ስህተት መፈፀማቸው የተረጋገጠባቸው የስራ ኃላፊዎች በዝምታ መታለፋቸው ቅር እንዳሰኛቸው ገልፀዋል፡፡ ከኃላፊዎች ለውጥ ጋር ግንኙነት እንዳለው ባይታወቅም በመስሪያ ቤቱ የተሰራው የአሰራር ማሻሻያ ጥናትና ትግበራ ችግር እንደነበረበት ሰራተኞች ገልፀው እንደነበረ ታውቋል፡፡ በተወሰኑ ዐቢይ የሥራ ሂደቶች አመራረጥ ችግር መኖሩንና ጥናቶቹም ጉድለት እንዳለባቸው፣ የጥናት ውጤቶች (የሥራ ሂደቶች፣ ማኑዋሎችና የመስሪያ ቅጾች) ለሰራተኛው በበቂ ሁኔታ ገለፃ ያልተደረገባቸውና ያልተተቸባቸው መሆኑ ሰራተኞቹ ገልፀዋል፡፡ ሰራተኛው በለውጡ ግንዛቤው አነስተኛ መሆኑ፣ በሰራተኞችና የስራ ሂደት ባለቤቶች ምደባ አድሎዋዊና የማጥቃት አሰራር እንደነበር፣ ጠንካራ የሽግግር ስርዓት ባለመኖሩ ትግበራው መጓተቱ በሚሉት መጠይቆች ዙሪያ "በዋና ዋና ጉዳዮችና ሌሎች ተዛማጅ ነገሮች ላይ ስም የማይገለፅበት፣ ነፃ፣ እውነታ ላይ የተመረኮዘ ድርጅቱን ለተሻለ ውጤት የሚያበቃ አስተያየት በጽሁፍ"". እንዲሰጡ ታህሳስ 30 ቀን 2000 ዓ.ም አቶ ተኮላ በፊርማቸው ጠይቀው ነበር፡፡ በሌላ ዜና በአዲስ የአሰራር ጥናት ማሻሻያ የስራ ምደባ ያልተሰጣቸው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽንስ ኤጀንሲና ከዋናው መሥሪያ ቤት በድምሩ 500 የሚጠጉ ሰራተኞች ሚኒስትሩን በዛሬው እለት ለማነጋገር ቀጠሮ መያዛቸውን ታውቋል፡፡ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትሩ ጁነዲን ሳዶ ቀደም ሲል ሰራተኞቹ ላቀረቡት አቤቱታ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ሃይል እንዲቋቋም መደረጉን ከሁለት ወር በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀው ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ህዳር 25 ቀን 2000 ዓ.ም በቁጥር ጠ80 - ሠጠ5/01/06ለሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በፃፈው ደብዳቤ "ይሁን እንጂ በግል ድርጅትም ሆነ በሌላ መንገድ ተቀጥረው ሊሠሩ የሚችሉ የዲፕሎማና የዲግሪ ተመራቂዎች ካልሆኑ በቀር ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሠራተኞች በአዋጅ ቁጥር 424/97 በአንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት በ20/45 ጡረታ ማስወጣቱ ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚያጋልጣቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ከሥራ ሳይፈናቀሉ ተጨማሪ ሥልጠና እየተሰጣቸው አማራጭ የሥራ ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር እናስታውቃለን" ደብዳቤ የደረሰው የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ተቋርጦ የነበረውን የሰራተኞች ደሞዝ እንዲከፍል ከማድረግ ውጪ ምደባውን ለማስተካከል ፈቃደኛ አይደለም፡፡ አማራጭ ተብሎ የቀረቡት የሥራ መስኮችም ሰራተኛውን የሚመጥኑ አለመሆናቸውን በመግለፅ ተቃውሞ የሚሰነዝሩት ሰራተኞች በአስራ አምስት ቀን ውስጥ መፍትሄ ያቀርባል የተባለው የሙከራ ሃይል ቢቋቋምም ያለአንዳች መፍትሄ ወራት ማስቆጠሩን በቅሬታ ይገልፃሉ፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |