| የንግድ ባንክ የሠራተኞች ማህበር... |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
![]() አቶ ምንተስኖት ጥበበ የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ የሠራተኞች ማህበር ትላንት ባካሄደው ስብሰባ የአስራ አምስት ቀን የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ አቀረበ፡፡ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ምንተስኖት ጥበበ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ማህበሩ በአስራ አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄው እንዲመለስ ለባንኩ አመራር፣ ለቦርዱና ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የፋይናንሺያል ኤጀንሲ ማመልከቱን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ምንተስኖት ገለፃ ማህበሩ የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ መንግሥት ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ለባንኩ ሠራተኞች አልተጨመረም፡፡ በዚህም ምክንያት ማህበሩ ለባንኩ የሥራ አመራርና ለባንኩ ቦርድ እንዲሁም ለፋይናንሻል ኤጀንሲው በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ላለፉት ሰባት ወራት "ጠብቁ" ከሚል መልስ ውጪ ፍትሀዊ ምላሽ አልተሰጠም፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሚመለከታቸው የባንኩ አመራር አካላት የሠራተኛውን የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ተገቢ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ የጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጠራ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ምንተስኖት በጠቅላላ ጉባኤው በሚወሰን ውሳኔ የቀጣይ እርምጃ እንደሚታወቅ ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ "የደመወዝ ማሻሻያው እኛንም ስለሚመለከት የባንኩ አመራር አካላት ፍትሀዊ ምላሽ ይስጡን" ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደ አየር መንገድ፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን የመሳሰሉ ድርጅቶች በአግባቡ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረጋቸውን ጠቅሰው "የንግድ ባንክ ማስተካከያ የማያደርግበት ምክንያት ግልፅ አይደለም" ሲሉ አማርረዋል፡፡ የስብሰባው ውሳኔ በሰርኩላር ለመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች፣ ለማኔጅመንቱ፣ ለቦርዱና ለፋይናንሻል ኤጀንሲው መገለፁን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ የሠራተኞቹን የደመወዝ ጥያቄን በተመለከተ የንግድ ባንክ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት "ከቢሮ ወጥተዋል" በሚል ምላሽ አልተሳካልንም፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |