Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow የከተማ መሬትን እንደገና ማደላደልን...
የከተማ መሬትን እንደገና ማደላደልን... Print E-mail
Wednesday, 13 February 2008
የከተማ መሬትን እንደገና ማደላደልን የሚጨምር ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

አዲሱ የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ የመሬት እንደገና ድልደላንና ከተማን መልሶ የማልማት ልዩ ልዩ ረቂቅ ድንጋጌዎችን ይዞ ቀረበ፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሰረት ቦታን እንደገና የመደልደል ተግባር ማለት በተደራሽነት በመጠን አቀማመጥና በዋና ዋና የመሰረተ ልማት አውታሮች አቅርቦት ረገድ የተመቻቹ ሆነው ውጤታማና ቆጣቢ የመሬት አጠቃቀምን የሚያረጋግጡ የከተማ ቦታዎችን ለመስገኘት ሲባል ክፍለቦታዎችን የመከፋፈልና የማስተካከል ተግባር ነው፡፡
ቦታን እንደገና የመደልደል ተግባር የሚከናወነውና የሚመራው፣ ገደቡ በሚመለከታቸው ቻርተር ያላቸው ከተሞች ወይም የከተማ አስተዳደሮች መሆኑን በረቂቁ ላይ ተመልክቷል፡፡

 ይህ የህግ ሃሳብ በተግባር ላይ እንዲውል የታሰበ ማናቸውም ቦታን እንደገና የመደልደል እቅድ በከተማው የቦታ አጠቃቀም ፕላን ጋር ተጣጥሞ መገኘት ያለበት መሆኑን እንዲሁም የመሬት ሃብትን በተሻለ ደረጃ ለህዝብ ጥቅማ ዓላማ ለማዋል ዓላማ ካልሆነ በስተቀር የከተማ ቦታን እንደገና የመደልደል ተግባር እንደማይከናወን ያመለክታል፡፡

አንድ ከተማ ውስጥ የሚታዩትን የፈራረሱ፣ ያረጁና የተተዉ ስትራክቸሮችን በከፊል ወይም በሙሉ በማስወገድ ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ በማድረግ አላማ ላይ አትኩሮ የሚፈፀመውን ከተማን የማደስ ተግባር በከተማው መዋቅራዊ እና የአካባቢ ልማት ፕላን በሚባሉ ሁለት የፕላን አይነቶችን በተመለከተው ማዕቀፍ ውስጥ በበቂ ምክንያት ተደግፎ የሚታቀድና የሚፈጸም መሆኑን ረቂቁ ያቀረበው የህግ ሃሳብ ይገልፃል፡፡

የከተማ እድሳት ይከናወንበታል ተብሎ በታሰበ አካባቢ የሰፈሩ ነዋሪዎች እድሳቱ በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በቅድሚያ ስለ ሁኔታው እንዲያውቁና እንዲመክሩበት እንደሚደረግ ያመለክታል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች በሙሉ ተፈፃሚ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀው የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ በማናቸውም ደረጃ ላይ የሚገኙ ከተሞች መዋቅራዊና የአካባቢ ልማት ፕላኖቻቸውን የማዘጋጀትና የመከለል ተግባራቸውን ራሳቸው ወይም በተመሰከረላቸው የግል ወይም የመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት ሊያከናውኑ የሚያስችላቸውን ሥልጣን የሚሰጥ የህግ አሳብ አቀረበ፡፡

ከተሞች የየራሳቸውን መዋቅራዊ እና የአካባቢ ልማት ፕላን የሚባሉ ሁለት የፕላን አይነቶች የማዘጋጀትና የማጽደቅ ሥልጣን ቢኖራቸውም በረቂቅ አዋጁ መሰረት የፌደራሉ መንግስት ወይም የክልል መንግስት ፕላኑ ከረቂቅ ህጉ ከተደነገጉት መሰረታዊ መርሆዎች ጋር የማይጣጣም ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ የፀደቀ የከተማ ፕላን የማገድ ሥልጣን አለው፡፡

በዚህ ረቂቅ ሕግ መሰረት እያንዳንዱ ከተማ የየራሱ የተለየ ወሰን ቢኖረውም "አካባቢውን ይዞ እንዲለማ ለማድረግ ሲባል አግባብ ባለው የመንግስት አካል የዕድገት ማዕከል ሆኖ ሊመረጥና እውቅና ሊሰጠው ይችላል" የሚል የህግ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

(ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና ጉዳዩም ያስከተለውን እስከ አሁን ያልተፈታ ፖለቲካዊም እየሆነ የመጣ ችግር የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚሉት በተለይም የዚህ ረቂቅ ድንጋጌ መነሻ የአዲስ አበባ፣ እልባት ያጣ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49/5 እና በሌሎችም የአዲስ አበባ መስተዳድር ቻርተሮች "አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ" ከተማ ተብሎ ዕውቅና ያገኘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡም ከዚህ ችግር ጋር ተያይዞ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የዋሽንግተንን ከተማ ጠቅሰው በሌሎች ክልሎች ውስጥ ገብቶ የመልማትን አብነት መጥቀሳቸው አይዘነጋም)

ረቀቅ ህጉ በአንድ ከተማ ውስጥ በልማት እንቅስቃሴ ለመሰማራት የሚፈልጉ የትኛው አልሚ፣ አስቀድሞ የልማት ፈቃድ ካልተሰጠው በስተቀር "የልማት እንቅስቃሴ ማከናወን የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል፣ እንደ ህንፃ ፈቃድ ያለተጨማሪ ፈቃድ የሚያስፈልጋቸው የልማት ሥራዎች በልማት ፈቃድ አወጣጡ ሂደት ውስጥ በመዋሃድ እንደ አንድ ፈቃድ ሆነው ለአልሚው እንደሚሰጡም የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል፡፡

ልማት ማለት በረቂቁ ህግ መሰረት በመሬት ላይ ወይም ከመሬት በታች የሚካሄድ የግንባታ የምህንድስና የማዕድን ወይም ሌላ ሥራ ወይም በማናቸውም ስትራክቸሮች መንደሮች የአገልግሎት ዘመን ላይ የሚደረግ ከፍተኛ ለውጥ ሲሆን ይህንን በተመለከተ ለአልሚ የተሰጠ የልማት ፈቃድ ያንኑ ፈቃድ በሰጠው ቻርተር ያለው ከተማ ወይም የከተማ አስተዳደር በስተቀር በማንኛውም ሌላ አካል ሊታገድ የማይችል መሆኑን ረቂቁ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም በማናቸውም ከተማ ክልል የሚከናወን ስትራክቸሮችን ወይም መንደሮችን የማፍረስ እንቅስቃሴ ያለ ፈቃድ የማይፈፀም መሆኑን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልል ወይም የፌደራል መንግሥት አካላት በቅድሚያ የጽሁፍ ስምምነት ካልተገኘ በስተቀር በባህሪያቸው ለየት ያሉ ስትራክቸሮችን ለማፍረስ የሚቀርብ ጥያቄ ተቀባይነት እንደማይኖረው ረቂቁ ያቀረበው የህግ ሃሳብ ይወሰናል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >