| የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ከፍተኛ... |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ከፍተኛ አክሲዮን የያዘበትን ድርጅት ሠራተኞች በሙሉ ከሥራ አገደ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር 98 በመቶ የአክስዮን ድርሻ የሆነው ሕይወት ትራንስፖርትና ቴክኒክ አገልግሎት አክስዮን ማኅበር ድርጅት ሰራተኞቹን በሙሉ ከየካቲት 1 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ አገደ፡፡ ሠራተኞቹ ከሥራ የታገዱት፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በቁጥር ሕትቴአ1/1-05 ጥር 29 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ሰራተኛው በሙሉ ከጥር 30 እስከ የካቲት 5 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ የአመት ፈቃዳቸውን እንዲሞሉ በማሳሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል በጥበቃ ሠራተኞች፣ "ከየካቲት 1 ቀን 2000 ጀምሮ ማንም ሠራተኛ እንዳይገባ" የሚል ትዕዛዝ እንደደረሳቸው የተገለፀላቸው መሆኑን ሠራተኞቹ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት በመሆኑ አብዛኛዎቹ ሾፌሮች በመስክ ሥራ ላይ መሆናቸውንና ቤተሰቦቻቸውም የጥር ወር ደመወዛቸውን እንኳን እንዳልወሰዱ ተናግረዋል፡፡ ቀይ መስቀል ማኅበር በከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ ድርጅቱን ሲያቋቁም በዝውውር የተመደቡት እነዚሁ ሠራተኞች እንደገለፁት፣ "በቀይ መስቀል ማኅበር ክቡር ዓላማና መርሆዎች ስር መኖር ከማንም በላይ የህሊና እርካታን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ የሰው ልጆችን ከስቃይና ከመከራ ለመታደግ የታደሉ ወገኖች ራሳቸውን ለመስዋዕትነት የሚያቀርቡበት ድርጅት ነው" በማለት አሁን እየተሰራ ያለው ሥራ ግን የማኅበሩን ክቡር ዓላማና መርሆዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አጥብቀው ተናገረዋል፡፡ "አንድ ድርጅትን ለመዝጋትና ሠራተኛን ለማሰናበት መሠረቱ ህግ ነው፡፡ የቀይ መስቀል መሠረታዊ መርሆዎችን አለማክበር አንዱ የሞራል ጉዳይ ቢሆንም፣ የአገሪቱን የንግድ ህግና የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅን መጣል ሌላው ህግን የመጨፍለቅ ድርጊት ነው" ያሉት የድርጅቱ መሰረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ዓለሙ ናቸው፡፡ ማንኛውም ጉዳይ ኃላፊነት በጎደለውና በዜጎች ላይ የሚፈጸም ህገወጥ ተግባር የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ለአቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስና ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አዱኛ በፃፈው ደብዳቤ የማኅበሩን ክቡር አላማና መርሆዎች በመጥቀስ ከ15 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሠራተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን አደጋ ላይ እንዲወድቁ ማድረግ አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል፡፡ በድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ረፍት ውጡ፣ ትዕዛዝ ግራ ተጋብቶ ወደ መስሪያ ቤቱ የዕለት ሥራውን ለመስራት የካቲት 1 ቀን 2000 ዓ.ም ጠዋት ሰራተኛው ቢሄድም በድጋሚ በቃል ለጥበቃ ሠራተኛ በተነገረ የስልክ ትዕዛዝ ከሥራ ገበታ መታገድ አግባብነት ያለው ባለመሆኑ፣ በድርጊቱ ላይ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ፕሬዚዳንቶቹን ማኅበሩ በደብዳቤው ጠይቋል፡፡ አንድ ድርጅት ከስሮም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ከተዘጋና የድርጅቱ ሠራተኞች ከሥራ ከታገዱ የዋና ሥራ አስኪያጁም ኃላፊነት የሚያበቃ በመሆኑ፣ የሚሰጡት አመራር እንዲቆምና (በድርጅቱ ተንቀሳቃሽ ስልክና ተሽከርካሪ በመጠቀም) ለሥራ አስኪያጁ ቅርበት ያላቸው ሠራተኞችም እንዲገቡ ማድረግ በሰነዶችና ንብረት ላይ ያለውን ጥርጣሬ እንደሚያጎላው ማኅበሩ በደብዳቤው አሳስቧል፡፡ የአክስዮን ማኅበሩ ሥራ አመራር ቦርድ እንደገለፁት፣ "በእኛ በኩል ምንም ያስተላለፍነው ትዕዛዝ የለም፡፡ በሁኔታው እኛም ተገርመን እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ነገር ለመለየት በመነጋገር ላይ ነን፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ የተቋቋመው በአምስት ባለድርሻዎች ነው፡፡ አመራር አካሉ የአክስዮን ሥራ አመራር ቦርድ ብቻ ነው" በማለት ያነጋገርናቸው የቦርድ አባላት ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ቦርድ፣ ከአክስዮን ማኅበሩ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለውና ስልጣንን ተጠቅሞ አላግባብ ውሳኔ ማስተላለፍ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ "እንኳን የቀይ መስቀል ቦርድ አባላትና ዋና ፀሐፊዋም ቢሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ አያገባቸውም" የሚሉት የቦርድ አባላት የንግድ ድርጅት ሲቋቋምና ሲፈርስ በመመስረቻ ህግና በመተዳደሪያ ደንብ መሰረት ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ዋና ፀሐፊን በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ብንሞክርም፣ "ከቀይ መስቀል የቦርድ አባላት ጋር ተነጋግሬ ምላሽ እሰጣለሁ" በማለት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |