| "ፅንፈኛ አንድነትም ፅንፈኛ ብሔርተኝነትም ይቅር"< |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የሶስዮሎጂ ምሁር ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ጥናቶች ከሚያደርጉ ምሁራን ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ካበረከቱዋቸው መፃህፍቶች መካከል "ዘ ግሬተር ኢትዮጵያ" እና "ዋክስ ኤንድ ጎልድ" ይገኙባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጥናት የጀመሩበት 50ኛ ዓመታቸው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አክብረዋል፡፡ በቅርቡ በተመድ የስብሰባ አዳራሽ በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በተዘጋጀው ውይይት ላይ "ዘ ፕሮሚስ ኦፍ ኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ የጥናት ፅሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ ስለዚህና ሌሎች የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከባድ ፈተናዎች ተደቅነውባታል፡፡ እርስዎ ግን አሁንም ስለ "ኢትዮጵያ ተስፋ" ይናገራሉ፡፡ ይሄ ማንም ፖለቲከኛ ሊለው ይችላል፡፡ የእርስዎ አባባል ምን ለማለት እንደሆነ ሊያብራሩልኝ ይችላሉ? ፕ/ር ሌቪን፡- ኢትዮጵያ ተስፋ ማድረግም በእሱ ላይ ልትኖርም ይገባታል፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎችና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እኔ የምጠቁማቸውን ለውጦች ማምጣት ከቻሉ "ተስፋ" ይኖራል፡፡ ሪፖርተር፡- የጠቆሙዋቸው ለውጦች ምን ምን ያጠቃልላሉ? ፕ/ር ሌቪን፡- ዋነኛው የሚፈለገው ለውጥ ፖለቲካዊ ለውጥ ነው፡፡ በ97 ምርጫ የተፈጠረው ፅንፈኝነት ሊሰበር ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ተቃዋሚ"ዎች አገርን የሚጎዳ አካሄድ ወደጎን በመተው ተቀራርበው የጋራ መድረክ የሚፈጥሩበት መንገድ በማፈላለግ ላይ ነኝ፡፡ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ያመከነቻቸውን መልካም አጋጣሚዎች በተመለከተ የፃፍኩት ነገር አለ፡፡ በ1952 ዓ.ም የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት፣ በ1966 ዓ.ም የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ተግባራዊ አለመደረጉ፣ ኢህአዴግ ስልጣን የተቆጣጠረበት (1983 ዓ.ም"፣ የ1991 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና የ1997 ዓ.ም ምርጫ ናቸው፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና ዘመናዊነትን ለማምጣት እነዚህ አምስት ዕድሎች መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ አገሪቱ ሁሉንም አመከነቻቸው፡፡ ሪፖርተር፡- ችግሩ ምንድን ነው ይላሉ? ፕ/ር ሌቪን፡- አንዳንድ የአገሪቱ ባህሎች እነዚህ ለውጦች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል፡፡ አሁንም እንዳሉ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው "ወንድነት"ን ነው፡፡ ማለትም ችግሮች ሲፈጠሩ ለመፈታት አንድ ወታደራዊ መሪ የሚያደርገው ዓይነት በኃይልና በፉክክር በ"ማን አለብኝነት" መሄድ፡፡ በዚህ ምክንያት ሁለት ዕድል ብቻ አለህ፡፡ መሪውን ትከተላለህ ወይም ትሸፍታለህ፡፡ ሪፖርተር፡- በምሳሌ ቢያስረዱኝ፣ መፍትሄውስ? ፕ/ር ሌቪን፡- የ1997 ምርጫ ስናይ መንግሥት ሰዎችን ሲገድል ነበር፡፡ በርካታ ባለሃብቶች መንግሥት በጣም ጠንካራ እንዲሆን ፈልገዋል፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚዎቹ በጣም ጠንካራ እንዲሆኑ ወይም እንዲሸፍቱ አስበዋል፡፡ ኃይል የመጠቀም አዝማሚያም ነበር፡፡ "ከመንግሥት ጋር ምንም የምንሰራው ነገር የለም" የሚል አመለካከት ነበራቸው፡፡ በመሆኑም አንዳንዶቹ ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ወይም ወደ እስር ቤት ሲገቡ ሌሎችም ወታደራዊ አመፅ ማደራጀት ጀመሩ፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ሰዎች ፅናት (ካሬጅ) በአዲስ መልክ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፊት ለፊት የመገናኘትና የመነጋገር ፅናት፡፡ ይህ ሲቪክ ፅናት እለዋለሁ፡፡ ሰዎች እርስ በርሳቸው በማይነጋገሩበት፣ በማይደራደሩበትና ፍላጎታቸውን በማያስታርቁበት ሁኔታ ዴሞክራሲ አይታሰብም፡፡ ይህ አንድ የኢትዮጵያ መጥፎ ባህል ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ያደረግኩት ንግግር ረበተመድ የስብሰባ አዳራሽ የጥናት ፅሑፋቸው ባቀረቡበት ወቅትሪ የዚህ ተቃራኒ የሆነ የኢትዮጵያ ባህል አቅርቤ ነበር፡፡ ሰላማዊ የሆነ ውይይት፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ይህ ባህል ያላቸው በርካታ ማህበረሰቦች ጠቅሼያለሁኝ፡፡ እነዚህ ባህላዊ ውሎች ወደ ማዕከል ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ለዘመናት የቆየው "ማን አለብኝነት" (ወንድነት) ወታደራዊ አስተሳሰብ ሊቋጭ ይገባል፡፡ ይህ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ሌላው መለመድ ያለበት "ይቅር መባባል" ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥታት በታሪክ ይህ የቆየ ባህል አለ፡፡ አብዛኛዎቻቸው የኢትዮጵያ ነገስታት በዚህ ያለፉ ናቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሃንስ ህሞ፣ አፄ ሚኒሊክ ህህና አፄ ኃይለሥላሴ ወዘተ ሁሉም ይህንን አሳይተው አልፈዋል፡፡ ሶስቱም ትላልቅ እምነቶች ተቻችለው ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ክርስትና፣ እስልምና የአይሁድ እምነት፤ ሁሉም እምነቶች ስለ ይቅር መባባል ይሰብካሉ፡፡ ነገር ግን ይቅርታ ሰላማዊ የሆነው ሁኔታ እንዲያመጣ ከተፈለገ ከሁለቱ ወገኖች መሆን ይኖርበታል፡፡ ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ይቅርታ መጠያየቅና ይቅር መባባል አለባቸው፡፡ ሪፖርተር፡- በቅርቡ ስለተደረገው ይቅርታ/ምህረት የሚሉት ነገር ካለ? ፕ/ር ሌቪን፡- ከተቃዋሚዎቹ ልጀምር፡፡ ምህረት መጠየቅና ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀል ማለት "እንዲህ ዓይነት አፍራሽ ነገሮች ከመፈፀም አቁመናል" ማለት ነበር፡፡ ሆኖም የቅንጅት አመራሮች ረየቀድሞሪ ከእስር ቤት ልክ እንደወጡ በመጀመሪያ ያደረጉት ወደ አሜሪካ መጓዝን ነው፡፡ ለሚሊኒየሙ በዓል አልቆዩም፡፡ ከኢንጂነር ኃይሉ ሻወልና ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በስተቀር የተቀሩት አመራሮች ወደ ውጭ በረሩ፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ መንግሥትም ትልቅ ስህተት ፈፅሟል፡፡ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብን ጭምር መሆን ነበረበት፡፡ ሁለቱም ወገኖች ስህተት ፈፅመዋል፡፡ እውነተኛና ከልብ የመነጨ ይቅርታ ሊኖር ይገባል፡፡ መንግሥት ይቅርታ ሲጠይቅ፣ ተቃዋሚ ወገን "አይ እውነቱ አይደለም" ማለት የለበትም፡፡ አንድ መቶ ዶላር ከሰጠሁህ "ለምን እንዲህ እንዳደረገ ገርሞኛል" ልትል ትችላለህ፡፡ ይሁን እንጂ ቢያንስ ዶላሩን ሰጥቼሃለሁ፣ በፀጋ ልትቀበለው ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- ከ1950ዎቹ በፊት በሀገራችን ይቅር የመባባል ባህል ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመን ፅንፈኛ ፖለቲካ ስር ሰደደ፡፡ ያሄ የተፈጠረው ችግር ምንድን ነበር ? ፕ/ር ሌቪን፡- ያኔ ላስጠነቅቅ ሞክሬ ነበር፡፡ ይህ እንደሚመጣ ቀድሜ ማየት ችዬ ነበር፡፡ "ሠሮቦ and ሀቄቁሳ" በተሰኘው መጽሐፍ ደርግን በስም አልጥራው እንጂ የሚከተለውን አዲሱን የሶሻሊዝም ርዕዬተ አላማ ይዞ እንደሚመጣ ተንብዬ ነበር፡፡ እንዳልኩትም ተከሰተ፡፡ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ፈፅሞ የሚሄድ አልነበረም፡፡ በማርከሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም ሕዝቦች ጥሩና መጥፎ ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ፡፡ ስርዓቱ መጥፎ ለሚላቸው ሰዎች የነበረው ጥላቻ ስር የሰደደ ነበር፡፡ ለውይይት ክፍተት አልነበረውም፡፡ በቀጥታ እንዲገደሉ የተመቻቸ አሰራር ነበር፡፡ የተማሪዎች ንቅናቆ የሚሄደው በዚህ መልክ ነበር፡፡ በአፄው ስር የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ጀምረው የነበሩትን ሕዝቦች ስርዓታዊ አስተዳደር የሚገነባውን የሕብረተሰብ ክፍል እና መሪያቸውን አጠፉ፡፡ በ1950ዎቹ ሀገሪቱ በትክክል በእድገት ጎዳና ላይ ነበረች፡፡ ተማሪዎቹ ግን እያሉ የነበሩት "የኋላ ታሪካችንም ሆነ የካፒታሊስቱ ስርዓት መጥፎ ነው" የሚል ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኤርትራ ሕዝቦች ነፃነት ግንባር (ኢፒኤልኤፍ"፣ የትግራይ ሕዝቦች ነፃነት ግንባር (ቲፒኤልኤፍ"፣ መኢሶን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢፒአርፒ) እና ኦሮሞ ነፃነት ግንባታ (ኦኤልኤፍ) በሙሉ ማርክሲስት ሆነው ነበር፡፡ ነገር ግን አሰቃቂው ጉዳት የደረሰው በደርግ ነው፡፡ ደርግ "ያለፈው የኢትዮጵ ታሪክ በሙሉ መጥፎ ነው" የሚል ድምዳሜ ነበረው፡ አጠቃላይ አዲሱ ትውልድ ስላለፈው የኢትዮጵያ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ጥሩ አመለካከት ሳይኖረው እንዲያድግ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ አሁን ያሉት ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ በዚህ መልኩ እያሰቡ የተቀረፁ ናቸው፡፡ ስርዓቱ አስገራሚ የፅንፈኝነት ባህል የተንሰራፋበት ለዚህ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ያለፈውን ታሪክ በበጎ ጐኑ ያላዩ እንዴት ብሩሀማ መጭ ጊዜን ማለም ይችላል? ስለ ኢትዮጵያ መልካም እጣ ፈንታስ ለመናገር አስቸጋሪ አይሆንም? ፕ/ር ሌቪን፡- ለዚህ ሁሉን አቀፍና የተቀናጀ ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባየሁት ሁኔታ ያን ለመፈፀም የተዘጋጀ አካል አይታየኝም፡፡ እንደማስበው አገሪቱ አሁን የምትፈልገው ሕዝቦቿ የሚግባቡበት የጋራ የሆነ ነገር ማግኘት ነው፡፡ ታሪካቸውን ወደ ኋላ ተመልሰው መፈለግ አለባቸው፡፡ አሜሪካ ለዜጎቿ ሁሉ መልካም ምሳሌ ሆና መቀጠል ግድ ሆኖባት ነበር፡፡ ታሪካቸውን መከለስና ሁሉን አቀፍ የተሻለ ታማኝ ስርዓት መዘርጋትን የታሪክ አጋጣሚ አስገድዷት ነበር፡፡ ለኢትዮጵያስ ሕዝቦቿ በጋራ ታሪካቸውን ከልሰው ፅንፈኛ ያልሆነና ካለፈው ታሪክ መልካም ነገሮችን በበጎ ጐኑ የሚያይ ትውልድ ከማግኘት በላይ ምን የተሻለ ነገር ያስፈልጋታል? ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እየታየ ላለው የፅንፈኝነት ጎራ አንዱ ምክንያት በ1950ዎቹ ለነበረው የተማሪዎች አመፅ የኮሚኒስት አስተሳሰብ የተላበሰ በመሆኑ ነው ይላሉ? ሌላስ? ፕ/ር ሌቪን፡- ይህንን ጥያቄ ስለአነሳህልኝ ደስተኛ ነኝ፡፡ "ኢትዮጵያ ያመከነቻቸው እድሎች" በሚል የጥናት ፅሑፌ ለዕድሎቹ ማምለጥ ሶስት ዋነኛ ምክንያቶች አንስቼአለሁ፡፡ አንደኛው ከልክ ያለፈ "ወንድነት" (ማን አለብኝነት) ሲሆን ሁለተኛው ከውጭ የተዛመተ ርእዮተ ዓለም ነው፡፡ ሌላኛው "ዋክስ ኤንድ ጎልድ" በሚል መጽሐፌ አስቀምጨዋለሁ፡፡ እሱም ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው እንዴት ይነጋገራሉ (ይመለከታሉ) የሚል ነው፡፡ ለፅንፈኝነት አንዱ ምክንያት ይሄኛው አሮጌው አስተሳሰብ አንዱ በሌላው ላይ ያለው አለመተማመን የእርስ በርስ መጠራጠርና፣ መናናቅ፣ መሰዳደብ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ዋነኛ ተቃዋሚዎች አሃዳዊ መንግሥት መመስረት ይፈልጋሉ፡፡ መንግሥትም ደግሞ በብሔር የተመሰረተ ፌዴራሊዝምን ያራምዳል፡፡ እነዚህን ተቃራኒ ስርዓቶች እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? ፕ/ር ሌቪን፡- ባለፈው ሳምንት ከኒው ጄኔሬሽን ኮሌጅ ተማሪዎች ጋር ውይይት አድርጌ ነበር፡፡ አመለካከታቸው "ይሄኛው" ወይም "ሌላኛው" የሚል ነው፡፡ የብሔር ማንነትና ኩራት እንዲሁም የኢትዮጵያ ማንነትና ኩራት አንድ ላይ መያዝ ይቻላል፡፡ የማይቻል አይደለም፡፡ ችግሩ ይሄ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግሮች ምንድን ናቸው? ብዙ ፖለቲከኞች በብሔርና በአንድነት ፖለቲካ ተጠምደው ስለሌሎች ችግሮች የሚያስቡበት ጊዜ በጭራሽ የለም፡፡ በኮሌጁ ስብሰባ ስለ ኤድስና ስለ ረሃብ በተመለከተ የተነሳ ጥያቄ የለም፡፡ የሕዝብ መጠን ዕድገት በመጪው አስር ዓመታት ውስጥ ትልቅ ችግር ይፈጥራል፡፡ የደን ጭፍጨፋ ሌላ ችግር ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች በወቅቱ ሊፈቱ ይገባል፡፡ አንዱ በሌላው ላይ እጅን መቀሰሩ ለውጥ አያመጣም፡፡ ፅንፈኛ አንድነትም ፅንፈኛ ብሔርተኝነትም አያስፈልግም፡፡ አንዱ የሌላው መንስኤ ነው፡፡ ሁለቱም አስተሳሰቦች ሊወገዱ ይገባል፡፡ አንድ ሰው ተስፋ መፍጠር ካለበት የራሱን መለያዎች/መገለጫዎች መመልከትና መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከዚህ አንፃር ምን ማድረግ ትችላለች? ፕ/ር ሌቪን፡- በታሪክ ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ መገለጫዎች አሏት፡፡ በአሁኑ ወቅት ሚሌኒየም አንዱ ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡ የሚሌኒየሙ አንዱ አካል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ነው፡፡ ሚሌኒየሙ በጣም አስፈላጊ የሆነው ግን ህወሓት ስልጣን በመያዙ ረከያዘ ጀምሮሪ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ መናገር ጀምረዋል፡፡ አሁን ስለ ኢትዮጵያ የትም ቦታ ማውራት ማወደስ ትችላለህ፡፡ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ በተለይ አዲሱ ትውልድ ስለኢትዮጵያ ያለውን ዕውቀት በጣም አናሳ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እስላምና ክርስቲያን አብረው የሚኖሩባት ብቻ ሳትሆን አብረው በርካታ ታሪክ የሰሩባትና አብረው ያመለኩባት ብቸኛ ሥፍራ ነች፡፡ ከዚህ ውስጥ አንድ ልዩ መገለጫ (ሲምቦሊዝም) መፍጠር ይቻላል፡፡ ሪፖርተር፡- የቀድሞ የአገር ግንባታ (ኔሽን ቢዩልዲንግ) አሃዳዊ መንገድ በ1950ዎቹ የብሔር ጥያቄዎች በማስነሳቱ ሂደቱ እንደተኮላሸ ይነገራል፡ ያ ሂደት በኢትዮጵያ ተቃውሞ ስለገጠመው መቀጠል አልቻለም፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የፌዴራሊዝም ስርዓትም በተመሳሳይ ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡ ሌላ አማራጭ ይኖራል? ፕ/ር ሌቪን፡- የብሔር ኢፍትሃዊነትን ለማስወገድ የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ መንገድ የሕዝብ መድረኮችን መፍጠር ነው፡፡ ሕዝብ ችግሩን የሚገልፅበት መድረክ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ከብሔር ጥያቄ የተያያዙ ችግሮች በጣም ውሱን ናቸው፡፡ ከፍተኛ ችግር እያስከተሉ ያሉት ረሃብ፣ ኤድስ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ መሃይምነት የመሳሰሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ደርግ መጥቶ ጥሩውን የትምህርት ስርዓት ካፈረሰ ጀምሮ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ እነዚህ የመሳሰሉ ችግሮች ላይ መወያየት፣ መከራከርና መፍትሄ መፈለግ በአንድ ጉዳይ ውስጥ ከማተኮር ያድናል፡፡ የፖለቲካ ፅንፈኝነትንም ያስቀራል፡፡ ይሄ ሊለመድ ይገባል፡፡ በብሔር የተመሰረተው ፌዴራሊዝም ለአንድ ትልቅ ችግር መፍትሔ አስገኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጊዜያዊ መፍትሔ ነው፡፡ ያልተማከለ ስርዓት ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ በአንድ የአገሪቱ ክፍል ረሃብ ከተከሰተ በሌላው የአገሪቱ ክፍል ደግሞ የተትረፈረፈ ምርት ከተገኘ ችግሩን ለማስወገድ እንዴት ፍትሃዊ/አገራዊ የሆነ የሀብት ስርጭት መንገድ ትፈጥራለህ? ይህንን ችግር ለማስወገድ "ሕዝባዊነት" የተላበሰ የአገር ሕዝብ መኖር ግድ ይልሀል፡፡ ሁሉም ወገኖች ይህንን ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን የማዳን ሂደት ሊደረግ ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- ስለ ኤች አር 2003 የሚሰጡን አሰተያየት ካለ? ፕ/ር ሌቪን፡- በዕርዳታ የሚገኝ ገንዘብ ታች ወደ ሕዝብ እንዲወርድ እፈልጋለሁ፡፡ ለክሊኒኮች፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለመሳሰሉ ማዕከላት ውሎ ሕዝቡ ቢገለገልባቸው ይመረጣል፡፡ በአጭሩ ግን ስለ ረቂቁ ማለት የምችለው "ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ የተለያዩ የመንግሥት አካላት መካከል የውክልና ጦርነት እያደረጉ ነው"፡፡ እዚህ አገር ውስጥ እኮ ጦርነት የሚያስፈልጋቸው ችግሮች ሞልተዋል፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |