Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ህዝባዊ ተቀባይነት በኢትዮጵያ
ህዝባዊ ተቀባይነት በኢትዮጵያ Print E-mail
Wednesday, 13 February 2008
በምርጫ 97 የኢትዮጵያ ህዝብ የተሳትፎ መጠን ዓለምን፣ መንግሥት እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አስደንግጦ ነበር፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የሚፈልገውን ነገር በምርጫ ካርዱ አማካኝነት ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ለማሳየት ብርዱ፣ ፀሐዩ፣ ጨለማው፣ ሰልፉ፣ ግፊያው አልበገረውም ነበር፡፡
የነፃነቷ አገር ኢትዮጵያ የዲሞክራሲን ጮራ ልትፈነጥቅ ነው ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ ምርጫውን ተከትሎ የተፈጠረውን መዘርዘር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ መንግሥትም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሎም ህዝቡ ያጠፋውን ጥፋት ተከትሎ ባደግንበት ፍጥነት ወደ ኋላ ተሽቀንጥረናል፡፡ ባለፈው ሳምንት (ጥር 30) የተጠናቀቀው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ የተመዘገበው ዳታ ከተጠበቀው በታች መሆኑ ከበርካታ ማሳያዎች አንዱ ነው፡፡

በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምሁራን መንግሥት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚፈጥረው አለመግባባት ይልቅ መንግሥት ከህዝቡ ጋር የሚፈጥረው አለመግባባት አደገኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በቅርቡ በኢንተር አፍሪካ ግሩኘ አማካኝነት በተዘጋጀ አውደ ጥናት ታዋቂው አሜሪካዊ ኘሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ለኢትዮጵያ ህብረተሰባዊነት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ነበር፡፡ የታሪክ ኘሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴም መንግሥት ከህዝብ ስሜትና ፍላጎት ጋር መቀራረብ አለበት ብለው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ በቅርቡ ከእንግሊዝ ጋርዲያን ጋዜጣ ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግሥታቸው በምርጫ 97 ስህተት መስራቱንና ከዚያ ስህተት መማሩን ተናግረዋል፡፡ ከወራት በፊት የኢዴአፓ-መድህን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ልምድ በመነሳት ከህዝብ ጋር የበለጠ ከምርጫ 97 በኋላ መቀራረብ መጀመሩን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ "ከስህተታችን ተምረናል" የሚለው ንግግር ከህዝብ ጋር የማንቀራረብ የነበረ በመሆኑ አሁን ከህዝብ ጋር ይበልጥ እየተቀራረብን ነው ተብሎ ከተተረጎመ ብልህ እርምጃ ነው፡፡ የብዙ አፍሪካዊ መንግሥታት ችግር በመሆኑ ህዝባዊ ተቀባይነትን ለማግኘት መሞከር የሚበረታታ ነው፡፡ ችግሩ ህዝባዊ ተቀባይነት በቀላሉ አይገኝም፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ የዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት፣ በጋና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከልና በሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ትብብር አፍሮ ሜትር የተባለ ድርጅት ባወጣው ጥናት በጉስቁልና፣ በብጥብጥ፣ በበሽታና በሰላም እጦት የተቸገሩ የ18 የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ህዝባዊ መሠረት ያላቸው መንግሥታት በሀገራቸው እንዲፈጠሩ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ ጉዳዩ በጋና፣ ኬንያና ሴኔጋል ያለው ድጋፍ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ጥናቱ ያካተታቸው አፍሪካዊያን ከ8ዐ ከመቶ በላይ "ዲሞክራሲ ብዙ ችግር ቢኖርበትም ከእሱ የተሻለ አመራር የለም" ብለዋል፡፡ አፍሪካዊያኑ መንግሥታት "ዲሞክራሲያዊ" የሚል ቅጥያ ያላቸው ቢሆንም የመረጧቸው መሪዎች ለህዝቡ ትኩረት እንደነፈጉ ያማርራሉ፡፡

ይህ ተስፋ መቁረጥ በሀገራችን ሥር እንዳይሰድ መንግሥት፣ ሲቪክ ማህበረሰብ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝባዊ ተቀባይነት ያለው አስተዳደር ለመመስረት ጠንክረው ተስፋ ሳይቆርጡ ሊሰሩ ይገባል፡፡

ጀርመናዊው የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያና ፖለቲካዊ ኢኮኖሚስት ማክስ ዌበር "ህዝባዊ ተቀባይነት በእምነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን መታዘዝን ያበረክታል" ይላል፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ የኖረው ቶማስ ሆብስ "መንግሥትን ዜጎች የመቆጣጠር አቅም የላቸውም" ብሎ ያምን ነበር፡፡ በተቃራኒው ጆን ሎክ "ህዝቦች በማህበራዊ ውል አማካኝነት በሙሉ ፈቃዳቸው መንግሥት ያቋቋሙት ህይወታቸውን፣ ነፃነታቸውንና ንብረታቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ነው" ብሏል፡፡ ሎክ መንግሥት እነዚህን ኃላፊነቱን በመወጣት ተፈጥሯዊ መብቶችን ካላስከበረ ህዝቦች ከሥልጣኑ ሊያስወግዱት እንደሚችሉ ያብራራል፡፡

ማክስ ዌበር እንደሎክ ሁሉ በመንግሥት ተግባራት ላይ ህዝቡ ከፍተኛ ጫና ማሳደር እንደሚችል ይከራከራል፡፡ የመተማመን ባህል፣ በስሜት የመተሳሰርና የመቅዳት (አንዱ ከአንዱ የመዋስ) ልምድ፣ ስነ አመንክዮን መሰረት ያደረገ አብሮ የመስራት ቁርጠኝነት፣ በፈቃደኝነት ላይ የመረኮዘ ስምምነት እንዲሁም ለሥልጣኑ ባለቤት በፍላጎት ላይ የተመረኮዘ መታዘዝን መስጠት በህዝቦችና በመንግሥት መካከል ካልሰረፀ አስተዳደሩ ችግር ውስጥ እንደሚሆን ይገልፃል፡፡

የመንግሥት ተቀባይነት በዋነኛነት ፖለቲካዊ፣ ህጋዊና ማህበራዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ፖለቲካዊ ተቀባይነት በስርዓቱ አካሄድና በመንግሥት ተግባራት ገደቦች ላይ ሲያተኩር ህጋዊ ተቀባይነት ስርዓቶች የሚገነቡበትንና የሚፈርሱበትን ህጋዊ ማዕቀፍ መሠረት ያደርጋል፡፡ ማህበራዊ/ህዝባዊ ተቀባይነት ደግሞ ህዝቦች ከመንግሥት የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች፣ መዋቅሮች፣ ስነ ስርዓቶች፣ አድራጎቶች፣ ውሳኔዎችንና ፖሊሲዎችን በትክክል በአግባቡና በጥሩ ሁኔታ እንዲፈፀሙ ህዝብ በፍቅር በሚተባበርበት ሥርዓት ይገለፃል፡፡ ስለዚህ ህዝባዊ ተቀባይነት ከፍተኛ ሀይል አለው፡፡

መታዘዝ በጉልበት አልያም በመተማመን ይገኛል፡፡ በመተማመን መታዘዝን የሚያገኝ መንግሥት በሚሰራቸው አግባብ ያላቸው ሥራዎች መታዘዝንና መከበርን ያገኛል፡፡ ተከብሮና ተወዶ የሚሰራ ሥራ ደግሞ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ይህም በተለመደው ጊዜም ሆነ በቀውስ ወቅት የፖለቲካ ተቋሞች ተረጋግተው እንዲሰሩ እድል ይሰጣል፡፡

ተቀባይነት የሌለው አገዛዝ መቸገሩ አልያም መውደቁ አይቀርም ይላሉ በርካታ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፡፡ ሮበርት ዳህል ጉዳዩን ከውሃ ገንዳ ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ገንዳው ሲቀንስ የነበረው መረጋጋት በአደጋ ይተካል፡፡ በተመለሳሳይ ተቀባይነት ሲቀንስ የሚፈጠረውን ያለመፈለግና የውድቀት ዘመን ተገማች ያደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1918 የሩሲያ ዛር ረአፄሪ መንግሥት እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1959 የፈረንሳዩ አራተኛ ሪፐብሊክ ተቀባይነታቸው መሟጠጡን ያወቁ ነበር፡፡

እንደ ጆሴፍ ሮዝቻይልድ ዓይነት የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ ተቀባይነት ሲቀንስ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ውድቀትን መታደግ ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ተፈጥሯዊ ጥፋት፣ ከባድ ጦርነት፣ ከመጠን ያለፈ የቀረጥ ጫና፣ እና አስተዳደራዊ ሙስናን ተከትሎ የሚወስዱ እርምጃዎች የሰዎችን ስሜት የመቀልበስ እድላቸው አነስተኛ ነው፡፡ ተቀባይነት በመኖርና ባለመኖር የሚገለፅ ሳይሆን የሚጨምር ወይም የሚቀንስ ሂደት ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

ተቀባይነት ያገኘ መንግሥት ተቀባይነቱን ይዞ ለማቆየት ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ፣ ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ አስተዳደር፣ ቋሚና የሚያድግ ህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ፣ ህዝባዊ ተሳትፎ፣ ጠንካራና ነፃ ሚዲያ፣ እርስ በርስ የሚገማገሙ የመንግሥት ቅርንጫፎች፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መረጋጋትን ሊፈጥር፣ ሊያስፋፋና ሊያጠናክር የሚገባው፡፡

በአንፃራዊነት ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው የጋና፣ ዛምቢያ፣ ቦትስዋናና ታንዛኒያ መንግሥት በምርጫ አሸንፈውና ጥሩ የኢኮኖሚ እድገት አሳይተው ህዝባዊ ተቀባይነት ካጡት የኬንያው ኘሬዚዳንት ሞዋይ ኪባኪ ሊማሩ ይገባል፡፡ ወይም ደግሞ የተሰሩ ጥፋቶችን አምነው ለለውጥ እንደተዘጋጁት (የእውነት ከሆነ) እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መስመራቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ምርጫ 97ትን ተከትሎ ከህዝብ ጋር ለመቀራረብ መንግሥት ተነሳሽነት ያሳየ ሲሆን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ግን የከረረ ልዩነት አጎልብቷል፡፡ ለአካባቢና የማሟያ ምርጫው አራት ሚሊዮን እጩዎች ያቀረበ አንድ ፓርቲ የህዝብ ድጋፍ የለውም ሊባል አይችልም፡፡ በድብቅ በሥልጠና ለፓርቲው አካል የሚመለምልበትን ልማድ በመጣስ በአደባባይ (እርግጥ ይህን ማድረግ የተከለከለባቸውን የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉ በመጠቀም) ለአባልነት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በርካታ የውይይትና ቅሬታ ማቅረቢያ ስብሰባዎችንና አወደ ጉባኤዎችን አዘጋጅቷል፡፡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በቅርብ በመሆን አናግሯል፡፡ አሁን ደግሞ በቀበሌ እንኳን የምክር ቤት አባላትን ቁጥር 300 በማድረስ ያለተወዳዳሪና ተፎካካሪ ምርጫውን እየጠበቀ ነው፡፡ ይህ ለአቴና ዲሞክራሲ የቀረበ የቀጥተኛ ዲሞክራሲ ቅርፅ ያለው ተግባር ብዙ ህዝብ በማሳተፍ ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል የሚሉ ያሉትን ያህል ይህን የመንግሥት ተግባር የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን አፋዊ በማድረግ በተግባር የመቅበር አድራጎት ያደረጉት ብዙ ናቸው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከአራት ሰዎች ሦስቱ መራጭ አንዱ ተመራጭ እንደሆነም ተዘግቧል፡፡

የቀድሞው የኢሲኤ ዋና ፀሐፊ ኬ.ዋይ. አሞኮ አፍሪካዊያን መንግሥታትን ህዝባዊ ተቀባይነትን ማግኘት ያለባቸው በራሳቸው ልዩ ብሔራዊ አውድ እንጂ ድህነትን ለማስወገድ፣ ሶሻልና ኢኮኖሚያዊ እድገትና የህዝቦች ሰላም ለማምጣት የውጭ አካላት በሚያደርጉት ጫና እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለጋርድያን የውጭ መንግሥታት ለአፍሪካ ሀገራት ዲሞክራሲን በመጫን ለውጥ እንደማያመጡ ገልፀዋል፡፡

ለዲሞክራሲያዊ ባህል ያልተዘጋጀ ማህበረሰብ በብዛት በሚኖርበት ሀገሮች የተገደበ ዲሞክራሲ እንጂ ልቅ ዲሞክራሲ አያስፈልግም ሲሉ የሚከራከሩትን ምሁራን ኘሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅ በቅርቡ መወረፋቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሉት ጥሩ እሴቶች ዲሞክራሲን በራስ አውድ እንዲያጠናክሩት መሪዎች እድል እንዳልሰጡ ይከራከራሉ፡፡

ኬ.ዋይ.አሞኮ የህብረተሰብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ስድስት ፈተናዎችን ይጠቅሳሉ፡፡
የመጀመሪያው ፈተና ሰላምን ማረጋገጥ ነው፡፡ ግጭቶች መሠረተ ልማቶችን ያፈርሳሉ፣ ደካማ የመንግሥት መዋቅርን ይፈጥራሉ፣ የብሔር ውጥረትን ያነግሳሉ በውይይት ሳይሆን በጉልበት የማመንን ባህል ይፈጥራሉ፡፡ ኢትዮጵያም ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የብሔር ውጥረትን ለማጥፋት ከልቧ ካልሰራች የማትወጣበት ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡ ከዚህም ሌላ በቅርቡ የተካሄደው ዓይነት የሀይማኖት ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳታመራ የሚያደርጉ ስብሰባዎች ሊደጋገሙ ይገባል፡፡

ሁለተኛው ፈተና ዲሞክራሲን በጠንካራ መሠረት ላይ መጣል ነው፡፡ በአፍሪካ ዲሞክራሲ ያስፈልጋል ወይ? ተብሎ አይጠየቅም፡፡ እንዴት፣ መቼና በምን ቅርፅ ዲሞክራሲን እናስፍን ዋነኛው ጥያቄ ነው ይላሉ አሞኮ፡፡ ኢትዮጵያ ምርጫ 97 ዲሞክራሲን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመጣል መልካም አጋጣሚዋ ነበር፡፡ አልተጠቀመችበትም፡፡ ነገር ግን መንግሥትና ተቃዋሚዎች ከሚካሰሱ አብረው ሊሰሩ የሚችሉበትን ቀዳዳ በመፈለግ ብልጭ ብሎ የነበረውን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ይመልሱልን፡፡ የህዝብ ተሳትፎም ይጎልብትና ወደ ህዝብ ተቀባይነት ይሸጋገር፡፡ ጠባብ የፖለቲካ አተያዮች፣ ግለሰባዊ የሥልጣን ሽሚያ እና ሙስናን የሚዋጋ አስተዳደር ያለ ህዝብ ድጋፍ ውጤታማ አይሆንምና፡፡ ባህላዊ የህዝብ ተሳርፎ የሚንፀባረቅባቸው አሰራሮች ከዘመናዊው ዲሞክራሲ ጋር መቀየጥ ያስፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ሊጠናከሩ ይገባል፡፡

ሦስተኛው ፈተና የሲቪሉን ማህበረሰብን ተሳትፎ ማረጋገጥ ነው ይላሉ አሞኮ፡፡ ጠንካራ አፍሪካዊ የሆነና ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደርን አቅጣጫ የሚያሲዝ የመንግሥት አጋዥ የሆነ የሲቪክ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል፡፡ የህዝብ ተቀባይነትን ለማረጋገጥ የሚጫወተው ሚና፣ እውቅና በመስጠትና በመቃወም ፖሊሲዎችን በህዝቡ ውስጥ እንዲንሸራሸር የሚያደርገው ተሳትፎ በአዎንታዊ መልኩ መታየት አለበት፡፡ የሲቪሉ ማህበረሰብ የአፍሪካ ዲሞክራሲ እንዲበለፅግ ህዝባዊ ተቀባይነት እንዲያገኝና የበለፀገ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር ያደርገው አስተዋፅኦ በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ የሲቪል ድርጅቶች ፍላጐት ሊጠና እውቅናና ተቀባይነት ሊያገኙ በሀገሪቱ የፖሊስ ቀረፃ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ሊፈቀድላቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንዳደረገችው የዳንኤል በቀለና የነፃነት ደምሴ የክስ ጉዳይ ይህን ባህል የሚያደክም በመሆኑ ሊደገም አይገባም፡፡

አራተኛው ፈተና የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሚለኒየሙ ግቦች አንዱ የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት ከመሆኑ አንፃርና በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ብዙ ድርጅቶች ከመኖራቸው አንፃር በዚህ በኩል አትወቀስም፡፡

አምስተኛው ፈተና የዲሞክራሲ ተቋሞችንና የዜጎችን አቅም ማጎልበትና የተሻለ ተሳታፊ ማድረግ ነው፡፡ ብቃት ያለው ዜጋ ሰፋ ያለ ራዕይ ይኖረዋል፡፡ ህዝቦችን እንደ አደጋ ፈጣሪ ሳይሆን በዋጋ የማይተመን ጥቅም እንደሚሰጡ ያስባል፡፡ ለመከፋፈል ሳይሆን ለማቀላቀል፣ ለመለያየት ሳይሆን ለማግባባት ይሰራል፡፡ በዚህ በኩል ኢትዮጵያ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር መሥሪያ ቤትንና ዩኒቨርሲቲዎቿን በመጠቀም እየተራራቁ ያሉትን የሀገር ዜጎች የበለጠ ለማቀራረብ ፖሊሲ መንደፍና ስትራቴጂዎችን መቅረፅ አለባት፡፡

የመጨረሻው የአሞኮ ፈተና መንግሥት ለለውጥ ያለው ፍላጎት ነው፡፡ ለውጡ በጫና ሳይሆን በሀገር በቀል የራስ መንገድ መፈፀም አለበት፡፡ እንደ አሞኮ አባባል "የኖርንበትን እንጂ የተላከልንን ልምድ ውጤታማ አንሆንበትም"፡፡ ኘሬፎሰር ኤፍሬም ይስሀቅና ኘሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ያሉትም ይሄው ነው፡፡ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህንኑ ደግመውታል፡፡ የሚያስደስትና ውጤታማ የግጭት አፈታትም ሆነ  የዲሞክራሲ ባህል የጠገብን በመሆናችን እነሱኑ በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡

ከላይ በተገለፁት መንገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሞላ ጎደል ምርጫ 97ን ተከትሎ የህዝብ ተሳትፎን በማበርከት ህዝባዊ ተቀባይነትን ለማግኘት በርካታ ሙከራዎችን እያደረገ ነው፡፡ ዋነኛው ጥያቄ ግን ይህ ድጋፍ ከልብ ነው? በሚሊዮን የሚቆጠሩት አዳዲስ አባላቱ ለጥቅም ወይስ በአላማው አምነውበት ነው ኢህአዴግን የተቀላቀሉት? የሚለውን ጥያቄ የመመለስ ጉዳይ ከፓርቲው ህልውና ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከህብረተሰቡ ኑሮ መለወጥ/አለመለወጥ ከዲሞክራሲ ስርዓቱ እድገት/ውድቀት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት አሁንም በጥርጣሬ የሚሞላ የሚያደርግ/ የማያደርግ ከመሆኑ አንፃርና የሲቪክ ማህበረሰቡን እንቅስቃሴ የሚጐዳ/ የሚጠቅም በመሆኑ በአፋጣኝ መልስ ይሻል፡፡

በቅርቡ ይፋ የሆነው የአሜሪካ የህዝብ አስተያየት ጥናት ድርጅት (ፓሉኘ) ሪፖርት በኢትዮጵያ ምርጫ 97ን ተከትሎ ህዝባዊ ተቀባይነት በአስፈሪ ፍጥነት እየቀነሰ ነው ብሏል፡፡ ሪፖርቱ ለመንግሥት፣ ለሚዲያ፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለሀይማኖት ተቋማት፣ ለመከላከያ ሰራዊትና ለምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያዊያን ያላቸው እምነት ከአማካዩ የአፍሪካ ቁጥር በጣም እንደሚያንስ ከመጠቆሙ አኳያ መንግሥት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበረሰቡ ይህ ነገር ከፍ የሚሉበትን መንገድ በትብብር ሊቀይሱ ይገባል፡፡ ህዝቡን በአስቸኳይ ሊሰሙት ለፍላጎትና ለስሜቱም አስቸኳይ መልስና መፍትሄ አልያም አማራጭ ሊያቀርቡለት ይገባል፡፡ ይህ የቅንጦት እቃ ምርጫ ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይ ነውና፡፡ የህዝብ ተቀባይነት የሌለው መንግሥት ስርዓት አልበኝነትን ይጋብዛልና፡፡

በሰለሞን ጐሹ
 
< Prev   Next >