Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ዓለም አቀፍ ማዕከሉን በጋራ ለማልማት...
ዓለም አቀፍ ማዕከሉን በጋራ ለማልማት... Print E-mail
Wednesday, 13 February 2008
ዓለም አቀፍ ማዕከሉን በጋራ ለማልማት ምክር ቤቱና አስተዳደሩ ተስማሙ

በቻምበር ኤግዚቢሽን የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር 15ዐ ደረሰ


የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከ24ዐ ማሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማስገንባት ላቀደው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከልን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ ለማልማት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡
ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ማዕከሉን ለመገንባት በአማራጭነት ቀርበው ከነበሩ በርካታ እቅዶች ውስጥ አንዱ ግንባታውን ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር መገንባት በመሆኑ በዚህ መሠረት የምክር ቤቱና የአዲስ አበባ አስተዳደር ኃላፊዎች ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱንና የመጀመሪያው የመግባበያ ሰነድ ስምምነት ፈርማም በቀጣዩ ሳምንት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ኘሬዚዳንት አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ እንደተናገሩት፣ የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የንግድ ማእከልን በጋራ ለማልማት ለአስተዳደሩ ጥያቄ ቀርቦ በጉዳዩ ዙሪያ የተደረጉ ውይይቶች መልካም ውጤት በማስገኘታቸው የመጀመሪያውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በመጪው ሳምንተ በሚከፈተው የአዲስ ቻምበር የንግድ ትርዒት ላይ ይፈረማል፡፡

በኤግዚቢሽኑ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የአቅም ግንባታ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ማሕሙድ ድሪር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙ ግብዣ እንደተደረገላቸው ታውቋል፡፡

በ12ኛውን የአዲስ ቻምበር የንግድ ትርዒት የአዲስ አበባ አስተዳደር የራሱ የሆነ ኤግዚቢሽን ማሳያ ቦታ እንዲኖረው ተደርጐ የራሱ ፓቢሊዮን ተዘጋጅቶለታል፡፡ ለብቻው በተዘጋጀው ቦታ ከሚሊኒየሙ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ገፅታ የሚያሳይና ሌሎች የንግድ ትርዒቶች የሚዘጋጁበት ሲሆን ይህንን ለአዲስ አበባ ተብሎ የተዘጋጀውን ልዩ የኤግዚቢሽን ቦታ ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ እንዲከፍቱት ይደረጋል፡፡

አዲስ አበባ ባለፈው ሚለኒየም ያሳለፈችውን ታሪካዊ ጉዞ የሚያስቃኘው ልዩ ዝግጅት ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ሚለኒየም ፅህፈት ቤት ጋር በጋራ በመቀናጀት መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሃፊና የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮው 12ኛው የአዲስ ቻምበር የንግድ ትርዒት ላይ ከ3ዐዐ በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ከ3ዐ በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎቻቸውን በማሳተፍ ቀዳሚ የሆኑት የህንድ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

የህንድ ኩባንያዎች 27ዐ ካሬ ሜትር ቦታ ወስደዋል፡፡ የህንድ ኩባንያዎች ቁጥር ማደግን በተመለከተ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ እንደገለፁት ህንዶች በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ተሳታፊ ማሳተፋቸው የአገሪቱ ኩባንያዎች ከአገራችን የግሉ ሴክተር ጋር ምን የጠበቀ ግንኙነት ስላላቸውና ለግሉ ሴክተር ትኩረት በመስጠታቸው ነው፡፡

ባለፈው ዓመት በተካሄደው 11ኛው የአዲስ ቻምበር የንግድ ትርዒት 17ዐ የሚሆኑ የአገር ውስጥ እና ከ3ዐ የውጭ አገራት የተውጣጡ 12ዐ ኩባንያዎች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከላቲን አሜሪካ ብራዚል ተሳታፊ ነበረች፡፡

ባለፈው ዓመት ከ12ዐዎቹ የውጭ ኩባንያዎች 21 በመቶው ከአፍሪካ፣ 43 በመቶው ከአውሮፓና 29 በመቶ ከኤስያ 7 በመቶው ደግሞ ከአሜሪካ የተውጣጡ ነበር፡፡

ዘንድሮ ግን ከጠቅላላ የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ ህንድ ብቻዋን ከ25 በመቶ በላይ ያለውን ድርሻ ይዛለች፡፡ ህንድ በዚህ ኤግዚቢሽን ያቀረበቻቸው ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና የገበያ ድርሻቸው ከፍተኛ የሆኑ ኩባንያዎችን ጭምር ነው፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከልም እነ ታታ ኢንተርናሽናል ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ዘንድሮ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ3ዐ ብልጫ አሳይቷል፡፡

አቶ ታምራት እንደገለፁት በዘንድሮው ኤግዚቢሽን ለመሳተፍ የፈለጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኩባንያዎችን በቦታ ጥበት ምክንያት ሊስተናገዱ አልቻሉም፡፡

በዘንድሮው የንግድ ትርዒት የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጡ ኩባንያዎች እኩል ቁጥር አላቸው ያሉት አቶ ታምራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ኩባንያ ይዘው ከሚቀርቡት ህንዶች ሌላ ቻይና፣ ግብፅ፣ ኢራን በርካታ ኩባንያዎችን አምጥተዋል፡፡

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ኤግዚቢሽን ተሳታፊ የሆነችው ፖላንድ ናት፡፡ ይህም በቻምበር ኤግዚቢሽን የሚሳተፉ አገሮችን ቁጥር 51 ያደርሰዋል፡፡ "የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ምክክር የጋራ ምክክር ለለውጥ" በሚል የተዘጋጀው በዘንድሮው ኤግዚቢሽን ላይ የተለያዩ የምክክር ኘሮግራሞች እንደሚካሄዱም ታውቋል፡፡

ከየካቲት 13 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚካሄደው ኤግዚቢሽን መሪ ቃል የመንግሥትና የግሉ ሴክተር ምክክር ለለውጥ የሚል ነው፡፡

በዳዊት ታዬ
 
< Prev   Next >