| የወደቀ አስከሬን |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
አንዳንድ ሰው አለ በፍርሐት ተንጦ፣
የወደቀ አስከሬን በድን ሲመለከት የሚሸሽ ሮጦ፡፡ እኔም እፈራለሁ ሜዳ የወደቀ በድን ስመለከት፣ እደነግጣለሁ እሸሻለሁ ድንገት፡፡ የወደቀ አስከሬን ዓይኑን ያፈጠጠ፣ አማዋች የሌለው ጥርሱን ያገጠጠ፣ እንዴት አያስፈራ በዕውነትም ያስፈራል፣ ቀርበህ እንዳታየው “ገደልከው” ያሰኛል፡፡ (ታደለ ገድሌ፣ ትንቅንቅ፣ 1993) ንጉሥ ሣኅለ ሥላሴና የማርቲን ጨዋታ ንጉሥ ሣኅለ ሥላሴ አንኮበር ከተማ የነበሩ ጊዜ አንድ ሰው ማርቲን የሚባል አይሮጳዊ ነበር፡፡ አንድ ቀን በቅሎ እሰጥሃለሁ ብለው ዋሹት፡፡ ቀን ቢበዛበት እየዋለ እያደረ ያስታውሳል፡፡ እርሳቸውም ዘወትር እሺ ይሉታል፡፡ በዚህ መሃል ንጉሡ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ወጡ፡፡ ማርቲንም ዘወትር መናገሩን ቢሰለቸው በገንዘቡ በቅሎ ገዝቶ ወደ ንጉሡ ዘንድ ደብረ ብርሃን ወጣ፡፡ ንጉሡ እንዴት ሰነበትክ? ብለው ሲያበቁ ማርቲን በምን በቅሎ መጣህ አሉት፡፡ እርሱም በእሺ በቅሎ መጣሁ አላቸው፡፡ ብዙውን ስቀው ያንጊዜውን በቅሎ ሰጡት፡፡ በዚያን ዘመን በቅሎ እጅግ አጥብቆ ውድ ነበር፡፡ (ማጆር ኢዲ፣ የአማርኛ መድብለ ምንባብ፣1993) አሰበተፈሪ ኘ ጭሮ “የቆረቆርከውን ከተማ ምን ብለት ትሰይመዋለህ?” ብለው በጥፈት ጠየቁኝ፡፡ እኔም፣ “በጥንት ስሙ ጭሮ እለዋለሁ፡፡ አለዚያም፣ ባጠገቡ ሞቲ የሚባል ጋራ አለና ሞቲ እለዋለሁ” ስል መለስኩላቸው፡፡ “አስበ ተፈሪ” ብለህ ሰይመው ብለው ጣፉልኝ፡፡ “በቁምዎ ለራስዎ ስያሜ ከማውጣት፣ ሕዝቡ በኋላ መታሰቢያ ብሎ አውቆ በስምዎ ቢሰይመው ይሻላል” ስል ጣፍኩላቸው፡፡ “እኛ እንዳልንህ አድርግ” ሲሉ በመቀየም ዐይነት ጣፉኝል፡፡ ብዙ ሰዎች ለመደለያ ስል፣ “እኔ አሰበ ተፈሪ” ብዬ ከተማውን የሰየምኩት መስሏቸዋል፡፡ እኔ ግን ይህንኑ ለመግለጥ አጋጣሚ ሲፈቅድልኝ አልቦዘንኩምና፣ “አንተ የሰየምከው መስሎን አምተንህ ነበር” እያሉ ይገረማሉ፡፡ አንድ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ብወጣ አልጋ ወራሽ ፊት ነሡኝ፡፡ በኋላም ተነጋገርን፡፡ “መተያያ ትቀበላለህ አሉ” ብለው ወቀሱኝ፡፡ “ሦስት ሰንጎች ተቀብያለሁ፡፡ ግን ለራሴ አልወሰድኩም፡፡ እዚያው ያንጊዜውን እየታረዱ ለግብርና ለድሆች፣ ለማስተናገጃ ተደረጉ” አልኳቸው፡፡ “ለወደፊቱ መተያያ አትቀበል” አሉኝ፡፡ ይህ ንግግራቸው አስገረመኝ፡፡ ከዚያ በኋላ መተያያ ሲያመጡልኝ አልቀበልም እያልኩ መለስኩ፡፡ (ተክለ ሐዋርያት ተክለማርያም፣ ኦቶባዮግራፊ፣ 1998) ከፍርድ ጋር የተያያዘ ባሕርይ ባላምባራስ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ፣የቀድሞው ጨዋ ኢትዮጵያዊ ጠባይና ባህል፣ በተሰኘው መጽሐፋቸው ከህዝቡ አይነተኛ ጠባይ መካከል እንደ አንዱና ዋነኛው ብለው የጠቀሱት ይህንኑ ከፍርድ (ከዳኝነት) ጋር የተያያዘውን ባህርይውን ነው፡፡ ይህንንም ተንተን አድርገው ሲያብራሩ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ፍትህ ጥልቅ የሆነ ስሜት ወይም ዝንባሌ አለው፡፡ . . .የተጣላን ለማስታረቅ፣ የተበደለን ለማካካስም ሆነ ዳኝነት ለማየት በተቀመጠበት ሸንጎ ሁሉ ቃል ሲሰነዝር ከእውነት እንዳይርቅ በጣም በመጠንቀቅ ነው፡፡ ተረቶቹንና ምሳሌዎቹን ብንመረምራቸው ጉልህ የሆነ የተጨበጠ ልማደ ህግን ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ወላጆች በተረት፣ በፈሊጥ፣ በዘዴ እያደረጉ ዳኝነት ትክክለኛ ሚዛን መሆን እንዳለበት ለልጆቻቸውም ያስተምራሉ፡፡ (ሺበሺ ለማ፣ ተጠየቅ፣ 1985) የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው በ1959 ሲሆን፣ የተጋጠመችውም ከእስራኤል ቡድን ጋር ነበር፡፡ እስራኤል አንድ ለባዶ አሸንፋለች፡፡ (15ኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር፣ 1987) የአገር ፍቅር ቲያትር በ1948 ዓ.ም ጃንሆን ለጉብኝት አሜሪካ ደርሰው ሲመለሱ ያሳለፉትን የጉብኝት ጊዜ በኤብዚቢሽን ለማቅረብ ትልቅ አዳራሽ በማስፈለጉ ዛሬ የምንጠቀምበት የአገር ፍቅር ቴያትር ቤት ታነፀ፡፡ የአገር ፍቅር ማኅበር የሚለው ስምምነት ቀርቶ በ1960 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተሰኘ፡፡ ለዚህ ስም የታገሉት ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን መሆናቸው ይነገራል፡፡ ለኢትዮጵያ የቲያትር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት አብያተ ተውኔቶች አንዱና ዋነኛው የሆነው ይህ ቲያትር ቤት የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎችን መሰብሰብና በሙዚቃ ቡድን ተቀናጅተው ጥዑም ዜማዎችን እንዲያፈልቁ ማስቻሉ፣ እንዲሁም መተኪያ የማይገኝላቸው እጹብ ድንቅ መሳሪያ ተጫዋቾችን፣ ድምፃውያን፣ ተወዛዋዦችን፣ የተውኔት ፀሐፊዎችንና ደራሲዎችን አፍርቶ ለአገራት ኪነጥበብ አስተዋጽኦ ያበረከተ የጥበብ ቤት ነው፣ ፋና፡፡ (ዘመን፣ ሰኔ 1999) ተዋናይ ተዋናይ በመድረክ ላይ ብቻ ሳይሆን በዕለታዊ ኑሮውም ተመልካች፣ አስተዋይ መሆን አለበት፡፡ ስሜቱን የሚሰርቀውን ሁሉ አተኩሮ መመልከት ይገባዋል፡፡ አንድን ነገር በሚመለከትበት ጊዜ እንደማንኛውም ተመልካች ሳይሆን በጥልቀት መመልከትና መመርመር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እንደማንኛውም ግለሰብ ስለሚሆን አመለካከቱ ለሥራው ጥቅም የማይሰጥ ይሆናል፡፡ ህይወትም ትርጉም አይኖረውም፡፡ በተፈጥሮ የመመልከትና የመመራመር ችሎታ ያላቸው አሉ፡፡ ያለምንም ጥረት ተመልክተው የማወቅና የመገንዘብ ኃይል አላቸው፡፡ እነዚህም ሰዎች ተመልክተው ስለሚሰጡት መግለጫ ስታዳምጡ የመመልከት ኃይል የሌለው ሰው የሚያመልጠውን መገንዘብ ትችላላችሁ" ሌሎች ደግሞ ደስ የሚላቸውን ነገር እንኳን የመመልከትና የመመርመር ኃይል የላቸውም፡፡ ታዲያ ሕይወትን ለመመርመር ምን ያበቃቸዋል? "አብዛኛው ሰው ዓይን ቢኖረውም የገጽን ሁኔታ የዓይንን አመለካከት የድምጽን ሁኔታ፣ እንኳን አብሮት ከሚያወራው ሰው የማጥናት ኃይል የለውም፡፡ በአመለካከት ኃይል ይህንን ጥበብ ለማወቅ ብዙ ድካምን ይጠይቃል፡፡ የማወቅ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል፡፡" "ፍላጎት ሳይሆን ችሎታ የሌላቸውን እንዴት ተፈጥሮና ህይወት ሊያይዋቸው የሚሞክሩትን ማስተማር እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ ማየትን መስማትን ውብ የሆኑ ነገሮችን ማጥናትን መማር አለባቸው፡፡ (ደበበ እሸቱ፣ የተዋናይ ሀሁ፣ 1971) የካቲት የካቲት፣ መክተት፣ መሰብሰብ ማለት ነው፡፡ ገበሬው አዝመራውን ወቅቶ ጎተራ ውስጥ የሚከትበት፣ ገለባውን ሰብስቦ የሚከምርበት ወቅት ነው የካቲት፡፡ የካቲት በሌላ በኩል ገበሬው ለወራት በየቱና ግድግዳው ተሰቅለው የከረሙትን ሞፈር ቀንበርና ምራኑን ወልውሎ፣ ማረሻውን ስሎ፣ ለበልግ አዝመራ መሰናዶ የሚጀመርበት ወር ነው፡፡ የካቲት የመከር መክተቻ፣ የበልግ መባቻ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ (ካሕሳይ ገ/እግዚአብሔር፣ ኅብረ-ብዕር፣ 1998) አፍሪካዊ ያደረገህ ምንድን ነው? 1. የስጦታ መሸፈኛህን በጥንቃቄ ክፈተው እናም መሸፈኛውን በድጋሜ መጠቀም ትችላለህ 2. ከዚህ ቀደም አግኝተኸው የማታውቀውን ሰው አጎቴ ወይም አክስቴ ብለህ ትጣራለህ 3. በቤትህ ውስጥ ከሚገኙት ካሴቶችና ሲዲዎች ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ህገወጥ ቅጅዎች ናቸው፡፡ 4. ጋራጅህ ሁልጊዜም በእቃዎች እንደተሞላ ነው ምክንያቱም ምናልባት አንድ ሰው ቢፈልገው በማለት ምንም አይነት እቃ ስለማትጥል ነው፡፡ 5. ሆቴል ውስጥ ተከራይተህ በቆየህበት ጊዜ ያገኘኸውን ሻምፖ በሙሉ ሰብስበህ ወደ ቤትህ ትወስዳለህ (ይመችህ፣ የኔ ውድ ኩሩው አፍሪካዊ) 6. በአውሮፕላን በተጓዝክ ቁጥር ከባባድ ሻንጣዎች ትይዛለህ 7. አንድ መደብር የምርት እጥረት ካጋጠመው እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በተለያየ ሰልፍ ተራ በመያዝ በተቻለ መጠን በዛ ያሉ ምርቶችን ለመግዛት ይሞክራል፡፡ (ስኳር፣ ሳሙና፣ ሩዝ፣ ዘይት) 8. ሁሉም ህፃናት የሚሰጣቸው ቅጽል ስም የሚያበሳጭ ነው 9. የአንተ ቤተሰብ አባል የሆነ ሰው ሊጎበኝህ መምጣቱን ቀድሞ አይነግርህም (አጎትህ፣ የአጎትህ ሚስት፣ አማችህ፣ ሁለት የአጎትህ ልጆች እና አንድ ጎረቤትህ በቤትህ ውስጥ ተጠራቅመዋል) 10. ኪሶችህ ከሬስቶራንት ባገኘሃቸው ቅመሞችና ስቴኪኒዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ 11. በቀላል ጉዳይ ከእህቷ ጋር አለመግባባት የፈጠረችው እናትህ ለአስር ዓመት ያህል አታናግራትም 12. ስልክ የምትደውለው ዝቅተኛ ዋጋ በሚያስከፍለው የምሽት ጊዜ ብቻ ነው (በተለይ ምልክት አድራጊዎች) የሚቻል ከሆነ ጥሪዎችህን ሁሉ የምትጨርሰው በቢሮህ ስልክ ነው፡፡ 13. የምታደርገው የአውሮፕላን ጉዞ የአገር ውስጥ ቢሆንም እንኳን በአውሮፕላን ማረፊያው ከሃያ ያላነሱ ሰዎች ተገኝተው ይሸኙሃል 14. የኢንተርኔት አገልግሎት መስመርህን በየጊዜው ትቀያይራለህ፡፡ ምክንያቱም ኢንተርኔት ባስገባህበት በመጀመሪያው ወር የነፃ አገልግሎት ማግኘት ትችላለህ 15. የቢሮ እቃዎች ሁሉ ቤትህን ያውቁታል (አዎ" ስቴፕለር፣ ኤ-4 ሳይዝ ወረቀት፣ ስፒል 16. በወጣትነትህ ጊዜ ቢያንስ ሁለት አይነት ትልልቅ መጠን ያላቸው ጫማዎችና ልብሶች ይገዙልሃል እናም የተገዙት ልብሶችና ጫማዎች ለረጅም ጊዜ ይቆያሉ 17 በቤትህ ውስጥ የሚገኙት ጥቅል ሶፍት ወረቀቶች ከቢሮ እና ከሬስቶራንት የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ ማስታወሻ፡- ይህንን በሙሉ ለሌሎች አፍሪካውያን አስተላልፍ፡፡ ትክክለኛ አፍሪካዊ ያደረጋቸውን ነገር ማወቅ ያስችላቸዋልና፡፡ ገራገር በቸኮሌት የመዝናኛ ቤት ተሠራ በኒውዮርክ ማንሃታን በተባለ አካባቢ በሚገኘው "ፓርክ ሆቴል" ስድስተኛ ፎቅ ላይ ለፍቅረኛሞች ቀን ማድመቂያ በቸኮሌት የመዝናኛ ቤት ተሰራ፡፡ የፍቅረኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተሰራው ቤቱ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ቁሳቁስ ወንበርና ጠረጴዛውም መሆኑን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ጌስታቭ ኪሊመትስ የተባለው የሕንፃ ባለሙያ ሳሎኑን በተለያየ ቀለማት በተዋቡ ቸኮሌቶች፣ መመገቢያ ክፍሉን በቡናማና በነጭ ቸኮሌት ማሳመሩ ተገልጿል፡፡ በቤቱ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጠው ሻማ ከቸኮሌት የተሰራ ሲሆን ቤቱ የተሰራው አንድ እሽግ ቸኮሌት በ23 ዶላር በመግዛት መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በዳቦ ውስጥ የተገኘችው አይጥ አንዲት ቺኮዝላቪያዊት ወይዘሮ የገዙትን ዳቦ በመቆራረስ ላይ ሳሉ በዳቦው ውስጥ አይጥ በማግኘታቸው ወቀሳ አቀረቡ፡፡ ሃና ኮሪንኮስ የተባሉት የ35 አመት ወይዘሮ አይጧን ያገኙት በዳቦው ውስጥ ተቀብራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የጤናና የደህንነት ተቆጣጣሪ የሆኑት ማርቲን ስሚዲቶቫ ጥቆማው እንደደረሳቸው ባደረጉት ምርመራ የዳቦ ቤቱ ማቡኪያ አንድ ክፍል ተሰብሮ እንደነበርና በዚህ ሁኔታ አነስተኛ እንስሳት በዱቄት ውስጥ ለመግባት ቀላል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የአምስት ዓመት ሕፃን የተቆለፈ የባንክ ቤት በር ከፈተ አንድ የአምስት አመት ህፃን ለ19 ሰዓታት "ተቆልፎ ነበር" የተባለውን ባንክ በር ከፈተ፡፡ የሕፃኑ አባት የክፍያ መመዝገቢያ ማሽን በመጠቀም ላይ ሳለ ልጁ መጥቶ ባንኩ መከፈቱን ቢነግረውም "ቀልድ መስሎኝ ነበር" ብሏል፡፡ ዳንኤልና ኦሊቨር የተሰኙት አባትና ልጅ ሁኔታውን ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ ባንኩ ክፍት መሆኑ የታወቀው ቅዳሜ ከሰዓት ሲሆን ተዘግቷል የተባለው አርብ ምሽት 4፡30 አካባቢ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የቅርንጫፍ ባንኩ ኃላፊዎች ችግሩ ከቁልፉ መሆኑንና በደንበኞች የቁጠባ ሂሳብ ላይ ችግር እንዳልተፈጠረ ገልፀዋል፡፡ የሕፃኑ እናት በበኩሏ ባንኩ የመጥሪያ ደወል ስለሌለው በልጇ ምክንያት ሁኔታው ባይጣራ ኖሮ ባንኩ እስከ ሰኞ ክፍት ሊሆን እንደሚችልም ተናግራለች፡፡ ውሾች ሲኒማ እንዲገቡ ተፈቀደላቸው በኦስትሪያ የሚገኝ ሲኒማ ቤት የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግ ደንበኞቹ ከሚወዷቸው ውሾች ጋር ፊልም እንዲያዩ ፈቀደ፡፡ በቬና የሚገኘው የአድሚራል ሲኒማ በቅርቡ በቅርብ ርቀት ከተከፈተው ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ጋር የተሻለ ተወዳዳሪ ለመሆን እቅዱን መንደፉን ተነግሯል፡፡ የሲኒማ ተጠቃሚዎቹ አራት ዶላር ሲከፍሉ ውሾቻቸውን በነፃ ማስገባት ይችላሉ፡፡ ፊልም ቤቱ ከሌሎቹ የሚለየው በአካባቢው በሚገኙት የእንስሳት ደህንነት ባለሙያዎች ምክር መሠረት የእንስሳቶቹን ጆሮ ላለመጉዳት የፊልሙ ድምጽ አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ቶማስ ፌልዲንገር የተባለው የ24 አመት ወጣት በአንዱ የውሾች የፊልም ቀን ፊልም መከታተሉን ገልጾ በጣም ደስ የሚል ሃሳብ መሆኑን ተወዳጅ ውሻው እንደተደሰተበት ሌሎችንም ውሾች ሊያስደስት እንደሚችል ተናግሯል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |