| "በፍትህ ሚኒስቴርና በማኀበራችን መካከል... |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
"በፍትህ ሚኒስቴርና በማኀበራችን መካከል የተፈጠረው ችግር ይህን ያህል ጊዜ የፈጀው ቁጭ ብሎ ካለመነጋገር ነው"የአቶ ታምሩ ወንድማገኝ፤ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኀበር ኘሬዚዳንት አቶ ታምሩ፤ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር ኘሬዚዳንት ናቸው፡፡ በ1964 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ1973 ዓ.ም. ከእንግሊዝ ማንቺስተር ዩኒቨርሲቲ በህግ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ከ1965 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ዳኛ ነበሩ፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤትንም ሆነ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በምክትል ኘሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ ዳኝነቱን በመተው በግላቸው መስራት ከጀመሩበት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር በአባልነት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኀበርን በኘሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባትና ስለሌሎች ጉዳዮች ሰለሞን ጐሹ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኀበር ከስም ጋር በተገናኘየገጠሙት ችግሮች ምንድናቸው? አቶ ታምሩ፡- ይህን ማኀበር በ1958 ዓ.ም. እንደተመሰረተ ይነገራል፡፡ የጠበቆች ማኀበር በሚል እስከ 1968 ዓ.ም. ቀጥሎ ነበር፡፡ ከዚያም ወታደራዊ መንግሥት ሲቋቋም በሶሻሊስት ስርዓት እንመራለን የሚል ፍልስፍና በመከተሉ የማኀበሩ አጠራርና አሰያየም እንደዚሁም የአባላቱ ጥንቅር በሶሻሊስቱ ዓለም ከሚደረገው እንዲስማማ ተደርጎ መቀረፅ አለበት ስለተባለ የሕግ ባለሙያዎች ማኀበር በሚለው ተተካ፡፡ ይህም እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ ቀጠለ፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኀበር ቢባልም መምረጥ፣ መመረጥ፣ ድምፅ መስጠት የሚችሉት የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ብቻ ሆነው የጥብቅና ፈቃድ የሌላቸው የህግ ባለሙያዎች በተባባሪ አባልነት እንደሚመዘገቡ በደንቡ ተመልክቷል፡፡ በ1997 ዓ.ም. አካባቢ ስምን የሚመለከት ጥያቄ ተነሳ፡፡ ይህም እኛ በፍትህ ሚኒስቴር ከነበረን ውክልና ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ አዋጅ ቁጥር 199/1992 የፌደራል ጠበቆች የሚመሩበት አዋጅ ነው፡፡ በአዋጁ ላይ ቀደም ያለውን አሠራር ተከትሎ በዲሲኘሊን፣ በፈቃድ አሰጣጥ እና በፈተና አሰጣጥ ላይ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኀበር ሲሳተፍ ቆይቶ ነበር፡፡ በዲሲኘሊን ሁለት አባላት፣ በፈቃድ አሰጣጥ ሁለት አባላት፣ በፈተና አንድ አባል ከኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር እየተላከ ከፍትህ ሚኒስትርና ከዳኝነቱ ዘርፍ ከተውጣጡ አባላት ጋር አምስት ሆነው ውሳኔ ይሰጡ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ከቀጠለ በኋላ 97 ላይ አባሎቻችን እኛ ባላወቅነው ሁኔታ ከስብሰባው እንዲቀሩ ተደረገ፡፡ ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምን ነበር? አቶ ታምሩ፡- ምክንያቱን ስናጣራ እናንተ የጠበቆች ማኀበር ሳትሆኑ የሕግ ባለሙያ ማህበር ናችሁ በሚል ነው፡፡ ይህ ማለት በግል የጥብቅና ፈቃድ የሌላቸው ሰዎች በመካከላችሁ ይገኛሉ፤ ጠበቆችን ስለማትወክሉ እነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ መግባታችሁ ስህተት ስለሆነ መጀመሪያውኑም መግባት አልነበረባችሁም የሚል መልስ ስለተሰጠን በዚህ መነሻነት በአንድ በኩል ምንም እንኳን የሕግ ባለሙያዎች ማኀበር ብንባልም ድምፅ መስጠትና መመረጥ የሚችሉት ፈቃድ ያላቸው ብቻ እንደሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ መመልከቱን ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ የስም ከሆነም ወደ ቀድሞ ስማችን መመለስ እንደምንችል አስበን በመጋቢት 1998 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ስማችን በ1968 ዓ.ም. ወደ ነበረው የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኀበር ተብለን እንድንጠራ ውሳኔ ተላለፈ፡፡ ይሄ ውሳኔም ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ተላከ፡፡ ችግር የተፈጠረው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በፍትህ ሚኒስትር በኩል ያልተሟላ ነገር አለ የሚል ጥርጣሬ ተነሳ፡፡ ሪፖርተር፡- ጥርጣሬ ነው ወይስ የተረጋገጠ ስህተት? አቶ ታምሩ፡- እኛም ስህተት ካለ ለማረም፣ ነገር ግን ስህተት እንደሌለ ለማስረዳት ሞከርን፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር ያለምንም ጥርጥር የጥብቅናውን ዘርፍ የማስተዳደር በሕግ ስልጣን የተሰጠው አካል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ፍጥጫ ውስጥ መግባት አስፈላጊም፣ ተገቢም፣ ሕጋዊም አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ነው፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ደግሞ የመንግሥቱ ሕግ አስከባሪ ነው፡፡ የተሳሳቱ ነገሮች ሲከሰቱ ያንን የመጠየቅ ሕጋዊ መብት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ በዚህም የተነሳ የጠበቆች ማኀበር መባሉ በዓለም አቀፍ ሁኔታም ሲታይ ተገቢና አግባብ መሆኑን አስረድተናል፡፡ የጠበቆች ማህበር ወይም በእንግሊዝኛ ፣ባር አሶስዬሽን፣ ባለመሆናችን ኢትዮጵያን ወክለን ከአቻ ማህበራት ጋር ስንገናኝ አቻ ማህበራት ራሳቸውን ፣ባር አሶስዬሽን፣ ብለው እየጠሩ እኛ ፣ሎው ኘሮፌሽናልስ አሶስዬሽን፣ (የህግ ባለሙያ ማህበር) ማለታችን ያልሆነ ግንዛቤ በመፍጠሩ ለማህበራችን ብቻ ሳይሆን ለሀገራችንም የማይጠቅም በመሆኑ ይህን አስረድተን እንዲስተካከልልን አመልክተናል፡፡ በዚህ ረገድ የተሰሩ ስህተቶች ቢኖሩም ለማረም ዝግጁ መሆናችንን ገልፀናል፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር በኩልም ነገሮች በቀና መልኩ እየታዩልን ናቸው፡፡ ችግሩ በቅርቡ ይፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- ከ1994 በኋላ በተለይ ጠበቆችን ለማስተዳደር ከፍትህ ሚኒስቴር በተሻለ እኛ ብቃቱ ስላለን ይህን ስልጣን በህግ መንግሥት ሊሰጠን ይገባል እያላችሁ ስትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ተሳካላችሁ? አቶ ታምሩ፡- አንዳንድ መሠረታዊ ግንዛቤዎች ሊወሰዱ የግድ ይላል፡፡ የጥብቅና ማህበር አስተዳደርን በተመለከተ እኛ ከዓለም የተለየ የምናደርገው ነገር የለም፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “ኢት ኢዝ ኖት ሪሊ ኤ ማተር ኦፍ ኢንቬንቲንግ ዘ ዊል” ነው ወይም ደግሞ አዲስ ነገር አናመጣም፡፡ በዓለም ላይ ያሉትን የአስተዳደርና የአመራር ዘዴዎች ለእኛ እንደሚበጁን አስተካክለን በዚያ መልኩ መቅረፅ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በሁለት እንከፍለዋለን፡፡ በአንድ በኩል የጥብቅና ሙያን የሚያስተዳድር ስርዓት ሲኖር በሌላ በኩል ደግሞ ጠበቆች የራሳቸውን መብት የሚያስከብሩበት አካል አለ፡፡ ጠበቆች የራሳቸውን መብት የሚያስከብሩበት አካል “ባር አሶሲኤሽን” ይባላል፡፡ ጠበቆች ተባብረው ህብረት ፈጥረው የሚያቋቁሙት አካል ማለት ነው፡፡ ከሞላ ጎደል እንደ እኛ ያለ ማህበር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጠበቆችን አስተዳደር የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ማህበር አለ፡፡ በብዙ ቦታ በተለያየ መልክ ይቀረፃል፡፡ አንዳንድ ቦታ “ሎው ሶሳይቲ” (የህግ አስተዳደር ማህበረሰብ) ይሉታል፡፡ ይህ ተቋም ከሦስት መሠረታዊ አካሎች የተውጣጣ ነው፡፡ በብዛት ጠበቆች አሉበት፡፡ በብዛት ተከሳሽና ከሳሽ ሆኖ የሚቀርበው ተገልጋዩ ሕዝብ አለ፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጭምር መንግሥትን የሚወክሉም አሉበት፡፡ ስለዚህ ፈቃድ፣ ዲሲኘሊን እና ፈተናን የመሳሰሉት ይሄ አካል ይሰራዋል፡፡ የጥብቅናውን ደረጃ መወሰንን በተመለከተም ይወስናል፡፡ የዚህ አካል ዋናው ስልጣን ጠበቆችን መቆጣጠር ነው፡፡ የሙያ ክህሎት አለው ወይ? ዲሲኘሊን ያከብራል ወይ? የተማረው ትምህርትና ያለው ልምድ ይህንን ይመጥናል ወይ? የጥብቅና ስራ ከመጀመሩ በፊት መውሰድ የሚገባውን መሠረታዊ የሙያ ማዳበሪያ የሙያ ትምህርት (ፕ ሮፌሽናል ትሬይኒንግ) የሚባለው አለው ወይ? ለሚለው ስርዓት ዘርግቶ ህግ አበጅቶ ያ ተግባራዊ መሆኑን ይመለከትና በዚሁ መሠረት ቁጥጥሩን ያካሂዳል፡፡ የእኛ የጠበቃ ማህበር ከዚህ ይለያል፡፡ የጠበቆች ማህበር የጠበቆችን መብት ያስከብራል፡፡ በራሱ መንገድም የጠበቆችን የሙያ ክህሎት ያሳድጋል፡፡ በተከታታይ የህግ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ራሱ በሚያሰፍረው የዲሲኘሊን መስፈርት የጠበቆችን የስነ ምግባር ሁኔታ ይቆጣጠራል፡፡ በአገር ውስጥም ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ተቀራርበንና አንድ ላይ ሆነን እንደዚህ ዓይነት ነገሮች እንዲዘረጉ እና የጥብቅናው አስተዳደር ወደዚያው እንዲያመራ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእኛም ድርሻ አለበት፡፡ ከ1994 በፊትም ሆነ አሁን ጠበቆቻችንን ለማንቃት አንዳንድ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ሪፖርተር፡- 1994ን የፓን አፍሪካ የጠበቆች ህብረት አዲስ አበባ ላይ የተመሰረተበት ዓመት በመሆኑና . . . አቶ ታምሩ፡- የፓን አፍሪካ የጠበቆች ህብረትን በኢትዮጵያ ውስጥ የማቋቋሚያ ስብሰባ ማካሄዱና ዋና ፅህፈት ቤቱ አዲስ አበባ መደረጉ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር ለኢትዮጵያ ያበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነወ፡፡ የወቅቱ ባለሙያዎች በሌላ በኩል የአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ጠበቆች ስብሰባው እዚህ እንዲካሄድ ማህበሩ እንዲቋቋም ፅህፈት ቤቱም አዲስ አበባ እንዲሆን ስላደረጉ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የምስረታ በዓሉን አስመልክተው የተፃፉ ብዙ ጥናታዊ ወረቀቶች በራስ አስተዳደር ላይ የሚያተኩሩና ማህበራችሁም የህግ ከለላ እንድሰጠው የተንቀሳቀሳችሁበት ሂደት ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ አቶ ታምሩ፡- ስለጠበቆች አስተዳደር ከቅኝ ገዢዎች የተወረሱ አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ሲታይ የማንኛውም የአፍሪካ ሀገር የጥብቅና አስተዳደር ከእኛ ይሻላል፡፡ እኛ ለምን እንደዚያ አላደግንም አንልም፡፡ ማደግ አለብን ብለን ግን መስራት አለብን፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ጠበቆች ክለብ መስርተናል፡፡ ጠበቆቻችን አባሎቻችንና የህግ ባለሙያዎች በሙሉ እዚያ ቦታ እየተገናኙ እርስ በርስ ሙያቸውን ያሳድጋሉ፡፡ በአልባሌ ቦታ እንዳይገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለሙያ አስተዳደር ስለሙያ ኃላፊነት ስለዲሲኘሊን ስለጠበቆች ግዴታ ስለመሳሰሉት ጉዳዮች የመወያያ መድረክ ይፈጥርላቸዋል፡፡ የጥብቅና አስተዳደሩ ሁሉንም አሳታፊ በሆነ ሁኔታ ኃላፊነቱንም ጠበቆች ላይ በሚጥል ሁኔታ እንደገና መዋቀር እንዳለበት እናምናለን፡፡ ይህንን የፍትህ ሚኒስቴርም የሚያምንበት ነው፡፡ ተቋማዊ የሆነ ግልፅነት ያለው አሠራር እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ በሌላው አገር እንደሚደረገው እንደጥብቅናና ህክምና ያሉ ሙያዎች ሁልጊዜ በቀለም ትምህርት ብቻ የሚሰሩ ስላልሆኑ ተጨማሪ የሙያ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተግባራዊ ስልጠና የሚኖርበት ስርዓት መፈጠር አለበት፡፡ እነዚህ እንዲፈጠሩ ግፊት እናደርጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- በቀድሞው የማህበሩ ህገ ደንብ አባሎቻችሁ የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ነበሩ፡፡ ሌሎች ተባባሪ አባሎቻችሁ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ዳኞች፣ አቃቤ ህጎች፣ የዩኒቨርሲቲ የህግ መምህራን፣ የተመረቁ የህግ ተማሪዎች፣ በግል ከህግ ጋር የተገናኘ ስራ የሚሰሩ ግለሰቦች ከማህበሩ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? አቶ ታምሩ፡- አባልና ተባባሪ አባል ማለት በሌላውም ዓለም የተለመደ ነው፡፡ ይህ የጠበቆች ማኀበር ነው፡፡ ማንም ሰው ህግ ሊማር ይችላል፡፡ ግን ህግ ስለተማረ ጠበቃ አይሆንም፡፡ ከመነሻው በዓለም ላይ በሙያ ብቻ የሚከናወኑ ተግባሮች ሦስት ነበሩ፡፡ አንድ ሀይማኖት ነው፡፡ ሁለተኛው ህክምና ነው፡፡ ሦስተኛው የህግ ሙያ ነው፡፡ በኋላ እየሰፋ ሂዶ አሁን ብዙ ናቸው፡፡ ሙያው ራሱ በባለሙያው ላይ የሚጥለው ግዴታ አለ፡፡ ግዴታዎቹ የሙያ ስነ ምግባር፣ የቀለምና ተግባራዊ ትምህርቶች፣ የሙያ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ናቸው፡፡ ይህ ማህበር ፈቃድ አግኝተው፣ መሀላ ምለው በሙያው ስነ ምግባር በሚተዳደሩ የጥብቅና ባለሙያዎች የተቋቋመ ነው፡፡ ተባባሪ አባሎች በእኛ ህግ እንዲተዳደሩ አይገደዱም፡፡ ነገር ግን ለሙያው ባይተዋሮች አይደሉም፡፡ መሳተፍ እንዲችሉ የምንፈቅደውም ለዚህ ነው፡፡ መምረጥና መመረጥ ስለማይችሉ የጥብቅና ፈቃድ ባላቸው ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም፡፡ ከዚያ በመለስ ያለው መብት ሁሉ አላቸው፡፡ ሙያውን የሚያስተዳድሩት ግን ፈቃድ የያዙት በጥብቅና ሙያ ውስጥ ያሉት ናቸው፡፡ አዋጅ ቁጥር 199/92ትም የሚጠይቀው ይህንኑ ነው፡፡ ተባባሪ አባሎች ወደፊትም ጠበቃ የመሆን እድል ያላቸው ናቸወ፡፡ የሚሰጡትም አስተያየት ይጠቅማል፡፡ የህግ እውቀትም በውይይት ይዳብራል፡፡ ድሮም ነበሩ አሁንም ባለው ህገ ደንብ በተመሳሳይ ሁኔታ አሉ፡፡ ሪፖርተር፡- በህገ ደንቡ ያለው የአባላት መዋጮ በወር 1ዐ ብር ነው፡፡ አላማዎቻችሁ በርካታና አቅም የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እስከመቼ ድረስ ነው በውጭ እርዳታ የምትንቀሳቀሱት? አቶ ታምሩ፡- ይህ ትክክልና እውነትም ነው፡፡ በገንዘብ አቅም በኩል የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኀበር ድክመትም ችግርም አለበት፡፡ መዋጮው በወር 1ዐ ብር ነው፡፡ እሱም በአግባቡ አይሰባሰብም፡፡ ገንዘብ ማለት አቅም ነው፡፡ አቅማችን በዚህ ረገድ ደካማ ነው፡፡ አባላቱ ይህንን በሚገባ ይገነዘቡታል፡፡ ነገር ግን አባሎቻችን ማህበሩን ለመርዳት ከፍተኛ ፈቃደኝነት አላቸው፡፡ ባለፈው አመራር ከአምስት ዓመታት በፊት ማኀበሩ የቤት ኪራይ መክፈል እንኳን አቅቶት ችግር ውስጥ በገባ ሰዓት ቤት ለመገንባት በተደረገ የእራት ግብዣ አባላትና ከአባላት ውጪ ያሉ ተሳትፈውበት ከ800,000 ብር በላይ ተሰበሰበ፡፡ በቅርቡም የተከራየነው ክለብ ከአቅም በላይ በመሆኑ እሱን ለመደጎም በአንድ ቀን እስከ 200,000 ብር ለመስጠት አባሎቻችን ቃል ገብተውልናል፡፡ የእኛን የመዋጮ አቅም ደካማነት የተገነዘቡ አርባ የሚጠጉ አባላት ክፍያቸውን በወር 1ዐዐ ብር አድርገዋል፡፡ 5ዐዐ ከሚጠጉት አባሎቻችን ጋር ሲነፃፀር ትንሽ ቢሆንም ቁጥሩ እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው በራሳችን ለመቆም እየጣርን መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማህበር አሁን ባለበት ሁኔታ አባልነት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ግን በማህበሩ አስተዳደር የጎላ ተሳትፎ የጎላ ሥልጣን እንዲኖረው ቢደረግ (መደረግም ያለበት ይመስለኛል) አባሎች ለመክፈል የሙያ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ስለሚኖርባቸው (ሌላ ሀገር እንደሚደረገው ማለት ነው) የአባሎቻችን ቁጥር እየበረከተ ገቢያችንም እየዳበረ ስለሚሄድ ማህበሩንም ያጠናክረዋል፡፡ የድክመታችን አንዱ መሠረት አባል ለመሆን ብዙ ገፋፊ ነገሮች አለመኖራቸው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የህግ ማሻሻያ ኘሮግራም ላይ ያላችሁ ተሳትፎ ምንድን ነው? አቶ ታምሩ፡- አሁን ያለን ተሳትፎ መስራት ያለብንን ያህል አይደለም፡፡ ይህም ከእድገታችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የሌላውን ሀገር ጠበቆች ማኀበርና የእኛን ስናወዳድር በጣም ትልቅ ልዩነት እናያለን፡፡ በተሳትፎ በአስተዋፅኦ በሰው ኃይልም በገንዘብ አቅምም በተሰሚነትም አንፃር ደካማ ነን፡፡ ማህበራችን አሁን እየሰራ ያለው የሞፈር ዘመት ሥራ ነው፡፡ ከጠበቆቹ ውስጥ አንድም ሰው በቋሚነት ተቀጥሮ አይሰራም፡፡ ሌላ ሀገር አንድ ሰው የጠበቆች ማኀበር ኘሬዚዳንትና ፀሐፊ ሆኖ ሲመረጥ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ይሆናል፡፡ የሙያውን ሥራ ሌላ ሰው ይሰራዋል፡፡ ማህበሩም ጠንካራ በመሆኑ ደመወዝም ይከፍላቸዋል፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውንም ለጥብቅናው ሳይሆን ለማህበሩ ያወሉታል፡፡ ኮሚቴዎች ራሱ ቋሚ ተከታታይ አላቸው፡፡ እኛ ጋ ግን በትርፍ ጊዜ ነው የማኀበሩም ሆነ የተለያዩ ኮሚቴዎች ሥራ የሚሰራው፡፡ ማኀበሩ የራሱ የሆነ አቋም ጥንካሬ ያለውና ባለሙያዎቹ ራሳቸው ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያውሉበት የሥራ መስክ ነው፡፡ አሁን አንድ የሙሉ ጊዜ ዳይሬክተር ቀጥረናል፡፡ ጠበቃ ሀሳብ አፍላቂና ፈር ቀዳጅ መሆን መቻል አለበት፡፡ ይሁንና እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ቢኖሩብንም የኢትዮጵያ የህግ ስርዓት ማሻሻያ ኘሮግራም ላይ በተቻለን መጠን እየተሳተፍን ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን በምርጫ ህግ ላይ ፓርላማው አስተያየት እንድንሰጥበት ጠይቆን እሱን አድርገናል፡፡ ሪፖርተር፡- የዓለም የጠበቆች ማህበርና የፓን አፍሪካ ጠበቆች ህብረት አባል ናችሁ፡፡ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በስምና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተፈጠረ አለመግባባት ባልተቋጨበት ሁኔታ የትኛውን ስም ነው የምትጠቀሙት? አቶ ታምሩ፡- ፈረንጆቹ የዚህ ዓይነት ችግር የለባቸውም፡፡ ፣ባር አሶስየሽን፣ የሚል ስም ነው ያለን፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ሁኔታ ተቀባይነት ያገኘ ስም ነው፡፡ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ያለን አለመግባባት ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ በመነጋገር የማይፈታ ነገር የለም፡፡ ይህን ያህል ጊዜም የፈጀው በቅርበት ቁጭ ብሎ ካለመነጋገር ነው፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህንን ነገር በተገቢው መልኩ የመቋጨት ግዴታም አለበት፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |