| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
(በአፍሪካ የመጨረሻ የዋንጫ ውድድር ግብፅና ካሜሮን ሲጫወቱ ለማየት ከጓደኛቸው ጋር እቤታቸው ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ጨዋታው እየተሟሟቀ ሲሄድ ወሬያቸውም በስፖርቱ ዙሪያ ተሟሟቀ) - እኔ ግብፅ የምታሸንፍ ይመስለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እንጃ እስቲ የሚሆነውን ከዘጠና ደቂቃ በኋላ እናያለና፡፡ - ግብፅ በተከታታይ ውድድሮች በማሸነፏና በብዛት የውድድሩን ሻምፒዮን በመሆኗ የአፍሪካ ሪከርድ ትይዛለች ማለት ነው፡፡ - እነሱኮ ቀደም ብሎ የተደራጀ ፌዴሬሽን አላቸው መሰለኝ - አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ነበር የጀመሩት፡፡ ሶስቱ ብቻ እያሉኮ ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አሸንፋለች፡፡ - እኛም የድሮ ነን በለኛ፡፡ - አዎን የድሮ ነን፡፡ ድሮ ነበርን፣ ድሮ ሆነንም ቀረን፡፡ ለወደፊቱም ተስፋ ያለው አይመስለኝም፡፡ - ለምን አይመስልህም? - ጠንካራ ፌዴሬሽን የለንማ፡፡ - እንጀምራለን ተብሎ ለውጥ ተደርጎ የለም ወይ? - ክቡር ሚኒስትር መቀየሩ ጥሩ ነው፡፡ የማይረባ ነበር፡፡ - አዲሱስ እንዴት ነው? - በአዲሱማ ጥሩ ሰዎችም አሉበት፤ የማያስፈልጉ ሰዎችም አሉበት፡፡ ለመሆኑ ክቡር ሚኒስትር... - ለመሆኑ ምን? - የነበሩትኮ ገና አልለቀቁም፡፡ አናስረክብም ብለዋል፡፡ - ትቀልዳለህ? - እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ለምን አያባርሯቸውም? - ዋናውን ከግቢው ማስወጣት ሲያቅታቸው በእሱ የተቀጠሩ ናቸው ብለው ዘበኞቹን ያባርራሉ፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ እንደሆነ ይገርመኛል፡፡ - መንግሥት ራሱ ሜዳ ገብቶ ይጫወት እንዳትል፡፡ ምን ያድርግ መንግሥት? - ፈራ ተባውን ትቶ ቆራጥ እርምጃ ይውሰድ፡፡ - ባለሥልጣኖች ተሯሩጠው አይደለም ወይ የመቀየር እርምጃ የተወሰደው፡፡ - እርምጃ እንዲወሰድ ያደረጉትን ያህል ለውጥ እንዲመጣ ፈጣን እንቅስቃሴ የማያደርጉ ባለሥልጣናትም አሉ፡፡ - ወይ እኔ፣ ወይኔ ... ለጥቂት፣ ለጥቂት ካሜሮን ጎል አግብቶ ነበር፡፡ እንዴት አይነት እድል ነው ያመለጠው፡፡ ይህችንስ የእኛ ልጆችም ያገብዋት ነበር፡፡ - ፌዴሬሽኑ ደካማ ስለሆነ ጠንካራ ተጫዋቾች ማፍራት አልተቻለም፡፡ እስቲ የእኛን ተጫዋቾች ከናይጄሪያ፣ ከአይቮሪኮስት፣ ከጋና፣ ከካሜሮን፣ ከግብጽና ከአንጎላ ጋር ያወዳድሯቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - የእኛ ተጨዋቾች ችግራቸው ቁመትና ጉልበት ነው አሉ፡፡ - አይደለም፣ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ የጃፓን ቡድን ውጤት እያስገኘ ያለው ጉልበትና ቁመት ኖሮት ነው? - እኔ አላውቅም፡፡ ሰዎች ሲያወሩ የግብ ዕድል የላቸውም እንጂ ጥሩ ቴክኒክ ብቃት አላቸው ይላሉ፡፡ - እግር ኳስ ማለት ግብ ማግባት ማለት ነው፡፡ ግብ ካልገባ አይ ጠባይ፣ አይ ቴክኒክ እያሉ ራስን ማፅናናት አያስፈልግም ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ኢሕአዴግ ልማታዊ መንግሥት ነው፡፡ ስፖርት ላይ ለማተኮር ጊዜ የለውም፡፡ - ስፖርትና ስነ ጥበብም የልማት አካል እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - መጀመሪያ ስለሚበላና ስለሚጠጣ ነገር እናስብ ማለቴ ነው፡፡ - በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር ስፖርትና ስነ ጥበብ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭም እየሆኑ ነው፡፡ - እኔ አይገባኝም እንደዚህ ዓይነት ትንታኔ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ አልተሳተፍንም ተብሎ ነው ይህ ሁሉ ወቀሳ፡፡ - አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ እስቲ አሁን ጋናን ይዩት፡፡ ስታዲዮሞቹን እይዋቸው፡፡ እኛ አንድ ስታዲየም የለንም፡፡ እንዴት ስታዲዮም እንኳ አይኖረንም? - በአንድ ወቅት ይሰራል ተብሎ አልነበረም ወይ? - ይሰራል ተብሎ ያልተሰራ ስንት ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ቦታውን ግን ሰዎች አሳይተውኝ ነበር? - ምን ይታወቃል ነገ ደግሞ ለናይት ክለብ ማሰሪያ ይሰጥ ይሆናል፡፡ - ኢሕአዴግ ለእግር ኳስ እድገት ደንታ የለውም የምትል ትመስላለህ፡፡ - አዎን ክቡር ሚኒስትር ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ምንም ውጤት ሳይገኝ ንትርክና መጠላለፍ የበረታበት ፌደሬሽን ሆኖ ሲጓዝ ለአመታት ዝም ብሎ ማየቱ እርሶም እንዳሉት የሚበላ የሚጠጣ ስላልሆነ ደንታ የለኝም ብሎ የተወው ይመስለኛል እንጂ በሌላ ያስመዘገበውን ድል በዚህ ማስመዝገብ እንዴት ያቅተው ነበር? - ለሚበላና ለሚጠጣ፣ ለልማት ትኩረት የሚሰጥ መንግሥት መሆኑን ማመንህም ትልቅ ነገር ነው፡፡ - እሱም አሁንስ እያጠራጠረኝ መጣ፡፡ - ለምን ትጠራጠራለህ? - ክቡር ሚኒስትር የኑሮ ውድነቱ ነዋ፡፡ - አልገባኝም? - በየዕለቱ የምግብ፣ የልብስ ዋጋ እየጨመረ ነው፡፡ ትራንስፖርት ትልቅ ችግር ሆኗል፡፡ ቄጠማ ሳይቀር ዋጋ የሚጨምርበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ መንግሥት ዝም ብሎ ካየ ለሚጠጣውና ለሚበላው ትኩረት ይሰጣል ለማለት ያስቸግረኛል፡፡ ኑሮ ኮ እየከበደ ነው፡፡ - መንግሥት ምርት የሚበዛበት ፖሊሲ ያወጣል እንጂ መንግሥት ሙዝና ድንች አይሆንልህም፡፡ - ይቆጣጠር ማለቴ ነው፡፡ - ኧረግ፣ ኧረግ አንተ ግብጽ አገባ... ብራቮ.. - እኔ ካሜሮን እንዲያሸንፍ ነው የምፈልገው፡፡ ክቡር ሚኒስትር እርሶ ግን እንዴት ግብፅ እንዲያሸንፍ ይፈልጋሉ? - ግብፅ ጥሩ እየተጫወተ ስለሆነ ነዋ፡፡ - የአባይን ነገር ረሱት መሰለኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - አልገባኝም? - በአባይ ወንዝ ከግብፅ ጋር እንከራከራለን፡፡ - እሱ ሌላ ፌዴሬሽን ነው - ነው ነገር ግን... - አንተ ጨዋታው አለቀ፡፡ ቆይ ቆይ የሽልማቱ ሥነ ሥርዓት እንይ፡፡ - የእኛ ስፖርት እየከነከነኝ ነው፡፡ - ግድ የለም... በእግር ኳስ ባንበረታም በአትሌቲክስ ጠንካሮች ነን፡፡ - ክቡር ሚኒስትር እሱም ቢሆን አደጋ ላይ ነው፡፡ - የምን አደጋ? - አካሄዳችን መዳከምን እንጂ መጠናከርን አያሳይም፡፡ - ያሳያል እንጂ ኃይሌ አሸንፎ የለም? - በኦሎምፒክ አመርቂ ውጤት አላመጣንም፡፡ በኬንያው ውድድር አቋርጠን ወጥተናል፡፡ በሌሎች መድረኮችም እንደታሰበው አይደለም፡፡ - በሚባላና በሚጠጣው ላይ አተኮራችሁ እንዳትለኝ፡፡ - ፌዴሬሽኖች ራዕይ፣ እልህ፣ ሃላፊነት፣ የአገር ፍቅር ስሜት ይጎድላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እና ለቻይናው ኦሎምፒክ አልተዘጋጀንም ማለትህ ነው? - ወይ የቻይና ኧረ የአፍሪካው፡፡ - የአፍሪካ ደግሞ ምን አለ? - ክቡር ሚኒስትር የአፍሪካ አትሌቲክስ ውድድርኮ በሚያዚያ ወር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚካሄደው፡፡ - እኔ አላወቅኩም በየትኛው ሚያዚያ? - የፊታችን ሚያዚያ፡፡ - እና ተዘጋጅተናል? - ምን እንዘጋጃለን ገና ነን፡፡ ስፖርተኞቻችንም ገና የተዘጋጁ አይመስለኝም፡፡ - ወይ ግብፅ ባለፈውም ዘንድሮም አሸናፊ ሆነ አይደል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ግብፆች አሰልጣኝ ከውጭ ማስመጣት አለባት፡፡ - ክቡር ሚኒስትር የግብፅ አሰልጣኝ ግብፃዊ ነው እንዲያውም የሌሎች ናቸው አውሮፓውያን፡፡ - ግድ የለም አትጨነቅ ነገ እኛም በአንድ ነገር አሸናፊ እንሆናለን፡፡ - እሱማ በመጫወቱ አይደለም እንጂ በመመልከቱማ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሻምፒዮን ነው፡፡ - የኢትዮጵያ ሕዝብ ይከታተላል? - እንዴ ክቡር ሚኒስትር በቀደም እትዬ በቀለች ማንቸስተር ዩናይትድ እንዴት በማንቸስተር ሲቲ ተሸነፈ ብለው ከጋሼ በቀለ ጋር ተጣሉ፡፡ ይኸው ሶስት ቀናቸው አይነጋገሩም፡፡ - በል በል ነገ በጧት ሥራ አለኝ ልተኛበት፡፡ - ደህና ይደሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡ (በጧት ክቡር ሚኒስትር ወደ ቢሯቸው ይሄዳሉ፡፡ መንገድ ላይ ሾፌራቸው ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ከፍቶ የስፖርት ውይይት ይከታተላል) - ምንድን ነው የሚለው እባክህ? - የትናንትናው ጨዋታ ካሜሮን ባለማሸነፉ አናዶታል፡፡ - እና ለምን ግብፅ አሸነፈ ነው የሚለው? - የአባይ ነገር አለች አይደል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ለመሆኑ የስፖርት ስሜት አላችሁ? - እንዴት ክቡር ሚኒስትር? - ከግብፅ መማር አለብን፡፡ ጠንካራ ቡድን ነው፣ በዚህ ልናምን ይገባል፡፡ - መቼስ ብሄራዊ ስሜት ሆኖብን ነው፡፡ ጋዜጠኛው ራሱ ከፍተኛ ብሄራዊ ስሜት አለው፡፡ በዚህ የታወቀ ነው፡፡ - ምን ይላል? - አንዳንዴ ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ቡድን ጋር ስትጫወት በሬዲዮ ያስተላልፋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጎል ከሳተ ወይም ጎል ከገባበት አንደበቱ ሁሉ ይዘጋል፡፡ - እና? - ድምፁ ከተዘጋ አይ አይ... ካለ ተናዷል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነገር አያስችለውም፡፡ - እና ይኸ እውነት ጋዜጠኛ ይባላል? - ጋዜጠኛም አርበኛም ነው፡፡ - በል፣ በል እየተጠነቀቅክ ንዳ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ተመሣሣይ ስሜት የለዎትም? - እንዴት ገመትክ እባክህ? - ግብፅ አሸነፈ ካሜሮን አሸነፈ ደንታ የለዎትም፡፡ - አዎ ደንታ የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ብታሸንፍ ነው እኔ ደንታ የሚኖረኝ፡፡ - አርሰናልን ነው የሚደግፉት ወይስ ማንቸስተርን? - ምንድናቸው? - የእንግሊዝ የእግር ኳስ ቡድኖች ናቸው፡፡ - አላውቃቸውም፡፡ - ቴዲ አፍሮን፣ ጎሣዬን፣ ዘሪቱን አያውቋቸውም? - እኔ አላውቃቸውም፡፡ አጠፋሁ? ተሳሳትኩ? - አይ ሞደርን መሆን ጥሩ ነው ብዬ ነው፡፡ - ኮምፒዩተርስ ይችላሉ ክቡር ሚኒስትር? - ፀሐፊዬ ትችላለች፡፡ ይኼ በቂ ይመስለኛል፡፡ አሁንስ ሞደርን አይደለሁም? - ለነገሩ ጫካ ቆይታችሁ ይህን ማወቁ አስቸጋሪ ነው፡፡ - በል፣ በል አሁን እሱን ተወውና ቶሎ ቶሎ ንዳ፡፡ (ቢሮ ደረሱና ሚኒስትሩ ከመኪና ሲወርዱ ለሾፌሩ እርምጃ እንደወሰዱበት ነገሩት) - ከአሁን በኋላ የእኔ ሾፌር አትሆንም፡፡ የት እንደተመደብክ አስተዳዳሪውን አነጋግር፡፡ - ለምን ክቡር ሚኒስትር? - ጠባይህ መጥፎ ስለሆነ ከሾፌርነት ተነስተሃል፡፡ - የደብዳቤ ፣ የቃል ወይም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ? - እሱ የድሮ አሰራር ነው፣ የዘገየ፡፡ የአሁን አሰራር ለይት ይላል፡፡ የዘንድሮ አሰራር ሌላ ነው፡፡ - እንዴት ነው ሌላ ነው ሲሉ? - ሞደርን! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |