| አፍሪካ አህጉራችን! |
|
|
| Wednesday, 13 February 2008 | |
|
ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ የተሰበሰቡት የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች፤ “ማናቸውም ሕዝብ የራሱን የወደፊት እድል ለመወሰን መሰረታዊ መብቱ መሆኑን በማመን፣ የአፍሪካን ሕዝብ ተገቢ ፍላጎቶች ለማስገኘት ነጻነት፣ እኩልነትና ትክክለኛ ፍርድ የሰው ልጅ ክብር አስፈላጊ ግቦች መሆናቸውን በመረዳት፤ የሰው ልጅ ከሚያደርገው ጥረት ሁሉ ሕዝቦቻችን ጠቅላላ ዕድገት እንዲያገኙ የአህጉራችን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ጉልበት ለዚህ ተግባር እንዲውል ለማድረግ ያለባቸውን ሃላፊነት በመገንዘብ፤ ሕዝባችን የዘርና የወገን ልዩነትን በማስወገድ ወንድማማችነትንና አንድነትን በመፈለግ ያሳዩትን ጽኑ ምኞት በመከተል በአገሮቻችን መካከል መግባባትና መተባበርን ለመፍጠር በአንድ ዓላማ በመነሳሳት፤ ይህ ጽኑ ፍላጎት ለሰው ልጅ እድገትን የሚያስገኝ ብርቱ ኃይል እንዲሆን ለማድረግ ሰላምና ጸጥታ እንዲኖር ማስፈለጉን በማመን፤ በከባድ ትግል የተገኘውን ነጻነትና የአገሮቻችንን የግዛት አንድነትና መብት ለማረጋገጥና ለመጠበቅ እንዲሁም በልዩ ልዩ መልክ የሚቀርበውን ማናቸውንም ኒዮኮሎኒያሊዝም ለመቃወም ቁርጥ አሳብ በማድረግ፤ ለአፍሪካ ጠቅላላ የልማት ዕድገት ታጥቀን በመነሳት፤ በተባበሩት መንግሥታት ማህበር ቻርተር እንዲሁም ስለ ሰው ልጅ መሰረታዊ መብቶች መጠበቂያ የገባንበትን ቃልኪዳን በማክበርና ጽኑ መሰረት በማድረግ በመንግሥታት መካከል ሰላምና ሕብረትን ለማስገኘት በማሰብ፤ የአፍሪካ መንግሥታት ተባብረው አንድነታቸውን እንዲያፀኑና እንዲሁም ሕዞቦቻቸው ደህንነትና ብልጽግና እንዲያገኙ ለማረጋገጥ፤ በአገሮቻችን መካከል ግንኙነቶችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የጋራ ድርጅቶችን ለማጠንከርና ለማቋቋም በዚህ ስምምነት ቃል ኪዳን ገብተን ተፈራርመናል” አሉ፡፡ ቃል ኪዳን ገብተውም በተፈራረሙት ስምምነትም “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት”ን ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም አቋቋሙ፡፡ በጠቅላላ የ30 የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች መካከል አንዱና አንደኛው የኢትዮጵያው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች ስብሰባ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ስም ሆነው ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበትን ቃል ኪዳን በመፈረም ብቻ ሳይወሰኑ ይኸው ቃል ኪዳን በፓርላማ እንዲፀድቅ ተደርጎ በአስር ቀን ጊዜ ውስጥ ማለትም ግንቦት 27 ቀን 1955 ዓ.ም አዋጅ ሆኖ ወጥቷል፡፡ “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበትን ቃል ኪዳን ለማፅደቅ የወጣ አዋጅ” አማካኝነት በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተጠቀሱት ውለታዎችና ሁኔታዎችም ሁሉ ፀደቁ፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለጥርጥር ደግሞ እስከ አሁን “ለመጨረሻ” ጊዜ (ማፅደቂያው ብቻ ሳይሆን) በአዋጅ የፀደቀው ስምምነት ወይም ቃል ኪዳን ሕግ ሆኖ የወጣው ብቸኛው አለማቀፋዊ ስምምነት ይኸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቃል ኪዳኑ የተፈረመባት ቃል ኪዳኑን የፈረሙ አገሮች የተሰባሰቡበት እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ አገር ብቻ አይደለችም፡፡ የቃል ኪዳኑ መፈረምና መጽደቅ የሚመለከተውና ይኸው ስያሜና ርዕስ ያለው የቃል ኪዳኑ ድንጋጌ (አንቀጽ 24) 1) ቃል ኪዳኑ ነጻ ሆነው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ የአፍሪካ አገሮች ሁሉ ሊፈርሙት እንደሚችሉ የፈረሙትም አገሮች የእያንዳንዳቸው የሕገ መንግሥት ሥነ ሥርዓት በሚፈቅደው አኳኋን እንዲፀድቅ ማድረግ እንዳለባቸው፤ 2) ዋናው ሰነድ ቢቻል በአፍሪካ ቋንቋዎች በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ ተዘጋጅቶ በዚህ አኳኋን የተዘጋጁት ሰነዶች ሁሉ እኩል ዋጋ ያላቸው ሆነው በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ ተቀማጭ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትም የነዚህን ጽሁፎች የተረጋገጠ ትክክለኛ ግልባጭ ለአፍሪካ ነጻ መንግሥታት ሁሉ እንደሚያስተላልፍ፤ 3) ፈራሚ አገሮች ከፊርማ በኋላ የእያንዳንዳቸው የሕገመንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት በሚፈቅደው አኳኋን ቃል ኪዳኑን ካፀደቁ በኋላ የማፅደቂያ ሰነዶች በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ ተቀማጭ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትም የተባሉት ሰነዶች እያንዳንዳቸውን መቀበሉን ለፈራሚዎቹ መንግሥታት ሁሉ እንደሚያስታውቅ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቃል ኪዳኑን በሥራ ላይ መዋልና የቃል ኪዳኑን መመዝገብ የሚመለከቱት የቻርተሩ ድንጋጌዎች (አንቀጽ 25 እና 26) ከፈራሚዎቹ መንግሥታት መካከል ከሁለት ሦስተኛው የማጽደቂያ ሰነዶች የኢትዮጵያ መንግሥት እንደተቀበለ ወዲያውኑ ይህ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ እንደዋለ እንደሚቆጠር ቃል ኪዳኑም በሚገባ ከፀደቀ በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት አቅራቢነት በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በአንቀጽ 102 መሰረት በተባበሩት መንግሥታት ጽህፈት ቤት ዘንድ እንደሚመዘገብ ጨምረው ይወስናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቦታ የኢትዮጵያ ድርሻ ይህን ያህል የሚታወቅ ቻርተሩን በመፈረም ወዲያውኑም በማጽደቅ የተወሰነ ብቻ ሳይሆን ቻርተሩም (ቃል ኪዳኑም) ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰ የተወሰና የተወሳ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከላይ በተጠቀሱት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የቃል ኪዳኑ የምስረታ የመፈረምና የመጽደቅ እንዲሁም የመመዝገብ ወዘተ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት “ዋና ጽህፈት ቤት” ጭምር ነበር ማለት ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቃል ኪዳን ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም የፈረሙት የ30ዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎች በሙሉ ግን ከጥቂቶቹ የታደሉትን የየአገራቸውንና የአህጉራቸውን የፖለቲካ ታሪክ “ማታለል” ከቻሉት በስተቀር ከስልጣናቸው የወረዱት ተዋርደውና ተገልብጠው ነው፡፡ የራሳችንን የቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጨረሻ እጣ ፋንታ ምን እንደሆነ አይተናል፡፡ ይህን በግልጽና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው የአፍሪካን “የመጀመሪያ ትውልድ መሪዎች ክፋትና ጥፋት” ብቻ ሳይሆን የተተኪውንም ትውልድ እስከ አሁን ድረስ ከታሪክ መማር አልችል ያለ እዚያው ባለበት የረገጠ “ቢወቅጡት እምቦጭ” ሁኔታ ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቃል ኪዳን ከፈረሙት፣ ድርጅቱን ካቋቋሙት አገሮች መካከል የአንዳንዶቹ ስም የአሁኑ ተማሪ ትውልድ ግድሊኖረውም ሊማረውም ከሚችለው በላይ ተለዋውጧል፡፡ እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ቤኒን ዳሆሚ ነበረች፡፡ አፖርቮልታ የምትባለዋ የቃል ኪዳኑ ፈራሚ አገር ማለት የአሁኗ ቡርኪና ፋሶን ናት፡፡ የተባበረው አረብ ሪፐብሊክ የሚል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፈራሚና መስራች አገር ስታዩ ግብፅ ማለት ነውና እንዳትቸገሩ ወዘተ. ማለትን የመሰለ “ማስጠንቀቂያ” ወይም ቅድሚያ ማስታወቂያ የሚያስፈልጋቸው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሁን ታሪክ እና/ወይም ጆግራፊ የሚማሩ ተማሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ “ኢትዮጵያ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ሰርታለች አፍሪካውያን በጋራ እንዲሰባሰቡም መሰረት ጥላለች...” የሚል መግቢያና “ጥቅስ” ያለው የአፍሪካን የዋንጫ ግጥሚያ ስትከታተሉ ትሰሙት የነበረው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚነገረው የራሱ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማስታወቂያና ማስተዋወቂያ በዚያው ታሪካዊ አስተማሪ አዝናኝና አሳዋቂ የማስታወቂያ ዝግጅቱ ቀጠል አድርጎ የአፍሪካ ሕብረትን የቀድሞ ኮሚሽነር የኮናሬን የእንግሊዝኛ ንግግር ከነምስላቸው ያቀርባል፡፡ እሳቸውም /ኢትዮጲያነ ዜን ኖውን አስ አቢሲንያ፤ ወዝ ዘ ስፖክስማን ኦፍ አፍሪ ካ../ ይላሉ፡፡ ከዚያ በላይና በኋላ የሚሉት አይሰማም፡፡ ወዲያውኑና እዚያውኑ ይህንን የኮናሬን ንግግር ጠቀስኩ ተረጎምኩ የሚለው ጋዜጠኛ “በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት አቢሲንያ በሚል ተጨማሪ መጠሪያ የምትታወቀው ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ተወካይና የሕዝቦቿም ቃል አቀባይ ነበረች...” ይላል፡፡ እዚህ ትርጉም እዚህ የታሪክ ትምህርት ውስጥ ያለውን ችግር አስተካክላለሁ ትርጉሙን አርማለሁ፣ ታሪክ አቃናለሁ ብሎ መሞከር ጋንግሪን የሚያሰቃየውን ሰው ፎሮፎር አክማለሁ ከማለት የተለየ አይሆንም፡፡ ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሌላ መሰረታዊ ሰነድ እንመለስ፡፡ ድርጅቱ በአስራ ስምንተኛው የመንግሥታቱና የሀገሮች መሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከተመሰረተ ከዚያን ያህል ዓመት በኋላ ጁን 1981 የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን ተቀበለ፡፡ ይህ የሰብዓዊ መብቶች የአፍሪካ ቻርተር በሥራ ላይ ይውል ዘንድ ከአባል አገሮች መካከል ከግማሽ በላይ ብቻ የሆኑት የፈረሙትና ፈርመውም በየአገሮቻቸው ሕገመንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት በሚፈቅደው አኳኋን ያፀደቁት መሆን ይገባቸዋል፡፡ አፍሪካ ይህ የአህጉሩ የመብትና የነጻነት ሰነድ እንደ ሕግ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ መዋሉን ለመመስከር ግን እስከ ኦክቶበር 21 ቀን 1986 መጠበቅ ነበረበት፡፡ ያም ሆኖ አገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካን የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ቻርተር የተቀበለችው ከወጣ ከ15፣ ሥራ ላይ ከዋለ ከ12 ዓመት በኋላ ጁን 2/1998 (ወይም ግንቦት 25 1990 ዓ.ም) ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች የወጣው በድርጅቱ 18ኛ የመሪዎች ጉባኤ ማለትም (በኛ ዘመን አቆጣጠር በ70ዎቹ) ውስጥ በመሆኑ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት “በሌለበት” ተከሳሽ ተወቃሽ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን መንግሥት በተካው ወታደራዊው መንግሥት የስልጣን ዘመን ሌላው ቀርቶ የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ቻርተር የመጀመሪያ ረቂቅ ሰነድን አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰበሰበው ጉባኤ በ1979 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) መጨረሻ ላይ ሊመለከተው ታቅዶ የነበረው ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ስለዚህም በደርግ የሥልጣን ዘመን አልፀደቀም ተብሎ የሚታማ መንግሥት አልነበረንም፡፡ ደርግን የተካው መንግሥት ይህንን ቻርተር ለማጽደቅና የአገሪቷ ሕግ አድርጎ ለመቀበል እስከ 90 ዓ.ም (በኛ አቆጣጠር) ያለው ጊዜ ወስዶበታል፡፡ በዚያን ወቅት በወጣው አዋጅ ቁጥር 114/90 ቻርተሩን የተቀበለውም፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ዋና አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶችን የተቀበለ በመሆኑ፤ በአህጉራዊና በአለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች የኢትዮጵያ መንግሥት የሚደግፍ በመሆኑ” ከሚል መግቢያ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚያ ወዲህም የአፍሪካን ሕብረት ለማቋቋም የተደረገውን ስምምነት በአዋጅ ቁጥር 232/1993 አጽድቃለች፡፡ በ1995 ዓ.ም ደግሞ የመላ አፍሪካን ፓርላማ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የደህንነት ካውንስል ማቋቋሚያ ፕሮቶኮሎችን በአዋጅ ቁጥር 332/95 እና ቁጥር 333/95 አጽድቃለች፡፡ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ መንግሥት ለአፍሪካ ህብረት አካለት ውጤታማ ሆነው ማየት የሚፈልግ በመሆኑ፤ የመላ አፍሪካ ፓርላማ መቋቋም የአፍሪካ ህዝቦችና እነሱን ከታች አንስቶ የሚወክሉ ችግሩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ድርጅቶች በአህጉሪቱ ተጋርጠውባት ባሉት ችግሮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ውይይትና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል የታሰበ የጋራ መድረክ በመሆኑ፤ የመላ አፍሪካ ፓርላማ የተቋቋመው የአፍሪካ ህዝቦች በኢኮኖሚ ልማቱና የአፍሪካን አህጉር በማዋሃዱ ረገድ ሙሉ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማረጋገጥ በመሆኑ፤ የአፍሪካ ሕዝቦች በባህል በርዕዮተ ዓለም በዘር በሃይማኖትና በብሄር ልዩነት የማይፈጠር አንድ ትልቅ ማህበረሰብ ለመመስረት ላላቸው ትልቅ የህብረት፣ የአንድነትና የጥምረት ምኞት ድጋፍ ማድረግ አስገዳጅና አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ፤ ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችንና ሕዝባዊ ተሳትፎን ማጠናከር ዴሞክራሲያዊ ተቋማትና ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ” ነው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1995 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የመላ አፍሪካን ፓርላማ ለማቋቋም የወጣውን ፕሮቶኮል ያፀደቀው፡፡ የፓርላማውን ማቋቋሚያ እንዲሁም የአፍሪካን ህብረት የሰላምና የደህንነት ካውንስል ማቋቋሚያ ፕሮቶኮሎች ለማፅደቅ የታወጁት ሁለቱም የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው አዋጆች ሁለቱም በተመሳሳይ (ከሌላ ጊዜ በተለየ ምናልባትም ተለምዶ በማይታወቅ አለዚያም ከዚህ ቀደም እናውቀው ነበር ብለን አፋችንን ሞልተን ልንገልጸው በማይቻል አኳኋን) ማፅደቅ የሚለውን ቃል ተርጉመውታል፡፡ ማፅደቅ ማለት በሁለቱም አዋጆች መሰረት “ፕሮቶኮሉ ፀንቶ የሚገኝ ከሆነ መቀበልን ይጨምራል” ማለት ነው፡፡ ከአማርኛው ይልቅ የእንግሊዝኛው ቅጅ ግልጽና ትርጉም ያለው ነው፡፡ ራቲፊኬሽን ማለት አክሴሽንን /አክሴሽን/ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ ፕሮቶኮሉን አፀደቀች (ራቲፋይ አደረገች) ማለት ከተፈረመ በኋላ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት አፀደቀችው አጽድቃም ሥራ ላይ መዋል የሚያስችለውን የአጽዳቂ አገሮች ቁጥር ላይ አስተዋፅኦ አደረገች ማለት ነው፡፡ ተቀበለችው (አክሲድ አደረገች) ማለት ግን ከጊዜ በኋላ ፕሮቶኮሉ በቂ ቁጥር ያላቸው አገሮች አጽድቀውት ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ቆይታ ተቀበለችው ማለት ነው፡፡ አንድን ዓለማቀፋዊ ስምምነት አንድ አገር የገዛ አገሩ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት በሚፈቅደውና ዓለማቀፋዊ ሕግ በሚጠይቀው አኳኋን ለማፅደቅ/ ለመቀበል ይቻለው ዘንድ ወይም የተባለውን አለማአቀፋዊ ስምምነት ራቲፋይ እያደረገ ነው? ወይስ አክሲድ እያደረገ የሚለው ለማወቅ ይህ አገር የግድ እንደ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት (እንደ አሜሪካ የመንግሥታቱ ድርጅት) መቀመጫ መሆን የለበትም፡፡ ይህ የሆነው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመታደል ሆኖ የኢንተርኔት አቅርቦት (አክሰስ) ያለው ሁሉም ወይም ብዙው ሰው አይደለም እንጂ የየትኛውንም አለማቀፋዊ ስምምነት ሁኔታ (ስታተስ) ከዚህ አኳያ ለማወቅ አስቸጋሪ ባልሆነ ነበር፡፡ የአፍሪካ ህብረት ቋሚ የተወካዮች ኮሚቴ በዚህ ዓመት በጥር ወር አሁን ስብሰባ ላይ ላለው የሕብረቱ ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ለመረዳት እንደሚችለው ኢትዮጵያ፤ . የአፍሪካን የዲሞክራሲ የምርጫ እና የመልካም አስተዳደር ቻርተር . የአፍሪካን የወጣቶች ቻርተር . የአፍሪካን የማዳበሪያ ልማት፣ ማዕከል ማቋቋሚያ ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካን የመልሶ ማቋቋም (ተሀድሶ) ኢንስቲቲዩት ማቋቋሚያ የፈረመችው (ገና የፈረመችው) አሁን በቅርቡ ባሳለፍናቸው ሁለት ወሮች ውስጥ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት የተለያዩ አካላት ታላቁ ዘመቻና ጩኸት መንግሥታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን/ የአፍሪካ ህብረትን ስምምነቶች እንዲፈርሙ፣ እንዲያፀድቁ ወይም እንዲቀበሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አስራ አምስተኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ የ“ፊርማ ሳምንት” ማሰብና ማዘጋጀት እቅድ ሁሉ አለው፡፡ ይህ የሚያሳየው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ራሱ (የምናወራው ስለ አፍሪካ ህብረት በዚህ ተቋም ዘመን ስለወጡ ስምምነቶች አይደለም) ያሳለፋቸው ስምምነቶች አሁንም ያልፀደቁ ተቀባይ ያላገኙ አሉ ማለት ነው፡፡ አገራችን እያስተናገደችው ያለችው (ተጠናቆ ከሆነ ያስተናገደችው) የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ የዚህ ዓመት ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ የኢንዱስትሪ ልማት መሆኑ ተነግሮናል፡፡ የአፍሪካ ህብረት የመጀመሪያና ቅድሚያ የሚሰጥ “መጀመሪያ የመቀመጫየን” አጀንዳ ይኸ ነወይ? የሚል ጥያቄ ራሳቸው ተሰብስቢዎቹም ማንሳታቸው አይቀርም፡፡ ኬንያ፣ ሶማሊያ ሱዳን፣ ኮንጎ ወዘተ. የየአገሮቻቸው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቷም ችግሮች ናቸው ለነዚህ አገሮች እንዲሁም ለአህጉሩ የእርስ በርስ ብጥብጥ የሰላም መጥፋት መንስዔ ድህነት መፍትሄውም ልማት ብልጽግና የኢንዱስትሪ እድገት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሳ ችግሩን ከስር ከመሰረቱ መንቀል ዋንኛው መፍትሄ ላይ ማተኮር እንጂ እንጥፍጣፊ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ የተባለው መሰረታዊ የእድገት የልማትና የብልጽግና መፍትሄ ላይ ተስማምተናልም እንበል፡፡ የልማቱን መፍትሄ ለማምጣት የችግሩን መንስዔ ለመንቀል ግን እንኳንስ የአፍሪካ አህጉር አንድ ላይ እያንዳንዱ አገርም እንደምን አድርጎ ሕዝቡንና የተፈጥሮ ሀብቱን አዋድዶ በሕዝብና በመንግሥት በመንግሥት የሥልጣን አካላት በእርስ በርሳቸው አማካኝነት ምን ዓይነት ግንኙነት ኖሮ እንደሚሰራ ለልማት እንደሚነሳ ስምምነት መድረስ አለበት፡፡ እንዲፈረሙ፣ እንዲከበሩ እንዲተገበሩ የሚጠየቁት ሕጎችና ስምምነቶች የዚህ መግለጫዎች ድርና ማጎች ናቸው፡፡ በኬንያ የምርጫ ውጤት የተከተለው ሁከትና እልቂት ሕዝቡን ለስደት አካባቢውን ላለመረጋጋት የመላውን የአፍሪካ ዜጎች የምርጫና የዴሞክራሲ ተስፋና እምነት ላስደንጋጭ ተስፋ መቁረጥ ፀፀት በዳረገበት ወቅት ከየአገሩ ተወክለው በአፍሪካ ደረጃ ሕብረት ስለፈጠሩ የአፍሪካ ፓርላማ መናገር አይቻልም፡፡ የድህነት ቅነሳ የያንዳንዱ አገርም ሆነ የአህጉሪቱ አንዱ “ስትራቴጂ” ይዘት በአበዳሪና በተበዳሪ መካከል ሊኖር የሚገባው የዕዳ መቀነስ መሰረዝ ነው ተብሎ ከሌሎች ጋር እየተጋገዘ የሚያገለግል አቋም ሆኖ መያዙን የለመድነው፣ የተቀበልነው፣ የምናምንበት ፖሊሲ ሊሆን ይችላል፡፡ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ተባብረው ስለድህነት ቅነሳ ብቻ ሳይሆን ስለ እዳ ስረዛ ተናጋገሩ ማለት አንድ ነገር ሆኖ ከማህበርተኞች መካከል እንደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ብሩንዲ ያሉቱ ለምሳሌ የማህበርተኛነት መዋጮ ውዝፍ ዕዳ ይሰረዝልን አሉ፤ ይህም የህብረቱ አጀንዳ ሆኖ ተነሳ ማለት የህብረትና የአንድነት ምልክት የማህበርተኛነት ግዴታ መግለጫ አይሆንም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |