| “የኔና የናንተ ታሪክ” |
|
|
| Thursday, 14 February 2008 | |
ታውቁኛላችሁ፣ ሁሌም ባጠገቤ ስታልፉ “ወንድም! አስር ሳንቲም?” “እሙዬ! አስር ሳንቲም አለሽ?” የምላችሁ ነኝ፡፡ . . .አንዳንዶቻችሁ አየት አድርጋችሁ ታልፉኛላችሁ፤ አንዳንዶቻችሁ ሳንቲም ወርወር ታደርጉልኛላችሁ፡፡ አንዳንዳችሁ ደግሞ . . .እንተዋወቃለን፡፡ ዕለት በዕለት እንገናኛለን. . .አይደል?
አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የምታልፉኝስ? “የድሃ ድምጽ አይሰማም? ያልኳችሁ ለዛ ነበር፡፡ አዎን! ራሴው ነኝ፡፡ . . . ከታክሲ ስትወርዱ፣ ወይ ከፍቅረኛችሁ ጋር በምሽት ስትንሸራሸሩ፣ ትንሽ ልጅ አቅፌ፣ የሞቀ ወሬያችሁን አቋርጬ . . . “ወንድም! . . .ጋሼ! . . .የራት ሙላልኝ. . .” “እሙዬ! እርቦኛል” ያልኳችሁ . . . “የድሃ ድምጽ አይሰማም? ብዬ ያናደድኳችሁ፣ ወይም ምንም ስሜት ያልሰጠኋችሁ፣ ወይ ምናልባት ያሳዘንኳችሁ. . . ያቺ ልጅ እኔ ነኝ፣ እሷው ራሷ ነኝ፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል፣ የሴት ልጅ ግርዛት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን ለማስወገድ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤን ኤፍ ፒ ኤ) እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚጠቀስ ነው፡፡ በየዓመቱ ጥር 28 ቀን (ፌብሩዋሪ 6 ቀን) በሴቶች ላይ የሚደርሱትን ልዩ ልዩ ጥቃቶች የመቃወም በልዩ ልዩ መሰናዶ የማሰብ ዝግጅት የኢንተር አፍሪካ ልማዳዊ ድርጊቶች ኮሚቴ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያቀርባል፡፡ ዘንድሮ ዕለቱ የታሰበው ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ከመገናኛ ብዙኃን ጋር አጋርነት መፍጠር የሚል ነበር፡፡ በዓሉን ግንዛቤንና በታሪካዊ እውነታ ለማስደገፍ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ሒልተን በተዘጋጀው መሰናዶ የተባበሩት መንግስታት ሥነ ሕዝብ ፈንድ ከ”ዘመቻ በፆታዊ ጥቃት ኢትዮጵያ” ጋር በመተባበር ያሳተመው መጽሐፍ ለአደባባይ በቅቷል፡፡ መጽሐፉ በጾታ ተኮር ጥቃት ዙሪያ ያጋጠሙ እውነተኛ ታሪኮችን “የኔና የናንተ ታሪክ” በሚል በአምስት ቋንቋዎች፣ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛና በእንግሊዝኛ ታትሟል፡፡ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የተጻፈው መንደርደሪያ “ምርጫ የሌለው ምርጫ” በሚል ርእስ የልጅቷን እውነተኛ ገጠመኝ በሥነጽሁፋዊ ለዛ የቀረበበት ነው፡፡ ልጅቷ ገጠመኟን እንደሚከተለው ትቀጥላለች፡፡ ብዙ ነን፤ ምንአልባት እኔ እንኳን ትዝ ባልላችሁ አንዷ ጓደኛዬ ትዝ ትላችኋለች፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ ወይ ቀና ብላችሁ ታዩኛላችሁ፤ ወይ ሳንቲም ትሰጡናላችሁ፤ ወይ አቀርቅራችሁ ታልፋላችሁ እንጂ አንዳችሁም ስለእኛ አስባችሁ አታውቁም፡፡ ለነገሩ አልፈርድባችሁም፡፡ ስንት ሃሳብ አለባችሁ፡፡ ልክ እንደ ድሮዋ እኔ. . . .፡፡ አሁንማ ቀኑን ከመግፋት ሌላ የሚያሳስበኝ ነገር የለም፡፡ እኔም እንደ እናንተ ባለ ብዙ ሃሳብ፤ ባለ ብዙ እቅድ ነበርኩ፡፡ ያኔ . . .ገና ደብረዘይት እያለሁ ማለቴ ነው፡፡ ያኔ እናቴ ትሞታለች፣ ወታደር የነበረው አባቴ ከቤት እንደወጣ ይቀራል፡፡ ቤት ውስጥ እኔ፣ ታላቅ ወንድሜና ታናናሾቻችን እንቀራለን፡፡ ታናናሾቻችንን መንከባከብም ሆነ የቤቱን ኃላፊነት በሙሉ ተሸክሞ መኖር ከባድ ቢሆንም አላማረርኩም፤ ችዬው ነበር፡፡ በቆይታ ግን አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠመኝ፡፡ ታላቅ ወንድሜ ሌሊት ላይ በተደጋጋሚ የተኛሁበት ድረስ እየመጣ ሊደፍረኝ ይሞክር ጀመር፡፡ ስለተገዶ መደፈር በየጊዜው ሲወራ ብሰማም፤ ይህ አስነዋሪ ድርጊት እኔ ላይ ይሞከራል ብዬ ጨርሶ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ለዛውም በገዛ ወንድሜ! ይሄን ጊዜ ነው እንግዲህ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ተስፋ መቁረጥ ላይ የወደቅሁት፡፡ ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥም ወደቅኩ አይኑን ማየት አስጠላኝ! ምን የሱን ብቻ? ወንድ የሚባል ፍጡር አስጠላኝ! ቤቱን ጥዬ ወጣሁለት! ወደ አዲስ አበባ! አስረኛክፍል የደረስኩትን ትምህርቴን እቅዶቼን. . . ህይወቴን ሁሉ እርግፍ አድርጌ ይኸው እዚህ መጣሁ! ለማኝ ለመሆን ግን አልነበረም፡፡ የሰው እጅ እንዳላይ ብዙ ጥሬአለሁ አንዴ ማስቲካና ከረሜላ በማዞር፣ ሌላ ጊዜ ቆሎ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ. . . ባጭሩ ብዙ ሞክሬያለሁ፡፡ የከተማ ቀማኞች በተደጋጋሚ ጥረቴን መና አስቀሩት እንጂ፡፡ እኔም አንደኛዬን ልመናዬን ተያያዝኩት፡፡ ህይወት በጎዳናስ? ምንን ልንገራችሁ? እንደምታዩኝ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ብደፈርም፣ በዚያ ምክንያት ብታመምም ህፃን ልጅ ብታቀፍም፣ ሕይወቴን፣ ህልሜን ምኞትና እቅዴን. . . ሁሉን እርግፍ አድርጌ ብተወውም፣ ልክ አባቴን የሚመስለው ወንድሜ ያንን ሲያደርግ ከማይ. . . ሁሉን ትቼ፣ ይሄን መርጫለሁ፡፡ “ወንድም! እስኪ የምሳ ሙላልኝ. . . እሙ.. ለልጄ ዳቦ መግዣ. . . .” በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በዓለም ዙሪያ በስፋት የሚስተዋል ወንጀል መሆኑን ያወሱት ዶክተር ሞኒክ ራኮቶማላላ የዩ.ኤን.ኤፍ.ፒ.ኤ የኢትዮጵያ ተወካይ፣ ልዩ ልዩ ጾታዊ ጥቃቶች ሴቶች የሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያግዳል፣ ክብራቸው እንዲገሰስ ያደርጋል፣ በተጨማሪም ጤናቸውና ደህንነታቸው እንዲሁም የወደፊት ተስፋቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥል አስምረውበታል፡፡ የእውነተኛ ታሪኮች ስብስብ ምረቃ ላይ የተገኘችው የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗና የተባበሩት መንግሥታት የሥነሕዝብ ፈንድ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር መሠረት ደፋር ባስተላለፈችው መልዕክት በትምህርት ቤቶች፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ በሚዲያና በተለያዩ መድረኮች በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በተመለከተ ግልጽ ውይይት እየተደረገ ችግሩ የሚፈታበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብላለች፡፡ ሴቶች በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በመንገድ ላይ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ቢደርስባቸውም ከኅብረተሰቡ ይደርስብናል የሚሉት መገለል በመፍራት አደባባይ አውጥተው ለመናገር አይደፍሩም ያለችው አትሌት መሠረት በመጽሐፉ ላይ የወጡት እውነተኛ የጥቃት ታሪኮች ሴቶች የደረሰባቸው ጥቃት ገሃድ ለማውጣት መድረክ የከፈተላቸው መሆኑን ጠቁማለች፡፡ ‘የኔና የናንተ ታሪክ” እውነተኛ ታሪኮች ስብስብ በግርዛት፣ በጠለፋ፣ በወሲብ ትንኮሳ፣ በደፈራና በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ያቀናበረችው ሰላማዊት ተስፋዬ ናት፡፡ “. . . ወላጆቼ በሕፃንነቴ በሰው ስለተገደሉ ያደግሁት ከአጎቴ ጋር ነው፡፡ 11 ዓመት ሲሞላኝ ትዳር መመስረት እንዳለብኝ ተወሰነ ወዲያው ከእኔ ሦስት እጥፍ ከሚበልጠኝ ሰውዬ ጋር አብሬ እንድኖር ተደረገ. . . (የጽጌረዳ ጥፋት) (ስለ ጠለፋ) “. . . ራሴን ስቼ ነበር፣ ሊነጋጋ ሲል ነበር ራሴን ያወቅኩት ሁለት ሴቶች ተንበርክከው የሞቀ ቅቤ እያጋቱኝ ነበር፡፡ እናቱና እህቱ፡፡ ሴት ሆነው እንዴት ዝም ይላሉ? የበለጠ አዘንኩ፤ ወዲያው ግን አንድ ነገር በሐሳቤ መጣልኝ! አባቴ!” ጀግናው አባቴ ይህንን ሲሰማ ጠመንጃውን ይዞ “አካኪ ዘራፍ ልጄን!” ብሎ ሲበር መጥቶ ከዚህ ጉድ እንደሚያመጣኝ ተሰማኝ. . ዝር ያለ ነገር የለም፡፡ (ሶስቱ ምኞቶቼ) (ስለ ወሲባዊ ትንኮሳ) “. . .ውድ ማስታወሻዬ፣ ዛሬ ምን እንዳጋጠመኝ ልንገርሽ፡፡ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ጎረቤታችን ጋሽ ይርጉን መንገዱ ላይ አገኘኋቸው፡፡ መኪናቸውን አቆሙልኝ፡፡ ትምህርት ቤት ረፍዶብኝ ስለነበር ደስ ብሎኝ ገባሁ፡፡ . . .ጋሽ ይርጉ የሊዛ አባት ናቸው፡፡ ሊዛ እኔን በአንድ ዓመት አይደለም የምትበልጠኝ? ታዲያ ለእኔም እባቴ ማለት አይደሉ? ዓይን ዓይኔን እያዩ “ቆንጆ እኮ ነሽ!” አይሉኝም መሰለሽ. . .ከዛ እጃቸውን ጉልበቴ ላይ አያስቀምጡት መሰለሽ? በስንት መከራ አወረዱኝ፡፡.. (ጣጣ) “የኔና የናንተ ታሪክ” ፆታን መሠረት አድርጎ የሚፈፀም ጥቃትን በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ኅብረተሰቡ በቀላሉ ሊረዳው በሚችል መልኩ የቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመለካከትና ልዩነት በትረካዊ መልኩ እያዋዛ መልዕክቱን በቀላሉ የሚያስተላልፍ መሆኑም በምርቃው ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ የመጽሐፉ ዋና አላማ በተለይ የተጎጂዎችን ችግሮች ለኅብረተሰቡ በትረካ መልክ ማስተላለፍና ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ መታተም በፆታ ላይ መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በጥቂት የሴት ድርጅቶች ብቻ ከሚሰሩ አጠቃላይ የኅብረተሰቡ ጉዳይ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |