Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ኢህአዴግ 36 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና...
ኢህአዴግ 36 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና... Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
ኢህአዴግ 36 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ መምህራን አባሎቹ መሆናቸውን ገለፀ

ኢህአዴግ በአሁኑ ጊዜ 36 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ከመምህራን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑትና ከ4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች አባላቱ መሆናቸውን አቶ መለስ ዜናዊ ገለፁ፡፡
የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ይህንን ያሳወቁት የካቲት 11 የህውሓት ምስረታ ቀን አስመልክተው ከትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

እንደ አቶ መለስ አባባል፣ ኢህአዴግ በ1993 ዓ.ም ተሃድሶ ከማካሄዱ በፊት አጠቃላይ የአባላቱ ቁጥር 700 ሺህ ብቻ የነበሩ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ግን ከፍ ያለ ቁጥር አባላት መመልመል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከተሃድሶ በፊት የነበሩት የድርጅቱ አባላት በተለያየ ምክንያት የደኸዩና በትግል የተሰው ታጋዮች ቤተሰቦች ብቻ እንደነበሩ ገልፀው፣ ከተሃድሶ በኋላ ይህ የአባልነት መመልመያ መስፈርት መቀየሩን ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል በገጠር አካባቢ የነበሩት የድርጅቱ አባላት ቁጥራቸው ውሱን ከመሆኑ ባሻገር ችግር እንደነበረባቸውና፣ ጉዳዩ በተሃድሶ ወቅት ለውይይት ቀርቦ የኢህአዴግ አባል መሆን ያለባቸው “የድርጅቱን የልማት ስትራቴጂ ተጠቅመው በኑሮአቸው ላይ በሁሉም ዙሪያ ለውጥ ያመጡና ለሌሎች አርአያ የሆኑ አርሶ አደሮች” ብቻ እንዲሆኑ መወሰኑ አቶ መለስ አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል በተደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ፣ በድርጅቱ መስመር ላይ ስልጠና ተሰጥቶዋቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሪነት እየተጫወቱ ያሉት የድርጅቱ አባል አርሶ አደሮች ቁጥር ከ4 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ መለስ አገላለፅ በተደረገው እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ምክንያት ገጠራማው የአገሪቱ ክፍል በመልካም አስተዳደርና በልማት ከከተማው ጋር ሲነፃፀር ሁለት እጥፍ ቀድሞ ሄዷል፡፡

በከተሞች አካባቢ ድርጅቱ ከተሃድሶ በፊት ሊጠቀስ የሚችል አደረጃጀትና አቅም እንዳልነበረው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ “ከተሃድሶ በኋላ በከተሞች በተለይም በትምህርት ቤቶች አካባቢ በተደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ”. እስከ 80 በመቶ መምህራኖች የድርጅቱ አባል አድርገናል” ብለዋል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርስቲና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበሩት የድርጅቱ አባላት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ እንደነበሩ ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሱቲዎች ብቻ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎች የድርጅቱ አባል መሆናቸው ገልፀዋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሃድሶው ዘመቻ መሪ አባላት በማፍራት ላይ ያለመ እንደሆነና ይህ በመልካም አስተዳደርና በልማት ዙሪየዎች ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቡን ገልፀው፣ በሚቀጥሉት 3 እና 4 ዓመታት ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ለአፍሪካ ህብረት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት በአውሮፕላን ተዘዋውረው በከተማው ያለውን መንፈስና የልማት እንቅስቃሴዎች መመልከታቸው እንዲሁም ሌሎች እንደተራ ሰው በእግር ተዘዋውረው በከተማው ምን እየተሰራ እንደሆነ መታዘባቸውን ጠቁመው፣ አብዛኛዎቻቸው “ይሄ አገር ድንገተኛ በሆነ ጊዜ ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ እየተቀየረ ነው” ብለው እንደመሰከሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

 ሙሉ ዝርዝሩን በፖለቲካ ገፅ ይመልከቱ፡፡

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >