| የተወካዮች ምክር ቤት አዳዲስ... |
|
|
| Sunday, 17 February 2008 | |
|
የተወካዮች ምክር ቤት አዳዲስ መመሪያዎችን እያወጣ ነው
የተወካዮች ምክር ቤት በዘንድሮው የሥራ ዘመኑ 3ዐ የሚጠጉ መመሪያዎችን እንደሚያወጣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለፁ፡፡ ከትናንት ወዲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንዳስታወቁት መመሪያዎቹ የሚወጡት በሥራ ላይ ያለውን ምክር ቤት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ አብዛኞቹ የምክር ቤቱ ድንጋጌዎቹ ጥቅል በመሆናቸው በአሰራር ላይ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን የጠቆሙት አፈ ጉባዔው የሚወጡት መመሪያዎች የምክር ቤቱ አባላት ድንጋጌዎቹን በሚጠቀሙበት ጊዜ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚረዷቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የምክር ቤቱን አሰራር ይበልጥ አሳታፊ እንደሚያደርገውና ግልፅነትንም እንደሚያላብስ አመልክተዋል፡፡ አፈጉባዔው እንዳሉት የጥያቄ አቀራረብን በሚመለከት ዝርዝር መመሪያዎች ወጥተዋል፡፡ በኘሬዚዳንቱ ንግግር ላይ በሚደረግ ሞሽን ኦፍ ታንክስ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች በሚቀርቡ ጥያቄዎችና በሞሽን አቀራረብም ዙሪያ የተለያዩ መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ምክር ቤቱ እያዘጋጃቸው ያሉት መመሪያዎች ዝርዝር በመሆናቸው ሥራውን ለመስራት የህግ ባለሙያዎችና የፓርላማ ልምድ ያላቸው ሰዎች ማስፈለጋቸውን አምባሳደር ተሾመ ተናግረዋል፡፡ ፓርላማው ለእረፍት ከተዘጋ ከአንድ ሳምንት በኋላ የ2000 ዓመት የሥራ ዘመን አፈፃፀምን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት አፈጉባዔው ባለፉት አራት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን ዘርዝረዋል፡፡ ምክር ቤቱ እስከአሁን ድረስ ባካሄዳቸው 16 መደበኛ ስብሰባዎች 22 ረቂቅ ህጐች መቅረባቸውንና ከነዚህ ውስጥ አሥራ ሁለቱ ፀድቀዋል፡፡ “የተወሰኑ የቅንጅት የፓርላማ ተመራጮች በፓርላማ ውስጥ በፓርላማ ውስጥ በቡድን እንዳይደራጁ የተከለከሉበት ምክንያት ምንድነው?” በሚል ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደሩ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የቅንጅት አባላት ወደ ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ የሚል ጥያቄ ባነሱበት ወቅት አብዛኞቹ የቅንጅት ተመራጮች ወደ ፓርላማ የገቡት በራሳቸው ውሳኔ እንደነበር ያስታወሱት አፈጉባዔው በጊዜው ከነበረው ችግር አኳያ ተመራጮቹ ተደራጅተው እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ አምባሳደር ተሾመ እንደሚሉት ቅንጅት የሚለው ፓርቲ ከምርጫ በኋላ የተቋቋመ ቢሆንም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማመዛዘን መግባባት ላይ ስለተደረሰ ሚያዚያ 1998 የተቋቋመው ቅንጅት የፖርላማ ቡድን አቋቁመው ለመንቀሳቀስ የጠየቁ 14 የቅንጅት ተመራጮችም በጋራ እንዲደራጁ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ አዲሱ የምክር ቤት ደንብ ተሻሽሎ በቀረበበትም ወቅት ደንቡ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የነበረውን አደረጃጀት አቻችለን እንሂድ በሚል መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡ በአገሪቱ የሚደረገው የዴሞክራሲ ግንባታ ፓርቲን መሰረት ያላደረገ ከሆነ አስቸጋሪ እንደሚሆን የጠቆሙት አፈ ጉባዔው ተሻሽሎ የቀረበው የምክር ቤት ደንብ የፓርላማ አባላት በተመረጡበት ፓርቲ እንዲንቀሳቀሱ እድል መስጠቱን ገልፀዋል፡፡ የተሻሻለው ደንብ ከወጣ በኋላ በቡድን ለመደራጀት የጠየቁት የቅንጅት ተመራጮች ፈቃድ የተከለከሉትም በምክር ቤቱ አሠራር ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡ “ከአንዱ ፓርቲ ወደ ሌላው ፓርቲ በየጊዜው እየዘለሉ መሄድ የፓርቲውን ፖለቲካና የምክር ቤቱ ሥራ የተረጋጋ እንዳይሆን ያደርጋል” ያሉት አምባሳደር ተሾመ እያንዳንዱ የፓርላማ ቡድን ከሌላ የፓርላማ ቡድን ጋር አለመግባባት በፈጠረ ቁጥር የፓርላማ ቡድን ላቋቁም ብሎ መሄድ ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በፓርቲ ኘሮግራምና ዓላማ ተወዳድረው ምክር ቤት ከገቡ በኋላ ከወከላቸው ፓርቲ የሚወጡ ተመራጮችም የፓርቲያቸውን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የምክር ቤቱንም አሰራር እንደሚያበላሹ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር ለአቶ አየለ ጫሚሶ መሰጠት እንዳለበት የሚገልፅ ደብዳቤ ከምርጫ ቦርድ የደረሳቸው መሆኑን አምባሳደር ተሾመ አስታውቀዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ካስተላለፈም በኋላ “የአመራር ውሳኔው ትክክል አይደለም፡፡ አቶ አየለ በሚመሩት ቅንጅት ተደራጅተን አንንቀሳቀስም” የሚል የ41 ሰዎች አባላት ፊርማ ያለበት ጥያቄ የቀረበላቸው መሆኑን የጠቆሙት አፈጉባዔው ጉዳዩ ጥናትና ውሳኔ ስለሚፈልግ በጥንቃቄ እየታየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በኃይሌ ሙሉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |