| “የሐብሊ አመራር አምባገነናዊ ሆኗል” |
|
|
| Sunday, 17 February 2008 | |
|
አቶ አብዱልጀዋድ አህመድ
ሐዲድ የአመራር ለውጥ አደረገ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) አመራር አምባገነናዊ እንዲሁም ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሆኗል ሲሉ የሊጉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብዱልጀዋድ አህመድ ዩኒስ ለሪፖርተር ገለፁ፡፡ የሐረሪ ዲሞክራሲዊ ድርጅት (ሐዲድ) በበኩሉ የአመራር ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ሊጉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የካቲት 1 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲባረሩ መደረጉ ህግን የጣሰ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱልጀዋድ፤ “የሊጉ አመራር አምባገነናዊና ኢ-ዴሞክራሲዊ ሆኗል” ብለዋል፡፡ አቶ አብዱልጀዋድ በሊጉ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልን ሊያስወግድ እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡ በዚህም የሥራ አስፈፃሚው ህጋዊ አካሄድና እርከን የጣሰ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ አብዱልጀዋድ ገለፃ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከፓርቲው ሊወገድ የሚችለው በሊጉ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ብቻ ነው፡፡ የሥራ አስፈፃሚው ለማዕከላዊ ኮሚቴ በጥፋተኝነት ያቀረበው አባል በ2/3ኛ ድምፅ ከኮሚቴው አባልነት ሊታገድ እንደሚችልና በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ከአባልነት ሊወገድ የሚችልበት አካሄድ መኖሩን አቶ አብዱልጃዋድ የሊጉን መተዳደሪያ ደንብ አጣቅሰው ገልፀዋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የሊጉ ሥራ አስፈፃሚ ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያገዳቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም “የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ውሳኔ ህገወጥ ነው፤ አመራሩም አምባገነናዊ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡ አቶ አብዱልጀዋድ የሊጉ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ “አፍራሽ ተልእኮ ያለው የሐዲድ ድርጅት አባል ሆነሀል” በሚል ሰበብ ያባረራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ “እኔ የሊጉ ታማኝ አባል ነኝ” የሚሉት አቶ አብዱልጀዋድ “ከሊጉ ማፈንገጤንና የሌላ ድርጅት አባል ወይንም ደጋፊ ስለመሆኔ ማስረጃ ካለ ይቅረብ” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በማያያዝም “ሊጉ ከመተዳደሪያ ደንብ ውጪ የሚሰራ ከሆነ የማንኛውም ድርጅት አባል የመሆን መብት አለኝ” ሲሉ አቶ አብዱልጀዋድ አመልክተዋል፡፡ ውሳኔው ሲወሰን ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል የተባሉትን የሊጉ የአዲስ አበባ ሊቀመንበርና የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳሚያ ዘከርያ ጉዳዩን አስመልክቶ “አቶ አብዱልጀዋድ የተባረሩት በራሳቸው ጥፋት ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የሊጉ የስራ አስፈፃሚ ውሳኔ ህግን መሠረት ያደረገና የተለመደ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ሳሚያ የሊጉ ስራ አስፈፃሚ ከዚህ ቀደም ጥፋተኛ ያላቸውን አባላት ጠቅላላ ጉባዔ ከመጠራቱ በፊት ያባረረ መሆኑን አስታውሰው፤ “እንደዚህ ዓይነት አባል ተሸክመን አንቆይም” በማለት ተናግረዋል፡፡ ስብሰባው በተካሄደበት ወቅት ፣ወ/ሮ ሳሚያን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ አባላት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፣ ለሚለው “የውሸት አሉባልታ” ሲሉ ወ/ሮ ሳሚያ አጣጥለውታል፡፡ በሌላ ዜና በቅርቡ ሰርተፊኬት ያገኘው የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ሐዲድ) የስድስት ወር የሥራ ሂደቱን ከገመገመ በኋላ በቀድሞው ኘሬዚደንት ምትክ አቶ አብዲ ሰብሪን ጊዜያዊ ኘሬዚደንት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ጊዜያዊ ኘሬዚደንት ሆነው የተሾሙት አቶ አብዲ ለሪፖርተር እንደገለፁት የኃላፊነት ሽግሽግ የተደረገው ከስድስት ወር በኋላ ለሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና ለሀረሪ ህዝብ የተሻለ አማራጭ ይዞ ለመቅረብ ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ድርጅቱን ይጠቅማሉ ተብለው የታመነባቸው ሴቶች የሥራ አስፈፃሚ ቦታውን እንዲይዙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |