Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የወርቅ በሽታም አይምሬ ነው!
የወርቅ በሽታም አይምሬ ነው! Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
Imageበወርቅ ዙሪያ እየታየ ያለው ዝርፊያ፣ ማጭበርበርና ወንጀል እጅግ የሚዘገንንና የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን የሚቆጭና የሚያደናግጥ ነው፡፡ በርግጥ ሌላውም ወንጀል ይህም ወንጀል ነው፡፡ ከወንጀልም ወንጀል ይመረጣል ወይ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገሩ ከወንጀል ወንጀል የመምረጥ ጉዳይ ሳይሆን እጥፍ ድርብ፣ አደገኛ፣ ፀረ አገርና ፀረ ሕዝብ ወንጀል መሆኑ አፅንኦት ሊሰጠው ስለሚገባ ነው፡፡
ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ባሌስትራ፣ ወርቅ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ራሱን የቻለ ወንጀል ሆኖ በዓለም ፊት ኢትዮጵያን መሳቂያ ማድረጉ ደግሞ ራሱን የቻለ ነገር ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን እንዲቆጣጠሩ የተቀጠሩት የመንግሥት አካላትም ለመቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተው ወደ ውጭ የሚላከውን ባሌስትራ ወርቅ ነው ብለው አፅድቀውና ፈርመው መላካቸው አገርን መሳቂያ የሚያደርግ ነው፡፡ መንግሥት የለም ወይ የሚያሰኝ ነው፡፡

ልብ እንበል፡፡ በተመሳሳይና አሳሳች ዕቃ አይደለም አገር የተበደለችው፡፡ በወርቅና በባሌስትራ መካከል ባለ ልዩነት ነው፡፡ ተቋሞቹም አገርን መሳቂያ እያደረጉ ናቸው፡፡

የወርቅ በሽታው አይምሬ እየሆነ ነው፡፡ በስስትና ስግብግብነት አገር ብትቃጠልና ብትወድም ደንታ የሌለው አውሬነት ነው፡፡ ተራና ቀላል አደጋ ሳይሆን አገርን ለሞት የሚዳርግ አይምሬ በሽታ ነው፡፡

መዛመቱም አይምሬ ያሰኘዋል፡፡ ቀደም ብሎ ወደ ጅቡቲ ሊላክ የሚገባው ወርቅ በማስወጣት ብዙ ክስና እስር ያስከተለ ጉዳይ ነው፡፡ በኋላ ደግሞ ወርቁ አለ ብሄራዊ ባንክ ገብቷል ተባለ፡፡ ገባ ተብሎ ያውም በፖሊስ ገቢ ተደርጓል የተባለው ወርቅ የውሸት ወርቅ ነው እየተባለ ነው፡፡ ባሌስትራ ባይሆንም ወርቅ የመሰለ አርቴፊሻል ነገር ነው ተብሏል፡፡ አርባ አንድ ኪሎ ግራም ያክል ወርቅ የተጭበረበረ ወርቅ ሆኖ ባንክ ቤት ያውም ብሄራዊ ባንክ ገብቶ ከተገኘ የወርቅ በሽታ አይምሬ ሆኗል፤ ቢባል ይገርማልን?

በቅርቡ ደግሞ ኬንያ የተያዘ ወርቅ መኖሩ ይሰማል፣ እውነት ከሆነም አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ይገመታል ይባላል፡፡ በማጭበርበር ድንበር ሊሻገር የታሰበ ወርቅ ነበር፡፡ ሰዎች እንዴት ያሉ ቢሆኑ ነው ይህን ያህል ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ያገር ወርቅ ሊያሸሹ የቋመጡት?

መንግሥት ይህን የወርቅ በሽታ በልዩ ጥንቃቄና ዓይን ሊመረምረው ይገባል፡፡ ማን አጭበረበረ፣ ሰረቀ የሚለውን ጥያቄ ለፍርድ ቤት እንተወው፡፡ ማንም ይሁን ማን፣ አገር መሳቂያ እየሆነች ነው፡፡ መሳቂያ እየሆነች ያለችውም በአቶ እገሌ ብቻ ሳይሆን እንትና በተባሉ የመንግሥት ተቋም ጭምር ነው፡፡ አደጋውም እዚህ ላይ ነው፡፡

ኢኮኖሚው አደጋም ያስከትላል፣ መንግሥት ተቋሞች ምን ይመስላሉ? የሚል ፖለቲካዊ ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ጥያቄ አግባብ ነው የሕዝብ ሞራል ይነካል፤ አገር ያዋረዳል፡፡ ድግምግሞሹ ደግሞ ተዛማች በሽታ መሆኑንና አይምሬ መሆኑን ያሳያል፡፡

መንግሥት ልዩ ጥናትና ምርመራ አካሂዶ ስለሁኔታው ግልፅ ሪፖርት ሊያቀርብ ይገባል፡፡ የፍርድ ቤት ሂደት እንዳይደናቀፍ ከተባለም በኋላ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ፍርዱ በአስቸኳይ በልዩ ሁኔታ ይታይና ይቀላጠፍም ይጠናቀቅ፡፡

የወርቁ ልዩ አሳሳቢነት ፈጠነ እንጅ የሙስና ነገር በአጠቃላይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ የሚገርሙ ሁኔታዎችም እየተፈጠሩ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን የውስጥ ኦዲተር የኦዲት ሪፖርቱን አቀረበ፡፡ ሪፖርቱን ማኔጅመንትና ቦርድ አፀደቀው፡፡ በሕግ መታየት አለበትም፤ ተባለ፡፡ እግድም ክስም ወዲህ ወዲያ ሲባል ይታያል፡፡ ነገር ግን አካሄዱ የሚያምር አይደለም፡፡ በሃጥአን መካከል ለይቶ መላዕክት ለማድረግና ለማስመሰል እንቅስቃሴ ይታያል፡፡

ክሱ እውን እንዲሆን መጠየቅ ያለባቸው ግለሰቦች እንዳይጠየቁ ለማድረግ ሽርጉድ እየተስተዋለ ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ቆራጥ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤት ነፃ ሆኖ ጉዳዩን እንዲመረምርና ወንጀለኛን ተጠያቂ እንዲያደርግ ሊያበረታታ ይገባል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ይህ በቢልዮን የሚቆጠር የሃገር ሃብት የባከነበትን ሙስና እንደ ብረት ጠንክሮ ዳር ሊያደርሰው ይገባል፡፡

በቴሌ ጉዳይ “የቀለጠው መንደርም” ከመሆን አልፎ “የቀለጠው አገር” ሊባል የሚበቃ ሆኗል፡፡

የቴሌ ጉዳይ የሙስናን አይምሬነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ነገር ግን የሙስና ችግር ያለው በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች ለራሳቸው ተሰባስበው የፈጠሩዋቸው ማህበራትም በሙስና እየተዘፈቁ ናቸው፡፡ ይህም ስለሆነ ነው ከመቶ በላይ የሚቆጠሩ ማህበራት ሊታገዱ የቻሉት፡፡ በጎ ነገር ይሰራሉ፤ ተብለው የተቋቋሙት ማዕከላት “የስኳር ማህበር” የሚል ስም እየወጣላቸው ነው፡፡

መንግሥት መልካም አስተዳደር ለማስፈን ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በጉባኤው መልካም አስተዳደር አሰፍናለሁ፤ ብሎ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን በየክፍለ ከተማው ወደ ሕዝቡ እየወረደም በዚህ ጉዳይ ቃል ገብቷል፡፡ ውጤቱ ግን አልተሻሻለም፡፡ እልህ የገባ የሙስና ወገንተኛ ቡድን እየተበራከተ መጥቷል፡፡

ጉዳዩ አሳሳቢ ነው፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ቆራጥ እርምጃ ይውሰድ፡፡ በስኳርና በበርበሬ ዋጋ መጨመር ከዝርፊያና ከማጭበርበር ጋር አያይዘን መናደዳችን ሳይበርድ ወርቅ መጣና ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጠረብን፡፡ በሽታው አደገኛ ነው! አይምሬ ነው፡፡ መድሃኒት በአስቸኳይ!
 
< Prev   Next >