Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow “መንግሥታት የፈለጉትን ይበሉ፣ ሁለቱም...
“መንግሥታት የፈለጉትን ይበሉ፣ ሁለቱም... Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
Image“መንግሥታት የፈለጉትን ይበሉ፣ ሁለቱም ሕዝቦች ወንድማማችነታቸውን ሊያድሱ ይገባል”
አቶ መለስ ዜናዊ

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ የኤርትራን ስደተኞች አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ስደተኞቹ በአገር ውስጥ ትምህርት የሚያገኙበት ወይም ወደ ውጭ የሚሄዱበት መንገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ማመቻቸቱን ገልፀዋል፡፡ “የጦርነት በራችን ዘግተን የሰላም መስኮት ክፍት አድርገናል” ያሉት አቶ መለስ፣ ሁለቱም ሕዝቦች ያለምንም ቅድመ ሆኔታ ወንድማማችነታቸው እንዲያድሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ መለስ የህወሓት የምስረታ ቀን የካቲት 11 ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት፣ የሁለቱም ሕዝቦች የወደፊት እድል አስመልክተው፣ “መንግሥታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፣ ይጠፋሉም፤ የማይጠፋና የማይተካ ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ሁለቱም ህዝቦች ደግሞ ወንድማማች ሆነው መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡ ሕዝቦቹ ከነዚህ መንግሥታት በፊት የነበሩ፣ ከነዚህ መንግሥታት በኋላም የሚኖሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በህዝቦቹ መካከል መቃቃርና ፀብ እንዳይፈጠር፣ መከታተልና መቆጣጠር ያስፈልጋል” በማለት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጀመርና ግንኙነታቸውን እንዲጠናከር ፍላጎታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሁለቱም አገሮች መካከል የተደረገው ጦርነት የቆጫቸው አቶ መለስ፣ “ያ ጦርነት የፈጠረው ጠባሳ ይበቃል፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ደረጃ እንዳይሸጋገር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ትኩረታችን ይሄ መሆን አለበት” በማለት ከወዲሁ በሁለቱም አገሮች መካከል ጦርነት የማይታሰብ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

“ሕዝቦቹ ወንድማማች መሆናቸውን አውቀው፣ መንግሥታት ምን ይበሉ ምንም፣ የፈለጉትን ያድርጉ ሁለቱም ህዝቦች ወደ ኋላ መለስ ብለው እንደ ሕዝብ ማሰብ መቻልና ወንድማማችነታቸውንና ጉርብትናቸው ማሳደስ ይኖርባቸዋል” ብለዋል አቶ መለስ፡፡

ኤርትራ ውስጥ ካለው አሰቃቂ ሥርዓት ሕይወታቸውን ለመታደግ ወደ አጎራባች አገራት የሚሰደዱ (በተለይ ወጣት) ኤርትራውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ሸሽተው የሚገቡ እስከ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በትግራይ ክልል የሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ሽመልባ ውስጥ ብቻ ከ15ሺ በላይ ኤርትራውያን እንደነበሩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘገባ ማወቅ ተችሏል፡፡

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወር ጀምሮ ችግሩን እየተባባሰ በመምጣቱ በየወሩ ከ600 በላይ ወጣቶች ሸሽተው እየመጡ እንደሆነ ዋልታና የመሳሳሉ የዜና ማዕከላት ዘግበዋል፡፡ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመምጣት እንዲሁም የስደተኞቹ ፍላጎት የተለያየ መሆንና የኢትዮጵያ ዓቅም ማነስ ምክንያት ቀደም ሲል ስደተኞቹ ችግር ላይ እንደነበሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ለስደተኞቹ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱና ችግሩ መቀነሱን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይናገራሉ፡፡

“የእኛ ምርጫ የኤርትራ ወጣቶች (ወታደሮችም ሆኑ ሲቪሎች) በሃገራቸው ውስጥ ከቤተሰባቸው ጋር በሰላም ቢኖሩ ነበር፡፡ ወደየ ቦታው (ውጪ) እንዲሰደዱና እንዲፈናቀሉ ረየኢትዮጵያ ሕዝብም የኢትዮጵያ መንግሥትም ፍላጎት አይደለምሪ፡፡ በመሰረቱ ግን በአገራችን ውስጥ መኖር አልቻልንም፣ መኖር ተቸግረናል ብለው ከመጡ እንደ ወንድሞቻችንና ጎረቤታችን ልናያቸው ይገባል፡፡ አቅማችን የፈቀደውን ያህልም እናግዛቸዋለን” በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ለስደተኞቹ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ግልፅ አድርገዋል፡፡ የአገሪቱ ዓቅም የፈቀደውን ያህል በስደተኞቹ ካምፕ የሚገኙ ኤርትራውያን መንግሥት በየጊዜው በማሻሻል አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ መለስ አባባል ለስደተኞቹ ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ መንግሥት ሶስት መንገዶች ተጠቅሟል፡፡ የመጀመሪያው ትምህርታቸውን አቋርጠው የመጡ ወደ ትምህርት እንዲገቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተሰብ ያላቸውም (ከፈለጉ) በነፃነት እንዲኖሩና እንዲማሩ የተደረገ ሲሆን፣ ውጭ ቤተሰብ ያሉዋቸውን እንዲወስዱዋቸው ፍቃደኞች ከሆኑ ያለአንዳች መስተጓጎል እንዲከናወን መንግሥት ሁኔታውን አመቻችቶላቸዋል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚገኙ ስደተኞች እዚህም ሆነ ውጭ ቤተሰብ የሌላቸውና በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ከፍቶባቸው የሚኖሩ ኤርትራውያን የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ወስደው እንዲያኖሩዋች የኢትዮጵያ መንግሥት ላቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አብራርተዋል፡፡ ይህ ጥረት በየወቅቱ እየተሻሻለ የሚሄድ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

“ከስደተኞቹ አብዛኛዎቹ ወጣቶችና ልጆች በመሆናቸው ይኸ ለጋ እድሜያቸው በካምፕ ከፍቷቸው ከሚያሳልፉት ውጭ መሄድ የሚችሉ በአስኳይ እንዲሄዱ፣ መማር የሚችሉ ደግሞ እዚህ እንዲማሩ የቻልነውን ሁሉ ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ቀደም ሲል አንድ አንድ ምሁራን ስደተኞቹ ለወደፊቱ የሁለቱም ህዝቦች ዕድል ድልድይ ሆነው እንደሚያገለግሉ ጠቁመው አያያዛቸው እንዲሻሻል አስተያየት መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞቹ አያያዝ ተሞክሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ በብዙዎች ዘንድ የሚያስመሰግን መሆኑን እየተገለፀ ነው፡፡ የህዝቦቹ አንድነትና ወንድምነትም ሊታደስ የሚችለው ከዚህ ጀምሮ በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እንዲህ እያለ አንድ አንድ ምሁራንና አስተያየት ሰጪዎች በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሻዕቢያ መንግሥት ከፍተኛ ስቃይና ኢሰብዓዊ አያያዝ ስር እንደሆነ ታውቆ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ መንቀሳቀስ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአገር ውጭ በተለይ በአረብ አገር ለሚገኙ ዜጎቹ የሚሰጠውን ትኩረት አናሳ መሆኑ ሲያስወቅሰው ቆይቷል፡፡

ኤርትራን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መለስ፣ “የኤርትራ የውስጥ ጉዳይ አይመለከተንም፣ የኤርትራ ጉዳይ የሚመለከተን ሰላማችን የሚዘርግ ከሆነ ብቻ ነው” በማለት የኤርትራ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ የኤርትራውያን ጉዳይና መብት ብቻ እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስለ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ትኩረትና ስለ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ፕሮፖጋንዳዎች አስመልክተው፣ “ከተሳካለት ይለፍልፍ፣ ሻዕቢያ የኤርትራ መንግሥትና ነው የሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ፣ ወይስ የጅቡቲ መንግሥት ነው?” በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ በጥያቄ መልሰውታል፡፡

የድንበሩን ጉዳይ በተመለከተ የህግደፍን (ሻዕብያ) መንገድ ምንም ይሁን ምንም የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱ የፀና አቋም እንደሚከተል ገልጸዋል፡፡ “ግልጽ ስትራቴጂ ልንከተል ይገባል” ያሉት አቶ መለስ “ግልፅ ስትራቴጂ”. ከአሁን በኋላ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የሚያዳማ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም” በማለት ሁለቱም ሕዝቦች ያለፈውን ታሪክ ትተው ተደጋግፈው መኖር እንዲችሉ በመካከላቸው ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከማድረግ ውጪ አማራጭ እንደሌለ አስገንዝበዋል፡፡

የድንበሩንም ጉዳይ በዚህ መስመር እንደሚያዩት ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ “በድንበሩ እያደረ የሚቃጠል የተዳፈነ እሳት ትተን አንሄድም” በማለት ሰላማዊ የሆነው ውይይት በማድረግ የሁለቱም አገሮች አጠቃላይ ግንኙነት መሻሻል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

“ይህ ህግደፍ ይቀበለው አይቀበለው፣ ሁለቱም ህዝቦች የሚቀበሉትና የሚፈልጉት መስመር በመሆኑ ኃያል መስመር ነው” ብለዋል፡፡

“ባለፈው ጦርነት ተቆሳስለናል፡፡ በእሱ ይብቃ” ያሉት አቶ መለስ ከአሁን በኋላ ጦርነት የሚባል ነገር ስሙ እንዳይነሳ አጥብቀው ገልፀዋል፡፡

“ይህ የሰላም መስመር እስከተከተልን ድረስ አያስጨንቀንም፣ የሰላም መንገድ አስቀምጠናል”. የሰላም መስኮቶች መክፈት አንድ ነገር ሆኖ የጦርነት መስኮቶች መዝጋት ደግሞ ሌላ ነገር ነው” ብለዋል አቶ መለስ፡፡

ኢትዮጵያ በሚሊንየሙ ያመጣችው ተቀባይነት እና ለውጥ እንዳለ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ በአፍሪካ የኢትዮጵያ ስዕልና ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ከድሮም ቢሆን ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ነፃነትና ሰላም ከፍተኛ ሚና ማበርከቷ አስታውሰው ስሟ የገነነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“ኢትዮጵያ እየተለወጠች ነች፣ ትናንትና የምናዝንላትና የምናስብላት የነበረች አገር ከወዲሁ የምናስብላት ሳትሆን የምንኮራባት ሆናለች” የሚል ስሜት በአፍሪካ ህብረት መሪዎች መፈጠሩ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

መሪዎቹ፣ ኢትዮጵያ ከድህነት እየወጣችና ወደ አዲስ የህዳሴ መስመር እየተሸጋገረች መሆኗን ተገንዝበው ደስታቸውን ገልፀውላቸው እንደሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >