Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Monday
Sep 08th
Home arrow Sections arrow የዲሞክራሲ ትክል ድንጋይ በትምህርት ቤቶች
የዲሞክራሲ ትክል ድንጋይ በትምህርት ቤቶች Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከኢኒሽየቲቭ አፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር “የተማሪዎች መማክርትን ማጠናከር” በሚል ርዕስ አገር አቀፍ አውደ ጥናት ጥር 3ዐ እና የካቲት 1 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቃሊቲ በሚገኘው በክርስቲያን በጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ማሰልጠኛ ማዕከል አካሂደዋል፡፡
በሁለቱ ቀን አውደ ጥናት በርካታ የጥናት ወረቀቶች የቀረቡና ጥልቅ ውይይት የተካሄደ ሲሆን “በትምህርት ቤቶች ዲሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንፃር የተማሪዎች መማክርት ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ በአቶ ማርቆስ ታደሰ የተዘጋጀው አንዱ ነው፡፡

ኢኒሽየቲቭ አፍሪካ ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጋር በመሆን የተማሪዎች መማክርትን የማጠናከር ኘሮጀክት በመተግበር ላይ መሆናቸውን አቶ ማርቆስ ጠቁመው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ህብረት እንዲመሰርቱና እንዲያጠናክሩ አዲስ መስመር ለመክፈት ያለመ ያሉት ኘሮጀክት አጠቃላይ አላማ የወጣቶች ህገ-መንግሥታዊ መብቶች በአግባቡ እንዲተገበሩ ለማበረታታት፣ ዲሞክራሲያዊ የተማሪዎች አመራርን ለማጠናከር እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዓላማውን ከማሳካት አኳያ የሚጠበቅባቸውን ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ነው፡፡

ጠንካራ እና ሰላማዊ የሆነ የተማሪዎች ህብረትን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማቋቋም ኃላፊነት የሚሰማው፣ በህግ የሚተዳደር፣ በራሱ የሚተማመን እና ራዕይ ያለውን ወጣት የማሳደግ እና የማበልፀግ ሥራን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ የሚያወሱት አቶ ማርቆስ “ውጤታማ የተማሪዎች መማክርት መኖር በተማሪዎች እና በትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች መካከል የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ በተጨማሪ የወጣቶችን ውሳኔ አሰጣጥ እና አመራር እንቅስቃሴ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የወጣቱን አቅም መገንባት የዚህን ትውልድም ሆነ የቀጣዩን ትውልድ ማኀበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ህይወት ለማሳደግ ይጠቅማል” ሲሉም ያክላሉ፡፡

አቶ ማርቆስ አጉላር ጄ የተባሉ ደራሲ “አንድ ልጅ ዲሞክራሲን ሊማር የሚችለው በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በቀጣይም በማህበረሰብ ደረጃ ባለው ተግባራዊ ተሳትፎ ነው” ማለታቸውን ጠቅሰው የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብን አስተሳሰቦች በንድፈ ሀሳብ በማስተማር ብቻ ዲሞክራሲያው ህብረተሰብን ለመገንባት ማሰብ አይቻልም ይላሉ፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች በየትምህርት ቤታቸው በሚደራጁ የተማሪዎች ህብረት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ልናለማምዳቸው ይገባል፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ዲሞክራሲዊ ባህልን ለመፍጠር ተማሪዎችን ስለ ዲሞክራሲ ማስተማር ብቻ ሳይሆን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ማሳተፍ የግድ ይላል እንደ አቶ ማርቆስ እምነት፡፡

ፀሐፊው በአገራችን የትምህርት ስርዓት እየተሰጠ ያለው የስነ ዜጋ እና የስነ ምግባር ትምህርት ተማሪዎች ዲሞክራሲዊ ሂደቶችን እና እሴቶችን እንዲተገብሩ ማበረታታት እንዲሁም ተማሪዎች ውስብስብ በሆኑ ማህበራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲወያዩ በመጋበዝ በህብረተሰባቸው ህይወት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲደርጉ በቂ እድል መሰጠት አለበት ይላሉ፡፡

ጥናት አቅራቢው ለራሳቸው ህይወትና ለሚኖሩበት ማህበረሰብ መካከል ኃላፊነት ሊወስዱ የሚችሉ ዜጎችን መፍጠር እንዴት ይቻላል? ብለው ጠይቀው ኃላፊነትን የሚሸከም ትውልድ ለማዘጋጀት እንዲችሉ ተማሪዎች ራሳቸውን፣ የእድሜ አቻዎቻቸውን እና አጠቃላይ ትምህርት ቤታቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል አጠቃላይ ስልት በመቀየስ እንደሆነ መልስ ይሰጣሉ፡፡

አቶ ማርቆስ ተማሪውን ማህበረሰብ የሚወክል አካል ዲሞክራሲዊ በሆነ መንገድ መምረጡ፤ ተማሪዎች እንደ የትምህርት ቤት ዩኒፎርም፣ የትምህርት ቤት ህጎች እና ደንቦች ባሉ ጉዳዮች ላይ በተማሪዎች በመማክርቶቻቸው በኩል ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ለዲሞክራሲ መበልፀግ መነሻ ሃሳብ ነው፡፡

ትምህርት ቤቶች በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ተቻችሎ አብሮ መስራትን፣ በግለሰቦች እና ቡድኖች መካከል መከባበርን፣ ለሌሎች አስተያቶች ክብርን መስጠትና ሰው ሁሉ እኩል የሆነ የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመፃፍ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶች እንዳለው ማስተማር እና በተግባርም ማለማመድ እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ ማርቆስ በትምህርት ቤት አመራር ውስጥ የተማሪዎች ተሳትፎ ከፍ ባለ ቁጥር የትምህርት ጥራት ያድጋል፣ የተማሪዎች የትምህርት ስኬታማነትም እንደሚያድግ ጥናቶች ያመለክታሉ ብለዋል፡፡

ሀርበርሲ የተባሉት ደራሲ “የፖለቲካ ባህልን የሚፈጥሩ እና የዲሞክራሲ ዋልታ የሆኑ እሴቶች፣ ክሂሎች እና ባህሪያት በተፈጥሮ የሚወረሱ ሳይሆኑ ሰዎች በህብረተሰባዊ ህይወት ውስጥ የሚማሩት በመሆኑ ትምህርት ቤቶች ሰፊ ሚና ሊጫወቱ ይገባል” ማለታቸውን ጠቅሰው የሚነሱ ግጭቶችን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሚፈቱበት እና ከአካላዊ ቅጣቶች ይልቅ በሰላማዊ ውይይቶች፣ በመቻቻል እና በመከባበር መፋታት በመቻላቸው ልክ ውጤታማነታቸው ያመዝናል ብለዋል፡፡

በአሜሪካ አገር በኬንታኪ በሚገኙ 310 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዴት መሳተፍ እንደሚችሉ ለመለየት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከተገኙት በርካታ አካሄዶች መካከል ተማሪዎቹ በትምህርት አስተዳደር፣ በትምህርት ቤት ስርዓተ ትምህርት፣ በትምህርት ቤት ውስጥ መልካም ግንኙነቶችን እና ድጋፍን በማበረታታት፣ በመማር ማስተማር ሂደት፣ በትምህርት ቤት የፖሊሲ ዝግጅት አስተዋፅኦ ማድረግ፣ የተጓዳኝ ትምህርት እንቅስቃሴ፣ ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተማሪዎቹ ያላቸውን ተሳትፎ ለዲሞክራሲዊ ባህል መበልፀግ ጉልህ ሚና መጫወቱን አቶ ማርቆስ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ብልጭ ያለው በተማሪው እንቅስቃሴ ሲሆን መልሶ ድምጥማጡ የጠፋውም በተማሪው እንቅስቃሴ ነው፡፡ ያለፈውን ተማሪ መራሽ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ድክመትም ሆነ ጥንካሬ ባለመከለሳችን ዛሬም ለሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመሪነት ኃላፊነት የተሰማቸው ተማሪዎች ግጭት ፈጥረው ትኩረት የሳቡበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ በርካታ ነው፡፡ ይህን የተማሪዎቹ አዝማሚያ በመጠቀም ግጭቱን የፖለቲካ ዓላማቸው ግብዓት ያደረጉት ኃይሎች መኖራቸውም አልቀረም፡፡

ትምህርት ቤቶች ከሃይማኖትና ከፖለቲካ የተደራጀ እንቅስቃሴ የታቀቡ መሆናቸው በህግ የተደነገገ ቢሆንም እሴቶቹ ሊዳብሩ የሚገባቸው ትክክለኛ ቦታዎች ግን ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተለይ ወጣቶች ዲሞክራሲያዊ ጨዋታን ለመረዳት ጉጉት የሚያሳድሩበት የመጀመሪያ ወቅት ከመሆኑም በላይ ነገሮችን በተሳሳተ መልኩ ከተረዱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡም ሆነ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡ እንዲሁም በሥራ ዓለም ለሚይዙት ፖለቲካዊ አቋም መሠረታዊ ናቸው፡፡

ነገሮችን ካለፈ ልምድ አንፃር አጥብቆ መያዝና አኩራፊነት ይቅር ያለማለት ልምድ በተንሰራፋበት ሀገር ወጣቶች በሁለተኛ ደረጃ የዲሞክራሲ መገለጫ የሆኑ ነገሮችን እየተገበሩ እንዲለማመዱ በዚያውም የነገሮችን መጥፎና ጥሩ ጎኖች በተግባራዊ ህይወት እየፈተኑ መኖርን እንዲለማመዱ እድል እንዲሰጣቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርም ሆነ ኢኒሽየቲቭ አፍሪካ እያደረጉ ያሉት ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ ያልተበከሉ ንፁህ ወጣቶች ያለፈውን የሶሻሊስት ኢትዮጵያ የተረት ተረት ልምዶችን በልጆቻቸው አእምሮ ላይ ለመጫን ከሚሞከሩ ያለፈው ትውልድ አባላት ተላቀው የአዲሲቱን ኢትዮጵያ በራሳቸው የህይወት ተሞክሮ መሠረትነት ያለፈውን ደግሞ በታሪክነቱ መጥፎና ጥሩውን ከልሶ የሚይዝ በራስ መተማመኑ የጎለበተ በስነ ምግባር የታነፀ፣ የሥራ ፍቅሩና ለለውጥ ያለው ተነሳሽነትም ከፍተኛ የሆነ እንዲሆን መንግሥትም ድጋፍ ሊሰጥ ይገባል፡፡

መብቱን የሚጠይቅ፣ ግዴታዎቹን የሚወጣ፣ ተፈጥሯዊ የሆነ አካሄድን እንጂ ማስመሰልንና ይሉኝታን የሚፀየፍ፣ ለማጭበርበርና ለሙስና ጥላቻ ያደረበት ወጣት ያፈራች ሀገር እንዳታድግ ማን ይይዛታል? በተማሪዎች መማክርት ደረጃውን የጠበቀ ዲሞክራሲን በተግባር ያየና የተገነዘበ ወጣትስ በቅንጅት፣ ህብረት፣ ኤደአፓ መድህን፣ ኦብኮ፣ ኦህኮ፣ ኦፌዲን፣ ኢህአዴግ . . . ሲታቀፍ ራሱን ላልጠራና በውዥንብር ለተሞላ የፖለቲካ ሂደት አሳልፎ ሰጥቶ በአውላላ ሀሳብ እንዴትስ ዥዋ ዥዌ ይጫወታል?

በሰለሞን ጎሹ
 
< Prev   Next >