| ለዘለቄታዊ የመሬት አጠቃቀም ድጋፍ ተጠየቀ |
|
|
| Sunday, 17 February 2008 | |
ዘለቄታዊ ለሆነ የመሬት አጠቃቀም ከለጋሾች 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቢገኝም ዘርፉ ከሚፈልገው ኢንቨስትመንት አንፃር በቂ ስላልሆነ እገዛው በእጥፍ እንዲጨምር ተጠየቀ፡፡የዘለቄታዊ የመሬት አጠቃቀም ሀገራዊ ፕሮግራምን ለመግለፅ ባለፈው ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2000 ዓ.ም በጀርመን ሐውስ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮ-ጀርመን ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም ለተሻለ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር አንድሪያ ባሐም እንደተናገሩት፣ ዘለቄታዊ የመሬት አጠቃቀም ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ የሆነ የፖሊሲ አካባቢ፣ ግልጽና አመቺ የሆነ አሰራር አስፈላጊ ነው፡፡ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም ሆነ የዘርፉን አቅም ለመጠቀም የመሬት መራቆት ችግር እየፈጠረ መሆኑንና በየዓመቱ ከ30ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚራቆት፣ እስከአሁን ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መጎዳቱ ተገል”ል፡፡ የመሬት መራቆት ችግርን ለመፍታት የተቀናጀና ተመሳሳይነት ያለው ፕሮግራም ለመዘርጋት ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግ ለዚህም በለጋሾች፣ ከመንግሥት ተቋማትና ከሚመለከታቸው ልዩ ልዩ አካላት ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር እንድሪያ ገልፀዋል፡፡ ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቀም ፕግራም በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር፣ በአለም ባንክ፣ በጀርመን የልማትና ተራድኦ ድርጅት፣ በአለም የእርሻና የምርምር ድርጅትና ሌሎች ድርጅቶች ጥምረት የተመሠረተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከ177 የውኃ ተፋሰሶች 8500 ሄክታር መሬት መልሶ ለመቋቋም አቅዷል፡፡ በፕሮግራሙ ከ1.4 ሚሊዮን ሔክታር በላይ አካባቢ መልሶ ለማልማት መታቀዱና በዚሁ መሰረት በተመረጡ 24 ወረዳዎች በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ በፕሮግራሙ የመሬት ሠርተፊኬት አሰጣጥና ቁጥጥር፣ ለማህበረሰቡ መረጃ መስጠት፣ የመሬት ሕግና የሕግ ከለላ እና የመንግሥት ፖሊሲና ፕሮግራም ለመሬት አጠቃቀም መሠረታዊ ሂደቶች መሆናቸው ተገል”ል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ በመሬት አጠባበቅ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ዘላቂነታቸውን፣ ያላቸውን ጥራትና ለወደፊት የሚኖራቸውን ለውጥ ከማጥናት ይልቅ በቁጥር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ዶ/ር አንደሪያ ተናግረዋል፡፡ የዝቅተኛ አመራሮች ያላቸውን ተጠያቂነት፣ የዘርፉ አጥኚዎች ቴክኖሎጂውን ለሕብረተሰቡ የሚያስተላልፉበት አሠራር፣ በጋራ የመስራት ተነሳሽነት፣ በመሥሪያ ቤቶች መካከል ያለ ትስስርና በስራ ላይ የሚሰጡ ስልጠናዎችና የስልጠና ጥራት ችግር መኖሩ የተገለፀ ሲሆን፣ የመሬት አጠባበቅ ካለው ተፈጥሯዊ ባህርይ አንፃር የልማት ባለሙያዎችና የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት፣ የሕዝብ የለጋሾች ፍላጎት ልዩነትና የለጋሾ እገዛ በሚፈለገው ጊዜ አለመገኘት ችግር ተገል”ል፡፡ ለጋሾች የሚሰጡት እገዛ ወጥነት እንዲኖረው የተጠየቀ ሲሆን፣ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባልዳበረ ደረጃ እንደሚገኝና በመንግሥት አብዛኛው በመሬት አመራር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተገል”ል፡፡ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አህመድ ናስር እንደገለፁት፣ ዘለቄታዊ የሆነ የመሬት አጠቃቀም የሁሉም ዲሲፒሊን ጥምረት የሚጠይቅ በመሆኑ የባለሙያዎች ተነሳሽነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመሬት አጠቃቀም የመሬትን ደህንነት መጠበቅ የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር የመሬት አጠቃቀም የአፈር ልማትና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ስለሺ ጌታሁን በበኩላቸው በመሬት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አሰጣጥና በተፋሰስ አመራር በተመረጡ አካባቢዎች የተገኘው ውጤት መልካም ጅምር መሆኑን ተናግረውይህን በሁሉም ደረጃ ለማዳረስ የለጋሾች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አሠራሮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ የተፈጥሮ ሐብት በረዥም ጊዜ ከሚኖረው ለውጥ አንፃር ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት እንደሆነባቸው አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ የመሬት አጠቃቀምን ለማስተካከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ገንዘብ ፈጣሪ መሆናቸው የገበሬዎችን አቅም እንደሚያሳድግ ገልፀው የሚደረጉትንም እንቅስቃሴዎች ታእማኝነትና ዘለቄታ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡ ገበሬዎች የአመራረት ዘይቤያቸውን እንዲቀይሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲቀበሉና በመሬት ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አስፈላጊነትንም ገልፀዋል፡፡ በኢኮኖሚና በግብርና፣ በሕዝብና የግል ዘርፎች መካከል ያለው ትስስር ደካማ መሆኑ ያለውን ሐብት በተገቢው ቦታ ላይ ለማዋል እንቅፋት መሆኑ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡ ለጋሾችና የግል ባለሐብቶች በዘርፉ የሚደረጉትን የምርምር ስራዎች በቀላሉ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ ሥራ ላይ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል፡፡ በቤዛዊት ሥዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |