| የዋጋ ንረቱ ከርሮ ከርሮ እንዳይበጠስ |
|
|
| Sunday, 17 February 2008 | |
|
ከሩሃማ በላይ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተንተርሶ በረቡዕ ጥር 21 ቀን 2000 ዓ.ም በኢኮኖሚ ገጽ ስር የወጣው ጽሁፍ ለምሰጠው አስተያየት መንደርደሪያዬ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መሄድና መንግሥትም ድጎማ የማድረግ አቅም የለኝም ማለቱ ዛሬ በሚሊዮን በሚቆጠር ካፒታል ለሚንቀሳቀሱትና እስከ 25 ሺህ ብር የሚያወጣ ሶፋ ለሚገዙት ገበሬዎቻችንና ንግግራቸው ሁሉ በሚሊዮን ለሆነ በጣት ለሚቆጠሩት የንግድ ሰዎቻችን ምንም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ የነዳጅ ጭማሪው ያስከተለው የሸቀጦች፣ የጥራጥሬ እህሎችና የትራንስፖርት ዋጋ ንረት በቅጡ የቆጠቆጠውና እየገዘገዘው ያለው የአገሪቱን አብዛኛውን ደሃ ገበሬና የሕብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ለምን የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል ወይም መጨመር የለበትም የሚል ድርቅ ያለ አቋም የለኝም፡፡ ላነሳ የምፈልገው ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እንደአስፈላጊነቱ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ ሕብረተሰቡ በሌላ መልኩ ሊደጎም የሚችልበት መንገድ ሊታይ ያልቻለበትን ጉዳይ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መደረግ ከጀመረበት እለት ጀምሮ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ምክንያት በማድረግ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን እቀጣለሁ እያለ ሲያስፈራራና ሲዝት ቆይቷል፡፡ ሆኖም ከትንሽ እስከ ትልቅ በሚባሉ የምግብም ሆነ ማንኛውም አይነት ምርትና ግብዓት ላይ እስከ እጥፍ ድረስ ዋጋ ሲጨምር እዚህ ነው የሚባል ያየነውና የሰማነው እርምጃ አልተወሰደም፡፡ አብዛኞቹ ሸቀጦችም ከነበራቸው ዋጋ ከሳንቲም ደረጃ እስከ እጥፍ ሲጨምሩ የሚመለከተው አካል እንዳላየና እንዳልሰማ ሆኖ ሲያልፍ ቆይቷል፡፡ በየሰበብ አስባቡ በምርቶች ላይ ዋጋ መጨመሩ ሁኔታው ሁሉ መረን ለቆ ጠያቂም ተጠያቂም የሌለበት መፈንጫ መሆኑ መቆጣጠር የሚገባውን አካል በእጅጉ የሚያስወቅሰው ነው፡፡ እንኳን የነዳጅ ዋጋ ጨምሮና ምክንያት ተገኝቶ አይደለም ህብረተሰቡ ምንም መረጃ ሳይኖረውና ምክንያቱን ሳያውቀው በቀናት ልዩነት በእያንዳንዱ ምርት ላይ ዋጋ ሲጨምር የሕዝቡ ጉዳይ ይመለከተኛል ብሎ መንግሥት ዋጋ ሲያረጋጋም ሆነ አለአግባብ እየናረ ለመጣው የዋጋ ንረት መፍትሄ ሲያበጅ አልታየም፡፡ የዋጋ ንረቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያሳይ ነው ብሎ መልስ ከመስጠት ውጭ፡፡ መንግሥት በማንኛውም ዘርፍ ላይ የዋጋ ንረት ሊያስከትል የሚችለውን ነዳጅ መደጎም ከአቅሜ በላይ ሆኗል በሚልበት ሰዓትም ከትንሹ እስከ ትልቁ ነጋዴ ዋጋ ብትጨምር ዋ ብሎ ማሳሰቢያ መስጠቱ በራሱ መፍትሄ አያመጣም፡፡ መንግሥት እንደመንግሥትነቱ በድጎማ ያልደረሰለትን ደሃ ሕብረተሰብስ ነጋዴው ደጉሞ ሊያኖረው ይችላል ወይ? ለአምራቹም ሆነ ለአከፋፋዩ የተለየ ድጎማ ተደርጎለታል ወይ? በቂ ምርት አለን ወይ? ገበያ ላይ ወጥቶስ የፈለጉትን ምርት አወዳድሮና መርጦ ለመግዛት የሚያስችል ሁኔታ ተመቻችቷል ወይ? እነዚህ ሁሉ ባልተመቻቹበትና ገበሬው በቅጡ በማይደጎምበት ሁኔታ የነዳጅን ዋጋ እየጨመሩ መሄዱ በሃብታሙና በደሃው መካከል ልዩነትን ማስፋቱ ብቻ ሳይሆን ትንሽ ገቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በችጋር መቅጣት ነው፡፡ የገበሬውን አቅም ለማጠናከርና ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማድረስ ተነስቻለሁ የሚለው መንግሥታችን አብዛኛው ደሃ ገበሬ ለኩራዙ የሚጠቀምበትን የኪሮሲን ዋጋ በሊትር ከ4 ብር 03 ሳንቲም ወደ 5 ብር ከ75 ሲያደርሰው የታዛቢ ያለህ የሚያሰኝ ነው፡፡ መንግሥት ከነዳጅ ምርቶች አብዛኛው ደሃ ሕብረተሰብ የሚጠቀምበትን ኪሮሲን በተለየ መልኩ መደጎምስ አቅቶት ነው ወይስ? አስተያየታቸውን የሰጡት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወልዳይ አመሃ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ሕብረተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኝ ድጎማ መስጠትና ፍላጎትን እንዲቀንስ ማድረግ እንደ አማራጭ ሊወሰድ እንደሚችል፣ ድጎማ መስጠት ግን ካለው የመንግሥት አቅም ጋር የማይቻል መሆኑን እንዲሁም የነዳጅ ፍላጎትን በአጭር ጊዜ መቀነስ አስቸጋሪ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ድጎማ መስጠት የሚለው መንግሥት አቅም የለኝም ከማለቱ አንፃር ውድቅ የሆነ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ፍላጎትን መቀነስ ባሉት ጉዳይ ግን ጥያቄ አለኝ? ፍላጎትን መቀነስ ማለት በራሱ ድፍን ያለ አመላለስ ነው፡፡ ዛሬ የአብዛኛው ደሃ ሕብረተሰብ ፍላጎት መዝናናት ሳይሆን በልቶ ማደር ነው፡፡ በልቶ ማደር ሲባል ያሻውን አማርጦ ማለትም አይደለም፡፡ ነፍሱን ሊያቆይለት የሚችል ምግብ ነው፡፡ የነዳጅ ፍላጎትን ለመቀነስ ደግሞ የተመቻቸ አማራጭ ሃይል ያስፈልጋል፡፡ በቂ የአማራጭ ሃይል አቅርቦት አለን ወይ የሚለው አንዱ ትልቁ ጥያቄ ሆኖ፡፡ የነዳጅ አጠቃቀም ፍላጎትን ለመቀነስ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ሶላር ወይም ባዮ ጋዝ የመሳሰሉትን የመጠቀም አማራጮች በአገራችን እዚህ ግባ ባይባሉም እንደ አማራጭ የሚጠቀሙ አገሮች አሉ፡፡ የድፍድፍ ዘይት ዋጋ በአለማቀፍ ገበያ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱ አብዛኞቹን በነዳጅ ማስመጣት ላይ የተመረኮዙ የአፍሪካ አገራት ከነዳጅ ውጭ ሌላ አማራጭ ሃይሎችን የሚጠቀሙበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ የሚያስገድድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከቅርብ አመታት ወዲህ የአፍሪካ አገራት እያስመዘገቡ ያሉትን የኢኮኖሚ እድገት አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል፡፡ የድፍድፍ ዘይት ዋጋ በ2004 በበርሜል ከ40 ዶላር በታች የነበረ ሲሆን በ2006 ወደ 70 ዶላር እንዲሁም ባለንበት በ2008፣ 92 ዶላር ደርሷል፡፡ የዘርፉ ኤክስፐርቶች እንደሚሉት ወደፊትም ካለው የነዳጅ ፍላጎት አንፃር ዋጋው እያሻቀበ ይሄዳል፡፡ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መሄድ ነዳጅ ለሚልኩ የአፍሪካ አገራት ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ ነዳጅ ለሚያስመጡት ቀሪዎቹ 42 የአፍሪካ አገራት ደግሞ ከባድ ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በአለም ገበያ መጨመሩና መንግሥታትም በየአገራቸው ጭማሪ ማድረጋቸው ቀጥታ ተጎጂ የሚያደርገው አብዛኛውን ተጠቃሚ ህብረተሰብ ነው፡፡ በተለይ በምግቦች፣ በትራንስፖርትና መሰረታዊ በሆኑ ምርቶች ላይ የሚያስከትለው የዋጋ ንረት አብዛኛውን ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ ከሚመከሩ የአማራጭ ሃይሎች መካከል የሃይደሮ ኤሌክትሪክ ሃይልን መጠቀም አንዱ ቢሆንም እንደ አማራጭ ለመጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት ከፍተኛ ገንዘብና ጠንካራና እቅድን መዘርጋት የሚጠይቅ በመሆኑ ለአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ከባድ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ኤሌክትሪክን በተመለከተ እንደ አማራጭ ልንጠቀምበት የምንችልበት ደረጃ ላይ ነን ወይ? ከሚመለከተው አካል መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡ በአገሪቱ ያለው የኤሌክትሪክ ሽፋንስ? የሕዝቡ አቅምስ? አንድ የመንግሥት ሰራተኛ ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ክፍያውን በመፍራት ሸሚዙን ሳይተኩስ በሚወጣበት በአሁኑ ጊዜ ኤሌክትሪክን እንደ አማራጭ የሚጠቀምበት ሁኔታ ይኖራል ወይ? ዶ/ር ወልዳይ እንዳሉት ይህ በአጭር ጊዜ የሚሆን አይደለም፡፡ ከሕዝቡ ፍላጎት መጨመር፣ ከኑሮ መናርና፣ ከገቢ ማነስም ደሃው ሕብረተሰቡ ራሱን ከኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት በሚርቅበት ሁኔታ፣ እንዴት አመለካከት በአሰርት አመታትም መሳካቱ ያጠራጥራል፡፡ የማገዶ እንጨት ለመጠቀም የሚያስችል ክምችት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ብዝሃ ህይወትን ከመጠበቅ፣ የአየር ብክለትንና መዛባትን ከመቆጣጠር አንፃር እንጨትን እንደ አማራጭ ለማንሳት አንችልም፡፡ የሶላር ኢነርጂ (የፀሀይ ሃይልን) እንደ አማራጭ መጠቀም ነዳጅ የማይፈልግና ከአየር ብክለትም ነፃ ከመሆኑ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገራትም የፀሐይ ሃይልን መጠቀሙ የተሻለ አማራጭ ይሆናል፡፡ በአገራችን በተለይ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር በብዛት በሌለበት የገጠሪቷ ክፍል ለመብራት፣ ለስልክና መጠነኛ ሃይል ለሚጠይቁ ስራዎች እየዋለ ይገኛል፡፡ አፍሪካዊቷን ናሚቢያን የወሰድን እንደሆነ ደግሞ ከ1 እስከ 2 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን የምትጠቀመው ከፀሐይና ከንፋስ ሃይል ነው፡፡ በአገሪቱም ከፀሐይና ከንፋስ የሚገኘውን ሃይል ለማሳደግ መንግሥት የዘርፉን ፕሮጀክቶች ለመደጎም እየሰራ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ከፀሐይ የሚገኝ ሃይልን እንደ አማራጭ ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾና አጠናክሮ ወደተግባር መግባቱ በሕዝቡ ላይ የተጫነውን የኑሮ ውድነት በመጠኑም ቢሆን ያቃልላል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ነዳጅ የሚያስመጡ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች በአገራቸው ነዳጅ ለማውጣት የውጭ ኩባንያዎች በመጋበዝ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ሲሳካላቸው ከውጭ የሚያስመጡትን የነዳጅ መጠን ለመቀነስና ዋጋ ለማረጋጋት ያስችላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን በአለም ገበያ ያለው የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ከሄደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ደሃ አገራትና ሕዝቦች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ይሄዳሉ፡፡ የሕብረተሰቡ የመግዛት አቅም መዳከም፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ማዝገም ብሎም መውደቅ እንዲሁም የድህነት መስፋፋት ይከተላል፡፡ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በምርቶች በተለይ በትራንስፖርትና በምግብ እህሎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር መንግሥት ጠንቅቆና ቀድሞ ያውቀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ የመንግሥት ድክመት የምለው ከ5 አመት በፊትም በአመት አንዴ ይመረት የነበረ የሰብል አይነት ዘንድሮም በተመሣሣይ ሁኔታ ሲመረት ለውጥ አለማድረጉ፣ የሕዝቡ ፍላጎት ሲጨምር እጥረቱን ለመሙላት አመርቂ ስራ አለመስራቱ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የማንኛውም ሸቀጥ ዋጋ እየናረ ሲሄድ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያለማምጣቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የመሣሠሉ የደሃ አገራት መንግሥታትም ከጋና መንግሥት ትምህርት በመውሰድ ህብረተሰባቸውን በሌሎች ዘርፎች መደጎም፣ አማራጭ የሃይል ምንጮችን ማበልፀግ እንዲሁም የዋጋ ውድነትን ማረጋጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ድህነቱና ችግሩ እየከፋ ሲሄድ በየአምስት አመቱ የሚመጣው ብሄራዊ ምርጫ እንደ ኬንያው ምርጫ፣ ፖለቲካዊነቱ ቀርቶ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ብሶት ማራገፊያ ይሆናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |