Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ሸማች ተጠንቀቅ
ሸማች ተጠንቀቅ Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
(በመላኩ ደምሴ)

ከሁለት ሳምንታት በፊት በዚሁ ጋዜጣ “የሳምንቱ ገጠመኝ” አምድ ላይ ለሠርግ ዝግጅት ስለቀረበ የካርቶን ኬክ ጉዳይ ጽፌ ነበር፡፡ ጉዳዩ ከገጠመኝ ባለፈ እኛ ሸማቾች ከዘመኑ ነጣቂዎች እንዴት ራሳችንን መጠበቅ እንደሚኖርብን በማሰብ የዘመኑን የዲኰር (የቤት፣ የአዳራሽ እና የሙሽራ መኪና ማስጌጥ) ሥራን በተመለተ ከደረሰብን የማጭበርበር ተግባር ጋር እያገናዘብኩ አወጋችኋለሁ፡፡
ያለንበት ዘመን ሰዎች ገንዘብ ካላቸው የፈለጉትን በምርጫቸው መሠረት ያሻቸውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ለመሞሸር የሚፈልጉ ከሚበላውና ከሚጠጣው በተጨማሪ እጅግ የሚያሳስባቸውና የሚጨነቁበት ነገር ቢኖር በዲኰር ድርጅቶች የሚደረገው ዝግጅት ነው፡፡ የሙሽራ እና የሚዜ መኪኖችን ከማስጌጥ በተጨማሪ የሠርጉ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበትን የሆቴል አዳራሽ ወይም መናፈሻ የማሳመር ኃላፊነት የሚጣለው በእነዚሁ የሙያው ባለቤቶች ነን በሚሉት ላይ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እና በሀገሪቱ የክልል ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ እየበዙ ያሉት እነዚህ የዲኰር ድርጅቶች አቅማቸውና የመሥራት ችሎታቸው የተለያየ ቢሆንም፣ ሁሉንም እንደ አቅሙ ለማስተናገድ በራቸውን ወለል አድርገው ከፍተው ደንበኛን ይጠብቃሉ፡፡ በዚህ ሙያ ላይ ለበርካታ ዓመታት በቅንነት ደንበኞችን ሲያስተናግዱ የቆዩ እንዳሉ ሁሉ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ግን በአቋራጭ ለመክበር ያቆበቆቡ ወረበሎችም ሙያውን እየተቀላቀሉት ነው፡፡

ጉዳይ ይኖርዎትና ወደ ተለያዩ የዲኰር አገልግሎት ወደሚሰጡ ድርጅቶች ይሄዳሉ፡፡ በሃቀኝነት የሚሠሩትም አጭበርባሪዎችም መጀመሪያ የሚያቀርቡልዎት ከዚህ በፊት የሰሯቸውን ሥራዎች ወይም ከተለያዩ ቦታዎች የሰበሰቧቸውን የፎቶ አልበሞች ነው፡፡ በሥራው ላይ እውቅና ያተረፉና መልካም ዝና ያላቸው በራስ መተማመን የራሳቸውን ሥራዎች በፎቶ አልበም ከማቅረብ በተጨማሪ ወደፊት የሚያዘጋጁዋቸውን ሥራዎች በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱላቸው ይጋብዛሉ፡፡ አጭበርባሪዎቹ ከየትም የቃረሟቸውን ፎቶዎች እንደራሳቸው አድርገው ሊያሳዩዎትም ይሞክራሉ፡፡

ጥር 17 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የተከናወነውን የእህታችንን ሠርግ የዲኰር ሥራ እንዲሰራ በ5”500 ብር የተዋዋልነውን አቶ በኃይሉን ያገኘነው የገነት ሆቴልን አዳራሽ ከነ ምግብ ዝግጅቱ ከተከራየን በኋላ ከሆቴሉ ሰዎች በተሰጠን ጥቆማ ነበር፡፡ እድሜው በለጋ የወጣትነት አፍላ ላይ የሚገኘውና በዚሁ እድሜው የመኪና ባለቤት መሆን የቻለው ግለሰብ ከተሸከማቸው አልበሞች በተጨማሪ እኛ ሳናውቅ ሌሎች የሚሠሩትን ሥራ እንደራሱ እያደረገ የተለያዩ አዳራሾችን አስጐብኝቶናል፡፡ በተቀጣሪነት ከተሠማሩ የሌላ የዲኰር ድርጅት ጓደኞቹ ጋር እየተሻረከ እንደራሱ ያሳየንን ሥራዎች በማመን ነበር ለዲኰር ሥራ 5”500 ብር፣ ኬክ እንዲያቀርብ 2”200 ብር እንዲሁም የተለያዩ ቀለማት ላላቸው ናኘኪኖች 1”200 ብር የከፈልነው፡፡ ይህንን ሁሉ ሥራ ሰጥተነው ተገቢውን ዋጋ (ከቀብዱ የተረፈውን) ሠርጉ ሣምንት ሲቀረው እንድናጠናቅቅ ነገረን፡፡ እኛም ሥራችንን በተገቢው መንገድ እንዲያጠናቅቅልን አደራ ጣልንበት፡፡ ክፍያውም ሙሉ በሙሉ አጠናቅቀን፡፡

የሠርጉ ዕለት አዳራሹን ከጠበቅነው በታች በመናኛ ነገሮች አዥጐርጉሮታል፡፡ በውላችን መሠረት መቅረብ የነበረበት የተፈጥሮ አበባ በግማሽ አንሷል፡፡ አሥር የአዳራሽ ማስዋቢያ ስታንድ አቀርባለሁ ብሎ ለእኛ ያመጣልን ስድስት ብቻ ነው፡፡ የሙሽራውና የሚዜ መኪኖች ድምቀት ይጐላቸዋል፡፡ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ናኘኪኖች አቀርባለሁ ብሎ ለእኛ ያመጣልን ነጭ ናኘኪን ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ ስናልመውና ስንጠብቀው የነበረው የዲኰር ውጤት አፈር በልቷል፡፡ ከሠራተኞቹ በስተቀር እሱ በአካባቢው የለም፡፡ ስልክ ሲደወልለት መልስ አይሰጥም፡፡ አንጀታችን እንዳረረ ሙሽሮች ደረሱ፡፡ እንደ ጉድ ሲጠበቅ የነበረው ኬክና ሻምፓኝ አልደረሰም፡፡ በስንት ሙከራ በሌሎች ሰዎች የሞባይል ስልክ ተደውሎ ሲገኝ ኬኩን ሙቀት እንዳያቀልጠው ሊቆረስ ሲል ይደርሳል ብሎ ስልኩን ዘጋብን፡፡ ገንዘባችንን ኪሱ ከከተተ በኋላ እንዲህ የሚንቀባረርብን ሰው በስንት እግዚኦታ ተለምኖ ያመጣልን ኬክ ከዚህ በፊት የትም ቀርቦ የማይታወቅ ዙሪያውን በካርቶን ተለብጦ በቫኒላና በክሬም የተቀባባ አሻንጉሊት መሳይ ነገር ነበር፡፡ አንዱ ጠርሙስ መንገድ ላይ ተሰበረብኝ በሚል የሀሰት ምክንያት ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ አንድ ጠርሙስ ሻምፓኝ ብቻ ነው ያቀረበው፡፡


አንጀታችን እንዳረረ ንዴታችንን ውጠን የሠርጉን ኘሮግራም ካጠናቀቅን በኋላ ሙሽሮቹን አጅበን ወደ ማረፊያቸው ልንወስድ ስንነሳ ከየት የመጡ የማናቃቸው ወጠምሻ ጐረምሶች የሙሽሮቹን መኪና ከበቡ፡፡ የእነሱ አለቃ የሚመስል የሰማይ ስባሪ ቢጤ ከሙሽሮቹ መኪና ላይ ያለውን ጌጥ ሊያነሳ እንደመጡ ያስታወቀን፡፡ ይህን ጊዜ ነበረ የታመቀው ንዴታችን ገንፍሎ ሁላችንንም ወፈፍ አደረገን፡፡ ድርጊቱን ሲታዘቡ የነበሩና ቤተሰቦቻችን ጭምር ባደረጉት ርብርብ የሙሽራው መኪና ጌጥ ሳይገፈፍ በሠላም ከሆቴሉ ግቢ ወጣን፡፡ ለወራት እንደ ቤተሰብ እና ጓደኛ ሆኖ በሸንጋይ ቃላት እያግባባን ዘረፋ አካሄደብን፡፡ በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሃቀኛ ሰዎች ግን የተሠማሩበት የሥራ ዘርፍ የወንበዴዎች ምሽግ ከመሆን እንዲድን በማኀበር ተደራጅተው የሥነ ምግባር ደንብ ቢያወጡ ይበጃል፡፡

በሸፍጥ የተጠለሉበትን ይህ የሥራ መስክ ለበርካታ ዜጐች ሥራን የፈጠረ፣ በቅንነት ከሠሩበት ሰዎች ከድህነት ወደ ሀብት ጐዳና የሚገቡበት፣ በአገልግሎት ሰጪና በተቀባይ መካከል የመልካም ግንኙነት ምሳሌ መሆን የሚችልና በዘመኑ የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ከሆቴል ዘርፉ ቀጥሎ ለአገሪቱ በርካታ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል ነው፡፡ እንደ አገልግሎት ተቀባይነታችን (ሸማችነታችን) ማለት የሚገባን ነገርም ይኖራል፡፡ ከተወሰኑት የዲኰር ድርጅቶች በስተቀር ብዙዎቹ የሚያቀርቧቸው ውሎች የአስገዳጅነት ባህሪ አላቸው፡፡ ሠርጉ ሳይጠናቀቅ ሙሉ በሙሉ ክፍያ ይፈፀምልን ይላሉ፡፡

ሁላችንም በሕግ ጥላ ሥር እስካለንና የምንዋዋላቸው የውል አንቀፆች በሕጉ መሠረት እስከተቃኙ ድረስ ተገቢውን አገልግሎት ሰጥተው ለምን ክፍያ አይቀበሉም? አጣድፈው ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ በቃላቸው ለምን አይገኙም? ምንም የማያውቅ ጊዜያዊ ሠራተኛ አሰልፈው ከደንበኛ ጋር ለምን ያጣላሉ? ራሳችንን ከዘመኑ ጉደኛ ማፍያዎች እንጠብቅ፡፡
 
< Prev   Next >