Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ ባህል ልውውጥ...
የኢትዮጵያ ባህል ልውውጥ... Print E-mail
Sunday, 17 February 2008
Image
ዶ/ር ሰለሞን ዓሊ
የኢትዮጵያ ባህል ልውውጥ እምን ድረስ ነው?


በ1995 የወጣው የባህል ፖሊሲ የባህል ልውውጥና ግንኙነትን አስመልክቶ በሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች የሚደረስባቸው ግኝቶች በይፋ እንዲታወቁና ለአገር ልማት ለሚወጠኑ እቅዶች በመነሻነት እንዲያገለግሉ ማድረግ እንዲሁም የአገሪቱን ህዝቦች ባህል ለተቀረው ዓለም በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ በባህል እኩልነትና የጋራ ጠቀሜታ ላይ የተመሰረቱ ጠንካራ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች መፍጠር እንደሚገባ ያመለክታል፡፡
አገሪቱ ባህልን አስመልክቶ የገባቻቸውንና ለወደፊቱም የምትገባውን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎች ለመወጣት አስፈላጊው ትኩረት እንደሚደረግም ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ ከፖሊሲው አንዱ አካል የባህል ልውውጥና ግንኙነት ቢሆንም እስካሁንም ድረስ ቢሆን ቅርብ የሚገኙ ጎረቤት አገሮች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ መገለጫ አድርገው የሚያዩት ጦረኝነትና ረሃብን ነው፡፡

ዶ/ር ሰለሞን ዓሊ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከ30 ከሚበልጡ የአፍሪካ፣ የእስያ፣ የአወሮፓና የላቲን አሜሪካ አገሮች ጋር የባህልና ቱሪዝም ስምምነቶችን ተፈራርማለች፡፡ ስምምነቶቹን እንደየ አገሮቹና አንደ ስምምነቶቹ አይነቶች የሁለትና የሶስት ዓመት የአፈፃፀም መርሃ ግብር በተለያዩ የባህል ዘርፎች የትብብር መርሃ ግብሮች እየተዘጋጀ አቅም በፈቀደ መጠን በጀት እየተያዘ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡

ከ30 ከሚበልጡ አገራት ጋር የባህል ስምምነት ቢኖሩም የተወሰኑ አገሮች ተወስደውና አላማ ተደርገው በአውሮፓ፣ አሜሪካ ወቅታዊ ሁነቶች በሚኖሩበት ጊዜ ትኩረት እየተሰጠ ተሳትፎ ይደረጋል እንጂ ስምምነት ባለበት አገራት ሁሉ ለመስራት አቅም የለም፡፡

ዶ/ር ሰለሞን እንዳሉት፣ ሥነ በዓልን ከመጠበቅ አንፃር የሚሰሩ ሥራዎች በአብዛኛው ትኩረት የተሰጠባቸውና የተከናወኑ ናቸው፡፡ የስትራቴጂና የፖሊሲ አቅጣጫ ተነድፎም በአፍሪካ ውስጥ ቱሪዝምን ከማመንጨትና በጋራ ከመስራት አንፃር በባህል እንቅስቃሴዎች ውስጥ በአህጉራችን ምን እንሰራለን የሚለው በጥናትና በመረጃ የተደገፉ መሆን ስላለባቸው ከዚህ አንፃር በ1995 የወጣውን የባህል ፖሊሲ እየተዳሰሰ ነው፡፡ ከሁሉም የአፍሪካ አገሮች ጋር የባህል ስምምነት መፈራረሙ የሚጠቅም ነው፡፡ ሆኖም አፍሪካ ውስጥ ከባህል አንፃር ምን እየተደረገ ነው? በብዛት ትኩረት የማይሰጥበት የባህል ኢንዱስትሪው ላይ ምን ይደረጋል የሚሉትን ተዳስሰውና አቅም ታይቶ የሚንቀሳቀሱባቸው ይሆናሉ፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ በዚህ አመት እነዚህን ሥራዎች በአፍሪካ እንሰራለን ብሎ ለብቻ ማቃዱም አስቸጋሪ መሆኑን ነው ዶ/ር ሰለሞን የሚያብራሩት፡፡ አላማ የሚደረጉት አገራት ባህልና ቱሪዝምን በተመለከተ በአገራቸው የሚኖሩ ዝግጅቶችን ፕሮግራም በሚያደርጉት መሰረት ነው፡፡  እቅዶቹ መሳለጥ ያለባቸውም ከየአገሮቹ ፕሮግራም መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ እንዲሁም የቱሪዝም ማሰልጠኛን በስሩ አቅፎ ይሰራል፡፡

በዋና መስሪያ ቤት ደግሞ የባህል ትምህርትና ልማት ግንኙነትና የባህል ጥበባትና ፈጠራዎች መምሪያዎች አሉ፡፡ የእነዚህን ሁሉ ፍላጎቶች ያካተተ የአቅም ግንባታን የሚመለከት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን፣ በአገሮች የባህል ግንኙነት እንቅስቃሴ በሚዘጋጁበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ከመቶ በላይ ኤምባሲዎች አመታዊና የነፃነት በዓሎቻቸውን በሚያደርጉበት ኢትዮጵያም ተጋብዛ ወደየአገሮች በምትጓዝበት ጊዜ የሚደረጉ ልውውጦችን ሁሉ የሚይዝ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያቅፋል፡፡

የቅርስ ጥበቃንና እንክብካቤ፣ የሙዚየም ስራዎችን በተመለከተም የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርሟል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ታዳጊ ከመሆን አንፃር እነዚህን ሁሉ ለማሟላት የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ የተወሰኑት ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመስራት ተሞክሯል ይላሉ፡፡

ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት ባህልን አስመልክቶ በአብዛኛው ከአገሮች ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የየአገሮቹን ባህልና ስነጥበብ በሚገልፁ ኤግዚቢሽኖችና ፕሮግራሞች መሳተፍና በኢትዮጵያም በማዘጋጀት ነው፡፡ ኢትዮጵያም በእሲያ፣ በናይጄሪያ፣ በሴኔጋል በተዘጋጁ የአፍሪካ የጥበብና የባህል ፌስቲቫሎች እንዲሁም የባህል ሙዚቃ ቡድኖችም በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአፍሪካ አንዳንድ አገሮች እየሄዱ ይሳተፋሉ፡፡

በ1999 ዓ.ም ቬንዝዌላ በተካሄደው የጥቁር ህዝቦች ፌስቲቫል፣ ቱርክሜንያ ላይ በተካሄደው የጥበብ ፌስቲቫል፣ በብራስልስ የሚሌኒየም በዓል አስመልክቶ በተዘጋጁ ዝግጅቶች ላይም ተካፋይ ሆነዋል፡፡

አሁን በተያዘው ዕቅድ መሰረት በሚያዚያ ወር ለ37ኛ ጊዜ በሚዘጋጀው የሂውስተን አለማቀፍ ፌስቲቫል ይሳተፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከሌሎች የቱሪዝም ነክና የፋሽን ሾው፣ የቡና፣ የዕደጥበባትና ጨርቃ ጨርቅ ላይ በሚዘጋጀው የ2 ሳምንት ኤግዚቢሽን ላይ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚያንፀባርቁ የባህል የሙዚቃ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ በቀጣይም መጋቢት ውስጥ በቻይና በሚዘጋጀው አለማቀፍ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ይሳተፋል፡፡

ሚሌኒየሙን አስመልክቶ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን አልሰራም መባሉን አስመልከቶ ዶ/ር ሰለሞን እንዳሉት የሚሌኒየም አከባበር አገራዊም አለማቀፋዊም ዝግጅት በመሆኑ ሰፊ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አንፃር አልፎ የኢትዮጵያ የባህል፣ የተፈጥሮና የታሪክ ገጽታዎች ላይ ያተኮሩ ኢትዮጵያውያንን በይበልጥ በአለማቀፍ ደረጃ አመቱን ሙሉ የሚያስተዋውቅ ከፍተኛ ብሔራዊ ዝግጅት ነው፡፡ ከባህልና ቱሪዝም ጋር የሚያያይዘው ቀጥተኛ የሆነ ቁርኝት አለው፡፡ ነገር ግን ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ዜጎች በሙሉ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በራሱ አቅም በፈቀደ መሠረት ነው ዝግጅቶቹን ያደረገው፡፡ ሚሌኒየም አካባበሩ በይፋ ሰኔ ላይ ከመጀመሩ በፊት ሁለት አለማቀፍ ስብሰባዎችን አካሂዷል፡፡ ባለፉት አመታት ውስጥ የተገኙትን የስነቁፋሮ ውጤቶች አስመልክቶ በስነ ቁፋሮ፣ በቱሪዝም፣ በኢኮቱሪዝም 40 አለምአቀፍ እውቅና ያላቸው ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት አለማቀፍ ፓሊዮአንትሮፖሎጂካል ኮንፈረስ ተካሂዷል፡፡ ኤምባሲዎች ባዘጋጁት የሚሌኒየም ዝግጅት ላይ የቱሪዝም፣ የሥዕል ዐውደርዕይና የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ በአቡጃና በብራልስ ተዘጋጅቷል፡፡ ከናይጄሪያ የመጡ የባህል ሙዚቀኞች በሚሌኒየሙ ዋዜማና በዕለቱ በአዲስ አበባ ተገኝተው የዝግጅቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ሚሌኒየሙን በተመለከተ በበቂ ሁኔታ ተሳትፈዋል፡፡

የአገራችንን ባህል ለማስተዋወቅ ከትላልቅ ስብሰባዎች ይልቅ የባህል መገለጫ የሆኑትን ቁሳዊ ባህሎች ማሳየት ባህልን የማስረጽ ሃይሉ የጎላ ነው፡፡ ባህሎቻችንንም ለማሳየት በተደጋጋሚ የሚታዩት የፋሽን ትርዒት፣ ቡና ማፍላትና ጭፈራን ነው፡፡ ካሉን የተለያዩ ባህሎች አንፃር በቂ አለመሆናቸውን በተመለከተም ዶ/ር ሰለሞን በቂ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ፖሊሲ ስትራቴጂ ላይ ባህልና ቱሪዝምን የማስተዋወቅ ስትራቴጂ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያን የተለያዩ ባህሎች የማስተዋወቅ ሥራ አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ካሏት የተፈጥሮና የታሪክ መስህቦች አንፃር ተገቢውን ድርሻዋን እንዳላገኘች በስትራቴጂክ ሰነድ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መንግስት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች የሚሳተፉበትን የ5 ዓመት ስትራቴጂ ቀይሷል፤ ፖሊሲም ነድፏል፡፡ ኢትዮጵያም በቅርብ ጊዜ ተመራጭ መዳረሻ ሊያደርጋት የሚችል አቅጣጫና ተገቢውን ድርሻዋን ልታገኝ የምትችልበትን አካሄድ ተቀይሷል፡፡

ዘርፉ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ አንፃር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እንደሚያምኑ ዶ/ር ሰለሞን ተናግረው ሆኖም እስካሁን ባሉ እንቅስቃሴዎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን የአስጎብኚ ድርጅቶችም ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም፣ ባለሃብቶችም፣ ሌሎች ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሃብቶችንን በሙሉ ማሳየቱ ጊዜን የሚፈልግም በመሆኑ ወደፊት አግባብ ያላቸውንና አሁንም በስራ ላይ ያሉ የህግ ማዕቀፎችን አጠናክሮ በመቀጠል ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ያልተዳሰሱ በርካታ ሃብቶቻችን ገበያ ላይ ከማውጣት አንፃር ጅምር ሥራዎች መልክ እያያዙ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ዘላቂ የባህል ልማት ከአገርና አለማቀፍ ደረጃ ዘርፈ ብዙ አቅጣጫዎችን ሃብቶቻችንን በማሰባሰብ፣ አቅምን በመገንባት በአንድ ጊዜ የሚመጣም ባይሆን መልክ በማስያዝ መንግስት፣ ኅብረተሰቡና ባለሃብቶች በጋራ የሚሰሩት የስራ እንቅስቃሴ መሆኑ እሙን በመሆኑ አብሮ መስራትም ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የባህልና ቱሪዝም ልውውጥ ማድረጉ እንደ ትምህርትና ጤና ቅድሚያ የሚሰጠው ዘርፍ አይደለም፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >