| ትዳር ሲፈርስ - ወደ ልመና |
|
|
| Sunday, 17 February 2008 | |
![]() ወ/ሮ ደስታና ልጆቿ አራት ልጆቿን ይዛ ተቋሙ ቢሮ ስትጠብቀኝ ተበትኖ ጎዳና የወጣውን ቤተሰቧን ጠብቆ ለማቆየት አሁንም ተስፋ ያላት መሆኗን ፊቷ ላይ ይነበብ ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታት በጎዳና እየተዘዋወረች፣ በየሱቆች ደጃፍና በቤተክርስቲያን እያደረች ቆይታለች፡፡ ከቤቷ ሳትወጣ በፊት ከማኅበራዊ ኑሮ መገለልን ጨምሮ ሌሎች የቤት ውስጥ ጥቃቶች ሲደርሱባት ቆይተዋል፡፡ ትዳርዋን ላለመተው ታግሳ መኖሯን ትናገራለች፡፡ የመጨረሻ ልጇን ነፍሰጡር በነበረችበት ወቅት የግድያ ዛቻ ሲበዛባት አንዱ ቀን ጧት ልጆቿን ይዛ ፖሊስ ጣቢያ ሄደች፡፡ የልጆቿ አባት ሊገድላት ሲሞክር ስትጮህ የሰሙ ጎረቤቶቿ ጣቢያ ሄደው መሰከሩ፡፡ “ቀኑን ሙሉ አሰሩት፤ ከዚያ ማታ ተፈቶ እቤት መጣና አሳሰርሽኝ ከቤት ውጪ ብሎ አባረረኝ፡፡ ወጥቼ ጎዳና ወለድኩ” ትላለች ወ/ሮ ደስታ፡፡ ጎዳና የተወለደው ልጇ 2 ዓመት ሞልቶታል፡፡ ከቤት ከወጣች በኋላ በፍ/ቤት ክስ መስርታ፣ በሕግ የተፈፀመ ጋብቻ የሌላት በመሆኑ እንደ ሚስት አብራ መኖሯን አስመስክራ ልታገኝ የቻለችው የ50 ብር ተቆራጭ ነው፡፡ ይኸውም የልጆቹ አባት ከሚያገኙት ጡረታ ላይ የተቀነሰ ነው፡፡ አሁን በዘበኝነት ተቀጥረው ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙ ቢሆንም ማለት ነው፡፡ ወይዘሮ ደስታ ከዚህኛው ገቢ እንዲቆረጥላት አለመጠየቋን ነግራኛለች፡፡ ወ/ሮ ደስታ በጎዳና እየኖረችም ቢሆን ለልጆቿ የተሻለ ነገን ለማየት ትምህርት ቤት አስመዝግባ፣ በልመና ከምታኘውና ከተቆራጯ የትራንስፖርት እየከፈለች እያስተማረች፣ የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ ትጠብቃለች፡፡ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም በክፍለ ከተማ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ አደራዳሪነት ይኖሩበት የነበረው የቀበሌ ቤት ተከፍሎ፣ በግማሹ ውስጥ ትኖር እንደነበረው ሁሉ የራሷን ገቢ የሚያስገኝ ሥራ እየሰራች ልጆቿን ማሳደግ ነው፡፡ ቤቱ ለሁለት እኩል ተከፍሎ፣ መሀሉ ታሽጎ ይኖሩበት የነበረው ሁኔታ የተቀየረው የልጆቿ አባት የቤቱን /የተከፈለበትን/ በር እሽግ ከሰበሩት በኋላ ነው፡፡ “50 ብር ተቆራጭ መጥቶ ምን ያደርግልኛል፡፡ ለልጆቼ ትራንስፖርት እንኳን አይበቃም፡፡ ቤቱ ቢፈቀድልኝ እንጀራ፣ ቆሎ፣ ጠላም ቢሆን እየሸጥኩ ልጆቼን ማሳደግ አያቅተኝም፡፡ አሁን ግን የልጆቼ በረንዳ ማደር ያስጨንቀኛል፡፡ እንቅልፍ አልተኛም” የምትለው ወይዘሮ ደስታ እሷና ልጆቿ የድሮ ጎረቤቶቻቸው እርዳታ እንዳልተለያቸው ትጠቅሳለች፡፡ ቀደም ሲል የገቢ ምንጭ እንዲሆናቸው ላም ገዝተው ቢያረቡም፣ በኩበት መሸጥ የተወሰነ ገንዘብ ታገኝ የነበረ ቢሆንም ያንንም ጥላ መውጣቷን ገልፃልናለች፡፡ ወ/ሮ ደስታ የተወለደችው ሰሜን ወሎ ገጠር ውስጥ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ሰለነበር አልተማረችም፡፡ ከገጠር ከወጣች ከ20 ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ የመጀመሪያ መድረሻዋ ሸዋ ሮቢት ነበር፡፡ ሸዋ ሮቢት አጎቷ ጋ ስትደርስ ያጋጠማት በማረሚያ ቤት ውስጥ እንጀራ መጋገር ነበር፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ከሰራች በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ በሰው ቤት ሠራተኝነት ለ3 ዓመት ኖራ የአሁኑን የልጆቿን አባት አገኘች፡፡ የመጀመሪያ ስምምነቷ በሠራተኛ መልክ ልትቀመጥ፣ ቆይቶ ቤተሰቦቿ ጋ ሄደው ግንኙነቱ ተለውጦ በትዳር መኖር ሊቀይሩ ነበር፡፡ ይህም ሳይሆን በትዳር መልክ አብሮ መኖር ተጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ ወይዘሮ ደስታ ከቤት የመውጣት፣ ከሰዎች የመቀላቀል መብት ተነፈገች፡፡ የልጆቿ አባት ቤት ውስጥ ይውሉ የነበረ በመሆኑም ለቅሶ መድረስ፣ ከጎረቤት ቡና መጠጣት የማይታሰብ ነበር፡፡ ከቤት ሲወጡም የቤት መክፈቻ ቁልፍ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ጠጥተው ሲመጡ ፣የመጨረሻውን ልጅ ከእኔ አላረገዝሽም፣ በሚል ሰበብ ጠብ ይፈጥራሉ፡፡ ልጆቻቸው ፊት ይሳደባሉ፣ ያንጓጥጣሉ፣ ለግድያ ይዛትባቸዋል፡፡ ነገሮች መልካቸውን ሲቀይሩ ወደ ፍርድ ቤት ያመራቸው ወይዘሮ ደስታ፣ የፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ምላሽ ፣ተስማሙ፣ የሚል እንደነበር ያም ሳይሳካ ሲቀር ሚስትነታቸውን ለማስመስከር ጊዜ መፍጀቱን ትገልፃለች፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ጎዳና የወጣው ቤታቸው ከመበተኑ በፊት ነበር፡፡ ዛሬ እናቱም ጎዳና ስትወጣ የጎዳና ላይ ቤተሰብ አባል ሆኗል፡፡ ወይዘሮ ደስታ ዛሬም የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ ትጠብቃለች፡፡ ወ/ሮ ደስታ ዕቃ ለማስቀመጥ፣ የልጆቿን ልብስ ለመቀየር ስትፈልግ ወደ ድሮ ሰፈሯና ወደ ጎረቤቶቿ መመላለሷ ግድ ነው፡፡ ለሕይወቷ ሰግታ እስክትወጣ ድረስ በተደጋጋሚ በማትፈልገው የጥቃት ህይወት ውስጥ መኖሯን ትናገራለች፡፡ ከ20 ዓመት በፊት ጥላው መምጣቷን ወደገለፀችው ቤተሰቧ ለምን አትመለስም? ልጆቿን ይዛ የቤተሰብ ሸክም ለመሆን እንዳልፈለገች ትናገራለች፡፡ ከጎዳና የተሻለ ስለመሆኑም አታስብም፡፡ የወይዘሮ ደስታ ታሪክ የትምህርት ዕድል ባለማግኘታቸው ዕድላቸውና የወደፊት ሕይወታቸው የሚጨልም ሴት ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡ የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመሆኑ ሙሉ በሙሉ የኢኮኖሚ ጥገኛ በሚያደርጋቸው የጋብቻ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ታሪክ ነው፡፡ ልጆቻቸውን ይዘው በየጎዳናው የሚወድቁ ሴቶችም ታሪክ ነው፡፡ ወይዘሮ ደስታ ከጎዳና ወደ ቤት ለመመለሷ፣ ከልመና ህይወት ለመውጣቷ ምንም ዋሰትና የለም፡፡ ዕድለኛ ሆና ቤት የመካፈል ውሳኔ ብታገኝ የተበተነ ቤተሰቧ ይሰበሰብ ይሆናል፡፡ እስከዚያው ግን በመንገድ መብራት የሚያጠኑ ልጆቿን ለማስተማር ጥረቷን ትቀጥላለች፡፡ ሁለተኛ ልጇ የተሻለች ብትሆንም አምና በገንዘብ እጦት በማቋረጧ ዘንድሮም አንደኛ ክፍል ናት፡፡ የኑሮ ሁኔታዋ የተሻለ ውጤት እንድታመጣ ምን ያህል ይረዳታል? አጠራጣሪ ነው፡፡ በቤተልሔም ነጋሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |